
ኢትዮጵያ ውስጥ በዲጂታል ግብይትና ክፍያ ሥርዓት በተከናወኑ ተግባሮች በየዓመቱ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። የ2017 በጀት ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት እንደተመላከተው፤ በዲጂታል የተከናወነ ግብይት በአጠቃላይ 12 ነጥብ 51 ትሪሊዮን ብር ደርሷል። ይህ አኅዝ አምና በተመሳሳይ ወቅት ስድስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ነበር። ይህም ለውጡ ምን ያህል እንደሆነ ያመላክታል።
የምጣኔ ሀብትና የዘርፉ ባለሙያዎችም ለውጡን አበረታች ብለውታል። የዲጂታል የግብይት ሥርዓቱን ከተለያዩ አቅጣጫዎች አንጻር መለካት እንደሚቻል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ ማኅበር ከፍተኛ ተመራማሪ ሞላ ዓለማየሁ (ዶ/ር) ይገልጻሉ። ዲጂታል ግብይት ዓለም በሰፊው የገባበት አሠራር መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ የዓለም አንዷ አካል እንደመሆኗ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂ ለሕዝቧ ማቅረብ አለባት ይላሉ።
ከተጠቀሰው አንጻር በዲጂታል ግብዓት ሥርዓቱ የተፈጸመው ግብይት ከፍተኛ ለውጥ መሆኑንም አስታውቀዋል። ለውጡ ከፍተኛ ቢሆንም እንደ ኬንያ፣ ዑጋንዳና ታንዛኒያ ካሉት የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነጻጻር ወደኋላ የቀረ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ኬንያ የምሥራቅ አፍሪካ የዲጂታል ማርኬቲንግ ማዕከል/ሀብ/ እስከ መባል መድረሷን አስታውቀዋል። ‹‹ይሁንና ኢትዮጵያ ምናልባት ዘግይታ ስለጀመረች እንጂ፤ ከእነዚህ ተጠቃሽ ሀገራት ጋር ያለው አካባቢያዊ ሁኔታ ተመሳሳይ ስለሆነ ከሠራን ከእነርሱ የማንስተካከልበት ምንም ምክንያት የለም›› ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት ካሉት ስጋቶች አኳያ ሲታይ ብዙ ሰዎች ግብይቱ በዲጂታል ቢሆን ይመርጣሉ። ኢኮኖሚውም እመርታዊ ለውጥ እንዲያስመዘገብ እያደረገ በመሆኑ ይህ ሥራ እና አካሔድ ይበልጥ ሊበረታታ ይገባል።
ኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽንን በስፋት የጀመረችው በቅርቡ ሆኖ እንዲህ አይነት እመርታ ማሳየቷ ሕዝቡ ለዲጂታል ግብይቱ ምን ያህል ፍላጎት እንዳለው ይጠቁማል። ይህም ተግዳሮቶች ባይኖሩባት ኖሮ በቀላሉ በማስፋፋት ከዚህ የበለጠ ማከናወን እንደሚቻል ያሳያል።
የዲጂታል ማርኬቲንግና የዲጂታል ፋይናንስ መሠረተ ልማቱ በከተሞች በተለይም በዋና ዋና ከተሞች ላይ ብቻ ትኩረት ማድረጉን ጠቅሰው፤ የገጠሩ ሕዝብ ከመሠረተ ልማት አለመስፋፋት ጋር ተያይዞ በአብዛኛው የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንዳልሆነም ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በከተማ የሚኖረው የሀገሪቱ ሕዝብ 20 በመቶ በታች ሆኖ ሳለ የዲጂታል ግብዓቱ በዋና ዋና ከተሞች ላይ የተገደበ ነው፤ 80 በመቶ ያህሉን የገጠር ሕዝብ ተጠቃሚ አላደረገም። መሠረተ ልማቱን በደንብ በማስፋፋት የገጠሩን ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል።
ዲጂታል ግብይቱ በራሱ የሚያመጣቸው ስጋቶች እንዳሉም ጠቁመዋል። ኢንተርኔት በአስተማማኝ እንዲኖር ማድረግና ተዓማኒነትን መገንባት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል። ይህ ተደራሽነት ከተስፋፋ የዲጂታል ግብይቱን ሙሉ ለሙሉ የመቆጣጠር አቅም እንዳለ በየጊዜው እየተመዘገበ ካለው ለውጥ መገንዘብ እንደሚቻልም ያስረዳሉ።
በዲጂታል ዙሪያ የዳበረ ልምድ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ በዘርፉ በራስ ነባራዊ ሁኔታ ለመሥራት ዕድሉ እንዳለ ተናግረዋል። ሀገሪቱ ካላት የሕዝብ ብዛት አንጻር ለውጡ ትንሽ ቢመስልም በጥቅሉ ሲታይ ትልቅ እመርታ የተመዘገበበት ነው ብለዋል።
