ኢያሱ መሰለ
ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች የኑሮ ደረጃቸው ሊለያይ ይችላል:: በተንጣለለ ቪላ የሚኖሩ ባለጸጎችም ይሁን በደሳሳ ጎጆ የሚኖሩ ምስኪኖች እንደ አቅማቸው ልኬትና እንደስራቸው ባህሪ ቤታቸውን አሸንፈው ለመኖር ሲሉ ይታትራሉ:: አንዳንዶች ታትረው የድካማቸውን ዋጋ ሲያገኙ ሌሎች እዚያው ሞላ እዚያው ፈላ ህይወትን ይመራሉ::
የተደራጀና ሰፋ ያለ ሀብት የሚያንቀሳቅሱ የመኖራቸውን ያህል በትንሽ ነገር ላይ ተንጠላጥለው ራሳቸውን ለማሸነፍ የሚጥሩም አሉ፤ ሁለቱም ታትረው የሚኖሩ መሆናቸው ግን አንድ ያደርጋቸዋል:: አንዳንዶች ያገኙትን ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅመው እራሳችን ማሸነፍ ሲያቅታቸው ይታያል:: አንዳንዶችም እዚህ ግባ የማይባል ስራ እየሰሩ ቤተሰብ ሲያስተዳድሩ እናያለን::
የዛሬው እንግዳችን በደካማ አቅማቸው ሰርተው ለመኖር የሚጥሩ አዛውንት ናቸው:: ከአራት ኪሎ ወደ ስድስት ኪሎ በሚወስደው መንገድ በስተቀኝ በኩል ቅድስት ማርያም ካፌ አካባቢ አይታጡም:: እድሜያቸው በስልሳዎቹ መጀመሪያ ይገመታል:: ጋዜጣ ማስነበብ፣ ሎተሪና የሞባይል ካርድ መሸጥ የዘወትር ተግባራቸው ነው:: የአዛውንቱ የስራ ትጋትና ብርታት ብዙዎችን ያስገርማል::
ከአርባ ዓመት በላይ ጋዜጣ በማስነበብ አምስት ቤተሰብን አስተዳድረዋል:: ስራ የጀመሩት በ1972 ዓ.ም የአዲስ ዘመን እና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦችን በማስነበብ ነው:: በስራ ዘመናቸው የሚያጋጥሟቸውን ፈታኝ ሁኔታዎች እየተቋቋሙ እዚህ መድረሳቸውን ይናገራሉ:: በተለይም የ1997 ዓ.ም የምርጫ ውጤትን እና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የመጣው የአንባቢዎች መጥፋት ኑሯቸውን ፈታኝ አድርገውት እንደነበር ያስታውሳሉ::
አዛውንቱ ዛሬም በደካማ አቅማቸው ኑሯቸውን ለማሸነፍ ላይ ታች ይላሉ:: አሁን አሁን ግን አቅማቸው እየደከመ በመምጣቱ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ማስነበብ አዳጋች እየሆነባቸው መምጣቱን ይናገራሉ:: የባለታሪኩ ተሞክሮ ለሌሎች ትምህርት ስለሚሆን የዚህ አምድ እንግዳ ልናደርጋቸው ወድደናል::
አቶ አመርጋ ሹሜ ይባላሉ:: የትውልድ ሀገራቸው በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ነው:: ገና በወጣትነት ዘመናቸው ሰርቶ የመለወጥ ሞራል ታጥቀው ከትውልድ አካባቢያቸው ወደ አዲስ አበባ የመጡት ከዛሬ አርባ ዓመት በፊት ነው:: አዲስ አበባ እንደመጡ የሊስትሮ እቃዎችን አሟልተው ለአንድ ዓመት ያህል ጫማ በመጥረግ ስራ ላይ ይሰማራሉ::
ወትሮም እራሳቸውን ወደ ተሻለ ነገር የመለወጥ ፍላጎት እንደነበራቸው የሚናገሩት አቶ አመርጋ በሊስትሮ ስራ አንድ ዓመት ያህል ከሰሩና መጠነኛ ገንዘብ ከጨበጡ በኋላ ሌላ ስራ ለመስራት ያስባሉ:: ከዚያም የተለያዩ ሸቀጦችን ማለትም እንደ ሲጋራ፣ ማስቲካ፣ ካልሲ የመሳሰሉትን ተሸክመው ማዞር ይጀምራሉ፤ /በተለምዶ አጠራር ሱቅ በደረቴ/ የሚባለውን ማለት ነው::
