ግብይትን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚከውኑት የድሬዳዋ ነዋሪዎች

ነባር፣ ከፍተኛ ወጪ እና ጉልበት የሚጠይቁ ሥራዎች በቀላል እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እየተተኩ ይገኛሉ። ዘመናዊ መንገድን በመከተል ቀላል ከሆኑ መንገዶች መካከል ገንዘብ መላክ እና መቀበል እንዲሁም ለሚገኘው አገልግሎትም ሆነ ለሚፈፀም ግዢ ክፍያን በዲጂታል ማከናወን ተጠቃሾች ናቸው። ይህን ተከትሎ አሞሌ ጨውን የተካው እና እሱን ለማሳተም ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቀው የወረቀት ብር፤ ከገበያ ለመውጣት ዳር ዳር በማለት ላይ ይገኛል።

ጥቅምን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ዓለም በከፍተኛ ደረጃ እየተጠቀመበት ያለው የዲጂታል ግብይት በኢትዮጵያም ተግባራዊ መሆን ከጀመረ አጭር ጊዜ ቢሆንም ዓለም ከደረሰበት ደረጃ አንፃር ኢትዮጵያውያን የዲጂታል የገበያ እንቅስቃሴያቸው ዝቅተኛ መሆኑን በመጥቀስ የሚከራከሩ ጥቂቶች አይደሉም። የዲጂታል ገበያን ለማከናወን ከፍተኛውን ሚና እየተጫወተ የሚገኘው ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ፤ በስፋት እየሠራ መሆኑን እየጠቀሰ ነው። አገልግሎት መስጠት ከጀመረ 131 ዓመታትን ያስቆጠረው ይኸው ኢትዮ ቴሌኮም፤ በቴሌ ኮም አገልግሎት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ እንድትሆን ማስቻሉን ጠቅሶ፤ አሁንም ዓለም እየተጠቀመበት ያለውን የሚያስፈልገውን አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ እየገለፀ ነው።

ሰሞኑን መሠረተ ልማት ላይ ያተኮረ መድረክ ድሬዳዋ ከተማ ላይ በተካሔደበት ወቅት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ እንደተናገሩት፤ በሀገር ውስጥ ያለውን የቴሌኮም አገልግሎት ከማስፋት ባሻገር ሁለት ነጥብ አራት ቴራባይት የሚሆን በአምስት ኮሪዶሮች ኢትዮጵያን ከሌሎች ዓለማት ጋር የሚያገናኝ ዓለም አቀፍ (ኢንተርናሽናል ጌት ዌይ) የቴሌኮም መሠረተ ልማት ዝርጋታ ተሠርቷል። በዚህም በኬንያ፣ በሶማሊያ፣ በጅቡቲ እና በሱዳን ኢትዮጵያን ማገናኘት ተችሏል። በአጠቃላይ እንደ ሀገር ወደ 92 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች በቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽ በመሆን ተሳስረዋል። 52 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል።

ስለዲጂታል ኢንተርኔት እና ስለ ዲጂታል ኢኮኖሚ ሲነሳ፤ ዲጂታል አገልግሎት ከሞባይል አገልግሎት ጋር የተያያዘ መሆኑን አስታውሰው፤ የኢንተርኔት ተደራሽነት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል። ‹‹ኢትዮጵያውያን ዘግይተን የጀመርን ቢሆንም ስንገባ በጥሩ መልኩ በመግባታችን እና በማስቀጠላችን ዛሬ ከ52 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች አሉ።›› ሲሉ ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎ ከክፍያ መንገድ አንጻር አራት ዓመት ያስቆጠረው ቴሌብር በአጭር ጊዜ ዓለም ላይ ካሉ መሪ ከሚባሉ የክፍያ መንገዶች አንዱ ሆኗል ይላሉ። ዋና ሥራአስፈፃሚዋ፤ ገንዘብን ከማዘዋወር ባለፈ በቀላሉ ክፍያን የሚፈጽሙበትና የተለያዩ የዲጂታል ኢኮኖሚን የመገንባት ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አመላክተዋል።

