መላኩ ኤሮሴ
በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ሸቅብ መምዘግዘጉን ቀጥሏል፡፡ በተለይ በከተሞች በምግብና ምግብ ነክ ሸቀጦች፣ በመኖሪያ እና ንግድ ቤቶች፣ በአልባሣት፣ በትራንሥፖርት፣ በትምህርት፣ በሕክምናናና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን በመሣሠሰሉት ላይ እየተፈጠረ የመጣው ምጣኔ ሐብታዊ ጫና ከብዙሃኑ ሕዝብ ገቢ ጋር ያልተመጣጠነ ሆኗል፡፡ በዚህም ምክንያት በርካቶች ኑሮን ለመምራት እየተቸገሩ ናቸው፡፡
መንግሥትም የዋጋ ግሽበትንና የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ ቢሆንም አሁንም ከመሻሻል ይልቅ መባባሱ ቀጥሏል። በከተሞች አካባቢ የሚኖሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን ሕይወት የሚደጉሙ ሸቀጦችን በአነስተኛ ዋጋ ማቅረብ እና ምርት የሚሸሽጉት ነጋዴዎች ሱቅ እስከማሸግ የደረሱ ርምጃዎችን እየወሰደ ቢሆንም የዋጋ ግሽበቱ አሁንም ቀጥሏል፡፡
የምጣኔ ሐብት ምሁራን የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት እየጨመረ እንዲሄድ ያደረጉ የተለያዩ ምክንያቶችን ያነሣሉ፡፡ የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት የችግሩ ምንጭ አገሪቱ ከዚህ ቀደም ስትከተል ከነበረው ፖሊሲ ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ የችግሩ መፍትሄም ከፖሊሲ ጋር የሚገናኝ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
የምጣኔ ሐብት ተንታኙ አቶ ዋሲሁን በላይ እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለብዙ ዓመታት ፍላጎትን በሚያሣድጉ ፖሊሲዎች እና ተግባራት ላይ ብዙ ሠርቷል:: ነገር ግን በተመሣሣይ አቅርቦት ላይ ባለመሠራቱ ፍላጎት ከአቅርቦት እጅግ በጣም ከመብለጡ የተነሣ አሁን ላይ የኑሮ ውድነት ከፍተኛ ሆኗል፡፡
ከዕለት ወደ እለት አሳሳቢ እየሆነ የመጠውን የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር በቀጣይ ምርጫ መንግሥት የሚሆነው ፓርቲ በረጅምም ሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ አቅርቦትን የሚያሣድጉ ፖሊሲዎች ላይ በቅድሚያ ማተኮር ተገቢ መሆኑን ያነሣሉ፡፡
በቀጣይ ጊዜ በገበያ የሚሠራጨውን የገንዘብ መጠን በመቀነስ፣ የሥራ ፈጠራን በማበረታታት፣ የባንክ ዘርፉን በመደገፍ፣ ተጨማሪ ግብርና የገቢ ግብርን በመቀነስ፣ የንግድ ፉክክር እንዲፈጠር በማድረግ እንዲሁም የትምህርት ጥራትን በማሣደግ ምርትና ምርታማነትን እና አቅርቦትን ከፍ በማድረግ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ መሆናቸውን አቶ ዋሲሁን ያነሣሉ፡፡
እንደ አቶ ዋሲሁን ማብራሪያ፤ አቅርቦትን ለመጨመር አንዱ መፍትሄ ሞኒተሪ ፖሊሲ ነው፡፡ በገበያ ውስጥ የሚሠራጨውን የገንዘብ መጠን በመቀነስ እና በመጨመር አቅርቦትን ማበረታታት ይቻላል፡፡ አቅርቦትን በማበረታታት የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር አንዱ መፍትሄ ነው፡፡
ተጨማሪ ግብርን መቀነስና እና የገቢ ግብር መጠንን መቀነስም የሠራተኞችን እና የባለሐብቶችን የሥራ ተነሣሽነት ከፍ እንደሚያደርግ የሚናገሩት አቶ ዋሲሁን፤ የገቢ ግብር እና ተጨማሪ ግብር ዝቅ ሲል ባለሐብቶች እና ሥራ ፈጣሪዎች ሐብታቸውን ለተጨማሪ ሥራ እንዲያውሉት ስለሚያግዝ አቅርቦት እንዲጨምር ይረዳዋል ብለዋል፡፡
አቶ ዋሲሁን እንደሚሉት፤ ነጻ የሆኑ የሠራተኛ ማህበራትን ማጠናከር፤ ሠራተኛ የማሠናበት ሁኔታን ማላላት፣ ሠራተኞች የተሻለ ሥራ እንዲሩ እና የምርታማነት አቅም እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ይህም አቅርቦት ከፍ እንዲል ሚናው የላቀ ይሆናል፡፡
ለባንክ ሴክተሩ ድጋፍ ማድረግ፣ ለኢንቨስትመንት የሚሆን ካፒታል እንዲጨምር በማድረግ እና ቁጠባን በማበረታታት አቅርቦትን ለማሣደግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል የሚሉት የምጣኔ ሀብት ተንታኙ መንግሥት ለባንኮች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ከቅርብ ጊዜው ወዲህ የጀመረውን የባንኪንግ ዘርፉን የማነቃቃት ሥራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ይላሉ፡፡
መንግሥት አዲስ ሥራ ጀማሪዎችን የማበረታታት ሀላፊነት አለበት የሚሉት አቶ ዋሲሁን፤ ለአብነት ያህል፤ አዲስ ኢንቨስትመንት ለሚጀምሩ ባለሀብቶች የገቢ ግብር እፎይታ ማድረግ ይህም የተሻለ የሥራ ተነሣሽነት ስለሚፈጥር የአቅርቦት ሁኔታ ያሣድጋል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ጊዜ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው ሌላኛው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
አገሪቱ ከዚህ ቀደም ለረጅም ዓመታት ስትገለገልባቸው የነበሩ ሕጎች ውድድር እና ውጤታማነትን በማበረታታት ረገድ ውስንነቶች እንደነበሩባቸው የሚያነሱት አቶ ዋሲሁን ጤናማ የሆነ የንግድ ፉክክር እንዲፈጠር ለማድረግ፤ የኢንቨስትመንት ሕጎችን ማሻሻል እና ንግድ የመጀመር ተግዳራቶችን መቀነስ አቅርቦትን ለማሣደግ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡
እንደ ምጣኔ ሀብት ተንታኙ ማብራሪያ መንግሥት ሌላኛው ትኩረት ማድረግ ያለበት የትምህርት ዘርፍ ላይ ነው፡፡ ጥራት ያለው እና በተግባር የተደገፈ ትምህርት ምርታማነትን በማሣደግ አቅርቦትን የማሣደግ አቅም ስላለው የትምህርት ጥራት ለማሣደግ እና ለተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት የማቅረብ ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚሻ ነው፡፡
እነዚህን ፖሊሲዎች ማሣካት ከተቻለ ከእለት ወደ እለት ሽቅብ የሚሄደውን የዋጋ ንረትን መቆጣጠር፣ የሥራ አጥነትን መቀነስ፤ የንግድ ሚዛንን ማስተካከል በጠቅላላ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገትን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2013 ዓ.ም