ኃይሉ ሣህለድንግል
ምስጢር ድብቅ ነገር ነው::“ምስጢር የባቄላ ወፍጮ አይደለም” በሚል ማህበረሰቡ ውስጥ በስፋት ይነገራል::በመሆኑም ምስጢር ጮክ ብለው የሚናገሩት አይደለም። በምልክትም የሚናገሩት እንጂ ፣ ቱስ የሚሉትም አይደለም። ከንፈርን በሌባ ጣት ያዝ በማድረግ ኡስ … የሚሉት አይነት ነው::ምስጢር በጭራሽ መውጣት መባከንም የለበትም፤ ከምስጢር አነፍናፊዎችም መጠበቅ ይኖርበታል::
ለዚህ ሁሉ የምስጢረኛ ታማኝነት ወሳኝ::ምስጢረኛን እንዴት ማፍራት ይቻላል? መቼም ሁሉም ሰው ምስጢረኛ ሊሆን አይችልም::የምስጢረኛ ማግኛው መንገድ አፈሳ አይደለም፤ ምስጢር መያዝ ስለመቻሉ የሚታመንበት ወይም ምስጢር በመያዝ የሚታወቅ ብቻ ነው ምስጢረኛ ሊሆን የሚገባው::
ለመሆኑ መዝገበ ቃላት ስለምስጢር ምን ይላሉ። የደስታ ተክለወልዱ አዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ምስጢርን ሲተረጉመው ረቂቅ፣ ሰውርና ድብቅ ፣ሽሽግ ፣ ይለዋል::እክሌና እከሌ በምስጢር ይነጋገራሉ፤ ምስጢር ለምስጢር ይተዋወቃሉ፤ “ምስጢር የባቄላ ወፍጮ አይደለም” ሲል ያብራራል ::ምስጢራም ምስጢር ያለው፣ ምስጢር የያዘ ይለዋል::ምስጢረኛ የሚለውንም ባለምስጢር ፣የጌታውን ወይም የወዳጁን ምስጢር አዋቂ፣ ታማኝ ፣ ባለሟል፤ ባልንጀራ ይለዋል::
የእንግሊዝኛው መዝገበ ቃልም እንዲሁ ምስጢርን በጥቂቶች ብቻ የሚታወቅ፣ሌሎች እንዳያውቁት የተደረገ መሆኑን ያመለክታል::በአንድ ነገር ስኬታማ ለመሆን ብቸኛው ወይም ተመራጩ መንገድ ሲልም ያብራራዋል::
የምስጢርና ሚስጢረኛ ፍቺ ይህ ሆኖ ሳለ ግን ምስጢኛ ወጣ ሲባል ይሰማል::በሀገራችን ምስጢር የሚያወጣ እንደ ወንፊት ይቆጠራል፤ የማይቋጥር ማለት ነው::ምስጢር ከሚስጢረኞች በአንዱ ካፈተለከ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል::ምስጢረኛውንም እምነት ያሳጣል::
በአንድ ወቅት ምን ሆነ መሰላችሁ::ምስጢር ያዥ የቅርቤ ላለው ሰው ምስጢር ያለውን ያወራዋል፤ ቱስ አለው ልበል::የነገረው ምስጢር ነው ፤አደራ በምድር አደራ በሰማይ ብሎ ነው::
ምስጢር ተቀባዩም ምሎ ተገዝቶ ምስጢሩን እንዲነግረው ማረጋገጫ ይሰጣል::አብረን አይደል እንዴ የኖርነው፤ ታውቀኛለህ ፤ካልፈለግህም … ተውው ብሎ ሊሄድ ሲል ምስጢሩ ተነገረው ፡፡
ብዙም ውሎ ሳያድር ያ ምስጢር ወጥቶ ተገኘ::ብዙም ሰው የተቀባበለው ሆነ::በሁኔታው የተደናገጠው አደራ ባይ ጨሶ ሁኔታውን ጉድ ሆንኩ ብሎ ለሶስተኛ ሰው ይነግራል። ያ ሰውም ምስጢር አባካኙን ምስጢር ተብሎ የተነገረህን በትነህ እከሌን ጉድ አደርግከው ፤ለምን ይህን አረግህ ሲል ይጠይቀዋል።
