ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
ዛሬ ስለ ሴትና አገር እናወራለን..በማህበረሰባችን ውስጥ ያለችውን ጥንታዊቷን አሁናዊቷን ሴት እያነሳን እናወጋለን። ሴት ልጅ ለአገር ትልቅ እውነት ናት። የአሁኑ የአለም ስልጣኔ የመጣው ከፊት በቀደሙ አሊያም ደግሞ ከኋላ በሚከተሉ ሴቶች ነው እላለሁ። በአሁኑ ሰዓት ሴቶቻቸውን የተጠቀሙ አገራት ህዝባቸውን በብዙ ነገር እየጠቀሙ ይገኛሉ። ለሴት ልጅ ክብር የሌላቸው ደግሞ በተቃራኒው በኋላ ቀርነት ላይ ናቸው። በሴት ልጅ ችሎታና አቅም ከማያምኑ አገራት መካከል አንዷ አገራችን ኢትዮጵያ ናት። በአለም ዓቀፍ ደረጃ ለሴት ልጅ ምቹ ካልሆኑ አገራት ውስጥ አንዷም ሆና በቀዳሚነት ትጠቀሳለች።
በማወቅም ባለማወቅም በሴት ልጅ ላይ በርካታ በደሎችን ስንፈጽም ኖረናል። ሴት ልጅ ተፈጥሯዊና ህገ መንግስታዊ መብቷን እንዳትጠቀም ተደርጋ ለብዙ እልፍ ዘመናት በጭቆና ውስጥ ኖራለች። በፖለቲካው በኢኮኖሚው በማህበራዊ ህይወቷ ሳይቀር የበታች ተደርጋ ለራሷም ለአገሯም እንዳትበጅ በወንዶች የበላይነት ስር እንድትተዳደር ሞራላዊና ስነልቦናዊ ጫናን አሳድረንባታል። ለዘመናት ወንዶችን ስታጀግን፣ ስታሞግስ፣ ስልጣንና ክብርን አለቅነትንም ስትሰጥ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ለሆነችው ሴት ግን ከበታችነት በስተቀር ምንም አልነበራትም። ይሄ ሁሉ ዘመን አልፎ አሁንም ድረስ ይሄ አመለካከት በብዙዎቻችን ዘንድ አለ። ዛሬም ድረስ ሴት ልጅ ከወንድ ልጅ በታች አድርገን የምናስብ ብዙዎች ነን።
ሴት ልጅ ለወንድ ልጅ ሚስት ብቻ ሆና እንድትኖረ የተፈጠረች የሚመስለን እዛም እዚም በዝተናል። ሴቶች ከወንዶች በተሻሉበት አለም ላይ እየኖርን ወንድነትን እንሰብካለን። በነገራችን ላይ በርካታ ጥናቶች ሴት ልጅ ከወንድ ልጅ በብዙ ነገሯ የተሻለች እንደሆነች አመላክተዋል..በማመላከትም ላይ ይገኛሉ። ይሄን እውነት እያወቅን የሴቶችን አቅም የሴቶችን ተፈጥሯዊ ችሎታ ለልማትና አገር መጠቀም ሲገባን መሰረት በሌለው ኋላ ቀር አስተሳሰብ ተመርዘን ሴቶች እንዲህ ናቸው.. ሴቶች አይችሉም፣ ሴቶች አቅም የላቸውም እያልን ወንዝ የማያሻግረንን ተረት እንተርታለን።
የአሁኗ አለም በራስ ወዳድ በሆኑ ወንዶች እንደተገነባች የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው። አለም በወንዶች ቁመትና ወርድ ለወንዶች ብቻ እንድትሆን የተሰራች ናት ብለው የሚያስቡ ብዙ ወንድና ሴቶች አሉ። አንዳንዶች የአሁኑ የአለም ችግርና መከራ ሁሉ የወንዶች የበላይነት የፈጠረው ነገር ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ አለም ከወንድነት ተላቃ ሴትነትን እስካልተላበሰች ድረስ ገና ከዚህም የከፋ ችግርና መከራ ይገጥመናል የሚሉም አሉ። የሆነው ሆኖ ግን የአሁኗ አለም የሴቶች አስተሳሰብ የሌለባት በወንዶች ራስወዳድነት የቆመች ናት የሚለው አባባል ሚዛን ደፍቶ እናገኘዋለን።