የዓለም አቅጣጫ ዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት ነው። በኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ የመጣውን ለውጥ በማጠናከር የኢኮኖሚ እድገቱ እንዲቀጥልና የተሳለጠ እንዲሆን ማደረግ ይቻላል። የዲጂታል ግብይቱ የዲጂታል ኢኮኖሚው መሠረት ነውና ዲጂታል ኢኮኖሚ መገንባት የተሻለና የተረጋጋ የኢኮኖሚ እድገትና ለውጥ እንዲኖር ያደርጋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ብዙ ሰዎች ወደ ዲጂታል ግብይቱ መቀላቀላቸው ትልቅ አቅምና አጋጣሚ ፈጥሯል። ሀገሪቱ ይህንን በመጠቀም የተሻለ ማድረግ ይጠበቅባታል። ለእዚህም ተዓማኒነት ያለው የዲጂታል ግብይት ማከናወን ያስፈልጋል። ቴክኖሎጂ በራሱ ተግዳሮቶች ሊኖሩት እንደሚችል ጠቁመው፤ እርሱን በቀላሉ እየፈቱ መሄድ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ሞላ ዓለማየሁ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ ተደራሽነት ማስፋት፣ የኢንተርኔት ከሳይበር ደኅንነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አስፈላጊ ነው። አንዳንድ ጊዜ የሳይበር ጥቃት በማንኛውም ጊዜ ሊፈጸም ይችላልና ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ተዓማኒነት በመጨመር ላይ ትኩረት አድርጎ ግንዛቤ ከመስጠት ጀምሮ መሥራትም ይገባል። አብዛኛው የሀገሪቷ ሕዝብ ያልተማረ መሆኑንም ጠቅሰው፣ በእዚህ ላይ መሥራትና ተደራሽነትን ለማስፋት መሠራት አለበት።
የኢንተርኔት ተደራሽነትን ማስፋት፣ ተዓማኒነትን መገንባትና የሳይበር ደኅንነት ላይ መሥራት ወሳኝ ናቸው የሚሉት ተመራማሪው፤ ለዚህም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የዓለም አቀፉ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ግሎባል ቴክኖሎጂና ዲጂታል ሶልሽን ባለሙያ አበበ በቀለ (ዶክተር) በበኩላቸው ዲጂታል ግብይት ምርቶችን ወይም አገልግሎቶችን በበይነ መረብ በሌሎች ዲጂታል ቴክኖሎጂ የፍለጋ ሞተሮች (ሰርች ኢንጂን) ማኅበራዊ ሚዲያ፣ ኢሜልና ሞባይል መተግበሪያዎች የመሳሰሉት በመጠቀም የማስተዋወቅና የመሸጥ ሂደት የሚከናወንበት እንደሆነ ያብራራሉ።
የ2024 ዓለም አቀፍ የዲጂታል ማስታወቂያ ገበያ መጠን ሪፖርትን ዋቢ አድርገው ሲያብራሩ እንዳሉት፤ እ.ኤ.አ 715 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ2019 አንድ ነጥብ ዜሮ ሰባት ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ ይጠበቅ ነበር። ይህም ልዩነቱ በዓመት 8 ነጥብ አንድ በመቶ አካባቢ እድገት እንዳለው ያሳያል።
የዓለም ከተሞች የኢንተርኔት መረጃን ዋቢ አርገው ሲያስረዱ እንዳሉትም፤ እ.ኤ.አ 2024 በዓለም ዙሪያ ከአምስት ነጥብ 19 ቢሊዮን በላይ የበይነ መረብ ተጠቃሚዎች አሉ። ይህም ከዓለም ሕዝብ ስልሳ አምስት በመቶ ያህሉ የበይነመረብ ተጠቃሚ ነው።
መረጃው እንደሚያመላክተው፤ በአፍሪካ እ.ኤ.አ 2023 የበይነ መረብ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ540 ሚሊዮን በላይ ነበር። ይህም ከአጠቃላይ ሕዝቡ ከ40 በመቶ በላይ ተጠቃሚ መሆኑን ያሳያል። የአፍሪካ የሞባይል ስልክ ግንኙነቶችም እንዲሁ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ነው። ይህም ለዲጂታል ግብይት ትልቅ ለውጥ ፈጥሯል። ከአፍሪካ ሀገራት ናይጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪካና ኬንያ በዲጂታል ግብይቱ በፍጥነት እያደጉ ናቸው።
የዲጂታል 2025 መረጃ እንደሚያመላክተው፤ በኢትዮጵያ የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር 66 ነጥብ 7 ሚሊዮን ደርሷል። ይህም የኢኮሜርሱን እድገት ለማፋጠን ትልቅ ሚና ይጫወታል ሲሉ አስረድተዋል።
