በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
(ክፍል ሁለት)
መቼም በዚች ምድር እንደ ከሐዲውና እፉኝቱ ትህነግ ያለ መሠሪና አሪዎስ እግር እስኪቀጥን ዓለምን ቢዞሩ፤ በጉግል እርዝ ምድርን ቢያስሱ አይገኝም። ጠላት በደካማ ጎንህ ያጠቃሀል። አረመኔው ትህነግ ግን እንደ ጠላት በሚያያቸው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ደካማ ጎን ገብቶ ማጥቃት ስለማያረካው፤ የቀራቸውን እንጥፍጣፊ ጠንካራ ጎናቸውንም ወደ ደካማ ጎንነት ቀይሮ የማያዳግም ጥቃት መሠንዘርን የመረጠ በላዔ ስዕብና ሀገር ነው።
ላለፉት 30/47 ዓመታት ጥንካሬያችንን ወደ ድክመት ለመቀየር ሌት ተቀን መዋቅራዊና ተቋማዊ በሆነ አግባብ ጣረ፤ ጋረ። ለቀጣይ ጥቃቱ ዒላማ አደረገን። አመቻቸን። አዳክሞን ሲያበቃ ጥቃቱን ጀመረ። በሀገርና በሕዝብ ደረጃ የአኬሊስ ተረከዘ አበጀልንና በእሱው አጠቃን። በስስ ብልታችን ወጋን። ኢትዮጵያዊነት፣ አንድነት፣ ሕብረ ብሔራዊነት፣ ከምንም ነገር ሀገርንና ሕዝብን ማስቀደም፣ ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ መባባል፣ መረዳዳት፣ መተጋገዝ፣ ያለንን ተካፍሎ መብላት፣ የታረዘን ማልበስ፣ የተራበን ማጉረስ ወዘተረፈ…ጥንካሪያችን ነበር። የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም በግላዊና ቡድናዊ ጥቅም፤ ፍቅርን በጥላቻ፤ መተሳሰብን ጥሎ በማለፍ፤ አንድነትን በልዩነት፤ ታሪክን በፈጠራ ትርክት፤ ኢትዮጵያዊነትን በመንደርተኝነት በመቀየር እስከዛሬ በአብሮነት ያቆዩንን ወረቶች በማስጣል ደካማ ጎናችን አደረጋቸው።
ጥንካሬዎቻችንን በጀት መድቦና መዋቅር ፈጥሮ በሴራ፣ በደባና በጥላቻ ታግዞ ሌት ተቀን በመሥራቱ ወደ ድክመት ቀየራቸው። እንግዲህ እንዲህ ካመቻቸን በኋላ ነው እዚህም እዚያም የማንነት ግጭት የጎነቆለው፤ የሠሜን ዕዝን በውድቅት ሌሊት ያጠቃው። ይህ ብቻ አይደለም። ላለፉት 27 ዓመታት ሆን ብሎ ጠንካራና ገለልተኛ ተቋማት እንዳይኖሩን ውስጥ ውስጡን ሲያሻጥር የኖረው። ጠንካራ የዴሞክራሲ፣ የሚዲያ፣ የደህንነት፣ የፀጥታ፣ የውጭ ግንኙነትና የዴፕሎማሲ፣ የጥናትና ምርምር ወዘተረፈ… ተቋማት እንዳይኖሩን አድርጎ ሁሉን አቀፍ ጦርነት ከፈተብን።
በጦር ግንባር ሲረታ የደባና የሴራ ጦርነት አወጀብን። በሐሰተኛ፣ ሆን ተብሎ በተዛባና በተሣሣተ መረጃ የፕሮፓጋንዳና የዲፕሎማሲ ዘመቻ ጀመረብን። መረጃን በጦር መሣሪያነት በመቀየር በአባት፣ በአያት፣ በቅድመ አያቶቻችን ደምና አጥንት ዋጋ የታነፀውን ታሪካችንንና ማንነታችንን ናደው። በጦር ግንባር ያጣውን ግዳይ ለጊዜውም ቢሆን በሕዝብ ግንኙነትና በዲፕሎማሲው ግንባር እያሣካው ነበር። ድንገት የዲሲ፣ የኒው ዮርክ፣ የብራስልስ፣ የጄኔቫ፣ የሎስ አንጀለስ፣ የቶሮንቶ፣ የሲድኒ ወዘተረፈ…ታላላቅ ትዕይንተ ሕዝቦች ደርሠው ቀዝቃዛ ውሃ ቸልሰው ቆሌውን ባይገፉት። መረጃን የጦር መሣሪያ በማድረግ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር አብሮና ተባብሮ እየወጋን ነው። ምንም እንኳን እውነት ትሰላለች እንጂ ባትበጠስም።
