ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በመፍታት መቀራረብንና ጠንካራ አንድነትን የሚፈጥር ነው

አዳማ፡- ሀገራዊ ምክክሩ ያሉ ችግሮችን በመፍታት መቀራረብንና ጠንካራ አንድነትን የሚፈጥር መሆኑን ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ገለጹ።

አርቲስት ቀመር የሱፍ በኦሮሚያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ውይይት ትናንት ሲካሄድ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን ለመፍታትና ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ትልቅ እድል የፈጠረ ነው።

እንደ ሕዝብ ከሚያለያዩን ነገሮች ይልቅ የሚያቀራርቡን ነገሮች እንደሚበልጡ የተናገረው አርቲስቱ፤ የሚያቀራርቡንን ነገሮች ወደ ፊት ለፊት በማምጣት ችግሮችን በውይይት መፍታት አለብን ብሏል።

ሀገራዊ ምክክሩ በሰጠን ዕድል በመጠቀም ተወያይቶ ሰላም መፍጠር እንደሚቻል አመልክቶ፤ ሰላም ፈጥሮ የሀገር ዕድገት ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል።

ለችግሮቻችን መፍትሄ መፈለግ ያለብን እራሳችን ነን ያለው አርቲስት ቀመር፤ በሀገራዊ ምክክሩ ተነጋግሮ መስማማት ምርጫ የሌለው ግዴታችን ነው ብሏል።

አርቲስት ፀጋዬ ደንደና በበኩሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጸው፤ያለመመካከር ችግር ያመጣል። በአንጻሩ ደግሞ መመካከር የችግሮች መፍቻ ቁልፍ ነው፡፡

ከጥንት ጀምሮ ሰዎች በአካባቢያቸው በዛፍ ስር

ተቀምጠው በመመካከር ችግሮችን ይፈቱ እንደነበረ ያስታወሰው አርቲስቱ፤ መመካከር ለችግሮች መፍቻ መንገድ መሆኑን ተናግሯል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እየሠራ ያለው ሥራ የአመቻችነት መሆኑን ያመላከተው አርቲስቱ፤ ምክክሩ ሕዝቡ በራሱ ለግጭት መንስኤ የሆኑ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ለችግሮቹ መፍትሔ የሚፈልግበት ትልቅ መድረክ መሆኑን ተናግሯል። ምክክሩም ውጤታማ እንደሚሆን አክሎ ገልጿል።

ሌላኛው የኦሮሚያ ክልል ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑት አቶ አብዱራዛቅ ሙራድ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ ሰላምን የሚያመጣ ነው።

ሀገራዊ ምክክሩ ያሉብንን ያለመግባባት ችግሮች የምንቀርፍበት ትልቅ ሀገራዊ መድረክ መሆኑን ገልጸው፤ ችግሮች እንዲፈቱ ሁሉም ተሳታፊዎች አጀንዳዎችን ፊትለፊት በማምጣት በግልጽ መወያየት አለበት ነው ያሉት።

በመድረኩ ትልልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ለውይይት የሚቀርቡበት ነው ያለው አቶ አብዱራዛቅ፤ ይህንን ትልቅ ዕድል በመጠቀም ችግሮቻችንን ፈትተን ወደ ሰላም መምጣት አለብን ብለዋል።

ኮሚሽኑ በገለልተኛነት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ጥሩ መሆኑን ጠቁመው፤ እሱም እንደ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰብ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል።

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You