ከአዲሱ ስራቸው ጋር እየተላመዱና አቅማቸውን እያሳደጉ መሄድ ይጀምራሉ:: አቶ አመርጋ ሱቅ በደረቴ እየሰሩ በነበረበት ጊዜ ቀን ቀን ሸቀጥ ተሸክመው ሲዞሩ ይውሉና ማታ ማታ እቃቸውን አንዲት መጋዘን ውስጥ እያስቀመጡ ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ:: ታዲያ አንድ ቀን ጠዋት እንደተለመደው እቃቸውን ካሳደሩበት መጋዘን ለማውጣት ሲሄዱ ሌባ መጋዘኑን በመስበር ያለ የሌለ እቃቸውን ይወስድባቸዋል::
የዛን ጊዜው ወጣት የአሁኑ አዛውንት አቶ አመርጋ ቅስማቸው ይሰበራል፤ ለጊዜውም ቢሆን ሥራቸው ይስተጓጎላል:: ነገር ግን እጃቸውን ለችግር መስጠት የማይፈልጉት ታታሪ ሰው ብዙም ሳይቆዩ የቋጠሯትን ጥሪት ሰብስበው በአዲስ ሞራል እንደገና ወደ ስራቸው ይመለሳሉ:: ከሱቅ በደረቴ ስራቸው ወደ ጋዜጣ አስነባቢነት ይሸጋገራሉ::
አቶ አመርጋ በ1972 ዓ.ም የአዲስ ዘመን እና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦችን በርካሽ ዋጋ እየገዙ በአምስት እና አስር ሳንቲም ማስነበብ ይጀምራሉ:: በተለይም የአዲስ ዘመን ጋዜጦችን 25ቱን በሁለት ብር እየገዙ ግማሹን አትርፈው ይሸጣሉ፤ ግምሹንም ያስነብባሉ:: በሳምንት ስድስት ቀን ይታተም የነበረውን የአዲስ ዘመን ጋዜጣ በመግዛት ከድርጅቱ ጋር የረዥም ጊዜ ደንበኝነት እንደነበራቸው ይናገራሉ::
ኋላ ግን የደርግ ስርዓት አክትሞ ኢህአዴግ ሀገሪቱን መቆጣጠር ሲጀምር የጋዜጣው ይዘት ይለወጣል፤ ተነባቢነቱም ይቀንሳል፤ ነገር ግን የሽያጭ ዋጋው ይጨምራል:: ቀደም ሲል በስምንት ሳንቲም ሂሳብ ይሸጥ የነበረው አንድ ጋዜጣ በአንድ ጊዜ ሃምሳ ሳንቲም ይገባል፡ እንደዚያም ሆኖ እየሰሩ እያሉ ከድርጅቱ እየተረከቡ የሚከፋፍሉ ሰዎች አቶ አመርጋ በቀን የሚወስዱትን የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ብዛት ከ25 ወደ 50 እንዲያሳድጉ ይጠይቋቸዋል::
ወቅቱ አዳዲስ የግል ጋዜጦች ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩበት ስለነበር የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ ገብቶ እንደነበር አቶ አመርጋ ይገልጻሉ:: በዚህ የተነሳ ጋዜጣውን አብዝቶ መግዛት ኪሳራ ውስጥ እንዳይከታቸው በመስጋት አከፋፋዮቻቸው እንዲወስዱ ያዘዟቸውን ጋዜጣ መውሰድ እንደማይፈልጉ ይገልጻሉ:: አከፋፋዮቹም ከሃምሳ ጋዜጣ በታች መሸጥ እንደማይፈልጉ ያሳውቋቸዋል:: በዚህ ምክንያት ሥራ ካስጀመራቸውና የረዥም ዓመት ባለውለታቸው ከሆነው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ይለያያሉ::
አቶ አመርጋ እጃቸውን ያፍታቱበትን የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ትተው ፊታቸውን ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል ጋዜጦች ያዞራሉ:: እንደ ወንጭፍ፣ ኢትዮጲስ፣ ሚኒልክ የመሳሰሉ ጋዜጦችን ማስነበብ ይጀምራሉ:: በተለይም ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ከመንግስት በተቃራኒ ጎራ የቆሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች መፈጠራቸውን ተከትሎ የግል ጋዜጦችም በአዳዲስ ይዘቶች መቅረብ ይጀምራሉ::
አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጩኸታቸውን የሚያሰሙት በግል ጋዜጦች ላይ ስለነበር የጋዜጦቹ ተነባቢነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ይሄዳል:: የአቶ አመርጋ ስራም ነፍስ እየዘራ የእለት ገቢያቸውም እያደገ ይመጣል:: ከጋዜጣ ማስነበብ ጎን ለጎን ሎተሪ እየሸጡ አቅማቸውን ማጠናከር ይጀምራሉ::
አቶ አመርጋ ከብቸኝነት ኑሮ ተላቀው ወደ ትዳር ዓለም ይገባሉ:: በሚያገኟት የእለት ገቢ ትዳር መስርተው ቤት ተከራይተው መኖር ይጀምራሉ:: ልጆችም ይወለዳሉ:: የቤተሰቦቻቸው ቁጥር እየጨመረ ይመጣል:: የሶስት ልጆቻቸውና የቤት እመቤት ባለቤታቸው ወጪ በአቶ አመርጋ ጫንቃ ላይ ይወድቃል:: የቀለብ፣ የልብስ፣ የልጆች የትምህርት ቤት ወጪ፣ የቤት ኪራይ፣ የህክምና ወዘተ ወጪዎች ጋዜጣ በማስነበብና ሎተሪ በማዞር በሚያገኙት ገቢ እየሸፈኑ ከኑሮ ጋር ትግል ይጀምራሉ::
ከ1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ አዲስ አበባ ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ ከሚሄደው የኑሮ ውድነት ጋር ግብ ግብ እየፈጠሩ እዚህ እንደደረሱ ይናገራሉ:: አቶ አመርጋ ጋዜጣ በማስነበብ ስራቸው ከተፈተኑባቸው ወቅቶች አንዱ 1997 ዓ.ም እንደሆነ ይገልጻሉ:: ይህ ወቅት ኢህአዴግና ቅንጅት በምርጫ ውጤት ምክንያት እሰጥ አገባ ውስጥ የገቡበት ነው:: ኢህአዴግ በምርጫው ላይ የሰራቸውን ኢ-ዲሞክራሲዊ ስራዎች የግል ጋዜጦች እያጋለጡ ይተቹ ነበር::
በዚህ የተነሳ ተነባቢ የነበሩ ዋና ዋና ጋዜጦች እንዳይታተሙ ማዕቀብ ይደረግባቸው ነበር:: ጋዜጦችን እያዞሩ የሚያስነብቡ ግለሰቦችም እንዳይሰሩ ጫና ይደረግባቸው ነበር:: ከዚያም አልፎ ይታሰሩም ፣ጋዜጦቹን ይነጠቁም እንደነበር ይገልጻሉ :: በዚህን ወቅት ታዲያ አቶ አመርጋ የገቢ ምንጫቸው ይነጥፋል፤ የቤተሰባቸው ህልውናም አደጋ ውስጥ ይገባል:: ታታሪው ሰው ግን ሎተሪ በማዞርና ሌሎች ጋዜጦችን በማስነበብ ችግሩን ለማለፍ መጣራቸውን ያስታውሳሉ::
አዛውንቱ ወጪ ለመቀነስና በስራ ቦታቸው በሰዓቱ ለመድረስ ሁል ጊዜ ከሌሊቱ አስራ አንድ ሰዓት ከእንቅልፋቸው ተነስተው በሚኖሩበት ቅሊንጦ አካባቢ የአውቶቡስ ሰልፍ ይይዛሉ:: 12 ሰዓት ሲሆን ወደ አራት ኪሎ ይጓዛሉ:: አቶ አመርጋ አራት ኪሎ ከጆሊ ባር እስከ ዩኒቨርሳል መጽሐፍ መደብር ባለው ውስን ቦታ ከአርባ አመት በላይ ጋዜጣና መጽሔት እያስነበቡ ኖረዋል:: ሎተሪም ሸጠዋል:: አሁን አሁን የሞባይል ካርዶችንም ጨምረው በመሸጥ እጃቸውን ለምፅዋት ላለመስጠት በመታገል ላይ ናቸው:: አንዳንድ ቀን በትራንስፖርት ምክንያት ቢዘገዩ ወይም በሌላ ምክንያት ቢቀሩ ደንበኞቻቸው እንደሚከፋቸው ይናገራሉ:: እርሳቸውም ቢሆኑ ያለ እለት ገቢ ህይወታቸውን መምራት ስለማይችሉ መቅረት አይፈልጉም::