አምነን አልተቀበልንም እንጂ በእያንዳንዱ ወንድነት ውስጥ የማናውቃት ስውር ሴት አለች። አምነን አልተቀበልንም እንጂ ሁሉም ወንዶች የሴቶች ንብረት ናቸው። አምነን አልተቀበልንም እንጂ አለምም ታሪኳም በሴቶች ተጽዕኖ ውስጥ ናቸው። ካለ ሴት አገርም ማህበረሰብም ምንም ነው። ለአንድ አገር ስልጣኔ ሴት ከወንድ በላይ ታስፈልጋለች። የእስካሁኑ ክስረታችን፣ የእስካሁኑ ድህነታችን ለሴት ልጅ ክብርና እውቅና ካለመስጠት የመጣ ነው።
ካለሴት አገርም ወንድነትም ምንም ነው። ያለነው በሴቶች እውነት ውስጥ ነው ። ወንድነታችን ይታይ ዘንድ ሴቶቻችን መታየት አለባቸው። ይሄን ሁሉ ዘመን ሴትን ልጅ ለማጀት በሚል የማይረባ አመለካከት ኖረናል። ይሄን ሁሉ ዘመን ሴቶቻችን በልማትና በአገር ጉዳይ ላይ እንዳይሳተፉ አድርገን ኖረናል..ግን በእውቀትም በስልጣኔም ከኋላ ነን። ይሄን ሁሉ ዘመን ካለሴት ብቻችንን ቆመን አልደመቅንም። ሴት ልጅ የሌለችበት አለም ባዶ ናት። ብርሀናችን..ስልጣኔያችን ያለው ሴቶች ጋ ነው። ደምቀን እንታይ ዘንድ ሴቶች ያስፈልጉናል። ደምቀን እናበራ ዘንድ ከሴቶች ጋር መቆም አለብን። ወንድ ልጅ ብቻውን የሚፈጥረው ተዐምር የለም።
ሴቶቻችን ከወንድ እኩል በሁሉም መስክ ላይ መታየት አለባቸው። አሁን ላይ ደስ በሚል ምዕራፍ ላይ ያለን ይመስለኛል….ሴቶቻችን ወደ ስልጣን..ወደ ከፍተኛ የአመራርነት ስራ ላይ እየመጡ ነው። በስንዱ ገብሩ ፓርላማን ከጀመርን በርካታ ዘመናት አልፎናል። ግን የመጀመሪያዋ ሴት የፓርላማ አባል ከመባል ባለፈ ለሴቶቻችን የጠቀመው ነገር የለም። የሚያዋጣው ሴቶቻችን ወደ ስልጣን ወደ ከፍተኛ የአመራርነት እርከን መጥተው ከወንድ እኩል ሲያስቡና ውሳኔ ሲሰጡ ማየት ነው። አሁን ጥሩ ነገር እያየን ነው…በተለያየ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ ከፍተኛ ባለስልጣን ሆነው የምናያቸው በርካታ ሴቶች አሉ..ከዛም በላይ ለፕሬዚዳንትነት በቅተናል። የኔ ህልም ግን ሴቶቻችን አራት ኪሎ ቤተመንግስት ገብተው ማየት ነው። ይሄ እንዲሆን ደግሞ የማህበረሰቡ..የኔና የአንተ የአንቺም አመለካከት መቀየር አለበት። ሴቶች ይችላሉ ብለን ማሰብ አለብን። ሴቶችም እንችላለን ብለው መነሳት አለባቸው።
