የአንካራ ዲክላሬሽን የስኬታማ ዲፕሎማሲ ማሳያ !!

በተርኪዬ ዋና ከተማ አንካራ የተደረገው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች ስምምነት አሁንም ድረስ የብዙ መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ትኩረት ሆኖ ቀጥሏል። አንድ ዓመት ሊሆን ከወራት ያነሰ እድሜ የቀረው በኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የተደረገው ስምምነትን ተከትሎ በብዙ መንገድ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ውስጥ የከረሙት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመጨረሻም አንካራ ላይ ሰላም ማውረዳቸውም የሚታወስ ነው።

ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ከኢትዮጵያው መሪ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ንግግር ሊያደርጉ ነው የሚሉ የዜና ምንጮች የተለያዩ ዘገባዎችን ይዘው ወጥተው የነበረ ቢሆንም ስምምነቱ በሁለቱ መሪዎች ተካሂዶ ይፋ እስኪሆን ድረስ ሁነኛ ማረጋገጫ አልተገኘም ነበር።

ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ያደረጉት የባሕር በርን የሚመለከተው የመግባቢያ ሰነድ በብዙ መንገድ ሶማሊያ የግዛቴ አካል ናት ብላ ከምትጠራት ሶማሌላንድ ጋር ሊደረግ አይገባውም በሚል አላስፈላጊ ክሶችን እና ስም ማጠልሸት ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ በሌሎች መሪዎችም ሲደረግ ከርሟል።

ይሄን በሁለቱ ሀገራት የተፈጠሩ ችግሮችን ለማባባስ እና ለማቀጣጠል ያልተቀደሰ ጋብቻ በማድረግ ክፍተቱን ለአሉታዊ ጥፋት ለመጠቀም ከአስመራ እስከ ካይሮ እሳት ሲቆሰቁሱ መክረማቸውም የሚዘነጋ አይደለም። በተለይም የሶማሊያው መሪ ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ችግሩን በሁለትዮሽ መድረክ እና ውይይት ከኢትዮጵያ ጋር ከመፍታት ይልቅ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ወደ ሆነችው ግብጽ ሲኳትኑ መክረማቸው የሰውየውን ያልተጠና አካሄድ ቁልጭ አድርጎ ያሳየም ነበር። ሶማሊያ ስትከተለው የቆየችው ኢትዮጵያን የማጠልሸት መንገድ ለዓመታት ለሶማሊያ ደም እና አጥንቱን ሲገብር ለቆየው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እንኳን አልራራም ነበር።

የሶማሊያው መሪ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ሲያጠለሽ በአፍሪካ ህብረ ጥላ ስር ተሰማርቶ ለሶማሊያ ሰላም እና ደህንነት ውጋ ሲከፍል የቆየውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ እንደ አዲስ በሚደራጀው የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጦር እንዳይካተት እና አሁን ያለው ጦርም ከግዛቴ እንዲወጣልኝ በማለት ጫና ሲፈጥር መክረሙም አይዘነጋም።

ይህ ሁሉ ባለበት ነው እንግዲህ የአንካራው ስምምነት የመጣው። ይህ ስምምነት ሰላማዊ በሆነ መንገድ በቱርክዬ አሸማጋይነት መጠናቀቁ ከሁለቱ ሀገራት አልፎ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ውጥረትን እና ብጥብጥን ለማንገስ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ግብጽ መሰል ሀገራት መና ያስቀረ ነው ተብሎ ሊወሰድ የሚችለውም በዚህ ምክንያት ነው።

በሁለቱ ሀገራት የተደረሰውን ስምምነት ብዙዎቹ ታሪካዊ በማለት የገለጹት ሲሆን፤ በተለይም ‹‹በሁለቱ ሀገራት መካከል ጦርነት ይነሳ ይሆን የአፍሪካ ቀንድ ወድ ሌላ አስከፊ ጦርነት ያመራ ይሆን››የሚሉና ሌሎች የማይጨበጡ መላምቶችን በማስቀረት በሀገራቱ መካከል ሰላም እና ትብብር ሰፍኖ ዳግም ውጤታማ ግንኙነት እንዲኖራቸው የሚያደርግ በመሆኑ በብዙዎቹ ዘንድ እየተሞካሸ ይገኛል።

