ፍሬህይወት አወቀ
የበርካታ ባህላዊና መንፈሳዊ ቅርሶች ባለቤት መሆኗ ሰርክ የሚነገርላት ኢትዮጵያ ከባህላዊ ቅርሶቿ መካከል የሀገር ባህል አልባሳቶቿ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። ታዲያ የሀገር ባህል ልብስን ስናነሳ የዶርዜ ማህበረሰብን አለማንሳት አይቻልም። የዶርዜ ማህበረሰብ ድርና ማጉን አዋዶ፣ አስማምቶና አቀናጅቶ በሰው እጅ የተሰራ ነው ለማለት የሚከብዱ እጅግ የረቀቁ ውብ ጥበቦችን በመስራት የሚታወቅ የማህበረሰብ ክፍል ነው።
እነሆ ዛሬ ጥበብን ከነጠበብቱ ማንሳት የወደድነው ስለጠበብቶቹ ልናወጋችሁ ሳይሆን ከዚሁ ማህበረሰብ የተገኘውና ተማሪዎችን ቤት ለቤት ከማስጠናት ጀምሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ባለቤት ለመሆን የበቃውን ስኬታማ ወጣት የስኬት ጉዞ ልናካፍላችሁ ስለወደድን እንጂ። ወጣቱ በስኬት ጉዞ ውስጥ ተስፋ ቆርጦ እራሱን ለማጥፋት የወሰነበት ጊዜን ያሳለፈ ቢሆንም ነገም ሌላ ቀን ነው ብሎና ተስፋ ሰንቆ ግራ ቀኙን በማሰብ መሰናክሎችን ሁሉ በትዕግስትና በአልበገር ባይነት አልፎ ዛሬ ላይ ደርሷል – የሳታ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት እና ባለቤት አቶ አለማየሁ ካሳ።
ትውልድና እድገቱ በጋሞ ዞን ዶርዜ ጬንቻ ወረዳ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱንም በዶርዜ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። ለትምህርት ልዩ ፍላጎት የነበረው ይህ ስኬታማ ወጣት ወደ አዲስ አበባ ከተማ ለመምጣቱ ምክንያት የሆኑት ወላጅ አባቱ ነበሩ። በድርና ማግ ንግድ የተሰማሩት ወላጅ አባቱ ሥራ እንዲያግዛቸው ቢያመጡትም ከእገዛው ጎን ለጎን ትምህርቱን እንዲከታተል በማድረጋቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ፈረንሳይ ለጋሴዎን አካባቢ በሚገኘው በካራማራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል።
ከትምህርቱ የሚጠብቀውን ውጤት ማምጣት ሳይችል ቢቀርም በግል ተፈትኖ በቀድሞው የኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ በፊዚክስ ትምህርት በዲፕሎማ ተመርቋል። በዚህ ወቅት ታድያ ከአስር በበለጡ ቤቶች እየተዘዋወረ ተማሪዎችን በማስጠናት በወቅቱ ዳጎስ ያለ ገቢ ያገኝ ነበር። ሆኖም በተመረቀበት የፊዚክስ ትምህርት በአማራ ክልል በ460 ብር ደመወዝ በመምህርነት ተቀጥሮ ለመሄድ አስፈላጊውን ሁሉ ማሟላት ጀመረ፤ ቤተሰቡንም ተሰናብቶ ወጣ። ሆኖም ግን አዲስ አበባ ላይ ተማሪዎችን እያስጠና የሚያገኘው ገንዘብና አሁን የተቀጠረበት ደመወዝ ልዩነቱን ሲያስበው ለመሄድ ያደረገው ውሳኔ ተገቢ አለመሆኑን በማመኑ የተሳፈረበት መኪና አዲስ አበባን ከመልቀቁ በፊት የተሸከመውን ሻንጣ አውርዶ ወደ ቤቱ ተመለሰ።
በዚህ ጊዜ ታድያ የመንግሥት ስራ አገኘልኝ ብለው መልካሙ ሁሉ እንዲገጥመው መርቀው የሸኙት ወላጅ አባቱ ቅጥሩን ትቼዋለሁ ብሎ ወደ ቤቱ መመለሱን በመቃወም ‹‹ልጄ አይደለህም›› ብለው ከቤት እንዳባረሩት ያስታውሳል። ይሁን እንጂ የህይወትን ምዕራፍ በስኬት ጉዞ ‹‹ሀ ብዬ ልራመድ የቻልኩት በዚሁ ጊዜ ነው›› የሚለው ላለፉት በርካታ ጊዜያት ተማሪዎችን ቤት ለቤት ተሯሩጦ ሲያስጠና የነበረው ነው።
