ተገኝ ብሩ
ከልጅነቱ ጀምሮ ጥልቅ የሆነ የማንበብ ፍቅር በውስጡ አደረ። ለንባብ ፍቅር ማስታገሻ ይሆነው ዘንድ ደግሞ ቤተመፅሀፍ መዋያው፣ማንበቢያ ስፍራዎች ደግሞ ማዘውተሪያው ሆኑ። ማንበብ የማይደክመው፤የሚነበቡ መፅሀፍት ደግሞ ደጋግሞ ያበረከተ ደራሲ ነው። በመፅሀፍት ብቻ ሳይሆን ወደ ፊልሙ እጁን በመዘርጋት ለየት ያሉ ይዘቶች ያሏቸውን በፊልም እያዘጋጀ ለተመልካች አድርሷል።
አነቃቂና አስተማሪ በሆኑ በትላልቅ መድረኮች ላይ በተጋባዥነት እየተገኘ ጥልቅ ሀሳቦቹን ለሌሎች በማጋራት አዎንታዊ አተያይ እንዲጎለብት፣ ምክንያታዊ አስተሳሰብ በማህበረሰቡ ዘንድ እንዲሰርፅ ሁሌም በመጣር ይታወቃል። በጎ የሆነው አገራዊ አስተሳሰብና የተለየ ምልከታው ደግሞ ብዙዎች እንዲወዱት እንዲያደንቁትም አድርጓቸዋል፤ቡርሀን አዲስ በሚል ቅፅል ስም የሚታወቀው ደራሲ መሀመድ አሊ
ውብዋ ደሴ የልጅነት ውብ ጊዜውን ያሳለፈባትና ያደገባት ብሎም ፊደል ቆጥሮ ለቁም ነገር የበቃባት ከተማ ነች። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ቅዳሜ ገበያ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ እዚያው ደሴ በሚገኝ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀቀ። የመጀመሪያ ዲግሪውን በኢንዱስትሪያል ኬሚስትነት የወሰደ ሲሆን፣ በዚህም ከድርሰቱ ባሻገር ሳሙና የሚያመርት ማሽን በራሱ ዲዛይን አድርጎም ሰርቷል።
ይህ ባለ ድንቅ ተሰጥኦ ባለቤቱ ደራሲ ቡርሀን አዲስ በትምህርት ቤት ህይወቱ እጅግ በጣም ይወደው የነበረው እና ለእርሱ ጥሩ ቦታ ቤተ መፅሀፍት ነበርና የዘወትር መገኛው እዚያው ነበር። የማንበብ ፍቅሩ ደግሞ በርካታ መፅሀፍትን ለማንበብና በዚያውም የመፃፍ ልምድን ለማዳበር ምክንያት ሆነው።
የድርሰት ጅማሮና ስኬት
በእርግጥ ያነበባቸው መፅሀፍት ለሀሳበ ሰፊነት
ለምክንያታዊ አስተሳሰቡ መነሻዎች ለነገሮች የተለየ እይታ እንዲኖረው ሰበብ ሆነውታል። ያለውን ሀሳብ ለሌሎች ለማስተላለፍና ለመጻፍ ያነሳሳው ደግሞ ለሚታዩ ጉዳዮች የመፍትሄ ሀሳብ የማቅረብ ብርቱ ፍላጎት፣ለሚገጥሙ ችግሮች መውጫ መንገድ መጠቆም የነበረው ብርቱ ምኞት ነው። “ደሀ ሆኜ ማደጌ ፀሀፊ እንድሆን አደረገኝ” የሚለው መሀመድ አሊ ወይም ቡርሀን አዲስ፤ የአገራችን ሁኔታና የህዝባችን አጠቃላይ ጉዳይ እንድታስብና እንድታንሰላስል ያደርጉሀል በዚያም የመፃፍና ጉዳዮችን የማመላከት ብርቱ ፍላጎት እንዲኖርህ ያደርጋሉ በማለት ያስረዳ ል::
