
ወይዘሮ ጌጤ አስፋው ትባላለች:: ለአስራ ሰባት ዓመታት በመምህርነት ሀገሯን አገልግላለች:: ለእነዚህ ያህል ዓመታት ስታስተምር በየዕለቱ በሥራ ቦታዋ እጇን ከጠመኔ የምታዋህድ ታታሪ መምህር ሆና አሳልፋለች:: ይሁንና ሥራዋ ወጪዋን ለመሸፈን በቂ ባለመሆኑ፤ የተሻለ ገቢ ለማግኘት በማሰብ ምግብ ቤት ከፍታ ነበር::
‹‹ የበለጠ ሊሳካልኝ የሚችለውን መክሊቴን ፍለጋ ብዙ ነገር ሞክሪያለሁ” የምትለው ወይዘሮ፤ ጸጉር ቤትም ከፍታ ነበር:: በዚህ ሁሉ ጊዜ ቤት ስትሆን ከእጇ ኪሮሽ አይታጣም:: እጇና ኪሮሽ ተጣምረው በርካታ ውብ የዳንቴል ሥራዎችን ይሠራሉ:: ምንም እንኳን የሚያምሩ የዳንቴል ሥራዎችን ብትሠራም ለእራሷ ከመገልገልና ለምትቀርባቸው ሰዎች ሥጦታ ከመስጠት በዘለለ ሥራዎቿ ዋጋ አውጥተው መሸጥ መቻላቸውን አስባ አታውቅም::
ይህን ሁኔታ የሚቀይር አጋጣሚ የተፈጠረው በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ነው:: ሁሉም ቤት ለመቀመጥ በተገደደበት ወቅት እንኳን በየዕለቱ ቤት የመቀመጥ ግዴታ ተጥሎባት ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ከእጇ ኪሮሽ የማይታጣው ወይዘሮ ጌጤ፤ ያኔም ክሮችን ወደ የሚያምሩ ዳንቴሎች እየቀየረች ነበር:: በወቅቱ አብዛኛውን ጊዜዋን ማሳለፊያ ማኅበራዊ ሚዲያ ነበርና የእሷም ልጅ የፌስቡክ ማኅበራዊ ገጽን ስትጎበኝ በዳንቴል የተሠራ ማስክ አስተዋለች:: የእናቷን ጥበብ ታውቀዋለችና ለምን እንደዚህ አትሰሪም? ስትል ለእናቷ አሳየቻት:: ኪሮሽ ከእጇ የማይጠፋው እናት የሚያምር የዳንቴል ማስክ ሠራች:: የሠራችው ማስክ ያምራልና የተሠራውን ያዩ ጓደኞቿና የምታውቃቸው ሰዎች የሷን ማስክ መጠቀም ጀመሩ::
ሳታስበው የጀመረችው የማስክ ሥራ ገቢ ማስገኘት ጀመረ:: በዚህ ተበረታታ ከማስኩ ጋር አብረው የሚሄዱ ስካርቭና መሰል ምርቶችን መሥራት ቀጠለች:: ሥራዋን ለገበያ እንድታቀርብ መነሻ ሀሳብ ከፌስቡክ ያገኘችው ወይዘሮ ጌጤ፤ በተመሳሳይ ቲክቶክ ከተሰኘው ማኅበራዊ ሚድያ የተሻሉ ክሮችን እንድትጠቀም አስችሏታል:: በፊት ትጠቀምበት የነበረው የሹራብ ክር የሚያደክም፣ ብናኝ ያለውና ጊዜ የሚወስድ እንደሆነ በማንሳት ወደተሻሉት ፖሊስተርና ቲሸርቲያ ወደ ሚባሉ የክር አይነቶች ፊቷን ማዞሯን ትናገራለች::
ሥራዎቿን ለገበያ ማቅረብ ከመጀመሯ በፊትም የዳንቴል ሥራ የሚያስደስታት ስለሆነ ስትከውነው መቆየቷን ትናገራለች:: በዚህ የተነሳ ወደ ንግዱ ዓለም ስትገባም፤ ቢሸጥም ባይሸጥም ውስጧ ያለውን እንዲያወጣላት በማለት እንድታሰፋው አነሳሳት:: በተለያዩ ባዛሮች ላይ ስትሳተፍ የተለያዩ ተደጋጋሚ ምርቶች ሲታዩ፤ እሷና መሰሎቿ ውስን መሆናቸውንና ብዙ ባዛሮች ላይ ብቸኛ መሆኗ የበለጠ እንድትሠራ እንዳነሳሳት ትናገራለች::