የንግድ ድርጅቶችም ቀስ በቀስ የዲጂታል ግብይትን ጠቀሜታ እየተገነዘቡ መምጣታቸው በሀገሪቱ ዲጂታል ሥርዓት ውስጥ ትልቅ እመርታ እያመጣ ነው ሲሉ ባለሙያው ተናግረዋል። በወጣቱ ዘንድ ያለው የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ከፍተኛነት፤ እንደ ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ኢንስታግራም የመሳሰሉትን በመጠቀም የሚከናወኑ ዲጂታል ግብይቶች በጣም ብዙ ተደራሽነት እንዲያገኙና ከተለመደው የግብይት ሥርዓት በተለየ መልኩ እየሰፉ እንዲሄዱ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ባለፉት ጊዜያት በኢትዮጵያ የተከናወነው ዲጂታል ግብይት አዎንታዊና የሚያበረታታ ለውጥ የተመዘገበበት ነው። ዲጂታል ግብይቱ እየጨመረ መምጣቱ የቴክኖሎጂ ተደራሽነት እየሰፋ፣ የሸማቾች ባሕሪ ወደ ዲጂታል እየተቀየረ መሆኑንና የንግድ ድርጅቶችም የዲጂታል ግብይቱን ጠቀሜታ መገንዘባቸውን ያመለክታል። በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው የሞባይል ተጠቃሚ ቁጥር ከጠቅላላው ሕዝብ 63 ነጥብ ስምንት በመቶ መድረሱ ለለውጡ ትልቅ አስተዋፅዖ አለው።
ለውጡም ለኢኮኖሚው እድገት ወሳኝ ከመሆኑም በላይ በአጠቃላይ አዳዲስ የንግድ ድርጅቶችን የሚፈጥርና የውድድር አቅም የሚያሳድግ መሆኑን የግሎባል ቴክኖሎጂና ዲጂታል ሶልሽን ባለሙያ ያመላክታሉ። ይህ ማለት እድገቱ ያለምንም እንከን በዘላቂነት ይቀጥላል ማለት እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ ለማስቀጠልና የበለጠ ለማሳደግ ጥንቃቄ የተሞላበት ትግበራ እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ፤ በርካታ የዓለም ሀገሮች የዲጂታል ግብይትን ተጠቅመውታል። እንደ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ ያሉ ሀገራት ዲጂታል ግብይትን በማስፋፋታቸው ከፍተኛ እድገት አስመዝግበዋል።
እነዚህ ሀገራት ላይ ለመድረስ የተቀናጀ አሠራር፣ የመንግሥት ድጋፍ፣ የሸማቶችን መብት የሚያስከብሩ ጠንካራ የሕግ ማሕቀፎችና የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ያስፈልጋሉ። ለውጡን ይበልጥ ለማፋጠን የመሠረተ ልማት ግንባታ በማጠናከር አስተማማኝና ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት በስፋት ማድረስ፣ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶችንና የዲጂታል ክህሎትን ማስፋፋት፣ ኢኮሜርስና የኦንላይን ንግድን በደንብ ማበረታት እንዲሁም የኦንላይን ግብይቶችን ደኅንነት ማስጠበቅና ማረጋገጥ እጅጉ ያስፈልጋል።
በመንግሥት በኩል ምቹ የሆኑ ፖሊሲዎችን በመፍጠር የዲጂታል ለውጡን የሚያግዙ ፖሊሲዎች የማውጣቱ ሥራ መጠናከር እንዳለበት ገልጸው፤ አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ድርጅቶች በዲጂታል ንግድ ግብይት እንዲሳተፉ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ መስጠት እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል። የፈጠራ ቴክኖሎጂዎችን ትብብር ማጎልበትና ማበረታታት በጣም አስፈላጊ መሆኑንም ያነሳሉ። በባለድርሻ አካላት መካከል ቅርብ የሆነ ትብብር መፍጠር የዲጂታል ግብይትን ለማፋጠን ትልቅ ሚና እንዳለውም ይገልጻሉ።
በተጨማሪም በዲጂታል ግብይት ላይ የታየውን እድገት የተሻለ ደረጃ ለማድረስ የተቀናጀና የረጅም ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመው፤ የሌሎች ሀገራትን ልምድ በመውሰድ ከነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