መረጃን እንደ ጦር መሣሪያ የመጠቀም ጉዳይ ዛሬ ከበይነ መረብና ከማህበራዊ ሚዲያ መሥፋፋትና መጎልበት ጋር ተያይዞ ወደፊተኛው እረድፍ ቢመጣም ከሰው ልጅ ጋር አብሮ ያደገና ቤተኛ ነው። በሀገራችን ወሬ ወይም መረጃ ከጦር በላይ ጉልበት እንዳለው የሚያስታውሰው ፤”ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው፤” የሚለው አባባል ለዚህ ጥሩ ማሣያ ነው። ከ2 ሺህ 500 ዓመታት በፊት ታዋቂው የጦር ሊቅና ፈላሥፋ ሠን ሱ “The art of war” በተሠኘው ዘመን ተሻጋሪ መጽሐፉ፤ “ጠላትህን ያለ ውጊያ አንበርክክ” ማለቱ የመረጃ ኃያልነት ጥንትም እንደነበረ ያረጋግጣል። ሆኖም ዓለማችን በሦሻሊስትና በካፒታሊስት ጎራዎች ሥትከፈልና ቀዝቃዛው ጦርነት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ሲዘልቅ ጦርነቱ በታንክ፣ በጦር ጀት፣ በቢኤም ወይም በመድፍ ሣይሆን በፕሮፓጋንዳ፣ በርዕዮት ዓለምና በመረጃ ነበር የተካሄደው።
ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ የምትዘውረው ጎራ በአሸናፊነት ቢወጣም በዘመነ በይነ መረብና ማህበራዊ ሚዲያ አሠላለፉን ቀይሮ እንደ አዲስ ተከስቷል። ሕልውናዋ በአሜሪካና በሠሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት /ኔቶ/ አደጋ እንደተደቀነባት የምታምነው ሩሲያ መረጃን እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀሙን ተክናበታለች። እንደ ሕልውና ሥጋት የምትቆጥራቸውን ሉላዊነት /Globalization/፣ የአውሮፓ ሕብረትና ኔቶን ከሚገዳደሩ አጋጣሚዎች ጎን ተሠልፋ ግዳይ ጥላላች። የእንግሊዝ ከአውሮፓ ሕብረት መውጣት ሕብረቱን ያዳክመዋል ብላ ስለምታምን መነጠሉን ከሚያቀነቅነው ወግ አጥባቂ /Conservative/ ፓርቲ ጎን በሕዕቡ ቆማለች። ሕብረቱን ከሚጠሉ የምዕራባውያን ሕዝበኛ /Populist /ፓርቲዎች፤ ከአሜሪካ እሴቶች በተቃራኒው ቆመው የነበሩትን ኔቶንና ሕብረቱን ጠል ዶናልድ ትራምፕ ጎን በመቆም የ2016ቱን ምርጫ ውጤት እስከ መበየን ደርሣለች። የአሜሪካውን የ2020 ምርጫም በተመሣሣይ መንገድ ለመጫን ሞክራለች።
ዛሬም አሜሪካውያንን በዘረ ለመከፋፈል፤ በዴሞክራሲያዊና በመንግሥት ተቋማት እምነት እንዳይኖራቸው እስከ ማድረግ ደርሣለች። የትራምፕ ደጋፊዎች የምርጫውን ውጤት አንቀበልም ከማለት አልፈው እንደ የዴሞክራሲ ቤተ መቅደስ የሚታየውን ካፒቶል ሒል እስከ ማጥቃት ደርሠዋል። አሜሪካንን ጨምሮ የምዕራባውያን የደህንነት፣ የፀጥታና ቁልፍ የመንግሥት ተቋማትን የመረጃ ቋት በመሰርሰር መረጃ በመበርበርና በመዝረፍ እየተከሰሰችና እየተወነጀለች ትገኛለች። ሩሲያ ግን እንደ ሁልጊዜው በማስተባበሉ ገፍታበታለች ።
ወደ ከሐዲው ትህነግ ሠሞነኛ የፕሮፓጋንዳና የሐሰተኛ መረጃ ዘመቻ ስንመጣ መረጃን እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀምን ጥርሱን ነቅሎበታል ቢባል ማጋነን አይሆንም። መረጃን የጦር መሣሪያ ማድረግ፣ መረጃን እንደ ጉዳት ማድረሻ፣ እንደ ግብ መምቻ መሣሪያ የመጠቀም ሒደት ነው። ጥቃቱን የሚፈጽመው አካል እውቀትን፣ አስተሳሰብንና አመለካከትን ዒላማ አድርጎ በመሥራት ሥውር ዓላማን ዳር የማድረስ ሴራ ነው። ፕሮፓጋንዳን፣ የሴራ ኀልዮትን፣ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ሐሰተኛ ወይም ሆን ተብሎ የተዛባና ሐሰተኛ መረጃን መንዛት እና እንደ ጦር መሣሪያ የመጠቀም አውደ ውጊያ ነው። ከፍ ሲልም ኮምፒውተርን ሰርስሮ መረጃን መመንተፍንና ከጥቅም ውጭ ማድረግን ያካትታል።
ሆኖም መረጃ እንደ ጦር መሣሪያ ያገለግል ዘንድ ተደራሲና ታዳሚ ያሥፈልገዋል። ለዚያውም አንብቦ፣ አድምጦና ተመልክቶ ለታለመለት ድርጊት የሚቀባበልና የሚተኮስ። ለሠሞነኛው የትህነግ መረጃን እንደ ጦር መሣሪያ የመጠቀም ዘመቻ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ ዓለማቀፉ ሚዲያና ምዕራባውያን እንደ ጠብ መንጃ ቃታ በሐሰተኛ መረጃ ተቀባብለው ተተኩሰዋል። በዚህ የተሣሣተ መረጃ ላይ ተመርኩዘው የተለያየ ውሣኔ ላይ መድረሣቸውና ለተግባራዊነቱ መንቀሣቀሳቸው ዘመቻው ጊዜያዊ ድል እንዳስመዘገበ አንዱ ማሣያ ነው። ዓለማቀፍ የሠብዓዊ ተሟጋቾች ከእነ አመነሥቲና ሒውማን ራይትስ ብንጀምር የዲጂታል ወያኔን የፈጠራ ክስና የፕሮፓጋንድ ዘመቻ ሣያጣሩና ሣይመረምሩ ሎንደንና ዋሽንግተን ተቀምጠው በሥማ በለው ለዓለም አስተጋብተዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ከፍተኛ ምክር ቤት የእነ ቴዎድሮስ አድሀኖምን (ዶ/ር) ሐሰተኛና ሆን ተብሎ የተዛባን መረጃ ሣይመረምር እንዳለ በማስተጋባት ሀገራችን በዘርፈ ብዙ የሠብዓዊ መብት ጥሰት ከሷታል። የጆባይደን አስተዳደር ይባስ ብሎ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታዊ ምክር ቤት ባለወርነት በመጠቀም ኢትዮጵያን ለመወንጀልና ለማንበርከክ ጥረት ቢያደርግም ቻይና፣ ራሽያና ሕንድ ውድቅ አድርገውበታል። በዚህ ሲከሽፍበት ወደ ኋይት ሐውስ በመውሠድ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን አማካይነት የሀገራችንን ሥም ማጠልሸቱ ሣያንስ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ተገብቷል። አሜሪካ ከቀዝቃዛው ጦርነት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በሐሰተኛ እና ሆን ተብሎ በተዛባ መረጃ እየተናጠች እና ዋጋ እየከፈለች የዲጂታል ወያኔ ሐሰተኛ እና ሆን ተብሎ የተዛባ መረጃ ሠለባና መጠቀሚያ መሆኗ ለማመን የሚቸግር ወለፈንዲ ነገር ነው።
ከሀዲው ትህነግ ሐሰተኛ፣ ሆን ተብሎ የተዛባንና የተሣሣተ መረጃን እያፈራረቀና በአንድ ላይ እየተጠቀመ የፕሮፓጋንዳ እና የዲፕሎማሲ ጦርነቱን እያካሄደብን ነው። ሆን ተብሎ ሕዝብን ለማደናገርና ውዥንብር ውስጥ ለመክተት እንዲሁም እውነትን ለማለባበስ የሚሠራጭ የተዛባ መረጃ ዲስኢንፎርሜሽን ይሠኛል። መንግሥት ፓሊሲዎቹ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትን እንዲያገኙ ይህን መሠል የተዛቡ መረጃዎችን ሊጠቀም ይችላል። ትህነግ እንደ መንግሥትም እንደ ፓለቲካ ፓርቲም በዚህ የተካነ ስብስብ መሆኑን አረጋግጠናል። የፓለቲካ ፕሮግራሙም ሆነ ሥሁት ፓሊሲዎቹ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ በአምሣሉ ጠፍጥፎ በሠራቸው መገናኛ ብዙኃንንና በተለያዩ መድረኮች የተዛቡ መረጃዎችን በመንዛት ተቀባይነት ለማግኘት ረጅም ርቀት ተጉዟል።