በምትኖርበትና ምርቶቿን ለገበያ በምታቀርብበት ቢሾፍቱ ከተማ ብቸኛ የዳንቴል መሸጫ የእሷ መሆኑን በማንሳት፤ በርካቶች በመገናኛ ብዙሃን የሚታውቀውን ነገር በእጃቸው ስላስነካኋቸው ‹‹እናመሰግናለን›› የሚል አስተያየት እንደሚሰጧት ትናገራለች:: በማስክ ለገበያ ማቅረብ የተጀመረው የዳንቴል ሞያዋ አሁን የአንገት ልብስ፣ ሹራብ፣ ኮፍያ፣ ቦርሳ፣ ጫማ፣ እና የቤት ውስጥ ማስዋብያዎችና እቃ ማስቀመጫዎችን ወደ መሥራት አድጓል::
“ይህንን ሥራ ወደ ንግድ ሳልቀይረው ለሰው ሥጦታ ገዝቼ ሰጥቼ አላውቅም” የምትለው የቀድሞ መምህር፤ አሁን በርካቶች ከሷ ስጦታ የሚሆኑ ነገሮችን እየገዙ ለወዳጆቻቸው እየሰጡ መሆኑን ትናገራለች:: ሥራውን እንደዋና ሥራ ይዛ መሥራት ከጀመረች ሁለት ዓመት ያስቆጠረች ሲሆን፤ ለሥራዎቿ መሸጫ ቦታ በመንግሥት ከተመቻቸላት አንድ ዓመት ሆኗል::
የቀድሞ ሥራዋን መምህርነትን ወዳው መሥራቷን የምትናገረው ወይዘሮ ጌጤ፤ የአሁኑ ሥራዋ ሁልጊዜ በፈጠራ ራስን ለማሳደግ የምትተጋበት በመሆኑና ሰዎች ያላዩትን የተለየ ሥራ ለመሥራት የሚሠራበት በመሆኑ ደስተኛ ናት:: አንዳንድ ሥራውን የሚያደንቁና የሚያበረታቱ ሰዎች ቢኖሩም አብዛኞቹ ሰዎች ዋጋውን ከሰሙ በኋላ ሥራውን የማናናቅ አስተያየት ይሰጣሉ:: ለአብነትም “ቀላል አይደል እንዴ” እና መሰል አስተያየቶች እንደሚሰነዘሩና ይህም ከሥራው በላይ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሳለች::
በአሁኑ ወቅት ለሥራው የሚሆኑ ክሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ይመረታሉ:: ለሥራው ግብአት የሚሆኑ ከክር ውጭ ያሉ ግብአቶች ከውጭ ይመጣሉ:: የሴት ቦርሳዎች ቢሊሊ ክሮቼት ስትል በሰየመችው መሸጫዋ ከአራት መቶ ብር እስከ ሁለት ሺ ብር ትሸጣለች:: የሕጻናት ጫማ ከ800 ብር አንስቶ ሲገኝ፤ ውዱ ጫማ የወንዶች ሲሆን እስከ ሁለት ሺ የመሸጫ ዋጋ ተቆርጦለታል:: የአንገት ልብስ ለብቻው ከ300 ብር ጀምሮ ሲሸጥ ስካርፍና ኮፍያ አብሮ 900 ብር ይሸጣል:: የእጅ ሥራ ውጤቶቿን በማኅበራዊ ሚድያዎች፣ በሰዎች ምስክርነት፣ በመሸጫ ቦታዋ በመኖሪያዋ ቢሾፍቱ በባነር ታስተዋውቃለች::
