ምህረት ሞገስ
ለመላው ሕዝብ እንጂ ለአንድ ወገን ያደላ ፓርቲ ወገንተኛ በመሆኑ ሌላውን መጉዳቱ አጠራጣሪ አይደለም። እኛ ደግሞ የምንሻው ሁሉም በእኩልነት እንዲታይ ብቻ ነው። ተቋሞቻችን ማንንም ከማንም ሣይለዩ ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ነው። ምጣኔ ሐብቱ ለአንዱ አድልቶ ሌላውን ጎድቶ እንዲያንሠራራ ሣይሆን፤ የአንዱ ዘር ፋብሪካ ተዘግቶ የሌላው እንዲከፈት ሣይሆን፤ አንዱ ከንግድ ዓለም ተገፍቶ ከሥሮ ሥራ እንዲፈታ ሣይሆን፤ ሌላው ዕቃውን ከታክስ ነፃ እያስገባ እንደፈለገ ያለውድድር እንዲነግድ ሣይሆን፤ እኛ የምንፈልገው ሁሉም እኩል ግብር እየከፈለ ጠንካራውና በርትቶ የሠራው እያደገ ውድድሩ ፍትሃዊ በሆነ መልክ እንዲመራ ብቻ ነው።
አዎ! ፖለቲከኞቻችንን ሥሙን የምንለውና እንድታውቁት የምንፈልገው በገጠርም ሆነ በከተማ ያለው ሕዝብ መድልዖ ሠልችቶታል። ከአሁን በኋላ ሕዝቡ ለኔ ብቻ እያለ ራሱን አስበልጦ ሌላውን የሚረሣ ሥግብግብ መሪም ሆነ ፖለቲከኛን አይፈልግም፤ አይፈልግም ብቻ አይደለም መታገስ አይችልም። ከሥግብግቦቹ ፖለቲከኞችና ባለሥልጣናት ውጪ ማንም ቢሆን፤ በተለይ ተራው የአገሬ አርሶ አደር ከሌላው በመንጠቅ ለኔ ሥጡኝ የሚል አይደለም። ተራው የከተሜው ሕዝብም ቢሆን የሚፈልገው እኩል መታየት ብቻ ነው። እርግጥ ነው በከተማ ያለው ፖለቲከኛ ደግሞ ወገኔ የሚለው አካል እንዲዳላለት ይፈልጋል። ይህ ብልጣብልጥነት በፓርቲዎች ላይ በግልፅ ይሥተዋላል። ይሥተዋላል ሥንል ደግሞ ለቆሙለት ብሔር እንደሚያዳሉ የሚገልፁት በአደባባይ በሚጠሩበት በሥማቸው ጭምር ነው።
ለብሔር ፓርቲ ነን ባዮች አንድ የማቀርበው ጥያቄ አለኝ። በብሔር ሥም ተሠይማችሁ ዓላማችሁ ምንድን ነው? ያው እንደተለመደው የምትሠሩትም ሆነ የምታሥቡት ቆመልነታል ለምትሉት ብሔር መሆኑን ማሥረዳታችሁ አይቀርም። በእርግጥ አንዳንዶች ‹‹የሥያሚያችን መነሻ የአንድ ብሔር ሥም ይሁን እንጂ እኛ ዓላማችንና ዓላማችን ብቻ ሣይሆን አባሎቻችንም ከተለያዩ ብሔሮች የተገኙም ጭምር ናቸው፤ የትኩረት ነጥባችን እንድ ብሔር አይደለም።›› ይላሉ። ነገር ግን ሥማቸውን በአንድ ብሔር ሥም ተወሠኖ ምንም ቢሆን ለዚያ ብሔር ማድላታቸው አይቀርም።
እናም አሁን በአጋጣሚ የአንዱ ብሔር ፓርቲ ተሣክቶለት በምርጫው ብዙ ወንበር አገኘ እንበል፤ እና ይኼ ፓርቲ ታገልኩለት ላለው ብሔር የበለጠ አድልቶ አንዱ ወገን ተጠቃሚ ሆኖና አድጎ ሌላው ብሔር ተጎሣቅሎና ደህይቶ እንዴት መዝለቅ ይቻላል? ይኼ አጠያያቂ ነው። ምክንያቱም ምንም ቢሆን የተወሠነ አካል ብቻ በተለያየ መልኩ በምጣኔ ሐብቱ ውስጥ ገብቶ መቆጣጠሩ ሠላም አይሠጥም። ደግሞም አይጠቅምም። ምክንያቱም መጨረሻ ላይ የሚጋጥመው ውድመት ነው።
ነገሩ ምጣኔ ሐብቱን አልን እንጂ በአገልግሎት አሠጣጡም ላይ እንዲሁ መድልዖ ካለ በተቃራኒው ተጎድቻለው የሚለው አካል በብሶት መወጠሩ አይቀርም። የተወጠረ ነገር ደግሞ ቆይቶ ይፈነዳል። ሲፈነዳ ያለከልካይ ሲዘርፍና የበላይ ሆኖ እንደፈለገ የተገለገለው ሁሉ መግቢያ ቀዳዳ ይጠፋዋል። የዚያ ብሔር ተወላጅ ቢሆንም ያልተጠቀመው ደግሞ ባልበላው ተጎጂ ይሆናል። ከዚህ ሁሉ ይልቅ ትልቁ መፍትሔ እኩልነት ነው። ማንኛውም ሰው እኩል መታየት አለበት።
ማንኛውም ብሔር የበታች ብቻ ሣይሆን የበላይ ሊሆንም አይገባም። ሰዎች አገልግሎት የሚያገኙት ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው እና ያ አገልግሎት ስለሚገባቸው ብቻ ነው። አገልግሎቱን አንዱ እያገኘ ሌላው ሊያጣው አይገባም። ምክንያቱም ሁሉም ለአገሩ እኩል ነው።
