* ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ የህብረቱ ሊቀመንበር ሆኑ
አዲስ አበባ፦ አፍሪካውን ሊያተኩሩባቸው የሚገቡ ጉዳዮች በርካታ ቢሆኑም በሰላም ፣ደህንነት እና የጤና ፕሮግራሞች የማሳካት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለጸ፡፡ ፅዱ እና አረንጓዴ አካባቢን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረትም ሳይንሳዊ አሠራሮችን መከተል ይገባል ተብሏል።
ለሁለት ቀናት የሚቆየው 32ኛው የአፍሪካ ህብረት መሪዎች መደበኛ ስብሰባ ትናንት በአዲስ አበባ ሲጀመር ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በአደረጉት ንግግር እንደገለጹት፣አፍሪካውን ሊያተኩሩባቸው የሚገቡ ጉዳዮች በርካታ ናቸው፡፡ በሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች እና የጤና ፕሮግራሞች መሳካት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
የአፍሪካውን አንድ ፓስፖርት እና ነፃ ገበያ አሠራሮች የሚተገበሩበትን መንገድ በመፈለግ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ላይ ሊተኮሩ ይገባል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነት ስልጣን ከሩዋንዳው መሪ ፖል ካጋሜ ለቀጣዩ አንድ ዓመት የተረከቡት የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ፣ በኢትዮጵያውያን በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተደረገላቸውን ሞቅ ያለ አቀባበል አድንቀው፤ የህብረቱ ሊቀመንበር ሆነው በመመረጣቸው ለአህጉሪቷ ዕድገት የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ እንደገለጹት፤ ከአፍሪካውያን ዘርፈ ብዙ ችግሮች መካከል ሽብርተኝነት እና የጸጥታ ጉዳይ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ከሰላምና ደህንነት ችግሮች ባለፈ ድርቅና ረሃብ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም ሌሎች ችግሮች አፍሪካውንን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ እያስገደዱ የሚገኙ ጉዳዮች ናቸው፡፡
ሽብርተኝነትን ስለመከላከል ሲታሰብ ችግሩን ለማባባስ የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላትንም ለይቶ ስለመከላከል ሊታሰብ ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንት አል ሲሲ፣ በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደ ሽምግልና እና ድርድር ያሉ የግጭት መፍቻ መንገዶችን በስፋት መጠቀም ያስፈልጋል ሲሉም አመልክተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት አል ሲሲ እንደተናገሩት፤ ፅዱ እና አረንጓዴ አካባቢን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረትም በሳይንሳዊ አሠራሮች ላይ በመመርኮዝ አንድም የአየር ንብረት ለውጥ አደጋን መቀነስ በሌላ በኩል ደግሞ ረሃብና ድርቅን መከላከል ይገባል፡፡ ሁሉንም የአፍሪካ ችግሮች መፍ ትሔ ለማበጀት ግን በትብብር መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም ችግሮቹን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት አፍሪካውያን በጋራ መሥ ራት አለባቸው፡፡
ከጋራ ትብብሮቹ መካከል ደግሞ የእውቀትና ልምድ ልውውጥ ማድረግ እንዲሁም በመሰረተ ልማት አህጉሪቷን የበለጠ ማስተሳሰር ያስፈልጋል ያሉት ፕሬዚዳንት አል ሲሲ፣ የትብብር ሥራው በህብረቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በመሰረተ ልማት በኩል ደግሞ አፍሪካውያንን በመንገድ መሰረተ ልማት ለማገናኘት ከግብፅ ካይሮ እስከ ደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን እየተዘረጋ የሚገኘው አስፓልት እና ከሰሜን እስከ ደቡብ በኤሌክትሪክ መስመር ለማገናኘት የሚደረጉ ጥረቶች ምሳሌ መሆን ይችላሉ ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በአፍሪካ ያለው የዴሞክራሲ ስርዓት መሻሻል እያመጣ መሆኑ የሚያበረታታ ነው፡፡ ለዚህም በቅርቡ በተለያዩ አገራት የተደረጉ ሰላማዊ ምርጫዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አፍሪካ በበርካታ ችግሮች ውስጥ ያለች አህጉር ብትሆንም ለዜጎች ምቹ እንድትሆን የሚደረገው ጥረት መጠናከር አለበት፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒ ጉቴሬዝ በበኩላቸው፤ አፍሪካውያን በጋራ የመኖር ተምሳሌት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህም ተምሳሌትነት አንድ አራተኛውን የዓለም ስደተኛ በመቀበል ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡
አፍሪካውያን በሰላም ማስከበር ተግባር ላይ ያላቸውን ጉልህ ተሳትፎ ያደነቁት ዋና ፀሐፊ አንቶኒ ጉቴሬዝ፤ ከትናንትና በስቲያ በደቡብ ሱዳን አብዬ በሰላም ማስከበር ሥራ ላይ የነበሩ ሦስት ኢትዮጵያውያን በሄሊኮፕተር አደጋ ምክንያት በመሞታቸው የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን ገልጸዋል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ ፣የአፍሪካ አገራት መሪዎችን ፣የፍልስጤየም ፕሬዚዳንት ሙሃመድ አባስ ፣ የአረብ ሊግ ዋና ፀሐፊ አህመድ ቡልግሄይት፣ የፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም እና ቢልየነሩ ቢል ጌትስ ጉባኤውን ተካፍለዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 4/2011
በጌትነት ተስፋማርያም