እንዳለ ሀይሌ (PhD)
በግንቦት 2013 የሚካሄደው 6ኛው ብሔራዊ እና ክልላዊ ምርጫ ሀገራችንን አንድ እርምጃ ወደፊት ሊያራምድ ይችላል ብለው ከሚያስቡት (Optimist) አንዱ ስሆን፤ የተፎካካሪ ፓርቲዎቻችን ስለ ድህነታችን ወይንም ስለ ኋላ ቀር ዴሞክራሲያችን የሚነግሩን መሆን የለባቸውም። በእጃችን ስላሉ እድሎችና እነዚህን እድሎች እንዴት መጻኢ እድላችንን ሊወስኑ እንደሚችሉ (Future Oriented) የሚነግሩንና የሚያሳምኑን ፖለቲከኞች ሊሆኑ ይገባል። ከዚህ አንጻር የትኩረት አቅጣጫዎች ከፖለቲካ ከኢኮኖሚ እና ከማህበራዊ ጉዳዮች አንጻር ማየት ጠቃሚ ስለሚሆን ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጉዳዮችን በዚህ ጽሁፍ ለመዳሰስ ይሞክራል።
ከፖለቲካው አንጻር ሲታይ ኢትዮጵያ የብዙ ክፍለ ዘመናት ታሪክ ሀገር እንደሆነች በርካታ ማስረጃዎች ይነግሩናል። ሆኖም ግን የእድሜያችንን ያህል አሁን ዓለም ካላችበት እጅግ በጣም ወደ ኋላ ቀርተናል። በኢኮኖሚ መስኩም ይሁን በሌሎች ዘርፎች ወደ ኋላ ለመቅረታችን ተጠያቂው ፖለቲካውና ፖለቲካውን የሚዘውሩት አካላት ናቸው። የዚህ ጽሁፍ መነሻም የባለፈውን ለመወቀስ ሳይሆን ዛሬ ላይ ያሉ መሪዎቻችን ወይም በቀጣይ ለስልጣን የሚፎካከሩ ፓርቲዎችም ይሁኑ ግለሰቦች ዛሬ ላይ ቆመው ወደፊት ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያን እንዴት መገንባት እንዳሰቡ ሊነግሩን ይገባል። ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊ ስርአት መገንባት ሳንችል በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ዘላቂ ልማትና እድገት ልናመጣ አንችልም። ምንም እንኳን ያለ ዴሞክራሲ እድገት ያረጋገጡ ሀገራት ቢኖሩም፤ ለሀገራችን ዋቢ ሊሆኑ አይችሉም። የኢትዮጵያ የሁሉም ችግሮች ማጠንጠኛ የዴሞክራሲ እጦት ነው። በሀገራችን ዴሞክራሲ ሲረጋገጥ የተረጋጋ ሰላም መፈጠር ይቻላል። ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አቅም ይፈጥርልናል። በዜጎች መካከል የተመጣጠነ እና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ይኖራል። የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማስፋት ይቻላል። ዜጎች በፈለጓቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ተንቀሳቅሰው የመስራት እድል ይፍጥርላቸዋል።
ዛሬ በለጸጉ የምንላቸው እና የተሻለ ዴሞክራሲን የገነቡ ሀገራት ለምሳሌ አሜሪካ እንደ ሀገር በማትታወቅበት ሰዓት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ነበረች። በአንድ ወቅት አሜሪካ በእርሰ በርስ ጦርነት የምትናጥ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች ነግሰውባት የነበረ የበርካታ ደሀ ዜጎች ሀገር ብቻ ሳትሆን የሰዎችን እኩልነት በዘር እና በቀለም ልዩነት የምታደርግ ሀገር ነበረች። ዛሬ ላይ አሜሪካ ለደረሰችበት እድገት ባለ ራእይ መሪዎቿ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። የዛሬዋ ቻይናና ደቡብ ኮሪያ ከኢትዮጵያ በከፋ ድህነት