ሴቶች ከወንዶች የተሻለ የመወሰን፣ የማገናዘብ የማስተዳደርና የማሰብ አቅም እንዳላቸው በብዙ ጥናቶች ተረጋግጧል። በቀላሉ እንኳን ወቅታዊውን የኮሮና ወረርሽኝ ብናየው በሴት የሚተዳደሩ አገራት ቫይረሱን በመቆጣጠር በወንድ ከሚመሩት አገራት የተሻለ ውጤት ያመጡበት ሁኔታ አለ። ይሄ ብቻ አይደለም፤ በሴቶች የሚመሩ አገራት በውሳኔ አሰጣጥ ከሌሎች አገራት የተሻለ እመርታ ላይ ናቸው። አገራችን ኢትዮጵያ በመጪው ጊዜ ሴቶችን ለመካስና በውሳኔ ሰጪነት ላይ በማሳተፍ ለዘመናት ያደረስንባቸውን ግፍና መገለል መካስ አለብን ብዬ አስባለሁ።
የሴቶች ተሳትፎ፣ የሴቶች ሀሳብ የሌለበት ልማትና ብልጽግና መሰረት የለውም። እዚች አገር ላይ ለሴቶች የሚሆን ምንም ነገር የለንም። ሴቶች አይችሉም..ሴቶች ከወንድ ልጅ እኩል አይደሉም እየተባልን ያደግን ሰዎች ነን። በጣም ነው የሚገርመኝ በሆቴል በአስተናጋጅነት የሚሰሩ እህቶቻችን እንኳን ሰውነታቸውን የሚያሳይ አጭር እንዲለብሱ የሚገደዱ ናቸው። በነገራችን ላይ አደባባይ አይውጣ እንጂ የትኛውም ሆቴል አጭር የማትለብስ፣ ሰውነቷን ጭኗን ለመግለጥ ፍቃደኛ ያልሆነችን ሴት ቀጥሮ ማሰራት አይፈልጉም። በሁሉም ሆቴል ቤቶች ሊባል በሚችል ሁኔታ ጭን መግለጥ ሰውነት ማሳየት ለሴት አስተናጋጆች የቅጥር መስፈርት ሆኖ ዛሬም አገልግሎት ላይ እየዋለ ነው። ወንድ ፊት ጭኗን ያልገለጠች ሴት በጭራሽ ስራ አታገኝም።፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ የኢትዮጵያን ባህልና ስርዐት በሚያውቁ፣ ሁለት መልክ ጸጉር ባወጡ አሰሪዎች መገደዳቸው ነው።
አንድ እውነት ልንገራችሁ..የትኛዋም ሴት ጭኗን እያሳየች መስራት አትፈልግም..በዚህ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ ሁሉም አስተናጋጆች በአሰሪዎቻቸው ተገደው ገላቸውን እንደሚያሳዩ ተናግረዋል። በግሌም የጠየኳቸው አንዳንድ አስተናጋጆች ተመሳሳይ መልስ ነው የሰጡኝ። ስንት ባለሙያ፣ ስንት ሸማ ሰሪ ባለጅ ባለባት..ተነፋነፍ፣ ቡሉኮ፣ ጋቢና ነጠላ፣ እጀ ጠባብ በርኖስ ሌላም ሌላም ባለባት አገር ላይ የሁሉም ነገር መሰረት የሆነችን ሴት ወንድ ፊት ራቁትሽን ቁሚ ማለት ከኢትዮጵያዊነት ያፈነገጠ የጭካኔ ማሳያ ነው። ሴት ልጅ የሚያምርባት ስትሸፋፈን ነው፤ ባህላችንም ይሄ ነው። አስኪ አንድ ነገር በምናባችሁ አስቡ..የሀበሻ ቀሚሷን እስከ ተረከዟ የለበሰች ፈገግተኛ አስተናጋጅ በኢትዮጵያዊ ትህትና ምን ልታዘዝ ብላ ፊታችሁ ስትቆም አስቡት።
ይሄ ብቻ አይደለም በኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ሆኜ ስኖር ስለ ሴት ልጅ ጀብድና ገድል የተጻፈ ታሪክ አላነበብኩም። በአድዋ ጦርነት ወቅት እነ እቴጌ ጣይቱ፣ እነጻዲቄ ያን ሁሉ የጀግንነት ተግባር ፈጽመው እንኳን ከወንዶቹ ጋር ሲነጻጸር ስማቸው ደብዝዞ እናገኘዋለን። በነገራችን ላይ የወንዶቹ ጀግንነት እንዳለ ሆኖ የአድዋ ድል በዋናነት በእቴጌ ጣይቱ ብልሀት የመጣ እንደሆነ ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ? በሌላ ቋንቋ ጣሊያን ከአገራችን ተሸንፎ የወጣው በእቴጌ ጣይቱ አስተውሎት ነው እያልኩ ነው። እቴጌ የአድዋ ድልድይ እንዲፈርስ ሀሳብ አቀረቡ..ድልድዩም ፈረሰ..ጣሊያንም ተሸነፈ በቃ እንደዚህ ነው። ከአጼ ምኒሊክ እኩል፣ ከባሻ ዋሉ እኩል፣ ከገበየሁ..ከባልቻም እኩል፣ ከአሉላ አባነጋ እኩል ሴቶች በጦርነቱ ላይ ታላቅ ሚና ነበራቸው። ያለሴት ልጅ ስልጣኔ የለም። ሴቶቻችን ከማጀት ቤት ወደ አደባባይ መውጣት አለባቸው። ተፈጥሮ የሰጠቻቸውን ልዩ መስህብ ለአገርና ትውልድ ይጠቀሙበት ዘንድ እድሉን ማግኘት አለባቸው። ሴት ልጅ ሚስት ብቻ አይደለችም። ሴት ልጅ ብዙ ነገር ናት..ሴት ባለችበት ሁሉ ተዐምር አለ። እዚህ ላይ የሳንቡሩ ሴቶች ያስገርሙኛል..ሳንቡሩ በኬንያ የምትገኝ ትንሽ መንደር ናት..የወንዶች የበላይነት የገነነባት፣ ሴትነት ትርጉም ያጣባት መንደር እንዲህ ናት። በሳንቡሩ ሴትነት ምንም ነው፣ በሳንቡሩ የትኛውም ወንድ ከመሬት ተነስቶ ምንም ነገር ማድረግ ይችላል። በዚህ ቁጭት ተነሳስተው የሳንቡራዊያን ሴቶች አንድ ነገር አደረጉ..ወንዶች የሌሉበትን አሙጃ የምትባልን የግላቸውን መንደር መሰረቱ። አሙጃ የሴቶች የነጻነት መንደር ሆነ በምድረ ኬኒያ ዛሬም ድረስ አለች።
ሴቶች ዝም አትበሉ..ወንዶችን ታገሏቸው። ለክብራችሁ ለነጻነታችሁ ዝም አትበሉ። ያለፍቃዳችሁ ማንም ምንም እንዲያደርግባችሁ አትፍቀዱ። የኢትዮጵያ እናቶች ልጆቻቸውን የሚመክሩት አንድ ምክር አለ ‹የምታፈቅሪውን ሳይሆን የሚያፈቅርሽን አግቢ የሚል። እኔ የሴቶች የበታችነት ከዚህ የሚጀምር ነው የሚመስለኝ። እናቶቻችን ለአባቶቻችን ምን እንደነበሩ ስለሚያውቁት ያ ስቃይ በሴት ልጆቻቸው ላይ እንዳይደገም ‹ያፈቀረሽ ወንድ አይበድልሽም፣ አንቺን ትቶ ሌላ ሴት ጋ አይሄድም› ሲሉ ልጆቻቸው ላይ ጫና ያሳድራሉ። እንዲህ አይነቱ ምክር የሴትን የበታችነት የወንዶችን የበላይነትን አምኖ ከመቀበል ተቀብሎም ለልጅ ልጅ ከማስተላለፍ ባለፈ ጥቅሙ አይታየኝም።
የትኛዋም ሴት ያፈቀረችውን እንድታገባ እየተመከረች ማደገ አለባት። ለባሏ ሚስት ብቻ እንዳይደለች፣ ለራሷም ለሌሎችም አስፈላጊ እንደሆነች እየሰማች ማደግ አለባት። ማህበረሰቡ በተሳሳተ አመለካለት ለወንድ ልጅ የሰጠው የተሳሳተ እውነት ካልሆነ በስተቀር ወንድ ልጅ ያፈቀራትን መርጦ እንዲያገባ የሚያዝ ተፈጥሮም ስርዐትም የለም። እኛው ራሳችን ወንድ የበላይ ሴት የበታች፣ ወንድ አዛዥ ሴት ታዛዝ ብለን ከከፋፈልንበት ኋላ ቀር አመለካከት የመጣ እንጂ በራሱ የሆነ ምንም ነገር የለም።
