የፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጉብኝት የሀገራቱን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሻግር ነው!

ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የረጅም ዘመን የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ወዳጅ ሀገራት ናቸው። በእነዚህ ረጅም የግንኙነት ጊዜያት ውስጥ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በብዙ መልኩ የየሀገራቱን ብሔራዊ ጥቅሞች እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የሚያሳድጉ ሰፋፊ ተግባራትን አከናውነዋል።

ግንኙነታቸው በየወቅቱ ወደ ስልጣን በሚመጡ የየሀገራቱ መንግሥታት እና መንግሥታቱ ከሚከተሏቸው የፖለቲካ – ኢኮኖሚ አኳያ የተለያዩ ገጽታዎች ቢኖረውም፤ በአሁኑ ዘመን በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ከእስከ ዛሬው የተሻለ እና የደመቀ እንደሆነ በዲፕሎማሲና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ባለሙያዎች ሳይቀር እየተመሰከረለት ይገኛል።

በተለይም የለውጡ መንግሥትን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ በሀገራቱ መካከል በአዲስ መልክ የተጀመረው የትብብር ግንኙነት፤ የፈረንሳይ መንግሥት ለኢትዮጵያውያን የለውጥ መነሳሳት ያለውን ከበሬታ በተጨባጭ ያሳየ ነው። ለዚህም የፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው።

ፕሬዚዳንቱ በሀገራቱ መካከል የነበረውን ዘመናት ያስቆጠረ ግንኙነት፤ዘላቂ ወዳጅነትን እና ብሔራዊ ጥቅሞችን መሠረት ባደረገ መንገድ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አድርገዋል፤ በሀገራቱ መካከል መተማመንን እና ላቅ ያለ ወዳጅነትንም ፈጥሯል።

ለዚህም ላለፉት አምስት ዓመታት በፈረንሳይ መንግሥት በኩል የኢትዮጵያ ባሕር ኃይልን እንደገና ለማደራጀት፣ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ለመጠበቅና ለማደስ ፣ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ሙዚየምን ለማደራጀት የተገቡ ቃላት እና በተግባር እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ማሳያ ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው።

ከቅርሶች እድሳት ጋር በተያያዘ በፈረንሳይ መንግሥት የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ እየተከናወኑ የሚገኙት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የታላቁ ቤተ መንግሥት እድሳት ተጠቃሽ ናቸው። በፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ ወደ ሀገር ውስጥ የተመለሱ ቅርሶችም የዚህ እውነታ ተጨማሪ ማሳያ ናቸው።

የፈረንሳይ መንግሥት፤ በፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኩል፤ ቅርሶቹን ለማደስ እና ለማልማት እያደረገ ያለው ድጋፍ ሆነ ሌሎች ሀገርን የመደገፍ ፈቃደኝነቶች የፈረንሳይ ሕዝብ እና መንግሥት በሀገራቱ መካከል የነበረውን ግንኙነት ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት የሚገልጽ ነው።

ከዚህም ባለፈ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የፈረንሳይ መንግሥት ለኢትዮጵያ የሚያደርጋቸው የተለያዩ የልማት ድጋፎች ለኢትዮጵያ ያለውን አጋርነት በተግባር ያሳየ ነው። ይህ አጋርነት በቀጣይም በተለያዩ ዘርፎች ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሚሆን ይታመናል።

የፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የአዲስ አበባ ጉብኝት ከሁሉም በላይ በሀገራቱ መካከል እያደገ የመጣው የሁለትዮሽ ሁለንተናዊ ግንኙነት ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ሀገራቱ በጋራ በቀጣናዊ እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች የሚመክሩበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

በተለይም ለሀገራችን የህልውና ጥያቄ በሆነው የባሕር በር ጉዳይ ከዚያም ባለፈ፤ እንደ ሀገር ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ለጀመረችው አዲስ የልማት ጉዞ በተናጠል ሆነ ከሌሎች ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር በመሆን የፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ እንደ መልካም አጋጣሚ የሚታይ ነው።

በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እያደረገችው ያለውን ጥረት በመደገፍ፤ የቀጣናው ሀገራት የወደፊት እጣ ፈንታ ብሩህ እንዲሆን የፈረንሳይ መንግሥት እና ሕዝብ ሊያበረክቱ የሚችሉትን አስተዋጽኦ ለማሳየት የሚያስችል ነው።

ከዚህም ባለፈ አፍሪካውያን በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ውክልና እንዲኖራቸው እየተደረገ ላለው አህጉራዊ ጥረት የፈረንሳይን መንግሥት እና ሕዝብ ድጋፍ የሚሰበስብበት እንደሚሆን ይታመናል።

ጉብኝቱ በአጠቃላይ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተጀመረውን አዲስ የትብብር ግንኙነት ለማስቀጠል የሚረዳ ከመሆን ባለፈ፤ ቀጣናዊ የሰላም እና የልማት አጀንዳዎችን ትርጉም ባለው መንገድ ለማየት አህጉራዊ ጥያቄዎች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ የተሻለ ዕድል የሚፈጥር ነው!

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You