ምርቷ ከመኖሪያዋ ከተማ አልፎ እንዲወጣ በአዲስ አበባ በሚዘጋጁ የተለያዩ የንግድ ትርኢት ባዛሮች ላይ ትሳተፋለች:: ከዚህ ባሻገር አዲስ አበባ በሚገኙ የተወሰኑ ሱፐርማርኬቶች ምርቶቿን ማስቀመጥ ጀምራ ነበር:: ሆኖም ቦታዎቹ በቱሪስቶች የሚጎበኙ ስላልሆኑ መተዋን ትናገራለች:: ከልምዷ የእጅ ሥራ የሚመርጡት የውጭ ቱሪስቶች መሆናቸውን በማንሳት፤ ሪዞርቶችና የተለያዩ የውጭ ቱሪስቶች የሚያዘወትሯቸው ቦታዎች ምርቶቿን ብታስቀምጥ የተሻለ ገበያ እንደምታገኝ ታምናለች:: አሁንም አብዛኛው ገዢዎቿ የውጭ ሀገር ዜጋዎች ሲሆኑ፤ የሀገር ውስጥ ሸማች ደንበኞቿን “እንደ እኔ የእጅ ሥራን የሚወዱ ሰዎች ናቸው” ትላለች:: እነዚህ የሀገር ውስጥ ሸማቾች ሞያውን ከመውደድና ከማበረታታት አንጻር ካስቀመጠችለት ዋጋ በላይም የሚከፍሉበት ሁኔታ አለ:: ከራሳቸው በተጨማሪ ለሌሎች ሰዎች ሥጦታ የሚገዙበትና ምርቱን የሚያስተዋውቁበት ሁኔታም በተደጋጋሚ አጋጥሟታል::
ሌላኛው በእጅ የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርት ድርጅት ጤናዳም ፒኤልሲ ይሰኛል:: ድርጅቱ ቀርከሃን እንደዋና ግብአት በመጠቀም የተለያዩ ምርቶችን ያመርታል:: ድርጅቱ ከተመሰረተ ሁለት ዓመት ሲሆነው፤ እንደጀመሩ ቀርከሃውን አምጥተው ለሚፈለገው ምርት ከማስተካከል አንስቶ ዲዛይን አውጥቶ ወደምርት እስከመቀየር ያለውንም ሥራ በድርጅቱ ይከወን ነበር:: የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ውብሸት ለማ፤ ለሌሎችም የሥራ እድል ለመፍጠር ከማሰብ የቀርከሃ ምርቶች ባሉባቸው አካባቢ የሚገኙ ዝቅተኛ ገቢ የሚያገኙ እናቶችን አሰልጥነው ግብአቱን መረከብ መጀመራቸውን ያስረዳል:: ድርጅቱ ከእናቶች የተረከበውን የተወሰነ ሂደት ያለፈ ቀርከሃ በሚፈለገው ዲዛይን አምርቶ ወደ ገበያ ያቀርባል::
‹‹ሀገራችን በቀርከሃ ሀብት የታደለች ናት›› የሚለው አቶ ውብሸት፤ ሆኖም ስለቀርከሃ የሚገባውን ያህል መረዳት የለም ይላል:: ለአብነት ቻይናን በማንሳት በቻይና ከቀርከሃ ድልድይና የባቡር ሀዲድ መሥራት ተችሏል:: በጤናዳም ቦርሳዎች፣ መጋረጃዎች፣ የምግብ ቤት ጠረጴዛ ላይ የሚደረጉ ንጣፎች፣ የሴት ቦርሳ፣ የወንድ ዋሌት ቦርሳዎች፣ ቀበቶ፣ የጉዞ እንዲሁም የላፕቶፕ ቦርሳዎች፣ የአንገት ጌጦች፣ የእጅ አምባሮች፣ የጆሮ ጌጦችና ጫማ ያመረታሉ:: ለእነዚህ ምርቶች ዋነኛ ግብአት ቀርከሃ ቢሆንም እንደአስፈላጊነቱ ቆዳ፣ ጥለትና ሌሎችም ግብአቶችን በመቀላቀል ቀርከሃን ያሽሞነምኑታል:: ድርጅቱም በቀጣይ በተለያዩ ዲዛይን የሚመረቱ የቀርከሃ ወንበሮችን ለገበያ የማቅረብ ውጥን አለው ይላል::
ድርጅቱ ገበያ ላይ ካወጣቸው ምርቶች በተጨማሪ በሰዎች ምርጫ የተለያዩ ምርቶችን እንደሚያመርት ጠቁሞ፤ የሴት የእጅ ቦርሳዎች ከሁለት ሺ 500 ብር አንስቶ ስድስት ሺ ብር ድረስ እየሸጡ መሆኑን ይናገራል:: የላፕቶፕ መያዣ ቦርሳዎችና አነስተኛ የጉዞ ቦርሳዎች ከ7 ሺ ብር አንስቶ እስከ 12 ሺ ብር በድርጅቱ የተቆረጠላቸው የመሸጫ ዋጋ ነው::