በእርግጥ ከልጅነቱ ጀምሮ ድርሰትን ብሎ አስቦ ሳይሆን ፣በተደጋጋሚ የሚያስባቸውን ጉዳዮችና ለዚያም የሚሆኑ መፍትሄዎችን በተለያዩ ማስታወሻዎች ላይ የማሳረፍ ልምድም ነበረው። ዛሬ ላይ 35 መፅሀፍትን ጽፏል። ከዚህም ውስጥ የጥበብ ፈለግ፣ የማንነት ክንፎች፣ የፍልስፍና ህይወት፣አስደናቂ የህክምና ጥበብ፣ ትዳርና ህይወት፣ ታጋሾችን አበስራቸው፣ የዘር ካርድ እና የመሳሰሉት ተጠቃሽ መፅሀፍት ለአንባቢያን አድርሷል። ውሀና ወርቅ እና አለም በቃኝ የተሰኙት ፊልሞች የዚሁ ደራሲ ስራዎች ናቸው። በተለይም እጅግ ተወዳጅ የነበረው ውሀና ወርቅ የተሰኘው ፊልም በድርሰትም በዝግጅትም(ዳይሬክቲንግ) የተሳተፈበት ነበር።
የዝነኛው የእረፍት ጊዜ ለመሀመድ እረፍቱ ንባብ፤ ለቡርሀን አዲስ የመዝናኛ ምርጫው መፅሀፍት ናቸው። እጅግ አብዝቶ ያነባል። ያለውን የጽህፈት ጊዜ ከሁሉም ቦታዎች ይልቅ ለማንበብ ምቹ የሆኑና በፅሞና ለማሰብ ለመመራመርና ለፈጠራ የሚመቹ ቦታና ሁኔታዎችን ይመርጣል።
በእርግጥ የተለያዩ አመለካከትና እሳቤዎች ላይ የተጻፉ መጽሀፍት ቢያነብም፣ ለንባብ ምርጫው ግን የፍልስፍና፣ የታሪክና የስነ ልቦና መፅሀፍት ለማንበብ የሚመርጣቸው ለማንበብ የሚያጓጉት የመፅሀፍ አይነቶች ናቸው። ሀይማኖታዊ ይዘት ያላቸው መፅሀፍትም ለእሱ ተመራጭ ናቸው። የተለያዩ ሀይማኖቶች ላይ የተፃፉ መፅሀፍትም ያነባል።
አሁን ላይ ሙሉ ሰዓቱን ለድርሰት እና ለንባብ በማድረግ ላይ የሚገኘው መሀመድ አሊ ፣ ለህትመት ያልበቁ ያዘጋጃቸው መፅሀፍትም አሉት። እነዚህ መፅሀፍት እና ሌሎች ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅሙ ስራዎችን ለህብረተሰቡ ለማድረስና የራሱን በጎ አላማ ለመወጣት ጥረት ማድረጉን እንደሚቀጥል ይናገራል።
የዝነኛው መልዕክት ለኢትዮጵያዊያን
“እራስነት በአገር ይገለፃል፤ሀገርና እራስነት አይለያዩም። ከምንጊዜም በላይ አገሬ ታስፈልገኛለች። ለዚህች አገር መኖር እኔ ነኝ ትልቅ ሚና ያለኝ። ለዚህም የበኩሌን መወጣት አለብኝ ብለን ማመንና መተግበር ይገባናል። ያለፈው ታሪክ እንዳለ ሆኖ አሁንም እኛ ኢትዮጵያዊያን ትልቅ ታሪክ መስራት ያለብን ሰዓት ላይ እንገኛለን። ታሪክ ለመስራት ደግሞ በጣም ወሳኝ ሁኔታና ጊዜ ላይ ነን።
አሁን ያለነው ትውልዶች ለአገራችን የምንሰራው በጎ ነገር ነገ ትልቅ ታሪክ ይሆናል። ያም የታሪክ እድለኛ ያደርገናል። ለዚህ ደግሞ በህብረት መስራትና አንድ ሆኖ መቆም ይገባል።” በማለት ለኢትዮጵያዊያን የአደራ መልዕክቱን አስተላልፏል። እኛም ከዝነኛው ጋር በነበረን ቆይታ ያገኘነውን መረጃ መሰረት አድርገን ያዘጋጀነውን ፅሁፍ በዚሁ ቋጨን፤ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2013