«ከአንድ ሁለት ይሻላል» የሚባለው አንዱ ምክንያት ጥምረት መተጋገዝን ስለሚያመጣ ነው፤ ህይወት ትግልም አይደለች፣ ተጋግዘው ካልገፏት ጣዕም አልባ ትሆናለች። እናማ ውሃ አጣጭን ፈልጎ ጎጆ መቀለስና ሦስት ጉልቻን መመስረት የግድ ነው። ከተጠናቀቀ ጥቂት ቀናትን ያስቆጠረው ጥር ወር ደግሞ ለተጋቢዎች ተመራጭ የሆነ፤ እንደውም «የሠርግ ወር» እየተባለ እስከመጠራትም የደረሰ ነው።
ታዲያ በወሩ በርካቶችን አጋብተናል፤ ያላጋባንም መጋባታቸውን በብዙ ምክንያቶች አውቀናል። የተፋቱትም በዚያው ልክ ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል። ሳስበው ግን ለተጋቢዎች ከሚሰጠው የምስክር ወረቀት ግልባጭ የፍቺ ማመልከቻ ሳይኖረው አይቀርም። ምክንያቱም «እገሌ እና እገሊት ተጋቡ» ባሉን ጥቂት ጊዜ ደግሞ «ተፋቱ» ብለው ያስደምሙናል።
ለነገሩ «ሃሳቡን የማይቀይረው የሞተ ሰው ብቻ ነው» ይባል የለ። በህይወት ያለ ሰው በውሳኔው ሊጸጸት አሊያም በሚሆነው ነገር ተስፋ ሊቆርጥ ይችላል፤ እናማ ሃሳቡን ይቀይራል። መልካም የነበረችው ልትቀየር፤ ጥሩ የተባለውም ሊበላሽ ይችላል። ይህ ሲሆን ደግሞ የመጨረሻ አማራጩ ፍቺ ነው። የዛሬ ሰው ለፍቺ የሚያደርገው ፍጥነት ግን ሌላ አማራጭ ያገኘ እንጂ ያጣ አያስመስለውም።
የኩዌቷ ወጣትም ተሞሸረች እንጂ አልሞተችም ነበርና ሦስት ጉልቻዋን በመሰረተች በሦስት ደቂቃዎች ውስጥ ሰማኒያዋን በመቅደድ በሃገሯ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሆናለች። «አጀብ» እያሰኘ ያለው ይህ ጉድ የተፈጸመው ባሳለፍነው ወር ሲሆን፤ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ቀርቦም የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል።
ነገሩ እንዲህ ነው፤ ሙሽሮቹ ህጋዊ ጋብቻቸውን ለመፈጸም ከፍርድ ቤት ተገኝተውና መስፈርቶቹን ሁሉ አሟልተው በዳኛ ፊት ይፈራረማሉ። ስነ-ስርዓቱ ተጠናቅቆ ወደ ቤታቸው ለመመለስ ዕርምጃ በጀመሩበት ደቂቃም ሙሽሪት በፍጥነት ወደ መጣችበት ትመለሳለች። የተፈራረሙ በትን መዝገብ በቅጡ ያልከደኑት ዳኛም በተጠየቁት መሰረት ያልደረቀውን ፊርማ ሰርዘው በደቂቃዎች ውስጥ ፍቺ ፈጽመዋል (እርሳቸውም በሦስት ደቂቃዎች ውስጥ በማጋባትና በማፋታት ታሪካዊ ሳይሆኑ አይቀርም)።
ነገሩ ግራ አጋቢም አስደንጋጭም ነው፤ ግን ግን ሙሽሪትን «ምነው ለፍቺው እንዲህ ቸኮልሽ?» ቢሏት፤ ምላሿ ለበርካቶች ውሃ የሚያነሳ ሳይሆን አይቀርም። ምክንያቱም ሙሽራው ሚስቱን ከእጁ እንዳስገባ ባረጋገጠበት ቅጽበት «ደደብ» ብሎ ሰድቧት ነበርና ነው። ይህ ደግሞ በህግም ፊት ምክንያታዊ ያደርጋታልና የጠየቀችው ፍቺ ውጣ ውረድና ሌላ ተያያዝ ጉዳይ ሳያስፈልገው ተፈጻሚ ሆኖላታል።
ነገሩ በኩዌት የመጀመሪያውና ታሪካዊው ሲሆን፤ በዓለም ደረጃም ፈጣኑ ፍቺ ሳይሆን አይቀርም። ከዚህ ቀደም በዱባይ ጥንዶቹ በተጋቡ በ15 ደቂቃዎች ውስጥ ፍቺ መፈጸማቸው አስደናቂና አነጋጋሪ ጉዳይ እንደነበረም ኦዲቲ ሴንትራል በዘገባው አስታውሷል። ጉዳዩ በማህበራዊ ድረገጾች ላይም ብዙዎች ተቀባብለውታል። በርካቶች ሙሽሪቷን የደገፉ ሲሆን፤ «ሙሽራው በዚያ ፍጥነት ሚስቱን መሳደብ ከጀመረ ምን ዓይነት ህይወት ሊመሩ ነው?» ሲሉም ጠይቀዋል።አንዳንዶች በበኩላቸው «ታዲያ ለ3ደቂቃ ትዳር ለምን የዳኛውን ጊዜ ያባክናሉ?» ሲሉ ነው የተሳለቁባቸው።
የእኔ ጥያቄ ደግሞ ምናልባት እኮ ሙሽሪቷን «ወይዘሮ» የሚል ማዕረጓን አስቀድመን ስሟን ጠርተን ሳንጨርስ ይሆናል በቅጽበት ውስጥ ወደ ፍቺ ያመራችው። ታዲያ የሦስት ደቂቃው ትዳሯ ከዚህ በኋላም ወይዘሮ ያሰኛታል ወይስ፤ ሦስቱ ደቂቃ እንዳልነበር ታስቦ ወደ ወይዘሪትነቷ ትመለስ ይሆን? ምላሹን ለእናንተ።
አዲስ ዘመን የካቲት 4/2011
በብርሃን ፈይሳ