ቀርከሃ ለጤና ጠቃሚ ነው የሚለው አቶ ውብሸት፤ በሕብረተሰቡ ዘንድ የቀርከሃ ምርትን መጠቀም የቀርከሃ አቅምን ያህል አለመለመዱን ታዝቧል:: በተለይ ረዥም ሰዓት የሚቆሙ ሰዎች የቀርከሃ ጫማን ቢጠቀሙ ተመራጭ መሆኑን ይናገራል:: የድርጅቱ ምርቶች በእጅ ረዥም ጊዜ ፈጅተው የሚሠሩ በመሆኑና ከሥራው አለመለመድ ጋር ተያይዞ የምርቶቹ ዋጋ በአንዳንድ ሸማቾች ዘንድ እንደ ውድ ይታያል ይላል:: ምርቶቹ በሕብረተሰቡ ዘንድ እንደቅንጦት እቃ የመታየት ሁኔታ መኖሩንም ጠቅሷል:: ሆኖም ሥራው ከጅምሩ እስከፍጻሜው በርካታ ሰው የሚሳተፍበትና በርካታ እጆች አሻራቸውን የሚያሳርፉበት ከመሆኑ አንጻር፤ የመሸጫ ዋጋቸው መሆን ከነበረበት ያነሰ መሆኑን ይናገራል::
እንደ አቶ ውብሸት ገለፃ፤ ድርጅቱ ቀርከሃን በጥበበኛ እጆች አስውቦ ወደገበያ በማቅረብ ሂደት የቦታ ችግር አለበት:: ከመንግሥት ‹‹ለጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች እናመቻቻለን›› የሚል ተስፋ ስለተሰጣቸው እሱን እየጠበቁ ሲሆን፤ ድርጅቱ ቀርከሃውን ወደሚፈለገው ደረጃ ለማምጣት የሚያግዝ ማሽንና የተለያዩ ግብአቶች ከውጭ ያስመጣል:: በዚህ እቃ የማስገባት ሂደትና በሌሎች ወቅቶች ጉምሩክ ላይ ያለው ውጣ ውረድ ከፍ ያለ ነው:: ሆኖም በእነዚህ ተግዳሮቶች ከመቆም ይልቅ እየሠሩ መጠየቅ የተሻለ በመሆኑ፤ በቻሉት አቅም እየሠሩ የጎደሉ ነገሮች እንዲሟሉ መጠየቅ ምርጫቸው ሆኗል::
በሕብረተሰቡ ዘንድ ከእጅ ለሚሠሩ የጥበብ ውጤቶች የተሻለ መረዳት እየተፈጠረ ስለሆነ አሁን ለምርቶቹ የተሻለ ተቀባይነት መኖሩን ጠቅሷል:: አብዛኞቹ ሸማቾች ሥጦታ ለመስጠት ምርቶቻቸውን እየመረጡ እንደሆነና ሸማቾቹ የድርጅቱን ምርቶች “ለእናቴ፣ ለአያቴ” እያሉና ለተለያዩ ሰዎች ስጦታ ለመስጠት ምርጫቸው እያደረጉት በመሆኑ ደስተኛ ናቸው:: አሁንም ቢሆን ሰው ስለምርቶቹ የአሠራር ሂደት ከማወቅ ይልቅ ቀጥታ ዋጋ የመጠየቅና ምርቶቹን እንደቅንጦት የማየት ሁኔታ መኖሩን ይናገራል::
ዋጋቸውን ሰምቶ ውድ ናቸው ብሎ ከመፍረድ በተጨማሪ፤ ምርቶቹ ሲታዩ ስለሚያምሩ ውድ ይሆናሉ ብሎ የመፍራትና ዋጋም ያለመጠየቅ ሁኔታ ይስተዋላል:: የድርጅቱ ምርቶች ሰው እንደሚያስበው ውድ አይደሉም የሚለው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ ሕብረተሰቡ በድፍረት እንዲጠይቅና እንዲሸምት አበረታቷል::
