በ2000 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራውን የጀመረው የሰመራ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት በሰባት ኮሌጆች ከሰባት ሺ አምስት መቶ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛ መርሐ ግብር ተቀብሎ በማስተማር ላይ ነው፡፡ ተቋሙ አምስት የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችን እንዲሁም በ38 የትምህርት ክፍሎች ደግሞ በመጀመሪያ ዲግሪ በማሰልጠን ላይ ይገኛል፡፡ በሰላም አምባሳደርነቱ የሚታወቀው ዩኒቨርሲቲው ሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተሞክሮውን ሊጋሩት እንደሚገባ ይታመናል፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ልዩነት ሊፈጥሩለት ያስቻሉት ተግባራት ምን ምን እንደሆኑ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አሊ ሁሴን ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፦ የዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማሩ ሂደት ምን እንደሚመስልና የሚታወቅባ ቸውን ጉዳዮች ቢነግሩን ?
አቶ አሊ፦ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከሚታወቅባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራዎች ይጠቀሳል፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሲሆን፤ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ ዘንድሮም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን በተሻለ መልኩ እንዲተገበሩ በማሰብ ከተማሪዎች ቅበላ ጀምሮ ትምህርታቸውን አጠናክረው መማር እንዲችሉ የተለያዩ ሥራዎችን ከአስተዳደር አካላት፣ ከአካባቢው ማህበረሰብና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ የመማር ማስተማር ሂደት እንዳይስተጓጎል፣ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን በመለየት የመፍታት ሥራዎች ለመሥራት ተችሏል፡፡ በዝግጅት ምዕራፍ ሥራችን ተማሪን ባግባቡ ለመያዝ የሚያስችል፣ የመማሪያ ግብዓቶችንም በጊዜ በማሟላት የዝግጅት ሥራዎች በማከናወን የመማር ማስተማር ሥራው በተሳካ ሁኔታ አስጀምረን ማስቀጠል ችለናል፡፡
ተማሪዎቹም እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ እና እንዲግባቡ የሚያስችሉ ተግባራትን በጋራ አካሂደናል፡፡ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን ማህበራዊ አንድነትን በመጠበቅ ተቻችሎ መዝለቅ እንዲቻል በታዋቂ ሰዎች ምክር እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ እርስ በእርስ በየትምህርት ክፍሉ ለአዲስ ተማሪዎችና መምህራን አቀባበል ከማድረግ ጀምሮ የመማር ማስተማር ስርዓቱ ሰላማዊ እንዲሆን ተማሪዎችም ተግባብተው እንዲማሩ በየትምህርት ክፍሉ በስፋት መድረኮችን አድርገናል፡፡ ይህ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስጠበቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከተማሪዎች ጋር ባደረግነው ሰፊ ውይይት በመማር ማስተማሩ የሚታዩ ችግሮችን በመንቀስ ለመፍታት ተችሏል፡፡ ከተማሪዎቹ ጋር በነበረን ውይይት እርስ በእርስ እንዲፋቀሩ፣ የመጡበትን ዓላማ ትኩረት አድርገው ለውጤት እንዲበቁ ድጋፍ ለማድረግ እየሞከርን ነው፡፡
ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራውን ሊያደናቅፉ የሚችሉ የተለያዩ ምልክቶች እየተስተዋለ የነበረ ቢሆንም ተማሪዎች በተደረጀ መልኩ በመንቀሳቀስ ከዓላማቸው የሚያሰናክላቸውን ተግባራት ስለሚታገሉ የጎላ ችግር አላጋጠመንም፡፡ የመጡበትን ዓላማ ለማሳካት እርስ በእርስ እየተደጋገፉ ርብርብ ያደርጋሉ፡፡ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሰላማዊነታቸው የሚታወቁ ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታም ከመጀመሪያ ከገቡት ተማሪዎች አንስቶ እየተወራረሰ የመጣ ጥሩ ባህል ነው፡፡ ጥያቄዎቻቸውን በሰለጠነ መንገድ የመጠየቅ የተሻለ አካሄድ አላቸው፡፡ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ እነዛን ችግሮች ከተማሪዎች ጋር በመወያየት የሚፈቱትን እንዲፈቱ ይደረጋል፡፡ በጊዜ ሂደት ሊፈቱ የሚችሉትን በመግባባት እየተካሄደ ነው፡፡ ከሚለያዩ ነገሮች አንድ የሚያደርጉ ብዙ መሆቸውን እና ኢትዮጵያዊ ስሜትን ሊጎዱ ከሚችሉ ነገሮች እንዲጠነቀቁ እና እንደ አንድ ቤተሰብ ልጆች እንዲተያዩ የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
አዲስ ዘመን፦ ሰመራ ዩኒቨርሲቲ የሰላም አምባሳደር ተብሎ እንዲመረጥ ያስቻላቸው መለያዎቹ ምንድን ናቸው?
አቶ አሊ፦ ዩኒቨርሲቲው ያለበት የተለየ አካባቢ ነው፡፡ የአየር ሙቀቱ ከባድ ነው፡፡ ተማሪዎች ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ ናቸው፡፡ ይህንን ፈተና ተቋቁመው ማለፍ እንዲችሉ የአካባቢው ማህበረሰብ ተሳትፎ በጣም ትልቅ ነው፡፡ በተለይም የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዙር የገቡ ተማሪዎች አርያነታቸውን፣ ሰላማዊነታቸውን እና ጽናታቸውን ለማስጠበቅ ተችሏል፡፡ ተማሪዎች ማናቸውንም ጥያቄዎች መጠየቅ የሚችሉባቸውን ሁኔታ መፍጠር፣ ሊፈቱ የሚችሉ ጥያቄዎችን በጊዜ በመፍታት የማይፈቱትንም በግልጽ በመነጋገርና በመተማመን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራን ማስጠበቅ ችለናል፡፡ ተማሪዎችም ችግሮችንም ተቋቁመው ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊ መንገድ የመጠየቅ ባህላቸው እንዲዳብር ተደርጓል፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብ ለተማሪዎች የሚያሳዩት ፍቅርና አክብሮት፣ ተማሪዎች የመጡበት ዓላማ ላይ ትኩረት አድርገው ለውጤት መሥራታቸው፣ አንደኛው ዙር ተማሪዎች ለቀጣዩ ዙር እንደ ባህል ያስተላለፉት ነገር ዩኒቨርሲቲው ልዩነት እንዲፈጥር አድርጎታል፡፡ የተግባቦት ስርዓቱም ክፍት ነው፡፡ ማንኛውም ተማሪ ያለውን ጥያቄ በማናቸውም መንገድ መጠየቅ የሚችልበት መንገድ እና ግልጽነት ለመፍጠር የሚሠሩ ሥራዎች የሰመራ ዩኒቨርሲቲን በሰላም አምባሳደርነት እንዲታወቅ አድርጎታል፡፡ አዳዲስ ተማሪዎችም ሲሰሙ ይህንን ዩኒቨርሲቲው የተጎናጸፈውን ስም ለማስቀጠል በቅብብሎሽ የራሳቸውን ሚና እየተወጡ ናቸው፡፡ በመሆኑም እስከአሁን ያን ያህል የጎላ ችግር አልገጠመንም፡፡ የተማሪዎች ህብረት፣ የሰላም ፎረምና የተለያዩ አደረጃጀቶች ዩኒቨርሲቲውን በማስተዋወቅና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር በማድረግ ረገድ የነበራቸው ሚና ትልቅ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ ተማሪዎች ተከባብረው፣ ተቻችለው እንዲማሩ የምትከተሏቸው ወይም ስለ ተዘረጋው የአሠራር ስርዓት ቢነግሩኝ ?
አቶ አሊ፦ ሁሌ እንደምንለው ዩኒቨርሲቲዎች የትንሿ ኢትዮጵያ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት መጥተው በአንድ ማዕድ ዕውቀት የሚገበያዩበት መድረክ ነው፡፡ ስለሆነም ሁሉም ተማሪ የራሱ ባህል፣ ዕምነት፣ ወግና ሌሎች ልዩነቶችን ይዞ የመጣ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታ እንደ አንድ ቤተሰብ በመተባበር የመጡበትን ዓላማ ለማሳካት የሚፍጨረጭሩበት ሂደት ነው፡፡ ተማሪዎቹ ዕርስ በእርስ የሚተዋወቁበት የባህል ቡድን፣ የባህል ማዕከልና አልባሳት አላቸው፡፡ ይህ ተማሪዎቹ እንዲፋቀሩ፣ እንዲከባበሩና ተቻችለው እንዲኖሩ የሚያስችላቸውን የጊቢ ህይወት መፍጠር ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን፦ አልፎ አልፎ ችግሮች ለመፍጠር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች፣ የሰላም ሂደቱን ለማደፍረስ የሚታዩ ምልክቶች አሉ በማለት የገለጿቸው አሉ፡፡ እነዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? የለያችሁባቸው መንገዶችስ ምን ዓይነት ናቸው?
አቶ አሊ፦ የተቋማችን ቁልፍ ችግሮች ብለን የምንወስዳቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ከውሃ፣ ከኤሌክትሪክ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው፡፡ የሚቀርበው ውሃ ከፍተኛ ሙቀት አለው፡፡ ተማሪዎች በቀጥታ ሊጠቀሙት ስለማይችሉ መቀዝቀዝ አለበት፡፡ ተማሪዎች የሚጠቀሙበትን ውሃ ለማቀዝቀዝም በርካታ ማቀዝቀዣዎች በተማሪዎች ማደሪያ ሕንፃ ላይ ይቀመጣል፡፡ የኤሌክትሪክ የኃይል እጥረትም አለ፡፡ ጊቢው ሲሠራ የሚተላለፈውን ኃይል ሊሸከም የሚችል መስመር ዝርጋታ አልነበረም፡፡ እነዚህ ሁለቱ እጥረቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከውሃ እጥረት ጋር ተያይዞም የመጸዳጃ ቤት ለመጠቀም እጥረትም ይነሳል፡፡ እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር እየሠራን እንገኛለን፡፡
ሰላምን ለማደፍረስ አንዳንድ አዝማሚያዎች ታይተዋል፡፡ አሉባልታዎችን መንዛት አንዱ አዝማሚያ ነው፡፡ ያልሞተ ተማሪ ሞቷል፣ ያልተበከለ ውሃ ተበክሏል ወይም ያልሆነ ነገር ሆኗል ብለው በተማሪዎች መካከል ማሰራጨት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ እነዚህን ለመረዳት የምንከተላቸው መንገዶች የተማሪዎች ህብረት፣ የሰላም ፎረምና የጊቢ ፖሊስ አሉ፡፡ እነዚህ የጊቢውን ደህንነትን ለማስጠበቅ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ የሚዘረጉ ናቸው፡፡ በማንኛውም ሁኔታ አስጊ ናቸው ብለው የሚያስቧቸውንና አሉባልታ በመንዛት ትኩረት በመሳብ አዝማሚያውን ምክንያት በማድረግም ለመጉዳት የታሰበው የእገሌን ብሄር ለመጉዳት ነው በሚል የተደረጉ ሙከራዎች ነበሩ፡፡ እንደዚህ ዓይነት አሉባልታዎችን የተከሰተ ነገር እንዳሌለ በውይይት በመግባባት በማስረጃና በመረጃ እንዲገነዘቡ በማድረግ አሉባልታዎችን የመመከት ሥራዎች በድረ ገጽ ጭምር የእርምት ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡
አሁንም እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ይጠበቃሉ፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ማዕከል አድርጎ ብጥብጥን ወደ አገሪቱ የማስፋት ስትራቴጂ መኖሩን በመዋቅር የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክቱናል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትም አቅጣጫ ተሰጥቶን እየሠራንበት ይገኛል፡፡ ጥያቄዎች ይነሳሉ ሲመለሱ እርሱን ወደ ጎን ትቶ አሉባልታን በመንዛት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲስተጓጎል የማድረግ ዝንባሌ ነበረ፡፡ ከጊቢ ውጪም የመማር ማስተማር ሂደትን የሚያስተጓጉል ሂደትን በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫ ለመስጠት የሚያስችል የአማካሪ ምክር ቤት ተዋቅሯል፡፡ ከአካባቢው ማህበረሰብ፣ ከጸጥታ አካላትና ከንግዱ ማህበረሰብ የተዋቀረው አማካሪ ምክር ቤቱ የተሻለ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ለማድረግ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ አንዳንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግጭት የሚዘወተርባቸው፣ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚጎዳና የተማሪዎችን ዓላማ የሚያሰናክል እየሆኑ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮችና ተማሪዎች ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ ምን መማር አለባቸው ይላሉ?
አቶ አሊ፦ ግልጽነትና አሳታፊ የሆነ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ከተማሪዎች የሚደበቁ ችግሮች የሉንም፡፡ ተማሪዎች እንዲያውቁ የሚገቡ ጉዳዮችን እንዲያውቁ ማድረግ ይገባል፡፡ ግልጽ የግንኙነት መስመር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ተማሪዎችን የመፍትሔ አካል ማድረግ ከድንጋይ ውርወራ እንዲቆጠቡ ያደርጋል፡፡ መፍትሔ እስኪገኝ ትዕግስት እንዲኖራቸውም ያስችላል፡፡ አብዛኛውን ተማሪዎች መያዝ ከተቻለ መልካም ነው፡፡ የአካባቢውን ማህበረሰብም በጎ ተጽእኖ በመጠቀም ለአጥፊ ተማሪዎች ከለላ የማይሰጥ፣ ጥሩ ተማሪዎችን የሚያበረታታ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በሰመራ ማህበረሰቡ ለአጥፊዎች ከለላ አይሰጥም፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች ለተገኙ ተማሪዎች ጥሩ ፍቅር ይለግሳሉ፡፡ መምህራን የተለየ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ተማሪዎችን በመልካም ስነ ምግባር በማነጽ ከፍተኛ ሚና ይወጣሉ፡፡
የተማሪዎችና የመምህራን ግንኙነት አባታዊና ወንድማዊ ነው፡፡ የአስተዳደር ሠራተኞችም ኃላፊነታቸውን ባግባቡ የሚወጡበት ስርዓት አለ፡፡ ለተማሪዎች ፍትሐዊ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ በብሄር፣ በሃይማኖትና በአካባቢ ሳይለዩ ያገለግላሉ፡፡ አድሎአዊ አሠራሮችን የመከለካል ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ ካፍቴሪያ ወይም ሌሎች አገልግሎት መስጫ ላይ ፍትሐዊነት የለም ከተባለ አንዱ ለረብሻ መነሻ ስለሚሆን ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ ለማናቸውም ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት፣ በጊዜ የሚፈቱትን ፈጥኖ መፍታት፣ በሂደት የሚፈቱት ላይ ቀነ ገደብ በማስቀመጥና ግልጽነት በመፍጠር እየታዩ ያሉ አለመረጋጋቶችን መቀነስ ያስፈልጋል፡፡ አብዛኞቹ ተማሪዎች በንቃት ፖለቲካዊ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡ አስተዳደራዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ጥያቄንም ይዘው ይመጣሉ፡፡
አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገርም ለመግባባትም ቀላል ነው፡፡ ፖለቲካዊ ጥያቄ ሲሆን ግን ለተቋሙ አሠራርና አመራር ተጨማሪ ከባድ ሥራ ነው፡፡ ምላሽ ለመስጠትም ያስቸግራል፡፡ ተማሪዎችን ስናወያይ የምናገኛቸው አብዛኛዎቹ ጉዳዮች በእኛ ማዕቀፍ የሚወድቁ ናቸው፡፡ ግን በጣም በርካታ የሚሆኑ ጥያቄዎች የሚነሱት አካባቢያቸው ላይ እንደ አገር ሊፈቱ የሚገባቸውን የማንሳት ነገር ነው፡፡ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ማስጠበቅ እንዲቻል የጊቢው አመራር፣ መምህራንና ሠራተኞች፣ የአካባቢው ማህበረሰብ፣ የአካባቢው ጸጥታ አካላት፣ ታዋቂ ሰዎች የሃይማኖት አባቶች ሚና ወሳኝነት አለው፡፡ የሃይማኖት አባቶች በየቤተ ዕምነቶቹ ስለ መቻቻል፣ ስለ ሰላም እና ተማሪዎቹ የመጡበትን ዓላማ አሳክተው እንዲመለሱ የማድረግ ሚና አለባቸው፡፡ እነዚህ አካላት በርብርብ የሚሠሩ ከሆነ አሁን እየታዩ የመጡ ችግሮች እልባት ያገኛሉ፡፡ የተሻለ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ማስጠበቅ ይችላሉ፡፡
አዲስ ዘመን፦ ለሰጡን ቃለ ምልልስ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ!
አቶ አሊ፦ እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን የካቲት 4/2011
በዘላለም ግዛው