ያ ምስጢር አባካኝ / ለነገሩ ችግሩ በአንዱ ላይ ይብስ ይሆናል እንጂ ሁለቱም ምስጢር አባክነዋል፡፡/ ይቅርታ ማለት ሲገባው እሱ መሸከም ያልቻለውን ምስጢር እኔ ምን ቤት ነኝ ተሸክሜ የምቀመጠው ሲል ይመልሳል::ሁለቱም የባቄላ ወፍጮ ሆነዋል::
ወደ ሰፊው ትርጉም ስንወስደው ምስጢር ባለመጠበቁ ሳቢያ ብዙ የተደከመበት የቡድን፣ የመንግሥት፣የሀገር አላማ ከመሳካት ይቀራል፤ወይም ተግዳሮቶች ይበዙበታል። ሰራተኞች የድርጅታቸውን ምስጢር አሳልፈው ሰጥተው ወይም በየሜዳው ዘርተው ከሆነ የድርጅት ምስጢር አባክነዋል ተብለው ይጠየቃሉ፤ሊቀጡ፣ከኃላፊነት ሊነሱ፣ በስራቸውም ላይታመኑ ይችላሉ::እርምጃዎቹ ትክክል ናቸው፡፡
ምስጢር መጠበቅ ፈተናም ነው::አንዳንዱ ፈተና ከቅርብ ሰው ይመጣል::ምስጢር በጥቂቶች መካከል ሊያዝ የሚገባ መሆኑ ተዘንግቶም ይሁን በሌላ ለምን ለእኔ አልተነገረኝም የሚሉ አሉ:: እነዚህ አይነቶቹ ወገኖች ለካስ አንታመንም ፤ሳንተዋወቅ ነው አብረን እየኖርን ያለነው የሚሉበት ሁኔታ ያጋጥማል::ነገ ለምንሰማው ለምናየው ነገር ለምን እንደ ባእድ እንቆጠራለን ? ሊሉም ይችላሉ። ይህን አሉ ተብሎ ግን ምስጢር ሊነገራቸው አይገባም፡፡አደራው ምስጢሩን ከዚህ አይነቱ ፈተና ሁሉ መጠበቅ ነውና::
ምስጢር አዳኙ መብዛቱም ሌላው ፈተና ነው። ምስጢር የሚያዘው ለቡድን ፣ለሀገርና መንግሥት ጥቅም ሲባል ነው። ይህን ምስጢር በሆነ መንገድ ፈልቅቀው በማስወጣት ድርጅታቸውን ለማሳደግ ፣ ወይም ባለምስጢሩን ከአላማው ለማሳት የሚሰሩ በርካታ ናቸው። ምስጢረኞች እነዚህ ወገኖች ወጥመድ ውስጥ ላለመግባት ጠንካራና የማይበገሩ መሆን አለባቸው::ዘመኑ በአንዱ ሥራ ሌላው ለመበልጸግ ሳይተኛ የሚያድርበት እንደመሆኑ የምስጢረኞች አደራ ከፍተኛ ነው::
በዚህ ውድድር በበዛበት ዓለም ምስጢር እንኳን ሳይጠብቁት ጠብቀውትም ተፎካካሪ ድርጅቶች ምስጢር በእጃቸው አለ ተብለው የሚታሰቡ አካላትን አማለውም ይሁን አሞኝተው ወይም አስገድደው ምስጢር ለመስረቅ አጥብቀው ይሰራሉ::ይህን ለመከላከል ምስጢርን ብቻ ሳይሆን ምስጢረኞችን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡
በምስጢር መውጣት ሳቢያ ሀገርና ህዝብ በእጅጉ ሲጎዱ ይታያል::በሀገራችን እያሻቀበ ያለው የሸቀጦች ዋጋን እኔ ከምስጢር መባከን ጋር አያይዘዋለሁ::በሀገራችን የብዙ ሸቀጦች ዋጋ ከነዳጅ እና ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ጋር እንደሚያያዝ ይታወቃል::መንግሥት ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ የነዳጅ ዋጋ ለመጨመር የውጭ ምንዛሪ ክለሳ ለማድረግ ገና መምከር ሲጀምር መርካቶ ላይ የዋጋ ጭማሪ ይከሰታል::
ነጋዴዎቹ ገና ምክክር ሲጀመር ዋጋ ሊጨምር ይችላል፤ በሚል እሳቤ እቃ መደበቅ ከዚህም አልፎ ዋጋ መጨመር ውስጥ ይገባሉ::ህገወጥ ነጋዴዎች ይህን ለምደውታል። በኋላ መንግሥት በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ሲያደርግ ደግሞ ሌላ የዋጋ ጭማሪ ያደርጋሉ፤ ይችኛዋ ደግሞ ቦነስ ትሆናለች።
ያው ነጻ ገበያ ነው፤መንግሥት በእያንዳንዱ ዋጋ ትመና ውስጥ አይገባም::ነጻ ገበያ ነው ብሎ ግን ነገር አለሙን በሙሉ እርግፍ አድርጎም አይተውም::በነዳጅና በአንዳንድ የሸቀጦች ምርቶች ዋጋ ላይ ድጎማ እና የውጭ ምንዛሪ የሚያቀርብ እንደመሆኑ በተወሰኑ ሸቀጦች ዋጋ ላይ ጣልቃ ሊገባ የሚችልበት ሁኔታ አለ::ስኳርንና ዘይትን በአብነት መውሰድ ይቻላል::
ነጋዴው ግን ከዚህ በመለስ ያለውን ሸቀጥ ዋጋ እንደፈለገው ሲተምን ኖሯል::የህገ ወጥ ነጋዴው ሰንሰለት እኮ እኔ ነኝ ያለ ፓርቲ ሰንሰለት አይስተካከለውም፡፡የመርካቶ ዋጋ ያለምንም መገናኛ ብዙሃን እርዳታ ታችኛዋ መደብር ትደርሳለች፡፡
ይህ ሁሉ የሚከሰተው አንዳንድ የመንግሥት ባለስልጣናት ከነጋዴው ጋር ባላቸው ትስስር ነው::ነጋዴው በሸቀጡ እነሱ በያዙት ምስጢር ይተሳሰራሉ::ባለስልጣናቱ በሆነ መልኩ ነጋዴዎች ናቸው ተብሎም ይታሰባል፤ በዘመድ አዝማድ፣ በጓደኛ፣ ወዘተ. መሞዳሞድ /ሙስና/ ደግሞ ሌላው ነው ይባላል፤ የመጣንበት አጠቃላይ ሁኔታም የሚያመለክተውም ይህንኑ ነው::
ባለስልጣናቱ ምርት ደብቁ ፤ዋጋ ጨምሩ ብለው ይናገራሉ ተብሎ አይታሰብም፤ያንን የሚመስል ሰውር ነገር ግን ያደርጋሉ። ይህ ደግሞ ለህገወጥ ነጋዴ ትልቅ መረጃ ነው::
ህዝብ በዋጋ ንረት የሚሰቃየው አንድም የመንግሥት ምስጢር በዚህ መልኩ እየወጣ ነው ፤ ስቃዩ ህዝብ ላይ አይቆምም:: ህዝብን ገዝግዞ ገዝግዞ እየዳኸም ቢሆን ወደ መንግሥት ይተላለፋል:: መንግሥት ህዝቡን ከዋጋ ንረት ለመታደግ ከፍተኛ ዋጋ እስከ መክፈል ይደርሳል። እስከ አሁንም የዘርፉን ችግሮች እየፈተሸ መፍትሄ ሲያፈላለግ ኖሯል። የሚቀረው ግን አለ::ያልፈተሻቸውን ምስጢረኞቹንም መፈተሸ::መንግሥት ሆይ! ምስጢረኞችህንም ፈተሽ!!
አዲስ ዘመን መጋቢት 14/2013