ከሰባት መቶ ከተሞች በላይ እጅግ ዘመናዊ (አድቫንስድ) የ4ጂ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። ይህ በአጭር ጊዜ የኢንተርኔት ተደራሽነትን ለማሳደግ የተሠራ ሥራ መሆኑን አስታውሰው፤ በአፍሪካ በጣም ጥቂት ሀገራት ውስጥ ያለው የ5ጂ አገልግሎት በኢትዮጵያ 25 ከተሞች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ብለዋል። ይህ ሁሉ የዲጂታል ግብይት ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አያጠራጥርም።

በሌላ በኩል ዓለም ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያም ዲጂታላይዜሽን አሠራሮች እየተስፋፉ ከመሆናቸው ጋር ተይይዞ የወረቀት የገንዘብ ዝውውር እየቀረ ወደ ዲጂታል እየገባ ነው። በተለይም በአንዳንድ ከተሞች በወረቀት መገበያየትን በመቀነስ ዲጂታላይዜሽን በመቀላቀል ወደ ዲጂታል ግብይት መግባት የቻሉ ከተማዎች እየታዩ ነው። ምርቶች ወደገበያ የሚቀርቡበትም ሆነ ሸማች ከገበያው ምርትም ሆነ አገልግሎትን የሚገዛው በቴክኖሎጂ መታገዝ በዲጂታል ክፍያ ሥርዓት መሆኑ እየተለመደ መጥቷል። በዚህ በኩል ተጠቃሽ ከሆኑት መካከል አንዱ የድሬዳዋ ከተማ ናት።

በድሬዳዋ ከተማ ግብይት ለመፈፀም የወረቀት ብር ይዞ መንቀሳቀስ አስገዳጅ አይደለም። ከታች ትንንሽ የጉሊት ቸርቻሪ ነጋዴዎች፣ የባጃጅ አሽከርካሪዎች፣ መካከለኛ የሸቀጥ ሱቆች፣ በየደረጃው በሱፐር ማርኬትም ሆነ በሆቴል ለሚገዙ ሸቀጦችም ሆኑ አገልግሎቶች ግብይትን በዲጂታል መፈፀም ተለምዷል። የተማረው ብቻ ሳይሆን ያልተማረውም ሁሉም ወደ ዲጂታል በመቀላቀል እንደአቅሙ በስልኩ ተጠቅሞ በቀላሉ ገንዘብ መላክ እና መቀበል ጀምሯል። ብዙዎቹም ወደ ዲጂታል አሠራሩ መቀላቀላቸው ንግድና ግብይታቸውን በቀላሉ እንዲያካሂዱና የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጡና እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ይገልጻሉ።

የድሬዳዋ ነዋሪ አንተነህ አዲሱ ይባላል። የባጃጅ አሽከርካሪ ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ፎርስ ይነዳል። ከተሳፋሪዎች ገንዘብ የሚሰበስብበትን ሁኔታ በተመለከተ እንደተናገረው፤ ጠዋትም ሆነ ማታ በማንኛውም ሰዓት እና በቴሌ ብር እና በኢ ብር ገንዘብ ይቀበላል። እጁ ላይ ገንዘቡ አይቀደድም፤ ኪሱ ውስጥ ‹‹አስቀምጫለሁ›› ብሎ ብር አይጠፋበትም። መልስ ለመስጠት ዝርዝር ፍለጋ አይቸገርም። አገልግሎት ይሠጣል፤ ደምበኞቹ በቴሌ ብር ይከፍሉታል። እንደከፈሉት በቀላሉ ማወቅ ስለሚችል ከተሣፋሪ ጋር አይከራከርም።