አቶ አመርጋ ከራሳቸው ጋር አምስት ቤተሰብ ያስተዳድራሉ:: ሃያ ዘጠኝ ዓመታትን በኪራይ ቤት ያሳለፉት አዛውንቱ ከቅርብ ዓመታት በፊት የኮንዶሚኒየም ቤት ደርሷቸው መኖር ጀምረዋል:: ጋዜጣ እያስነበቡ የኮንዶሚኒየም ቤት እዳን መክፈል፣ የልጆችን የትምህርት ቤትና የቤት ወጪ መሸፈን ፈታኝ እንደሆነባቸው ይገልጻሉ::
ባለፈው አንድ ዓመት የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ ስራቸው መስተጓጎል ገጥሞት እንደነበር አቶ አመርጋ ይናገራሉ:: ምንም ገቢ ሳያገኙ ባዶ እጃቸውን ወደ ቤታቸው የሚገቡበት ቀን እንደነበርም ያስታውሳሉ:: የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ በኋላ የኑሮ ውድነት እየተባባሰ መምጣቱንም ይገልጻሉ:: የኮሮና ቫይረስ ባሳደረው የስነ ልቦና ጫና ምክንያት የአንባቢዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ይናገራሉ::
በዚህ የተነሳ ገቢ ማጣታቸው የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት ጫና የበለጠ አስከፊ እንዳደረገባቸው ይገልጻሉ:: በተለይም ኮሮና ቫይረስ በሀገራችን በተከሰተባቸው ጥቂት ወራት ሰዎች ከጋዜጣ ጋር ምንም አይነት ንክኪ ማድረግ አይፈልጉም ነበር ይላሉ:: አቶ አመርጋ በ1997 ዓ.ም የተፈጠረው የፖለቲካ ውዝግብና የኮሮና ቫይረስ መከሰት በሥራቸው ላይ ያሳደሩባቸውን ተጽእኖ አይረሱትም::
የኑሮ ውድነቱ እየተባባሰ መሄድ የደንበኞቻቸውን ቁጥር እየቀነሰው እንደሚገኝም ተናግረዋል:: ሰዎች መረጃዎችን ከተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች እና ሶሻል ሚዲያዎች ማግኘታቸውም የጋዜጣቸውን ተነባቢነት የቀነሰባቸው ሌላ ምክንያት መሆኑን አቶ አመርጋ ይገልጻሉ:: አዛውንቱ በቀጣይ የተለመደውን ህይወታቸውን ለመምራት የሚያደርጉትን ጥረት የሚፈታተኗቸው ሁኔታዎች መኖራቸውንም ይናገራሉ::
አብዛኛውን እድሜያቸውን ጋዜጣ በማስነበብ የገፉት አዛውንቱ አሁን አቅማቸው እየደከመ በመሆኑ እንደ ከዚህ ቀደሙ ተሯሩጠው መስራት እንደሚያዳግታቸው ይናገራሉ:: አቶ አመርጋ ከዚህ በኋላ ሌላ ስራ የመስራት ፍላጎት ባይኖራቸውም ይህንኑ ስራቸውን ለመቀጠል ሁኔታዎች ቢመቻችላቸው ይመኛሉ:: የጋዜጣ ማስነበቢያና የማረፊያ ቦታ ቢኖራቸው ቀጣይ ህይወታቸውን ለመምራት የሚያስችል ተስፋ እንደሚሆናቸው ይገልጻሉ::
አቅማቸው እየደከመ ሲመጣ ከወዲህ ወዲያ እየተዟዟሩ ማስነበብ እንደማይችሉ የተናገሩት አዛውንቱ የሚመለከተው ባለድርሻ አካላት የማስነበቢያ ቦታ እንዲተባበሯቸው ይማጸናሉ:: ኑሯቸውን ለማሸነፍ ሲሉ በዚህ እድሜያቸው ላይ ታች የሚሉት አባት ጥያቄያቸው ቢመለስላቸው የስራ ተነሳሽነታቸው እንደሚጨምር ይገልጻሉ:: በዚህ ስራ ከሚያገኙት ውጭ ሌላ ምንም አይነት ገቢ እንደሌላቸው በመናገር የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ምቹ የስራ ሁኔታ እንዲፈጥሩላቸው ይጠይቃሉ::
አዲስ ዘመን መጋቢት 11/2013