በመላ አገሪቱ በየትኛውም ቦታ ማንኛውም ሰው ያለምንም መሸማቀቅ መኖር አለበት። ብሔር አቀንቃኝ ይቅርታ ብሔር አቀንቃኝ ለማትም ይከብዳል፤ ዘር አቀንቃኝ ፖለቲከኞች ይህንንም ጉዳይ አሥቡበት። ለነገሩ በፍትሃዊ መንገድ እኩል መገልገልን ጠቀስን እንጂ፤ ምንም እንኳ አሁን ረገብ ያለ ነገር ቢታይም፤ ሰው በገዛ አገሩ እርሱ ብቻ ሣይሆን እናት አባቱ ተወልደው ባደጉበት አገር የዚህ ዘር ተወላጅ በመሆንህ ውጣ እየተባለ የሚሣደደው ሰው ቁጥር አነስተኛ አይደለም። የኛ ዘመዶች ባህር አቋርጠው ከአገራቸው ርቀው ሄደው በሌሎች አገሮች ላይ ሲኖሩ፤ ወልደው ሲያሣድጉ እነርሱም ሆኑ ልጆቻቸው በብሔራቸው ተሣደው እንደማይገደሉ እና እንደማይሣደዱ እርግጠኞች ናቸው። በኢትዮጵያ ግን የዘር ፖለቲካ ባመጣው ጦስ ሰው በገዛ አገሩ እንደባይተዋር እየታየ መድረሻ መሸሸጊያ ጥግ እያጣ ነው።
እኛ የምንፈልገው እንዳንዱ ክልል ማንኛውም ሰው አማራም ሆነ አፋር፣ ሶማሌም ሆነ ትግሬ እኩል እንዲታይ፤ ያለምንም መሸማቀቅ እንዲኖርና አሥፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኝ፤ በየትኛውም የንግድም ሆነ የመንግሥትና የግል ሥራ ላይ እንዲሣተፍ ብቻ ነው። በሁሉም ክልል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከየትኛውም ሰው እኩል ተገልጋይ፣ ተጠቃሚና ተወዳዳሪ መሆን አለበት።
ጠዋትና ማታ ስለአንድ ብሔር መጠቃትና ስለሌኛው ብሔር የማጥቃት ጉዳይ የሚወራበትና ወደ በቀል የሚኬድበት ዘመን ሊያበቃ ይገባል። ብሔር ተኮር አካሄድ ሰው በገዛ አገሩ እንዲሸማቀቅ የሚያደርግ ሲሆን፤ ዛሬ ተረኛ ነኝ ብሎ የተኮፈሰው አድሮ ውሎ ይተነፍሣል። መኮፈስና በልዩነት መጠቀም ዘላቂ ስለማይሆን ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም ሊጠላውና ሊሸሸው ይገባል።
ማንኛውም ፓርቲ በሁሉም ሕዝብ ዘንድ መከበርና ዘላለም ሲወሳ መኖር ከፈለገ፤ አሁን ላይ በኢትዮጵያ የተንሠራፋውን ፅንፈኛ የብሔር አንዳንዴም የሃይማኖት ሁኔታን ያርግብ። በተለይ ከፅንፍ ብሔርተኝነት ጋር ተያይዞ የተጋረጡትን ሥጋቶች ያንሣ። የትኛውም ብሔር አይጨቆን፤ የትኛውም ብሔር በተለየ ሁኔታ በብሔሩ አይጠቀም። ሁሉም እኩል ይታይ። ሰዎች ስለብሔራቸው እንታገላለን ብቻ ሣይሆን ስለሁሉም እኩልነት እንታገላለን ይበሉ።
በእርግጥ በኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔሮች አሉ። እነዚህ ብሔሮች እንደሌሉ መታየት የለባቸውም። ቋንቋቸው እና ባህላቸው ሊያድግ ይገባል። ይህ ማለት መለየትን መስበክ ማለት አይደለም። በእርግጥ የትግራዩም፣ የአማራውም፣ የአፋሩም፣ የሲዳማውም፣ የወላይታውም ሆነ የጋሞ ቋንቋና ባህል መከበር አለበት። ነገር ግን የጋሞ ወይም የሲዳማ አሊያም የአፋር ወይም የሶማሌ ባህልና ቋንቋ ብቻ ይከበር ብሎ መነሣት ጤናማ አይደለም። ሁሉም እኩል ቋንቋና ባህሉ ይከበር። ሁሉም እኩል ይታይ። የኔ እምነት እርግጠኛ ለመሆን ቢያስቸግርም የብዙ ኢትዮጵያውያን ፍላጎት እኩልነት ነው።
ሕግ የሁሉም የበላይ ይሁን። ሕግ ከየትኛውም ግለሠብና ብሔር በላይ ከሆነ ሁሉም ነገር መሥመር መያዝ የሚችልበት ዕድል ይኖራል። በሕግ ፊት ሁሉም እኩል ከታየ በየትኛውም መሥክ ላይ ፍትሃዊነት ከሠፈነ ችግሮች ይቃለላሉ። ምጣኔ ሐብቱ ጠንካራ ሆኖ የሕዝቡ ሕይወት ከተቀየረ የሚፈለግ ምንም ነገር አይኖርምና። ፖለቲከኞቻችን ከወሠን እለፉ፤ ስለሁሉም እኩልነትና ፍትህ ቁሙ። ሠላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2013 ዓ.ም