ወላጆች ያሳለፋችሁትን አጉል ባህል በልጆቻችሁ ላይ ለመጫን አትሞክሩ። አውቃለሁ እናንተ እጅግ አሳዛኝ ትውልዶች ናችሁ..ሳትወዱና ሳትፈልጉ የተጠለፋችሁ.. መማር እየፈለጋችሁ መለወጥ እየፈለጋችሁ በግድ ለማትፈልጉት ነገር የተላለፋችሁ ናችሁ። እናንተ ሳታፈቅሩ ያገባችሁ ናችሁ..ሳታፈቅሩ ብቻ አይደለም ሳትወዱ በግድ የተዳራችሁም ናችሁ ላለፈ ሴታዊ በደላችሁ ልጆቻችሁ ወንዶችን እንዲታገሉ፣ ከጭቆና እንዲወጡ አድርጋችሁ አሳድጓቸው እንጂ በሄዳችሁበት እንዲሄዱ አታስገድዷቸው። ሴት ልጅ ለዚህ አለም ለዚህ ተፈጥሮ ከወንድ እኩል ባለድርሻ ናት። ተፈቅረሽ ሳይሆን አፍቅረሽ፣ ተገደሽ ሳይሆን ፈቅደሽ፣ ተመርጠሽ ሳይሆን መርጠሽ ሚስት ለመሆን ሞክሪ። ሀይልሽን ተፈጥሯዊ መብትሽን ለወንድ ልጅ አሳልፈሽ አትስጪ። አገራችን ኢትዮጵያ ከጥንት እስከዛሬ የሴቶችን የበታችነት የሚያጎሉ በርካታ አባባሎች አሏት። ማህበረሰባችን ለታታሪዋ፣ ለልበ ብርኋ ሴት የሚሆን ምንም የለውም።
በየቤቱ፣ በየመስሪያ ቤቱ፣ በየትምህርት ቤቱ ዛሬም አድሎ ይደርስባታል። ለሴት ልጅ የሚሆን ምንም ሳይኖረን ለእድገትና ለብልጽግና የምናደርገው ሩጫ ይገርመኛል። ሴቶች ያልተሳተፉበት፣ ሴቶች ሀሳብ ያላዋጡበት ስልጣኔ የለም። ወደ ኋላ ተመልሰን የተውናቸውን ሴቶች፣ የረሳናቸውን እንስቶቻችንን ማስታወስ አለብን። እስካሁን ለብቻችን ሮጠን ኋላ ከመቅረት ባለፈ የቀደምንው የለም። መጪው ጊዜ እኛ ወንዶች ከራስ ወዳድነት ወጥተን ከሴቶች ጋር በአንድ የምናብርበት ጊዜ እንዲሆን እመኛለሁ።
ወንድ ለመውለድ ስለት የምንገባበት፣ ወንድ ልጅ ሲወለድ መሳሪያ የሚተኮስባት፣ እልል የሚባልባት አገር ላይ ነን። ታዲያ በዚች አገር ላይ ምን አይነት ሴታዊ ስልጣኔ ይኖራል? በነገራችን ላይ በዚህ ባገባደድነው የፈረንጆች 2020 ላይ የወጣ አንድ ጥናት ለሴት ልጅ ከማይመቹ የአለም አገራት ውስጥ ኢትዮጵያን አንዷ አድርጓታል። ይሄ ብቻ አይደለም አፍሪካ ውስጥ ሚስቶቻቸውን ከሚደበድቡ አገራት ውስጥ በሶስተኝነት ተጠቅሰናል። ሰሞኑን ይሄን ጽሁፍ ልጽፍ ስነሳ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሴት ልጅ የሚነገሩ አዋራጅና ነውረኛ አባባሎች ስሰበስብ ነበር..ምን ያክል እንደሰበሰብኩ ታውቃላችሁ?.. ከሰባ በላይ የሚሆኑ የሴትን ልጅ ክብር ዝቅ የሚያደርጉ አባባሎችን ማግኘት ችዬ ነበር። ‹ሴት ብታውቅ በወንድ ያልቅ፣ የባል ደግነቱ ባትናገር ሚስቱ..የመሳሰሉ ነውረኛ አባባሎችን ለማግኘት ችያለሁ። ጊዜው የእኩልነት ነው አሮጌነትን አውልቀን አዲስነትን መላበስ አለብን። ከግማሽ በላይ ሴቶች በሆኑባት አገር ላይ ሴቶችን ገፍተን የምናመጣው ለውጥ የለም ሴቶች ለምንም ነገር ያስፈልጉናል። በቃ እንዲህ እናስብ። ቸር ሰንብቱ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2013 ዓ.ም