በእጅ የሚሠሩ ምርቶችን አምራቾች ስላለው ገበያ ምን አስተያየት አላቸው? ብለን ቅኝት በወጣንበት ወቅት ያገኘናት ሌላኛዋ የእጅ ሥራ አምራች ወጣት ሀና ብርሀን ናት:: ወጣቷን ያገኘናት በአዲስ አበባ ከተማ በተዘጋጀ ኤግዚቢሽን ላይ በአባቷ ፊት አውራሪነት የሚመረቱ የሥጋጃ ምንጣፎችን ይዛ በተገኘችበት ወቅት ነው:: የአባቷ ድርጅት ብርሃን ወልደ ጊዮርጊስ ባኅላዊ ሥጋጃ አምራች ይሰኛል:: ከበግ ጸጉር፣ ከሱፍና፣ ከጥጥ እንዲሁም እንደአስፈላጊነቱ የተለያዩ ግብአቶችን በመጠቀም በእጅ የሚሠሩ ምንጣፎችን አምርተው ለገበያ ያቀርባሉ:: ድርጅቱ ምንጣፎችን በተለያዩ የዲዛይንና የመጠን አማራጭ ለገበያ ያቀርባል:: ምንጣፎቹን ለመሥራት ጊዜ የሚወስድ መሆኑን የምትናገረው ወጣቷ፤ ያም ቢሆን ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያቀርቡ ጠቅሳለች::
በድርጅቱ ተሠርተው ለገበያ የቀረቡት አነስተኛ ምንጣፎች ከ200 እስከ 800 ብር የተቆረጠላቸው የመሸጫ ዋጋ ነው:: ከዚህ በተጨማሪ ሰዎች የሚፈልጉትን ዲዛይንና ልኬት በመንገር የምርጫቸውን ማሠራት የሚችሉበት አማራጭ አለ:: ለዚህም ሰዎች ለቤተክርስቲያን እንዲሁም ለሳሎን ማስጌጫ የቤታቸውን ልኬት በመናገር የሚያሠሩበት ሁኔታ አለ:: በእንደዚህ አይነት ወቅቶች ዋጋ የሚወሰነው በምንጣፉ መጠን መሆኑን ትናገራለች:: ድርጅቱ መገኛው ደብረብርሃን ከተማ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ወደ ስድስት የሚደርሱ መሸጫዎች የድርጅቱን ምርት ተቀብለው ያከፋፍላሉ:: በደብረብረሃን መሸጫ ያላቸው ሲሆን፤ በዛም ምርቶቹ ለገበያ ይቀርባሉ:: ሕብረተሰቡ ስለድርጅቱ ምርት የተሻለ ግንዛቤ እንዳለው የምትናገረው ወጣት ሀና፤ ምርቶቹን ይዛ በተገኘችበት ኤግዚቢሽን ላይም ዋጋቸው ቅናሽ መሆኑን ከሸማቾች አስተያየት እየተቀበለች መሆኑን ታስረዳለች::
በኢትዮጵያ በእጃቸው ለፍተው ለብዙሀኑ መፍትሄ የሚያፈልቁ ወገኖችን “ቆዳ ፋቂ፣ ብረት ቀጥቃጭ” ሌላም ሌላም ያልተገባ ሥም እየተሰጠ ለውለታቸው የማይመጥን ጊዜን ያሳለፉበት ሁኔታ አሁን አብቅቷል:: የሠለጠነው ዓለም ሰዎች በእጅ የተሠራ የሚል ምርትን መጠቀም የክብር መገለጫ፤ በእጁ የሚያመርተውም የጥበብ ባለቤት ነውና ያከብሩታል:: ይሁንና መሻሻሎች ቢኖሩም በኢትዮጵያ አሁንም የሚገባውን ያህል ባይደርስም ይህ ጉዞ አንድ ተብሎ ተጀምሯል:: አሁን ከተለያየ የሙያ መስኮች የራስን ምርት ወደማምረት የሚሸጋገሩ ሰዎችን ማየት እየተላመደ መጥቷል:: ሸማቹም በእጅ የተሠሩ ምርቶችን ለመግዛት ከትላንት የተሻለ ተነሳሽነት እየታየ ነው:: ይህ ሂደት ይበልጥ ዳብሮ እንደሚቀጥል ባለሙሉ ተስፋ ነን:: ይህ ሲሆን ትላንት በራስ እጅ እነአክሱም፣ እነ ፋሲልን ያነፀው ሕዝብ በእጅ ሥራ የዓለም ገበያ ላይ የተሻለ ድርሻ ይኖረዋል የሚለው ምኞታችን ነው:: ሰላም!
በቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም