
ኢትዮጵያ ለዲጂታላይዜሽን ትኩረት ሰጥታ በመሥራቷ በፈጠራ ሥራ እና በቴክኖሎጂ ሽግግር እምርታ እያመጣች ትገኛለች። በተለይ ሕይወትን የሚያቀሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከመፍጠር፣ ከማስተዋወቅ አኳያ ለባለሙያዎች ድጋፍ እና ስልጠና በመስጠት ረገድ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው። ሰሞኑን የአዲስ አበባ የሥራ እና ክኅሎት ቢሮ ባለፈው አንድ ዓመት ለተሠሩ የፈጠራ ውጤቶች እውቅናና ሽልማት ለመስጠት ያለመ የማጠቃለያ ዝግጅት አካሂዷል።
‹‹ብሩህ አዕምሮ በክኅሎት ለበቁ ዜጎች›› በሚል መሪ ቃል ለአስራ አምስተኛ ጊዜ የተካሄደው ከተማ አቀፍ የቴክኒክ እና ሙያ ሳምንት በርካታ ፈጠራዎች እና ኩነቶች የተካሄዱበት ነው። በዚህም ከአንድ መቶ ሀምሳ በላይ ቴክኖሎጂዎች፣ ሰባ ሰባት የጥናት እና ምርምር ውጤቶች፣ ልዩ የተባሉ ችግር ፈቺ አቅም ማጎልበቻ የመፍትሄ ሀሳቦች፣ የፓናል ውይይት፣ ሌሎች የስፖርታዊ እና የፋሽን ውድድሮች የተካሄዱበት ነበር። የማጠቃለያ ፕሮግራሙን መሰረት በማድረግ የምስጋና፣ የእውቅና እንዲሁም የገንዘብ ሽልማቶችም ተሰጥተዋል።
ፕሮግራሙ ተቋማት ዓመቱን ሙሉ ላከናወናቸው ዝግጅቶች እውቅና፣ ሽልማት የተሰጠበት ሲሆን፤ በተለየ ሁኔታ የማኅበረሰቡን ችግር ይፈታሉ የተባሉ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን ለሠሩ ተማሪዎች እና ባለሙያዎች የገንዘብ ሽልማት የተሰጠበት መድረክ ነበር።
በዚህም ቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት በርካታ ባለሙያዎች የሚያፈሩ መሆናቸውም ታይቷል። በተለይ በግብርና ዘርፍ ችግር ፈቺ የሆኑ ፈጠራዎችን ለማኅበረሰቡ ከማቅረብ አኳያ ብዙ ሥራዎች መሠራታቸው ተጠቁሟል።
በተጨማሪ በዝግጅቱ ላይ የአዲስ አበባ ሥራ እና ክኅሎት ቢሮ የሠራቸው የፈጠራ ሥራዎች በቪዲዮ መልክ ለታዳሚ ቀርቧል። ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የተላበሱ፣ በሁሉም መስክ ቀላል እና ችግር ፈቺ በመሆን የማኅበረሰቡን የእለት ተዕለት ሕይወት የሚያቀሉ የፈጠራ ውጤቶች ታይተዋል። ለአብነት ከነባሩ የዳቦ መጋገሪያ በተለየ መንገድ በአንድ ሰዓት ውስጥ በርካታ ዳቦዎችን የሚጋጋር የዳቦ ማሽን፣ በግብርናው ዘርፍ ላይ ምርትን የሚያቀላጥፍ መሳሪያ እንዲሁም ሌሎች የፈጠራ ውጤቶች ቀርበዋል።
በአስራ አንድ ወራት ብቻ ሶስት መቶ አርባ ሺህ የከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ እድል ማግኘታቸው በመድረኩ ላይ ተነስቷል። በሴፍቲኔት ፕሮግራም የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመውሰድ የራሳቸው የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው ሲገለጽ፤ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ በመደበኛ እና አጫጫር ስልጠናዎቹ በተጨማሪ የካይዘን ሥልጠና እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፎች ለኢንተርፕራይዞች ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ የሥራ እና ክኅሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ፤ ኢትዮጵያ በርካታ የፈጠራ ባለሙያዎች ያሉባት ሀገር ናት። እድልና ሁኔታዎች ቢመቻቹላቸው መሥራት እና የመፍትሄ አካል መሆን የሚችሉ ተማሪዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ ባለፉት አስራ ሁለት ወራት የታየው ይኸው ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በከተማዋ የተሠሩ እና እየተሠሩ ያሉ ልማቶች፣ ማበልጸጊያ ማዕከላት፣ የኮሪደር ልማት ሁሉም ላይ የአዲስ አበባ የሥራ እና ክኅሎት ቢሮ እጅ አለበት።
በከተማዋ ልማት እና እድገት ላይ የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ እየሠራ የሚገኘው ቢሮ ወደፊትም ብዙዎችን በፈጠራ ላይ እንዲሳተፉ ያደርጋል ይላሉ።
ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች በመደበኛ እና በአጫጭር ሥልጠናዎች በርካቶችን ከሕልማቸው ያገናኙ ተቋማት መሆናቸውን አንስተው፤ ከነዚህ ስልጠናዎች ጎን ለጎን ባለሙያዎች ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን እንዲፈጥሩ እገዛ እና ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የኢንተርፕራይዝ እና የቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሀመድ ዲጋሊ በበኩላቸው፤ ቴክኒክ እና ሙያ ተቋማትን ከሁለንተናዊ የሀገር እድገት እና ወሳኝ የለውጥ ምዕራፍ ጋር አስተሳስረው ሀሳብ አጋርተዋል። ለአንድ ሀገር እድገት እና ብልፅግና በቴክኒክ እና ሙያ የበቃ ጠንካራ የሥራ ባሕልን የተላበሰ ትውልድ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረው፤ የተፈጥሮ ሀብትን ከሰው ኃይል ልማት ጋር አስተሳስሮ መሄድ አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።
አያይዘውም በዓለም አቀፍ ደረጃ በቴክኖሎጂ የበለጸጉ ሀገራት በሰው ሀብት ስልጠና በተለይ ለቴክኒክ እና ሙያ ልዩ ትኩረት የሰጡ መሆኑን አንስተው፤ ሀገራቱ በሙያ እና ክኅሎት በርካታ እድሎችን ፈጥረው ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች መትረፍ ችለዋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ዓመታት በጀት በመመደብ በከተማ ለሚገኙ የቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት በሰው ሀይል፣ በግብዓት፣ በአሰራር፣ በሥራ ፈጠራ አስተዋጽኦ እያደረገ ሲሆን፤ በዚህም ተጨባጭ ጅምር ውጤቶች እየታዩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ዘንድሮን ጨምሮ በየዓመቱ እየተከበሩ ያሉ የቴክኒክ እና ሙያ ሳምንታዊ አውደ ርዕዮች ዋና ዓላማቸው ሕብረተሰቡ በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን በመረዳት በሀገሪቱ እድገት እና ብልጽግና ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ መሀመድ በኤግዚብሽን ማዕከል ከመቶ ሀምሳ በላይ ቴክኖሎጂዎችን ለአውደ ርዕይ በማዘጋጀት የከተማዋን ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሌጁ ቤተሰቦች፣ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች፣ የመጀመሪያ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ወንዶች፣ የከተማ ነዋሪዎች እንዲጎበኙት መደረጉን አንስተዋል። በመድረኩ በውድድሩ ላለፉ፣ ላሸነፉ በአጠቃላይ ለተግባሩ መሳካት ሚናቸውን ለተጫወቱ ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት ከምስጋና እና ከሽልማት ባለፈ ምስጋና አቅርበዋል።
በተያዘው ዓመት ለአስራ አምስተኛ ጊዜ የተካሄደው የቴክኒክ እና ሙያ ሳምንት ሲከበር በኮሌጆች እየተከናወኑ ያሉ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎችን ሊያሳዩ የሚችሉ የክኅሎት፣ የቴክኖሎጂ፣ የተግባር እና ምርምር፣ ፋሽን ሾው፣ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ እንዲሁም የዘርፉን ስኬቶች እና ተግዳሮቶች ሊያመላክቱ የሚችሉ ጥናታዊ ጽሁፎች በማዘጋጀት በፓናል ውይይት እንዲመከር መደረጉን ጠቁመዋል።
በየደረጃው ላሉ ተወዳዳሪዎች ከእውቅና እስከ ዋንጫ ድረስ ያሉ ሽልማቶች ተሰጥተዋል። በርከት ያሉ ተሸላሚዎችን ያሳተፈው መድረኩ ወጣቶች ከራሳቸው አልፈው ለሀገር ለመትረፍ እያደረጉ ያለውን ትጋት የሚያሳይ ነበር። ሁኔታዎች ከተመቻቹ ችግር ፈቺ እውቀት መኖሩን ያሳየው የሽልማት መርሀ ግብሩ ቀጣዩን ጊዜ ለብዙዎች ምቹ ከማድረግ አኳያ ሚናውን ያሳየበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የማኅበረሰብ ችግር ፈቺ ፈጠራዎች ላይ ብዙዎች እንዲሰፉ እና እንዲበረታቱ ተመሳሳይ ዝግጅቶች አስፈላጊ መሆናቸው በማጠቃለያ መርሀ ግብሩ ላይ የተነሳ ሲሆን፤ በተለይ ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጎችን በመቅረጽ ለሁለንተናዊ ጥቅም ዋጋው የላቀ እንደሆነ ተጠቁሟል። ሽልማት ለነበረው ብርታት እና ጉብዝና የሚደፋ ዘውድ ሲሆን፤ በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ቃል የሚገባበት ጭምር ነው ተብሏል።
ሌሎችን በማበረታታት፣ በማንቃት እና የበለጠ ኃላፊነት እንዲሰማቸው በማድረግ ረገድ በበጎ የሚነሳ መሆኑን ጠቅሰው፤ ‹‹ብሩህ አእምሮ በክህሎት ለበቁ ዜጎች›› የሚለው መሪ ሀሳብ በርካቶችን አነቃቅቶ ለፈጠራ በማትጋት ለሽልማት አብቅቷል የሚል ሃሳብም ተመላክቷል። ብሩህ አእምሮ ክኅሎት የሚዳብርበት፣ ፈጠራ የሚፈልቅበት እንደዚሁም የመልካም ትውልድ መገለጫ ነው። ያለጥርጥር ሀገሪቱ እንዲህ ባሉ መሪ ቃሎች የተቀረጹ፣ የተፈጠሩ፣ የበሰሉ የፈጠራ ባለሙያዎች የሚያስፈልጉበት ጊዜ ላይ ነችም ተብሏል። ጊዜው ለመፍጠርም ሆነ ለመማር ምቹ መሆኑን በመጠቆም፤ መልካም ትውልድ ራሱን በእውቀት እና በክኅሎት የሚያደረጅ መፍትሄ ተኮር ነው የሚል ሃሳብም በውይይቱ ላይ ተሰንዝሯል።
ሀገሪቱ ድሃ እንደመሆኗ መጠን በርካታ ችግሮች አሉባት። ቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ውጤቶች ደግሞ ድህነትን በመቅረፍ የተሻለ እድል በመፍጠር አይነተኛ ሚና አላቸው። እውቀት ከአርነት ያወጣል። የዓለም አዳፋ መልኮች በእውቀት እንደተቀየሩ የሚጠራጠር አይኖርም። ኢትዮጵያም ከችግሯ እንድትላቀቅ የበሰሉ እና የተማሩ ዜጎች ያስፈልጓታል። ለዚህ የማሰልጠኛ ማዕከላት ወሳኝነት አላቸው የሚል ሃሳብም ተመላክቷል።
የቻይና እና የጀርመን የሥልጣኔ መነሻ የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ናቸው። በርካታ ሀገራት አሁን ለደረሱበት የሀያልነት ደረጃ የቴክኒክ እና ሙያን ተጠቅመዋል። በተለይ በፈጠራ እና በክህሎት ደረጃ ሰፊውን ድርሻ የሚይዘው የማሰልጠኛ ማዕከላት ናቸው። ከዚህ አኳያ በሀገሪቱ እየታየ ያለው መነቃቃት ይበል የሚሰኝ እንደሆነ ከቃል በላይ ተጨባጭ ድርጊቶች እያሳዩ ይገኛሉ።
ወጣቱ ተምሮ፣ ሰልጥኖ፣ አውቆ እና በቅቶ ሀገሩን ከድህነት ወገኑን ከችግር ለመታደግ እንደቴክኒክ እና ሙያ ያሉ የብስለት ማከላት በእጅጉ አስፈላጊ ናቸው። ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው ፈጠራ በሁሉም ዘርፍ ላይ ያለ ነው። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በፈጠራ የሚመጡ ናቸው። ለመፍጠር መማር፣ መሰልጠን ደግሞ ያስፈልጋል። እነኚህ የለውጥ ምዕራፎች እንዲቀጥሉ ቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት በአይነት እንዲበዙ በጥራት ደግሞ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደራሽነታቸው ሊሰፋ ይገባል። ሰላም!
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም