የኩፍኝ በሽታን ስጋት የመከላከል ጥረት

በኢትዮጵያ የኩፍኝ በሽታን ስርጭት ለመቀነስ የሚቻልባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ሆነው በዚሁ ልክ ደግሞ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች እንዳሉም የሚገልጹት በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በክትባት መከላከል የሚቻሉ በሽታዎች ምላሽ ባለሙያ አቶ ሚኪያስ አላዩ፤ ከእነዚህ ውስጥ ዋነኛው የክትባት ሽፋንን ወይም ተደራሽነትን ማሳደግ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

የበሽታውን ስጋት ለመቀልበስ በተለይ የክትባት ተደራሽነትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማሳደግና የወረርሽኝ ምላሽ ሥራዎችን ለማጠናከር በኢትዮጵያ የተለያዩ ሥራዎች እንደሚገኙም ይጠቁማሉ፡፡ በተጨማሪም ወረርሽኞችን በጊዜ የመለየትና አፋጣኝ ምላሽ የመስጠት ሥራዎችም በጥሩ ሁኔታ አብረው እየተሠሩ እንዳሉም አቶ ሚኪያስ ይገልጻሉ፡፡

ወረርሽኙ ባለባቸው ወረዳዎች ብዛት ሲታይ በፊት ከነበረበት ከ101 ወረዳዎች በአሁኑ ጊዜ ወደ 12 ወረዳዎች እንደወረደና ይህም የወረርሽኙን ስርጭት ለመቀነስ የተደረጉ በክትባት ሽፋንና በወረርሽኝ ምላሽ ላይ የተሠሩ ጠንካራ ሥራዎች መኖራቸውን እንደሚያመላክት ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ይህ የበሽታውን ስርጭት ስጋት መቀነስ እንደሚቻል አንዱ ማሳያ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

ከዚህ በፊት የኩፍኝ በሽታ ስርጭት ስጋትን ለመቀልበስ የሚደረጉ የታወቁ ጥረቶች እንደነበሩ የሚናገሩት ደግሞ የክትባት ባለሙያው አቶ ሙላት ንጉሴ፤ ቀደም ሲል በመደበኛ የኩፍኝ ክትባት ከሁለት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት እንደሚሰጣቸው ይጠቅሳሉ። ይህ ሥራ ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ ሲሠራበት መቆየቱን ያስታውሳሉ፡፡ በዚህ የክትባት ሥራም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናትን ሞት መቀነስ መቻሉን ያስረዳሉ፡፡

እ.ኤ.ኤ ከ2019 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ሁለተኛው ዶዝ የኩፍኝ ክትባት ከአስራ አምስተኛ ወር ጀምሮ እየተሰጠ መሆኑን አቶ ሙላት ይጠቁማሉ፡፡ የክትባቱን ተደራሽነት በማየት አንዳንዴ ከአምስት ዓመት ሌላ ጊዜ ደግሞ ከአስራ አምስት ዓመት በታች ክትባቱ እንዲሰጥ የሚደረግባቸው ሁኔታዎች እንዳሉም ይጠቅሳሉ፡፡ የበሽታው ቅኝትና ምላሽ ፍሰት ሥራዎች ሲሠሩ እንደነበርና በዚህም በበሽታው የሚከሰተው የሞት መጠን ከ80 ከመቶ በላይ መቀነስ እንደተቻለም ያወሳሉ፡፡

ከዚህ አንፃር አሁን ላይ በሽታን እንደ ሀገር መከላከል እንደሚቻል የሚናገሩት አቶ ሙላት፤ ዋናው ጉዳይ የክትባት አገልግሎቱን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ ነው ይላሉ፡፡ በጤና ሚኒስቴር በኩል በመደበኛና በዘመቻ መልኩ የሚሰጡ የክትባት አገልግሎቶችንና የሚደረጉ የበሽታ ቅኝቶችን የማጠናከር ሥራ እየተሠሩ እንደሚገኙም ጠቅሰው፤ እነዚህ ሥራዎች በተሻለ ሁኔታ ተጠናክረው እየተሠሩ በሄዱ ቁጥር በሽታውን በቀላሉ የመቀልበስ እድል እንዳለ ይናገራሉ፡፡

እድሜያቸው የበሽታውን ስርጭት ስጋት መቀልበስ ብቻ ሳይሆን ስርጭቱን ለመቀልበስ እየተደረገ ያለው ጥረት በሽታውን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ የሚያስችል እንደሆነ አመልክተው፤ ነገር ግን ደግሞ እድሜያቸው ከአምስትና ከሁለት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናትን በክትባት በመላው ሀገሪቱ ተደራሽ ለማድረግ የተረጋጋና ሰላማዊ አካባቢ እንደሚፈልግ አቶ ሙላት ይጠቁማሉ፡፡