እንደአንተነህ ገለፃ፤ ይሁንና ቴክኖሎጂው አዲስ በመሆኑ አንዳንድ ሰው ፈጣን አይሆንም። አልፎ አልፎ በዚህ ምክንያት መዘግየት ያጋጥማል። እርሱ ደግሞ ደቂቃዎች እንዲባክኑበት አይፈልግም። አንዳንድ ተገልጋዮች ቀድመው ሳይዘጋጁ መውረጃቸው ሲደርስ ለመክፈል ስልክ ቁጥር ይጠይቁታል። ሲነግራቸው ወዲያው ‹‹አስገባን›› ብለው ወርደው ይሔዳሉ። አንተነህ ግን ገንዘቡ መግባቱን ለማወቅ ለማረጋገጥ ሲሞክር፤ እርሱ ጋር ገንዘቡ መግባቱን ለማወቅ ይቸገራል። ‹‹ጊዜ የለኝም›› ብሎ ስለሚቸኩል ትቷቸው ይሔዳል። ይህ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ቆይቶም ቢሆን ገንዘቡ ይገባል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ተሳፋሪዎቹ ‹‹አስገብተናል›› ቢሉም ወደ እሱ የማይገባበት ሁኔታም እንደሚጋጥመው ይናገራል።

‹‹በሌላ በኩል አንዳንዴ ስልክ የሚጠፋበት ወይም የሚሠረቅበት አጋጣሚ ሲፈጠር ሁሉም ነገር ከስልክ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ችግር ይፈጥራል። በተለይ አሁን ላይ ከሞባይል ስልክ ውጪ ዕቃ መግዛትም ሆነ አገልግሎት ማግኘት እጅግ ያዳግታል። ›› የሚለው አንተነህ፤ ከዚህ ውጪ ዲጂታል ግብይት ከደንበኞች ጋር ላለ ግንኙነት መልካም ነው። ጤናማ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር ያግዛል ይላል።

ዲጂታል አሠራር ቀጣይነት ስላለው ሁሉም ሰው ወደ ዲጂታል መቀላቀሉ አይቀሬ ነው የሚለው አንተነህ፤ ግንዛቤ ማስፋትን ሁሉም ሰው ዲጂታል ግብይትን እንዲቀላቀል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግሯል።

በድሬዳዋ በተለምዶ አሸዋ ተብሎ በሚጠራው ገበያ መሃል ለውዝ መሬት ላይ ዘርግተው በጣሳ እየሠፈሩ የሚሸጡት ወይዘሮ አባይነሽ ግርማም፤ ግብይትን በዲጂታል መንገድ መቀበል ለምደዋል። ምንም እንኳ ተምረው ፊደል ባይለዩም ለፈፀሙት ሽያጭ ክፍያ ማግኘታቸውን የሚያሳውቀው የሞባይላቸው ድምፅ እና የሚደርሳቸው የክፍያ መልዕክት መተማመኛቸው ነው።

በቴሌ ብር ሲከፈል ወደ ከፋዩም ሆነ ወደ ተቀባዩ ወደ ሁለቱም መልዕክት የሚደርስ መሆኑን አስታውሰው፤ አንዳንዴ መልዕክቱ ሲዘገይም አንዱ ወይም ገንዘብ ከፋዩ ጋር ቢዘገይ ሌላው ወይም ገንዘብ ተቀባዩ ጋር ከገባ በመተማመን ግብይቱ ይፈፀማል ይላሉ። ‹‹አንዱ ጋር ክፍያ መፈፀሙን መልዕክት ከሰማሁ እና ካየሁ በኋላ ገንዘቡን ያጣሁበት ሁኔታ የለም። ›› ሲሉ ይናገራሉ።

‹‹የገበያ ሥፍራ ላይ ለውዝም ሆነ ሌላ ነገር ለመግዛት እና ለመሸጥ እንዲሁም ማንኛውንም ንግድ ለማከናወን ኢ ብር መጠቀም አስገዳጅ ነው። ምክንያቱም ድሬዳዋ ከተማ ላይ በዲጂታል ግብይት ለመጠቀም ፈቃደኛ ካልሆኑ ገበያ ማግኘት አይቻልም። ›› የሚሉት ወይዘሮ አባይነሽ፤ እርሳቸው ምንም እንኳ ፊደል ያልቆጠሩ እና ያልተማሩ ቢሆኑም ልጆቻቸው እያገዟቸው ግብይቱን ከአንድ ዓመት ወዲህ በቴክኖሎጂ በመታገዝ በዲጂታል የግብይት ሥርዓት እየተጠቀሙ በማከናወን ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።