ተማሪዎችን በማስጠናት ያገኝ የነበረውን ገቢ ለማሳደግ ሥራውን አጠናክሮ በመቀጠል የተሻለ ቦታ መድረስ እንደሚቻል ያምናል። ስለዚህ የበዙ ማስታወቂያዎችን በተለያዩ ቦታዎች በመለጠፍ የማስጠናት ሥራውን አጠናክሮ ቀጠለ። በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች በተለያዩ አካባቢዎች በማስጠናት በሚያገኘው ገቢ አድማስ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በኮምፒዩተር ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪውን ተማረ። ከዛም ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሁለተኛ ዲግሪውን ያዘ ።
ተማሪዎችን በማስጠናት የሚያገኘው ገቢ በውስጡ የቢዝነስ ሀሳብ መፍጠር እንድችል ጥሩ አጋጣሚ እንደፈጠረለት አቶ አለማየሁ ይናገራል። በተለይም አድማስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በሚማርበት ወቅት ቢዝነስ እንዴት መፍጠር እንዳለበት ያስብ ነበር። በአራት ዓመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታውም ሙሉ ለሙሉ የዩኒቨርሲቲውን አደረጃጀት በማጥናት ወደ ተግባር መግባቱን ያስታውሳል። ቢዝነሱን ለመጀመር መነሻ ካፒታል ያስፈልገዋልና ቤት ለቤት ማስጠናቱን ይበልጥ አጠናክሮ በመቀጠል መሰረታዊ የኮምፒዩተር ትምህርት ቤት ለመክፈት ደፋ ቀና ብሏል።
አዲስ አበባ ላይ መወዳደር ከባድ እንደሆነ በማሰብ ወደ ትውልድ አካባቢው አርባምንጭ አቅንቶ በአምስት ሺ ብር መነሻ ካፒታል እና በከፍተኛ ጉጉት ሥራውን ለመጀመር ማስታወቂያዎችን መስራት ጀመረ። በ1200 ብር ቤት ተከራይቶም ሳታ የኮምፒዩተር ማሰልጠኛ ማዕከል በሚል በሰፊው እያስተዋወቀ ሥራ ሲሰራ የነበረው አምስት ሺ ብር አልበቃ ብሎት ቢቸገርም በምዝገባና በወርሃዊ ክፍያ ከህብረተሰቡ ገቢ እንደሚያገኝ በማመን ሥራው እንዲቃና ተውተርትሯል። እንደ ጥረቱ ሆነና ተማሪዎች ተመዝግበው በሚያስገቡት ገቢም የመማሪያ ቁሳቁሶችን አሟልቷል።
በእንደዚህ ሁኔታ የተጀመረው ሳታ የኮምፒዩተር ማሰልጠኛ ማዕከል በርካታ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች ማግኘት ቻለ። ለጥራት በሰጠው ትኩረትም አንድ ተማሪ እጅግ ባጠረ ጊዜ መሰረታዊ የሆኑ የኮምፒዩተር እውቀቶችን አውቆ ይሄዳል። በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ወደ ማዕከሉ መምጣት ችለዋል። በመጀመሪያው ዓመት ብቻ 145 ተማሪዎችን ማሰልጠን ችሏል።
ይህ በወቅቱ ትልቅ መነቃቃትን የፈጠረለት በመሆኑ በቀጣዩ ዓመት በአርባምንጭ ከተማ ዙሪያ በኮንሶ፣ ሴቻ፣ ሲቀላና ምዕራብ አባያ በተባሉ አራት ቦታዎች ቅርንጫፎችን ከፍቷል። በጥራት እየሰራ ለመለወጥ ካለው ጉጉት የተነሳ አራቱም ቅርንጫፎች ላይ ተዘዋውሮ ሲያስተምር የድካም ስሜት የማይሰማው እንደነበር ይናገራል።
ሥራውን በጀመረበት አንድ ዓመት ውስጥ አራት ቅርንጫፎችን መክፈት የቻለው አቶ አለማየሁ፤ በሶስተኛው ዓመት ደግሞ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ማዕከልን ለመክፈት አቅዶ ወደ ሀዋሳ አቅንቷል። ሀዋሳ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ማዕከል ለመክፈት ማሟላት የሚገባውን ነገር በሙሉ ጠይቆ ተረድቷል። በመሆኑም አስፈላጊ የሆኑ ስትራቴጂዎችን አዘጋጅቶ ቢጨርስም ካፒታሉ አልፈቀደለትም። እናም የጀመረውን የስኬት ጉዞ ገንዘብ አጣሁ ብሎ ማቋረጥ አልፈለገምና በድፍረት ዕውቅና ሳያገኝ ከአርባምንጭ ከተማ ውጭ ባሉ ቦታዎች ብቸኛው ሳታ የቴክኖሎጂ ኮሌጅ በሚል የማስተዋወቅ ሥራውን በስፋት ሰርቷል።