ውስጥ የነበሩ በአንጻሩ ኢትዮጵያ በተሻለ ቁመና ላይ የምትገኝ ሀገር ነበረች። ስለዚህ የአሁኑም ይሁኑ የወደፊት መሪዎቻችን ለምርጫ ሲፎካከሩ ደምን ወይንም ጎሳን ማእከል ከሚያደረጉ አስተሳሰብን የትግላቸው የስበት ማእከል ቢያደርጉ በአጭር ጊዜ ትርፋማ ላይሆኑ ይችላሉ። ምክንያቱም የጎሳ ፖለቲካ በአጭር ወጪ ትርፋማ ሊያደርግ ይችላል። ነገር ግን ዘላቂ ዋስትና ግን ሊሆን አይችልም። ስለዚህ ለምርጫ ተፎካካሪዎች በማንፌስቷቸው ትኩረት የሚያደርጉበትን የፖለቲካ የኢኮኖሚ ወይም የማህበራዊ ጉዳይ በደንብ ለይተው ሊያቀርቡልን ይገባል። በዚህ ረገድ የሀገራትን የእድገት ሁኔታ ስናይ ለምሳሌ ሲንጋፖር በእጇ የነበረውን ጉልበት ካፒታል ቁስ እና ገበያ እንዴት ወደ ኢኮኖሚያዊ እድገት እና ሀብት መፍጠር እንደሚያስችላት በማቀድና ወደ ተግባር በመለወጥ ዛሬ ለደረሰችበት እድገት መሰረት ሆኗታል። (The real voyage of discovery consists not in seeking new landscapes but in having new eyes.—MARCEL PROUST) ጃፓን በ1950ዎቹ የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ከሜክሲኮ እና ከካምቦዲያ ያነሰ ነበር። ሆኖም ግን የስራ ባህላቸውን በመቀየር ትላልቅ እንደስትሪዎችን በማቋቋም እና የውጪ ገበያን በአግባቡ በመጠቀም ከአሜሪካ እርዳታ ጋር በአንድ ዘመን ከአሜሪካ በመቀጠል ባላ ግዙፍ የኢኮኖሚ ባላቤት የነበረችበትን ሁኔታ ማንሳት ይቻላል።
በአንጻሩ የኛ ሀገር አብዮቶች መንግስታትን ወይም መሪዎቻችንን ከመለወጥ ባሻገር የህዝብን ኑሮ በመለወጥ ወይም ሀገራዊ እድገት በማምጣት ረገድ የነበረው ሚና ዝቅተኛ ነው። ሀገራችን መለወጥ ያልቻለቸው የተፈጥሮ ሀበት እጦት ወይም የተማረ የሰው ሀይል (Talent) ወይም የሚሰራ እጅ ስለጠፋ ሳይሆን መሪዎቻችን ለስልጣን የተደረገውን ሩጫ ከጨረሱ በኋላ ስልጣናቸውን እንዴት ማቆየት እንደሚችሉ የሴራ ንድፈ ሃሳብ ላይ በመጠመድ ሌላውን ማየት ይሳናቸዋል። ስለዚህ የዛሬ ተፎካካሪ ፓርቲ የነገ የሀገር መሪዎች ከትንሽ ነገር እስከ ትልቅ ጉዳይ ሀገርን እንዴት ማሻገር እንደሚችሉ ሊያስቡ ይገባል።
በእኔ እይታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ትኩረት መስጠት ካለባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል አንዳንዶቹን መጠቋቋም እወዳለሁ። በዚህ ረገድ ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የፖለቲካ አብዮት ሳይሆን የሚያስፈልገን የኢኮኖሚ አብዮት ነው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በርካታ የፖለቲካ አብዮቶች አካሄደናል። ሆኖም ግን የፖለቲካ አብዮቶቹ የኢኮኖሚ አብዮት ሲፈጥሩ አይስተዋሉም። ስለዚህ የቀጣይ ምርጫ ውጤትም የኢኮኖሚ አብዮት እንጂ የፖለቲካ አብዮት እንዲያመጣ አንመኝም። ስለዚህ በምርጫው ተፎካካሪ ፓርቲዎቻችን የሀገር ልማት ያለ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ (Innovation) ሊተሳብ የሚችል ጉዳይ አይደለም። በዓለም ላይ ግንባር ቀደም ወይም ሀያላን ሀገራት የምንላቸው ለቴክኖሎጂ እና ለፈጠራ ትኩረት በሰጡት ልክ ነው። ለምሳሌ በአንድ አሜሪካና ጎሬቤቷ ሚክሲኮ በኢኮኖሚ መመዘኛ ተቀራራቢ የነበሩበት ሁኔታ ነበር። ሆኖም ግን አሜሪካኖች ለቴክኖሎጂና ለፈጠራ እጅግ በጣም ትኩረት በመስጠታቸው ዛሬ ላይ ላሉበት ከፍተኛ ልዩነት ምክንያት መሆን ችሏል። ይህን ጉዳይ አንዳንድ ጊዜ የሚረዳን አካል ላናገኝ እንችል ይሆናል። ነገር ግን ሀቅ ነው። ለምሳሌ በአንድ ወቅት ሞ ኢብራሂም የሚባሉ በብርቲሽ ቴሌኮም ዳይሬክተር የነበሩ በአፍሪካ ቴሌኮም ልገነባ ነው ስል ብዙ ሰዎች ሳቁብኝ (It is not an easy thing to be laughed at by a serious people, and serious people laughed at me when I told them I wanted to build a telecommunication network in Africa twenty years ago, they told me the reason the project will never succeed, somehow, I just kept thinking, I know there are challenges but why can’t they see the opportunity) እንዳሉት እኛም ይህን ጉዳይ ስናሰቀደም የሚስቁብን ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት አይከብድም። ስለዚህ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ገበያ ይፍጥራሉ። ገበያ በድርሻው ለቴክኖሎጂ እና ለፈጠራ የድርሻውን ሊያበረክት ይችላል።
በሁለተኛ ደረጃ ትከረት ሊደረግበት የሚገባው ጉዳይ የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ነው። (Liberalizing states will have to actively create the institutional structures within which market economies operate and redefine the particular rights, entitlements, and responsibilities that underlie economic activity- William Roy) ደሀ ሀገራት ደሀ የሆኑት ምቹ ጂኦግራፊ ወይም የስራ ባህላቸው ደካማ ስለሆነ ወይም ጭንቅላት ስለሌላቸው አይደለም። ይልቅስ ፖለቲከኞቻቸው ዴሞክራሲን ከወረቀት ባለፈ እውቀት ስለሌላቸው ነው። ስለዚህ በዚህች ሀገር ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባትም ይሁን ሀገርን ለማሻገር ለመንገድ ወይም ለጤና ተቋማት ወይም ለትምህርት ቤቶች በሚሰጣቸው ትኩረት ልክ ለዴሞክራሲ ተቋማት ትኩረትን ይነፍጋል። ይህ ማለት አንድ ኮምፒዩተር (ወይም ሀርድ ዌር) ያለ ሶፍትዌር እንደማይሰራ ሁሉ መሰረት ልማት ግንባታ ብቻውን ያለዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ሀርድ ዌር ያለሶፍት ዌር ማለት ነው። ለምሳሌ ናሬንድራ ሞዲ ወደ ስልጣን እንደመጡ የህንድ ዜጎች ከአስሩ አንድ ዜጎች በተቅማጥ ይሞቱ ነበር። ስለዚህ እርሳቸው ይህን ችግር ለመፍታት በ2014/15 አስር ሚሊየን ሽንት ቤት አስገነቡ። ነገር ግን በአመቱ አጋማሽ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ሽንት ቤቶቹን ሲጎበኙ አብዛኛዎቹ ሽንት ቤቶች ተጠቃሚ አልነበራቸውም። ይልቅ ዜጎች የተጠቀሙት ማታን ተገን አድርገው ክፍት ቦታን ነበር። ምክንያቱም የሚመለከታቸው አካላት ለህብረተሰቡ ስለ ሽንት ቤት አጠቃቀም፤ ትምህርት አልሰጡም ነበር። ከዚህ የምንወሰድው ትምህርት የሽንት ቤት ግንባታ ብቻውን በቂ ሁኔታ ስላለነበር በተቅማጥ በሽታ የሚሞቱትን አልቀነሰም። ይልቅ ከግንባታው ጎን ለጎን ህብረተሰቡን ስለ መጸዳጃ ቤቶች አጠቃቀምም ይሁን ጠቀሜታ ማስተማር ነበረባቸው።