እሳቸውም ግዢውን ሲፈፅሙ በኢ ብር የሚያከናውኑ መሆኑን ጠቁመው፤ አንዳንዴ ላልተማረ ሰው ከበድ የሚልበት ሁኔታ መኖሩን ያመለክታሉ። ክፍያ ለመፈፀም የይለፍ የሚሥጥር ቁጥር መጠየቁ ትንሽ እንደሚከብዳቸው አስታውሰው፤ ሆኖም ብዙ ሰው በዛ ስለሚጠቀም ከማህበረሰቡ ጋር ለመሥራት ወደ ዲጂታል ለመግባት መገደዳቸውን ያስረዳሉ።

ወይዘሮ አባይነሽ እንደሚገልፁት፤ ምንም ቢሆን የወረቀት ብርን በመሃረብ ቋጥሮ፤ በቦርሳ ሰብስቦ ከመያዝ ይልቅ ሁሉን ገንዘብ በሞባይል ይዞ መንቀሳቀስ መለመዱ መልካም ነው የሚል እምነት አላቸው። ይሁንና ላልተማረው ማህበረሰብ አገልግሎቱ የበለጠ ቀላል መሆን አለበት።

ዲጂታል ግብይት ሥርዓት የማይቀር ጉዳይ ስለሆነ ይልቁንም ያልተማረው የማህበረሰብ ክፍል ሁሉም ወደዲጂታል ግብይት ሥርዓቱ እንዲገባ ያስፈልጋል ያሉት ወይዘሮ አባይነሽ፤ ለዚህም የማህበረሰቡ የመረዳት አቅም ከግንዛቤ ውስጥ ያስገቡ ቀላል ሊለመዱና ሊተገበሩ የሚችሉ አሠራሮች ሊስፋፉ እንደሚገባም አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ ዲጂታል ስትራቴጂ እንደተቀመጠው በ2020 ከነበረው አንድ ሚሊዮን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚ በ2024 መጨሻ ወደ 128 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ ለማድረስ ታቅዷል። አሁን ላይ በቀን ሰባት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የክፍያ እንቅስቃሴዎች በመመዝገብ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ 26 ቢሊዮን ብር እንደሚንቀሳቀስ የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያመለክታል። ከአምስት ዓመት በኋላ በዲጂታል ግብይት ዘጠኝ ነጥብ ሰባት ትሪሊየን ብር ይንቀሳቀሳል የሚል እቅድም ተይዟል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚዋን ጨምሮ ብዙዎች የሚሠጡት ሃሳብ፤ ከኢትዮጵያ አንፃር ዘርፉ ላይ ፈታኝ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው መሠረታዊ ማንበብ እና መረዳትን የሚያውቅ ሕዝብ ቁጥር በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል የሚል ነው።

ይሁንና ያለውን አቅም ተጠቅሞ ክፍያዎች በዲጂታል መንገድ እንዲከናወኑ ማስቻል፤ ብዙዎችን የሚስማማ ነው። ምክንያቱ ደግሞ የዲጂታል ግብይት መንግሥት ለብር ሕትመት የሚወጣውን ወጪ ከመቀነስ ባሻገር ዜጎች ባንክ በመመላለስ የሚያጠፉትን ጊዜ እና ገንዘብ እንደሚቆጥብ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው።

በቀን 26 ቢሊዮን ብር ለማንቀሳቀስ ከባንክ ወደሚከፍለው ነጋዴም ሆነ አገልግሎት ሰጪ ለመሔድ የሚወጣው የሰው ጉልበት እና የሚባክነውን ጊዜ ጨምሮ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ የሚያስከፍለው ዋጋ ሲሰላ ጥቅሙ አጠያያቂ አይሆንም። ሆኖም ከድሬዳዋ ውጪ ባሉ ብዙ ከተሞች ከመካከለኛ እና ከትልልቅ ግዢዎች ውጪ ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ የዝግጅት ክፍሉ ጋዜጠኞች እንዳገኟቸው አይነት አነስተኛ ነጋዴዎች እና አገልግሎት ሰጪዎች ክፍያን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ሲጠቀሙ አይስተዋልምና። የድሬዳዋን ተሞክሮ መጋራት ይገባል እንላለን። ሰላም!

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You