ማስታወቂያውን ተከትሎም ተማሪዎችን መዝግቦ ማስተማር ቢጀምርም ህጋዊ ዕውቅና ገና ያላገኘ በመሆኑ በህግ ተጠያቂ ሆነ። በዚህ ጊዜ ተማሪዎችን ሊበትን ግድ ቢሆንም በወቅቱ የነበሩ አመራሮች ‹‹ለሥራው ያለውን ጉጉትና የቢዝነስ ሀሳቡን በመገንዘብ ከማሰር ይልቅ የዕውቅና ሂደቱን አጠናቅቆ ሥራውን ይስራ›› የሚል ቀና ምላሽ ሰጥተውታል። በተሰጠው ጊዜም ተማሪዎቹን ለጊዜው በማሰናበት ሂደቱን አጠናቅቆ ኮሌጁ ዕውቅናን አገኘ።
እውቅና ያገኘው ሳታ ኮሌጅ ያሰናበታቸውን ተማሪዎች እንደገና በማስታወቂያ ሲጠራቸው ኮሌጁ አስቀድሞ የተቀበላቸውን የሁለት ወር ክፍያ ታሳቢ አድርጎ በመሆኑ ሌላ ቦታ የከፈሉበትን ደረሰኝ ይዘው በመምጣት በነጻ መማር የሚችሉበትን ስትራቴጂ ቀረጸ። ይህም የተወሰኑ ተማሪዎችን መልሶ እንዲያገኝ አስችሎታል። በመሆኑም ሳታ ኮሌጅ በመጀመሪያው ዓመት በቴክኖሎጂ ዘርፍ 200 ተማሪዎችን በደረጃ አራት ለሶስት ዓመታት አስተምሮ አስመርቋል። ያስመረቃቸው ተማሪዎችም ሙሉ በሙሉ ሲኦሲ ማለፍ በመቻላቸው ተፈላጊነቱ ጨመረ። ከዚህም ባለፈ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመጻጻፍ ተማሪዎቹ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው አድርጓል።
የትምህርት ሥራውን በጥራት መምራት ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ የሰራው አቶ አለማየሁ፤ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች አደረጃጀታቸው ምን እንደሚመስል ጥናት አድርጓል። በጥናቱም ማሟላት የሚገባውን አሟልቶ ዕውቅና ያገኘው ሳታ የቴክኖሎጂ ኮሌጅ በ2008 ዓ.ም በጥራት ቀዳሚና ተወዳዳሪ በመሆን በጋሞ ዞን የመጀመሪያው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሆኖ የዲግሪ ተማሪዎችን በ2010 ዓ.ም ማስመረቅ ቻለ።
‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል›› እንደሚባለው በ2010 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን አስተምሮ ማስመረቅ የቻለው ኮሌጅ ደረጃው ወደ ዩኒቨርሲቲ አደገና በ2011 ዓ.ም የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ለመስጠት ዝግጅቱን ጀመረ። ፕሮግራሙ የሚጠይቀውን መስፈርት በጥናት ለይቶ ጠንካራ ዝግጅት ማድረግ በመቻሉ በ2012 ዓ.ም ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ብቸኛ የማስተርስ ፕሮግራም በቢዝነስና አድሚኒስትሬሽን መስጠት የሚያስችለውን ዕውቅና አገኘ።
ከስልጠና ማዕከልነት የተነሳው ሳታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ጥራት ላይ አበክሮ መስራት በመቻሉ በየዓመቱ መሰረታዊ ለውጦችን እያስመዘገበ በጋሞ ዞን ብቸኛው የግል ዩኒቨርሲቲ መሆን ችሏል። በጥንካሬው ይህን ያህል ርቀት በመጓዙም በአካባቢው ተዳክመው ለነበሩ ኮሌጆች መነቃቃት ፈጥሯል።