በአንካራው ስምምነት በመነሳት የተለያዩ ተቃዋሚ ኃይሎች ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት ውድቅ እንደሆነ እና ከዚህ በኋላ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው መሰረተ ቢስ አሉባልታዎችን በማንሳት እየጠቀሱ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን በስምምነት ነጥቡ ውስጥ አለማካተቱም እንደ ትልቅ የዲፕሎማሲያዊ ስኬት ተደርጎ የሚቆጠር ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ሶማሊያ በአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ስር ሆነው እንዲሁም ለሶማሊያ ሰላም እና ደህንነት የሀገር መከላከያ ሠራዊት የከፈለውን መስዋዕትነት ዕውቅና እንድትሰጥ ያስገደደበት መንገድ በቀላሉ ታይቶ የሚታለፍ አይደለም።

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት በተለያዩ መድረኮች ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው (MOU) ሳይቀደድ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር አልነጋገርም፣ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ይቅርታ ሊጠይቀኝ ይገባል የሚሉ እና ሌሎች መሰል የእብሪት ንግግሮችና ግትር አቋም በማስቀየር ስምምነት ላይ መደረሱን የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ አቅምና ውጤታማነት ያመላከተ ነው ማለት ይቻላል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልጋታል የሚል ጥያቄን ማንሳት ቀርቶ የባሕር በር ያስፈልጋታል ብሎ ማሰብ የማይቻልበት ደረጃ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ይህ ጉዳይ መልኩን ቀይሯል። የኢትዮጵያን ፍትሐዊ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ዓለም ተረድቶታል።

ይሁንና በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ብሔራዊ ጥቅምን ከመንግሥት ተቃውም ለይተው የማያዩ አንዳንድ ኃይሎች አሁንም ቢሆን ስምምነቱን እያጣጣሉት ይገኛሉ። ይሁንና ይህ ፈፅሞ ሊታረም የሚገባ የስህተት መንገድ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

መንግሥትን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መቃወም እና መተቸት የዲሞክራሲ ባህል በዳበረባቸው ሀገራት የተለመደ እና በእኛም ሀገር ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ ቢሆንም ሁሌም ቢሆን ከመቃወም አባዜ አለመውጣት ብሎም በአንድ አጀንዳ የተራራቁ ሃሳቦችን መያዝ ማንም ምክንያታዊ ነኝ ብሎ በሚያስብ ዜጋ ሊያስገምት የሚችል ጉዳይ ነው። ሁሌም የተቃውሞ አባዜ የተጠናወታቸውን እነዚህ አካላት ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ መንግሥትን ከመቃወም የዘለለ ሰፊ ጽንሰ ሃሳብ መሆኑን በቅጡ የተረዱት አይመስልም።

ይህ ስምምነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)ን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት በአንካራ ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠናቀቁ ሁሌም ግጭት እና ብጥብጥ በማያጣው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የሚያስችል ነው በማለት አድናቆትን ችረውታል።

ለአብነትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ ሀገራቱ የደረሱበትን ስምምነት ያደነቁ ሲሆን፤ ከተመድ በተጨማሪም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ጀርመን፣ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ስምምነቱን በማድነቅ በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት እና ገንቢ ትብብር ለመፍጠር የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መክረዋል።

የአንካራው ስምምነት አሁንም ድረስ የብዙ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆኖ እያለፈ የሚገኝ መሆኑም በገሀድ የሚታይ ሀቅ ነው። ይህን ስምምነት የተርኪዬ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ከሆነው ቲአርቲ ወርልድ እስከ አልጀዚራ ከዴይሊ ሜል እስከ ብሎምበርግ ሌሎች መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ የተለያዩ ዜናዎች እና ዘገባዎችን ተደራሽ እያደረጉ ሲሆን፤ ይሄም የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት መብት በመላው ዓለም ካለምንም ወጪ የተዋወቀበት ነው ማለት ይቻላል።

በዓለም ተለዋዋጭ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ አሁን ላይ የኢትዮጵያን ፍትሐዊ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ከታላላቅ ሀገራት እስከ ዓለም አቀፍ ተቋማት ግንዛቤ ከማግኘት በዘለለ አዎንታዊ ድጋፍ እየሰጡ መገኘታቸው ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ያሸነፈችበት ስምምነት ነው ማለት ይቻላል። የዲፕሎማሲው ውጤታማነት ማሳያ ሆኖ ሊጠቀስም የሚችል ነው።

ምንም እንኳን በተለያየ መንገድ ስምምነቱን ለማጣጣል የሚደረጉ ሙከራዎች ቢኖሩም እንኳን ማንም በምንም ሁኔታ ሊክደው የማይችለው ሀቅ ከዚህ ስምምነት ኢትዮጵያ ያተረፈችበት እንጂ የከሰረችበት ጉዳይ አለመሆኑን ነው።

ኤልያስ ጌትነት

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You