አዲስ አበባ፡- የኢትዮ- ፈረንሳይ የትብብር ግንኙነት 126 ዓመታት ያስቆጠረ እንደሆነ የተለያዩ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ የዘለቀው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በአሁኑ ወቅት በትምህርት፣ በኢንቨስትመንት፣ በባህልና ቅርስ ጥበቃ፣ በኃይል አቅርቦት፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እየተጠናከረ መጥቷል፡፡
የሀገራቱ ግንኙነት ከመንግሥታት ግንኙነት ባለፈ፤ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ከፍ ያለ ስፍራ ያለው ነው፡፡ በርካታ የፈረንሳይ ዜጎች በኢትዮጵያ ይገኛሉ፤ እንዲሁም በርካታ ኢትዮጵያውያም በፈረንሳይ ይኖራሉ፤ ይማራሉ፤ ይሠራሉ፡፡
የኢትዮጵያና ፈረንሳይ ግንኙነት ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመን ይነሳል፡፡የኢትዮጵያ የባቡር መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ሲነሳ ፈረንሳይ ቀዳሚዋ ሀገር ሆና ትጠቀሳለች፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ጉዳይ ሲነሳም ከአሜሪካው ቦይንግ ቀጥሎ የሚነሳው የፈረንሳይ ኤርባስ ነው፡፡
በቅርቡም በአፍሪካ የመጀመሪያ የተባለውን ግዙፉን ኤርባስ ኤ350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላን ኢትዮጵያ ከፈረንሳዩ ኩባንያ ተረክባለች፡፡ ሌሎች በርካታ የኤርባስ አውሮፕላኖችንም አዛለች፡፡
የከተማ ልማት፣ የትምህርት ፣ የቅርስ ጉዳዮችም ሲነሱ ሀገሪቱ ከፊት ለፊት ከሚጠሩት መካከል ትጠቀሳለች፡፡ ከቅርስ አንጻር የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት እድሳት እየተካሄደ ያለው በፈረንሳይ መንግሥት ወጪ ነው። ሌሎች ተመሳሳይ ድጋፎችን ፈረንሳይ እያደረገች ትገኛለች፡፡
ባለፉት ዓመታት የሁለቱ ሀገሮች መሪዎች ይህን ግንኙነት የላቀ ደረጃ የሚያደርሱ ጉብኝቶችን ማድረጋቸው ይታወቃል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በፈረንሳይ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፤የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ማክሮንም እንዲሁ ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል፡፡ የአሁኑ የፕሬዚዳንት ማክሮን ጉብኝት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁለተኛው ነው፡፡
የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ለኢትዮጵያ ብዙ ፋይዳዎች ይኖሩታል፡፡ ሀገሪቱ ባለፉት ዘመናት በኢትዮጵያ የከተማ ልማት ውስጥ አሻራቸው ከፍተኛ የሆነ ኢትዮጵያውያን መሐንዲሶችን በማሰልጠን ትታወቃለች።
ይህንን ተሞክሮዋን በከተማ መልሶ ልማት እንዲሁም ማዘመን ላይ በስፋት እየሠራች በአጠቃላይ ከተሜነት እየተስፋፋ በተቻለ መጠን ኢትዮጵያ ልማቱን በፕላንና በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን በማድረግ በኩል ሀገሪቱ የላቀ ሚና ይኖራታል፡፡
ሀገሪቱ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸው ምርቶች በየጊዜው እየጨመሩ ናቸው፤ በተለይ እንደቡና፣ ጥራጥሬ ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞች ያሉት የግብርና ምርቶች፣ የማእድን፣ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ የመሳሰሉ ምርቶችን በስፋት ለውጭ ገበያ እንደምታቀርብ ይታወቃል፡፡
በቀጣይም ይህ ምርታማነትና ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደመሆኑ፤ፈረንሳይን ያህል ትልቅ ሀገር አስፈላጊነቱ ከፍተኛ ነው፡፡
በእነዚህ ምርቶች ተቀባይነት ሀገሪቱ እስከ አሁንም አትኖርበትም ተብሎ ባይታሰብም መዳረሻነቷን ለማስፋት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
ሀገሪቱ ለቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው የቅርስ ጥበቃ ሥራዎች ላይ ድጋፍ እያደረገች መሆኗ ይታወቃል፡፡ የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናትን በማደስ በኩል ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች፡፡ በታችኛው ቤተመንግሥት እድሳትም እንዲሁ ድጋፍ ታደርጋለች። በቀጣይም እድሳት የሚፈልጉ በርካታ ቅርሶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በዘርፉ ሀገሪቱ ያላት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዛሬ ላይ የምታደርገው ድጋፍ ማሳያ ነው።
ኢኮኖሚዋ በእጅጉ እያደገ የመጣው ኢትዮጵያ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የወጪና ገቢ ንግድን ለማሳለጥ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የታመነበትን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ወደ ሙሉ ትግበራ ላሸጋገረችው ኢትዮጵያ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ፋይዳ የላቀ ይሆናል፡፡
ሀገሪቱ ወደ ትግበራ ያስገባችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንደ የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሲጠብቁት የነበረ እንደ መሆኑ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ይህን ወሳኝ እርምጃ ለማሳወቅና ለሀገሪቱ ባለሀብቶች ጥሪ ለማስተላለፍ ያስችላል። ሀገሪቱ በተለያዩ መስኮች እያሳየች ያለውን ለውጥ ለማስገንዘብም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
ጉብኝታቸው የኢትዮጵያንና ፈረንሳይን የቆየ ወዳጅነትና በተለያዩ ዘርፎች እየተጠናከረ የመጣውን ወዳጅነት ወደ አዲስ ምእራፍ ሊያሸጋግርም ይችላል:: ክቡር ፕሬዚዳንት እንኳን ደህናመጡ! ለማለት እንወዳለን፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲናሙፍቲ፤ ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በዲፕሎማሲ፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በባህልና በሌሎች ዘርፎች 126 ዓመታትን ያስቆጠረ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡
የፈረንሳይ መንግሥት በተለያዩ ምክንያቶች የተዘረፉ የአፍሪካ ቅርሶችን በመመለስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሆነ አመልክተው፤ ለላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ጥገና ድጋፍ እያደረገ ነው፤ ይህም ለሌሎች ሀገራት ትምህርት የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን አጠናክረው ለማስቀጠል የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመው፤ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሀገራቱን ግንኙነት ለማሳደግ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
በፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ደረጃ ያሉ መሪዎች ኢትዮጵያ መምጣታቸው የሀገሪቱ ተሰሚነት ማደጉን እንደሚያሳይ ገልጸው፤ የሀገሪቱን ገጽታ ለመገንባት እንዲሁም ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር እገዛ እንዳለው አምባሳደር ዲና አስታውቀዋል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13 ቀን 2017 ዓ.ም