ለሌሎች አርአያ የሆነው ሳታ ዩኒቨርሲቲ በቀንና በማታ ተማሪዎችን በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ እያስተማረ ይገኛል። የርቀት ትምህርትም እንዲሁ በአካባቢው በሚገኙ ከተሞች በሳውላ፣ በጅንካና በኮንሶ እየሰጠ ነው። በቀጣይ አምስት ዓመታትም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በየክልሉ ለማስፋፋት አቅዶ እየሰራ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት ሳታ ዩኒቨርሲቲ 230 ቋሚ እና 40 ለሚደርሱ የኮንትራት ሰራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሲሆን፤ አጠቃላይ ኢንቨስትመንቱም 30 ሚሊዮን ብር ካፒታል ደርሷል።
ሳታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም አሁን ለደረሰበት ስኬት የተቋሙ ሰራተኞች ትልቅ ድርሻ ያላቸው መሆኑን ያነሳው አቶ አለማየሁ፤ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ግለሰቦችና የመንግሥት ባለስልጣናትም ቀና ትብብር ያደረጉለት በመሆኑ ምስጋናውን ቸሯል። ሆኖም ግን በእንቅስቃሴው ሁሉ በርካታ መሰናክሎች ሲገጥሙት የነበረ ከመሆኑም በላይ የክልሉ መንግሥት ለመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ካለመስጠቱ ጋር ተያይዞ ፈተናዎች እንደነበሩ ያስታውሳል። ሆኖም ለችግሮች ሳይንበረከክ መሰናክሎችን በትዕግስትና በጽናት በማለፉ ዛሬ ስኬታማ ሆኗል።
አስር በሚደርሱ ቤቶች ተዘዋውሮ ህጻናት ተማሪዎችን በማስጠናት የተጀመረው ቢዝነስ ዛሬ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና ባለቤት በመሆኑ ስኬታማ ከሆኑ ሰዎች ተርታ ተሰልፏል። ችግር ፈቺ በሆነው የትምህርት ሥራ ላይ ይበልጥ ተጠናክሮ ለመቀጠልና በ2025 ሳታ ዩኒቨርሲቲን ምርጥ የሀገሪቱ የግል ዩኒቨርሲቲ የማድረግ ራዕይ ሰንቋል። ከትምህርት ሥራው በተጨማሪም በሸማ ሥራ የተሰማሩ ባለሙያዎችን በመደገፍ በዘርፉ የመሰማራት ሀሳብ እንዳለው ይናገራል።
ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ለአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ እገዛ ያደርጋል። ለአብነትም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ 50 ሺ ብር የሚገመት ወጪ በማድረግ የተለያዩ የምግብ ሸቀጦችን ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ለሚያደርገው ማንኛውም ጥሪ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የ50 ሺ ብር ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን አሳይቷል።
ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ ወርቅ የሆነ ሀሳብና ራዕይ ስላለው ይህንኑ ወደ ተግባር ለማምጣት ማቀድና መስራት አለበት የሚለው አቶ አለማየሁ፤ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ሙሉ ጊዜውን ሥራ ላይ ማዋል አለበት ሲል ይመክራል። በተለይም ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነውና ለሰላም ዘብ መቆም ይገባል ሲል ባስተላለፈው መልዕክቱ ሀሳባችንን ቋጨን። ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 14/2013