የፀጥታ ችግር ያሉባቸው አካባቢዎች፣ የተፈጥሮ አደጋ በተለይም ጎርፍና ድርቅ የተከሰተባቸው አካባቢዎችም ክትባቱን ተደራሽ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ፈተና ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠቅሳሉ፡፡ የጤና ባለሙያዎች ሥራ መልቀቅ፣ የክትባት አገልግሎት መሠረተ ልማት አለመስፋፋትም በክትባት አገልግሎቱ አሰጣጥ ላይ ክፍተት ሊፈጥር እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን የፀጥታ ችግር ባለባቸው፣ ድርቅና ጎርፍ በተከሰተባቸው እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች በከፍተኛ ደረጃ በሚለቁባቸውና የክትባት አገልግሎት መሠረተ ልማት ባልተስፋፋባቸው አካባቢዎች የሚታዩ ክፍተቶችን በመሙላትና ጠንካራ ሥራዎችን በመሥራት የክትባት ተደራሽነቱን አስፍቶ የበሽታውን ስርጭት ስጋት የመቀልበስ እድል መኖሩን አቶ ሙላት ያብራራሉ፡፡

እንደ አቶ ሚኪያስ ሃሳብ ደግሞ በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወረርሽኞች በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፉበት ጊዜ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት እንደነበር ያስታውሳሉ። በተለይ የኮቪድ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ መከሰት በአጠቃላይ የጤና ሥርዓቱ ወደዚሁ ወረርሽኝ አተኩሮ ስለነበር በዚህ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ የኩፍኝ በሽታ ስርጭትን መግታት ሳይቻል ቀርቷል ሲሉ አቶ ሙላት ያነሱትን ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡

ከዚህ በኋላ ግን የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ጥሩ እምርታ በኢትዮጵያ በኩል እንደታየ ይጠቅሳሉ፡፡ ተከታታይ የክትባት ዘመቻ ሥራዎች መሠራታቸውንም ያስታውሳሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2025 በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሠሩ የክትባት ዘመቻዎች በመኖራቸውና ሌሎችም ሥራዎች እየተከናወኑ በመሆኑ አሁን ላይ ያለውን የበሽታውን ስርጭት ስጋት መቀልበስ እንደሚቻልም ነው አቶ ሚኪያስ የሚናገሩት፡፡

የኩፍኝ በሽታ ስርጭት ስጋት መግታት ከተቻለ በበሽታው ሊያዙ የሚችሉና ይህንኑ ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን ሞት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ እንደሚቻል የሚናገሩት አቶ ሙላት፤ በሽታው ካለና ከበሽታው ጋር በተያያዘ ሞት የሚከሰት ከሆነ ደግሞ ምርታማነትና ከምርታማነት ጋር ተያይዞ በቤተሰብ ደረጃ የኢኮኖሚ ጫና እንደሚያሳድርም ነው የሚጠቁሙት፡፡

በተቃራኒው በሽታውን ቀድሞ መከላከል ካልተቻለ በዚህ በሽታ የሚሰቃዩ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ ባለፈ በሽታውን ለማከም በሚደረገው ጥረት ሀገሪቱን ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚያስወጣት ይጠቅሳሉ፡፡ ይህ ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚያሳድር ያመለክታሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ስጋቱ ካልተቀለበሰ በሕፃናት ላይ የሚከሰተው ሞት እንደሚጨምርና በቤተሰብ ደረጃ ለሕክምና የሚወጣው ወጪ የቤተሰቡን ኢኮኖሚ እንደሚያናጋም ነው አቶ ሙላት የሚናገሩት፡፡

አቶ ሚኪያስም በአቶ ሙላት ሃሳብ በመስማማት ኩፍኝ በቀላሉ የሚተላለፍና መሰራጨት ከሚችሉ በሽታዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ የወረርሽኙን ስጋት መቀልበስ ካልተቻለ ትልቅና ሀገር አቀፍ ወረርሽኝ የማስከተል ስጋት እንዳለው ይገልፃሉ፡፡

በተለይ በወረርሽኝ ላይ የቁጥጥርና የክትባት ሥራዎች ካልተሰሩ ወረርሽኙ ሰፍቶ የአካል ጉዳትና ሌሎች ተጓዳኝ የጤና ጉዳቶችን ከማስከተል ባለፈ ሞትንም እንደሚያመጣ ይጠቁማሉ፡፡ የጤና ሥርዓቱን እንደሚያዛባና ሌሎች የጤና ሥራዎችን እንደሚሻማም ይገልጻሉ፡፡

በተቃራኒው የኩፍኝ በሽታ ስርጭት ስጋትን መቀልበስ ከተቻለ በተለይ የክትባት ተደራሽነትን ማስፋት ከተቻለ ክትባቱ ውጤታማ ከመሆኑ አንፃር ሊፈጠር የሚችለውን የወርሽኝ መስፋፋት አደጋ ከመግታት ባለፈ በጤና ላይ ሊያስከትል የሚችለውን የአካል ጉዳትና ሌሎች ውስብስብ የጎንዮሽ ጉዳቶችን እንዲሁም ሞትን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ እንደሚቻል አቶ ሚኪያስ ያመለክታሉ፡፡

በበሽታው ምክንያት ሊወጣ የሚችለውን ሀብት ማዳን እንደሚያስችልም ይጠቅሳሉ፡፡ መደበኛ የጤና አገልግሎት ሥራዎችም ሳይረበሹ እንዲቀጥሉ ለማድረግ እንደሚረዳም ይገልጻሉ፡፡ በዋናነት በኢትዮጵያ በሽታውን ለመከላከል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ጠንካራ መሆናቸው ደግሞ የበሽታው ስርጭት ስጋት ሊሆን የሚችልበት ደረጃ እንደማይደርስም ነው የሚጠቁሙት።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You