ይህ ጽንሰ ሐሳብ በዓለማችን እ.አ.አ ከ1939 ጀምሮ የሚታወቅ ቢሆንም የማህበራዊ ሚዲያ መሥፋፋትን ተከትሎ ግን እጅግ ጥቅም ላይ እየዋለና እያነጋገረ ይገኛል። በሌላ በኩል የተሣሣተና አሣሣች መረጃ ሚስኢንፎርሜሽን ይባላል። ብዙውን ጊዜ ሁለቱን ጽንሰ ሐሳቦች እያቀያየሩ መጠቀም እየተለመደ ቢሆንም በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት የጎላ ነው። ዲስኢንፎርሜሽን ቀድሞ ለታቀደ ዓላማ ወይም ግብ አንድን እውነታ አዛብቶ ማሠራጨት ሲሆን፤ ሚስኢንፎርሜሽን ግን ሐሰተኛና የተሣሣተ መረጃን ማሠራጨት ነው። ትህነግ መንግሥት በነበረበት 27 ዓመታትም ሆነ በሕዝባዊ አመጽና በለውጥ ኃይሉ ከመንበሩ ከተፈነገለ ካለፉት 36 ወራት ወዲህ እነዚህን አሥገድዶና አዛብቶ ማጥመቂያ ጽንሰ ሐሳቦችን በሚቆጣጠራቸው መደበኛና ማህበራዊ ሚዲያዎች እያፈራረቀ ሲጠቀምባቸው ኖሯል።
እንደ መውጫ
በዲፕሎማሲውና በሕዝብ ግንኙነት ሥራው ዳተኛና ደካማ መሆናችን ፍትሕንና እውነትን ይዘን ተከላካይ ሆነናል። ውሸትን፣ ሆን ተብሎ የተዛባንና የተሣሣተ መረጃ እስከ አፍንጫው የታጠቀው የከሀዲው ትህነግ ርዝራዥና ዲያስፓራ ጭፍራ ጊዜያዊ ድል አሥመዝግቧል። ዓለማቀፍ ማህበረሰቡን፣ ሚዲያውንና ምዕራባውያንን አሳስተው ከጎናቸው ማሠለፍ ችለዋል። ምንም እንኳ አንድ ጊዜ የጎደፈን ሥም የጠለሸን ገጽታ ለማደሥ አስቸጋሪ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ባይሆንም እውነቱ ሲታወቅ በተወሰነ ደረጃ መስተካከሉ አይቀርም። በተለይ ትውልደ ኢትዮጵያ አሜሪካውያን፣ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራዊያን በዲሲና ኒውዮርክ ደርሰው ባያሥጥሉን ኖሮ ፈተናው ከባድ ነበር። በሎስ አንጀለስ፣ በላስቬጋስ፣ በብራስልስ፣ በጄኔቫ፣ በካናዳ ወዘተረፈ…የተካሄዱና የሚካሄዱ ሠላማዊ ሠልፎች የፓለቲካዊ ዲፕሎማሲው ነፍስ አድንና ወሣኝ መታጠፊያ ሆነዋል። በቀጣይ ግን ዲፕሎማሲውና የመረጃ ተደራሽነቱ ፍጹም ማሻሻያ ሊደረግበት ይገባል።
ሚዲያዎቻችን ከአረጠ ጋዜጠኝነት ማለትም ሁነት፣ ስብሰባ፣ ፕሮቶኮልና አኃዝ ከማሣደድ ወጥተው አጀንዳ ቀራጭ፣ ተንታኝና ተርጓሚ ሆነው ከፊት በመሆን ሀገርንና ሕዝብን መምራት ይጠበቅባቸዋል። አድማጭና ተመልካች የሚፈልገውን ከማቅረብ ይልቅ የሚገባውን ማቀበል ያሻል። ገና ለገና ስፓርትና ሙዚቃ ይወዳል ተብሎ አየር ስዓቱ በእነሱ መያዝና መሞላት የለበትም። ከፊት ሆኖ መምራት ያለበት አድማጭ፣ ተመልካችና አንባቢ ሣይሆን ሚዲያው ነው። በተለይ እንደ ኢቢሲ ያለ የሕዝብ ቴሌቪዥን ጭራ ሣይሆን መሪ ነው መሆን ያለበት። ሕፀፁን የሚያርም፣ የተጋደደ ሐሳብን የሚያርቅና ሕዝብንና እውነትን የሚያስቀድም ሊሆን ይገባል። ኢቢሲን ጨምሮ፣ ኢዜአና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መረጃን የሚያበጥሩበት፣ የሚያጠሩበትና የሚያረጋግጡበት ራሱን የቻለ የ(fact cheker) አደረጃጀትና አሠራር ሊዘረጉ ዘመኑ ያስገድዳል። ከዚህ ጎን ለጎን ዜጋው ስለሚዲያ አጠቃቀምና አመራረጥ ግንዛቤ (media literacy) እንዲኖረውና እንክርዳዱን ከሥንዴው የመለየት አቅም እንዲያጎለብት አበክሮ መሥራት ይጠይቃል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና በእውነተኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!!
አሜን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2013