በመሆኑም የመሰረት ልማት ግንባታ ብቻውን ኢኮኖሚያዊ እድገት (Growth) ያመጣ ይሆን እንጂ ዘላቂ ልማትን (development) አያረጋግጥም። ስለዚህ ዘላቂ ልማት ለማምጣት ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ሊረጋጥ ይገባል። ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የዴሞክራሲ ተቋማት ወሳኝ ናቸው። የዴሞክራሲ ተቋማት ስንል ከነጻ እና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ እስከ ገለልተኛ ፍትህ ተቋማት ከሰብአዊ መብት ጥበቃ ተቋማት እስከ ጠንካራ የህዝብ ምክር ቤቶች መኖርን ያጠቃልላል። ስለዚህ ባላፉት 30 ዓመታት እንደ ታዘብነው በአስፈጻሚ አካላት የሚሽከረከሩ ምክር ቤቶች እና የፍትህ ተቋማት በመሆናቸው በህዝብ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነትና ተአማኒነት የወረደ ነው። ስለዚህ መራጩ ህዝብ ፖለቲከኞቻችን ለዴሞክራሲ ተቋማት በሚሰጡት ትኩረት ልክ ሊመዝናቸው ይገባል።
ሶስተኛ ሀገር ግንባታ ነው። (Nation Building) ይህ ጉዳይ ከተቋማት ግንባታ ጋር ተያያዥነት ያለው ጉዳይ ቢሆንም፤ በኢትዮጵያ ሁኔታ ቀዳሚ እና ራሱን የቻለ የምርጫ አጀንዳ ሊሆን ይገባል። ሀገር ግንባታ ወይም ሀገረ መንግስት ግንባታ ዙሪያ ላይ በኢትዮጵያ ሁኔታ የተለያዩ ጫፍ እና ጫፍ የወጡ አስተሳሰቦችን እንገኛለን በአንድ ጫፍ የራሱን ብሄር የበላይነት ያረጋገጠ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅኑ በሌላ በኩል የተበጣጠሰች እና አንድነቷ የላላ ኢትዮጵያን በሂደትም ለመበታተን የምትበቃ ኢትዮጵያን ለመመስረት በሚታትሩ ፖለቲከኞች አንዳንዴም መሰሪዎች ትታመሳለች። ይህ ሁኔታ ደርግ ከወደቀበት ጊዜ አንስቶ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣበት እንዲሁም ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ወዲህ ያሉ ጊዜያቶችን ያጠቃልላል። ስለዚህ ፖለቲከኞቻችን እውነተኛ የፌደራል ስርአት በኢትዮጵያ ለማምጣት ምን ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው? እውነተኛ የፌደራል ስርአት ስንል ምን ማለታችን ነው? በቀጣይ ልዩነቶቻችንን (የቋንቋ የባህል የሃይማኖት የጎሳ) አክበረን አንድነታችንን አጠናከረን ወደ ብልጽግና መሻገር በምንችልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ከመንደር አጀንዳ ወጣ ብለው ቢችሉ በዓለም አቀፋዊ (Global) አጀንዳ አዋዝተው ሃሳባቸውን ለምርጫ ገበያ ቢያቀርቡ የቀጣዩ ምርጫ የተሳካ የሽግግር ሂደትን ማሳካት ያስችለናል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 14/2013