የ«ጉዞ ቴክኖሎጂስ» መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል ጌታቸው በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይ ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ በዲጂታል ግብይቱ ብዙ ለውጦችና እድገቶች መምጣታቸውን አስታውቀዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ የኮቪድ ወረርሽኝ ተጠቃሚው ወደ ዲጂታል ሥርዓቱ እንዲገባ አስገድዶ ነበር። ያ ወቅት በዲጂታል ግብይት ሥርዓቱ የሚደረጉ የገንዘብ ልውውጦችና ፕላት ፎርሞች እንዲጨምሩ ምክንያት ሆኗል። ወቅቱ ኢንተርኔት ተደራሽነቱ የሰፋበትና የኦንላይን የግብይት ሥርዓቱን የዳበረበት ተጠቃሚነቱም ሆነ ፍላጎቱም የጨመረበት እንደነበር አስታውሰዋል።
ለረጅም ጊዜ ክፍተት የነበረውና ዲጂታል ሥርዓቱ ማነቆ ሆኖ የቆየው የዲጂታል ፋይናንስ አሠራር ሥርዓት መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ የኦንላይን ግብይት ክፍያ መፈጸሚያ መንገዶች የተገደቡ እንደነበሩ አንስተዋል። ካለፉት ሦስት ዓመት ወዲህ ቴሌ ብር ብዙ ነገሮች ይዞ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ይህም ዲጂታል ግብይቱ ይበልጥ እንዲያድግ አድርጎታል። ሰዎች ከተለያዩ ቦታዎች ያላቸው ገንዘብ አምነው መጠቀም ጀምረዋል። ስልክ እንደባንክ አካውንት መጠቀም መቻሉ በራሱ የዲጂታል ሥርዓቱ የፈጠረውና እያሳደገ ያለው ሥርዓት መሆኑን አመላክተዋል።
አቶ ዳንኤል እንደሚሉት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የታየው ለውጥ ተጠቃሚዎች መብዛታቸውና ተደራሽነቱ እየተስፋፋ መምጣቱን ያሳያል። እነዚህ ሥርዓቶች ተዓማኒነታቸው እየጨመረ መጥቶ ሰዎች አምነው መቀበላቸውም ሌላው አመላካች ነው።
አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጭምር አገልግሎታቸውን ዲጂታል ማድረጋቸው ዲጂታል ግብይቱ እንዲጨምር አድርጓል ሲሉ ጠቅሰው፤ ሰዎች አምነው ገንዘባቸውን በዲጂታል ሥርዓቱ የመያዝና የመለዋወጥ ሁኔታው እያደገ መጥቷል ብለዋል። ይህም በየጊዜው እየጨመረና እያደገ የሚመጣ መሆኑንም እንደሚያመላክት ተናግረዋል።
በተለይ ከሌሎች ሀገራት አንጻር ሲታይ ተጨማሪ አዳዲስ ምርቶች መፍጠር የሚችሉ ግብይቶች መፈጸም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ማምጣት ጠቃሚ መሆኑንም ጠቁመዋል። ከውጭ የምናስገባቸው ቴክኖሎጂዎች በብዙ ነገሮች ላይ ጥገኛ መሆናቸውንም አስታውቀው፤ እነዚህንም በሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ በመለወጥ ዕሴት የሚጨመርባቸው አሠራሮችን መከተል ቢቻል የዲጂታል ግብይቱ የበለጠ ሊያድግ እንደሚችል አመላክተዋል።
አቶ ዳንኤል እንዳብራሩት፤ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ሲታይ ከየትኛው ሀገር የሚመጣ ሰው በቀላሉ እንዲገዛና እንዲቀበል የሚያደርግበት እንደ ማስተር ካርድ አይነት ዓለም አቀፍ መገበያያ ሥርዓቶች አሉ። እነዚህን በተወሰነ መልኩ ማላመድ ቢቻል የኢትዮጵያንም እቃዎች ወደ ውጭ የመሸጥ ወይም ወደ ሀገር የማስገባትና ማስወጣት የሚደረግበት ምርት ተመጣጣኝ እንዲሆን ያስችላል ሲሉ ጠቁመዋል።
አብዛኛው የዲጂታል ግብይት ሥርዓት ከተማ ላይ የተወሰነ መሆኑን አቶ ዳንኤልም ያመላክታሉ። ይህን ለመለወጥ በዘርፉ የሚሠሩ ባለሀብቶች መብዛትና በሌሎችም አካባቢዎች መሥራት መቻል እንዳለባቸው ጠቁመዋል። የፕላትፎርሞች መሻሻል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
እንደ አማዞን ያሉ ብዙ ሚሊዮን ተጠቃሚ ያላቸው የውጭ ሥርዓቶችን ማላመድ እንደሚገባም ጠቁመዋል። ከመደበኛ ኤክስፖርት ከሚደረጉ ምርቶች ውጪ አንዳንድ ፈጠራ የታከለባቸው እቃዎች ወይም ምርቶች ኢትዮጵያዊ የሆኑ ነገሮችን በአንድ ላይ ሰብሰብ የሚያደርጉ ፕላትፎርሞች ቢኖሩ ደግሞ በቀላሉ የተሻለ እድገት ማምጣት ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል።
በወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም