የተወለዱት በቀድሞው አጠራሩ በጎንደር ክፍለሃገር ወገራ አውራጃ ዳባት ከተማ ነው:: እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ በቀጥታ የቄስ ትምህርት ቤት ገቡ:: አስር ዓመት ሲሞላቸው ግን በጀርመን መንግስት ተራድኦ ድርጅት አማካኝነት በተቋቋመው ዳባት መንፈሳዊ ትምርት ቤት ገቡ:: የቤተክርስቲያን ተማሪዎችንና የአካባቢው ተወላጆችን ፈትኖ ያስገባ የነበረው ይህ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በጥራት በማስተማር ረገድ በወቅቱ ወደር የማይገኝለት እንደነበር ይጠቀሳል:: በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስር በነበረው በዚሁ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ ደብረታቦር በመሄድ ደብረታቦር መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገቡና እስከ 10ኛ ክፍል ተማሩ:: በመቀጠልም ወደ ዳባት በመመለስ 11ኛ እና 12ኛ ክፍልን ተማሩ:: ለትምህርት በነበራቸው ጥሩ አቀባበልም በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ ቻሉ:: የሁለተኛ ደረጃ ፈተናቸውንም ጥሩ ውጤት በማምጣታቸው ቀድሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስር በነበረው ሃረማያ እርሻ ኮሌጅ መግባት ቻሉ::
በእርሻ ኮሌጁ ኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል ገብተው ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ከተማሩ በኋላ ወደ ባህርዳር መምህራን ኮሌጅ ተዛውረው በኬሚስትሪ ዲፕሎማቸውን ያዙ:: በመቀጠልም በቀድሞው አጠራር አርሲ ክፍለሃገር አርባጉጉ አውራጃ ጉና የሚባል ቦታ ላይ ለሁለት ዓመት በመምህርነት አገለገሉ:: በዚያው ክፍለሃገር ጭላሎ አውራጃ ከተር ፏፏቴ በሚባለው ስፍራም ሁለት ዓመት ያህል ያገለገሉት እኚሁ ሰው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብተው በመማር ላይ ሳሉ የመንግስት ለውጥ በመምጣቱ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ:: ቡታጀራ ከተማ ላይ ተመድበውም ለዘጠኝ ዓመታት አገለገሉ:: የዩኒቨርስቲ ውጤታቸው ጥሩ ስለነበረም ሀዋሳ መምህራን ኮሌጅ የኬሚስትሪ ላብራቶሪ ቴክኒሽያን ሆነው በውድድር መግባት ቻሉ::
ለሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች እጅ መስጠትን የማይሹት እኚሁ ሰው ታዲያ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ድረስ እየተመላለሱ በመማር በኬሚስትሪ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል:: በሃዋሳ ዩኒቨርስቲም በአፈር ሳይንስ የማስተርስ ዲግሪያቸውን የሰሩ ሲሆን ሃዋሳና ወላይታ ዩኒቨርስቲ በተጋባዥ መምህርነት እየተመላለሱ በማስተማር የበኩላቸውን ኃላፊነት ሲወጡ ቆይተዋል:: በተለይም የወላይታ ዩኒቨርስቲ ሲቋቋም የመጀመሪያ ተማሪዎችን በማስተማርና ቤተሙከራ በማደራጀት ረገድ ስማቸው ጎልቶ ይነሳል:: በሃረማያ ዩኒቨርስቲ ነፃ የትምህርት እድል በማግኘት በአፈር ሳይንስ ዶክትሬት ዲግሪያቸውን የሰሩት እንግዳችን ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ ተቀጥረው በማስተማር ላይ ይገኛሉ:: ከዚሁ ጎን ለጎንም በፖለቲካው መስክ የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉ ሲሆን አንድ የግል ድርጅት ላይ ሥራ አስኪያጅ ሆነው በመስራት ላይም ናቸው:: እንግዳችን ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ አዳነ በወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋር ያደረጉትን ቃለምልልስ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል::
አዲስ ዘመን፡– በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ለመጣው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መንስኤ ምን እንደሆነ ያስረዱንና ውይይታችንን ብንጀምር?
ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ፡– እንደእድል ሆኖ የእኛ አገር የፖለቲካ ሁኔታ በሰከነ ሁኔታ ሊመራ አልቻለም:: አባቶቻችን ለዓለም ሊጠቅም የሚችል የሥነ-መንግሥት ሁኔታ ተክለውልን ነው ያለፉት:: ይሁንና በተለይም ከ1967 ዓ.ም ወዲህ ይህች አገር ከፍተኛ የሆነ ቀውስ ውስጥ ነው ያለችው:: እንዳው ወደኋላ መለስከኝ ካላልሽኝ አንድ ነገር ልንገርሽ፤ በ1966 ዓ.ም በተደረገው አብዮት ለኢትዮጵያ ትልቅ ነገር ሊያመጣ የሚችል እድል ቢኖርም ያለውን የአገሪቱን የአዕምሮ ሃብት በልቶታል ብዬ ነው የማምነው:: የነበረንን መልካም አጋጣሚ ቀይሽብርና ነጭ ሽብር፤ ኢህአፓና መኢሶን እየተባለ ለርስበርስ ግጭት ነው ያዋልነው:: ከመሰረቱም ቢሆን የፖለቲካ ስሪቱ የእኛ አገርን ነባራዊ ሁኔታ መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ አልነበረም:: ሃይማኖታችንን ፣ ባህላችንን የነበረንን ጥንታዊ የመንግሥት ስሪት ማዕከል አድርጎ የተሰራ አይደለም:: ከዚያ ይልቅም ከውጭ የተቀዳና እንዲሁ ረብ በሌለውና ዋልታ ረገጥ በሆኑ ቃላት እርስበርስ የምንባላበት ሁኔታ ነው የነበረው:: ‹‹እናቸንፋለን›› እና ‹‹እናሸንፋለን›› በሚል ውዝግብ እንኳን በርካታ ሕዝብ እንዲያልቅ ተደርጓል:: ከዚያ ሁሉ የተረፈውና ሊጠቅም ይችል የነበረውም ጭንቅላት ወደ ውጪ ተሰደደ:: በዚህ ምክንያት ሀገሪቱ አንድ የፖለቲካ ችግር ተፈጠረባት፤ በልማትም ወደኋላ ቀረች:: ለእኔ በዚያ ጊዜ ተንጋዶ የተተከለው የፖለቲካ ሥርዓት ነው አሁን ድረስ ለዘለቀው ውጥንቅጥ ምክንያት የሆነው::
ከዚህም ባሻገር የሱማሌ ወረራ፣ እንዲሁም በትህነግና በሻዕቢያ ጦርነት ወንድሞቻችን መባላታቸውና ልማታችንን ማውደማቸው፣ ደሃ ሆነን እንድንኖር አደረጉ:: ደርግ ከተወገደ በኋላ መልካም እድል ተፈጥሮልን የነበረ ቢሆንም ያንን እድል በአግባቡ መጠቀም ሳንችል ቀረን:: አገሪቱ ልትወጣው የማትችለው፣ ዓለም ላይ ተፈትኖ የወደቀበት እንደ ራሺያና ዩጎዝላቪያ ሞክረውት የጣሉትን የፖለቲካ ስሪት በማምጣት ጭራሽ የማናውቀው የዘር ፖለቲካ ውስጥ ከተቱን:: ክልል የሚል አደገኛ አጥር ውስጥ ከተውን ‹‹የእኔ ነው፤ የአንቺ ነው›› እየተባባልን 27 ዓመት ሙሉ ስንባላ ኖርን:: የሚያሳዝነው የኢኮኖሚ አልያም የፖለቲካ እድገት አለማምጣታችን ነው:: እርስ በርሳችን እየተጎዳዳን ነው እዚህ የደረስነው:: ፖለቲከኞቻችን እርስበርስ ካባሉን በኋላ አስተካክለው መምራት ባለመቻላቸው ምክንያት ነው ይሄ ለውጥ የመጣው:: ይህ ለውጥ እውነት ለመናገር ትልቅ እድል ነበር:: መጀመሪያ አካባቢ ለሁላችንም ተስፋ የጣልንበት ለውጥ ነው:: ከሌሎች አገራት ጋር ልትመጣጠን የምትችልበት የፖለቲካ ስሪት ልትመራ እንደምትችልም ጠብቀን ነበር:: እኔ በግሌ ይህንን ነበር የምጠብቀው::
አዲስ ዘመን፡– ይህንን ሲሉ ለውጡ በጠበቁት መንገድ እየሄደ አለመሆኑን እየገለጹ ነው?
ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ፡-ምን መሰለሽ፤ በ1987 ዓ.ም የተጫነብን በዘር የተመሰረተ ሕገ መንግስት ሀገሪቱን የትም ሊያደርሳት እንደማይችል እሙን ነው:: ለተወሰነ ጊዜ ከፋፍሎ ወይም እንደ ዳቦ ቅርጫት ሊበታትናት አልሞ የተዘጋጀ ሰነድ በመሆኑ፤ ይህንን ሕገ መንግሥት ማሻሻል ባለመቻላችን ከለውጡ በኋላም አንድነታችንን አጠናክረን መቀጠል አዳግቶናል:: እኔ ለዓመታት የተዘራብንን ቂም፣ ቁርሾ ተወግዶ የሰለጠነ የፖለቲካ ስሪት ይዘረጋል የሚል ትልቅ እምነት ነበረኝ፡ እንደ እድል ሆኖ ግን የቀጠለው ያልሰለጠነ ፖለቲካ ነው::
አዲስ ዘመን፡– የሰለጠነ ፖለቲካ መገለጫው ምንድን ነው?
ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ፡– የሰለጠነ ፖለቲካ ማለት ዓለም በደረሰበት ልክ መሆን ማለት ነው:: አሁን ወደኋላ ሄደን የዘር ፖለቲካ የምናራምድበት ጊዜ አልነበረም:: በእርግጥ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ለተወሰኑ ወራት ተስፋዎች ታይተው ነበር:: ለውጡን እናስቀጥላለን ብለው ለውጡን ይመሩ የነበሩት ፖለቲከኞቻችንም በውጭም ሆነ በአገር ውስጥም እየዞሩ አገሪቱን በተሻለ መንገድ የሚመሩ መሆኑን ቃል ገብተው ነበር:: የነበረው ሥርዓት ትክክል አለመሆኑ፤ የበደለ ማንኛውንም አካል ይቅርታ በመጠየቅ ከዚህ በኋላ በምንም አይነት መንገድ ሕዝብ እርስ በእራሱ የማይባላበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ተናግረውም ነበር:: በዚህ ምክንያት ፖለቲካው በሰከነ መንገድ ይመራል የሚል ተስፋ ሰጥተውን ስለነበር ያንንም በትልቅ ሁኔታ አይተነው ነበር:: ግን እድል ሆኖ ሊሆን አልቻለም:: ያልሆነበት ምክንያት ሰዎቹ የመጡበት መነሻ ነው::
የፖለቲካ መሪዎቻችን መነሻቸው የትህነግ ፕሮግራም ነው :: እንደምታስታውሽው የኢህአዴግ አባል ለመሆን የትህነግን ፕሮግራም መቀበል ያስፈልግ ነበር:: የትህነግ ፕሮግራም ደግሞ ይህችን አገር በቋንቋና በዘር መከፋፈል ነው :: ይህችን አገር በቋንቋና በዘር በመከፋፈል ወይንም ክልሏን፣ አውራጃውን በዚያ መልኩ በመከፋፈል ለውጥ ማምጣት እንችላለን የሚለውን የተቀበለ ብቻ ነው የኢህአዴግ አባልም አጋር ድርጅትም መሆን የሚችለው:: በኢህአዴግ ጊዜ አባል የነበሩ አራት ድርጅቶች በሙሉ ይህንን የተቀበሉ ናቸው፣ የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች የሚባሉትም ይህንን የተቀበሉ ናቸው ማለት ነው:: በግፊት ለውጡ ከመጣ በኋላ እነዚህ ሰዎች ናቸው በሌላ የሳንቲም ገጽታ የመጡት:: በሌላ የሳንቲም ገጽታ ሲመጡ መነሻቸውም ያው ሲያባላን የኖረው ሕገ-መንግሥትና የዘር ፖለቲካ ነው:: ስለዚህ እነዚህ ሰዎች በአዲስ መንገድ መጥተው ያደረጉትን ነገር ሊረሱት አይችሉም፤ አልረሱትምም::
አዲስ ዘመን፡– እርሶ እንዳነሱት አብዛኛው ማህበረሰብ ተቀብሎት እየኖረ በማንነት ላይ የፖለቲካ ስሪት አሁን ከ30 ዓመታት በኋላ መቀየር በራሱ የሚያመጣው ችግር አይኖርም? እንዲሁ በቀላሉ ተቀባይነትስ ይኖረዋል ብለው ያምናሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ፡– እኔ አሁን የነገርኩሽ መነሻውን ነው:: እንዳልሽው ለ30 ዓመታት መሰረት የጣለ አመለካከት በአንድ ጊዜ ይቀየር ማለት የማይቻል ነው:: በፊት የነበረውን መልካምም ሆነ መጥፎም ነገር የሚያውቀው በእኔ እድሜ የነበረው የህብረተሰብ ክፍል ነው:: ነገር ግን አሁን ላይ ያለው ወጣት የዓለም ሁኔታ ለማየት በርካታ ዕድሎች አሉት:: በየቀኑ ከቴክኖሎጂ ጋር ይገናኛል:: ፌስቡክ፣ ዩ ቲዩብ፣ ቴሌቪዥን፣ ጋዜጦችና የመሳሰሉት ከዓለም ጋር በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያገኝ ወጣት ነው ያለን:: እንዳውም አሁን ያለው ወጣት አዲስን ነገር ለመቀበል አእምሮው ክፍት ነው ብዬ አምናለሁ :: ይህ ወጣት ድንጋይ ይወረውራል እንጂ አሁንም ችግሩን ከመሰረቱ የሚፈጥሩት በ60ዎቹ ዘመን የነበሩት ፖለቲከኞች ናቸው :: እነዚህ ፖለቲከኞች ጡረታ ቢወጡ፣ ቢያቆሙና ወደ ማስታረቅ አልያም ወደ ፀሎት ቢሄዱ የተሻለ ነው ብዬ አስባሁ:: ነገር ግን አሁን ያለው ወጣት አዲስን ነገር ተቀብሎ ለመተግበር ወደኋላ የሚል አይደለም::
በእርግጥ በአንዴ ለመቀበል የማይቻልባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ:: ግን ደግሞ ቀድሞ ያልነበረውን ክፉ ነገር መሰረት ለመጣል 27 ዓመታት ፈጅቷል:: ከእዚህ ክፉ ነገር ለመውጣት ግን 27 ዓመታት ላይፈጅ ይችላል:: በመሆኑም አሁን መጀመር አለበት:: ይሁንና እነዚህ ፖለቲከኞች ችግሩን ለመቀነስና ለማስተካከል የሚሄዱበት መንገድ አለመኖሩ ነው የሚያሳዝነው :: በየመድረኩ፣ በየትምህርት ቤቱ የነበረው አካሄድ ትክክል እንዳልነበረ በሚያሳይ መንገድ መተግበር አለበት :: አሁንም ዘረኝነቱ በከረረ ሁኔታ ነው እየሄደ ያለው :: በህወሓት ዘመን ግድያ፣ እስር፣ ጥፍር መንቀል ነበር:: ግን የተመረጡ ሰዎች ነበሩ የሚጠቁት :: በተለይም ጭንቅላት የነበራቸው፣ የእነርሱን የፖለቲካ ሥርዓት ሊያዛቡና ህብረተሰቡን ሊቀሰቅሱ ይችላሉ የሚባሉ ከየቦታው ተለቅመው ነበር እስር ቤት ገብተው የሚገደሉት :: አሁን ግን ከምንም ነገር የሌለበት ፖለቲካ የማያውቅ ሰርቶ የሚበላ ገበሬ ነው በማይታወቅ አካል እየተገደለ ያለው:: በመሆኑም ይህንን ነገር ማስቆም የሚችልበትን መንገድ ፖለቲከኞቻችን ቢፈትሹ መልካም ነው::
በዚህ ረገድ አሁን ላይ ሁኔታውን ለመቀየር የሚያስችል ነገር አይታይም:: ይሄ የሚያመለክተው የተለመደው እንዲቀጥል የሚፈልግ ኃይል መኖሩን ነው :: አስከፊውና ከፋፋዩ አስተሳሰብ እንዳይቀጥል እያስተማሩ መቀየር ያስፈልጋል:: እንዳልሽው ሕገ-መንግስቱን ዝም ብሎ መቀየር አይቻልም:: ምክንያቱም የሕዝብ ነው፤ ሕዝብ ሊወያይበት ይገባል:: ያንን አምኖ የተቀበለ ማህበረሰብ አለ፤ ያልተቀበለም አለ:: የተቀበለውንና ያልተቀበለውንም ማህበረሰብ አወያይቶ ለህብረተሰብ የሚጠቅመውን ነገር ለይቶ ሕገ መንግሥቱን በማስተካከል የአገርን ችግር በተወሰነ መንገድ መፍታት ይቻላል::
አስቀድሜ እንዳልኩሽ ሕገ መንግሥቱ የተሰራበት ስሪት የአንድ ድርጅት ፖለቲካ ፕሮግራም ነው:: ይሄ እስካለ ድረስ ችግሩ አይፈታም:: አንዳንዴ የህወሓት ሃሳብ በፖለቲከኞቻችን ሲንፀባረቅ የሚታይበት ሁኔታ አለ:: ያንን ሃሳብ የተቀበሉ ሰዎች በማስተካከል ችግሩን መፍታት የሚቻልበት መንገድ አለ :: ብሔራዊ እርቅ ማድረግ ያስፈልጋል :: ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማ ላይ ቀርበው ይቅርታ ጠይቀዋል :: ይቅርታ ከጠየቁ በኋላ ወዲያውኑ መሆን የነበረበት በዚህም ሆነ በዚያ ያሉ ፖለቲከኞቻችና ይህንን ችግር የሚፈጥሩ ሰዎች ወደ እርቅ ማምጣት ይገባቸው ነበር :: የነበረው ፖለቲካ ትክክል እንዳልነበር በማስገንዘብ ከሰለጠነው አለም እኩል መጓዝ የምንችለው ::
አዲስ ዘመን፡– አንዳንዶች ግን ከብሔራዊ እርቅ በላይ ብሔራዊ መግባባት ነው መፍትሄው ሲሉ ይከራከራሉ:: በተለይም ከልብ ለአገርና ለሕዝብ ሲባል የማይደረጉ እርቆች ለውጥ ሲያመጡ ባልታየበት ሁኔታ ውጤት የለውም ሲሉ ለሚያነሱ ሰዎች ምላሽዎ ምንድን ነው የሚሆነው?
ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ፡– መሰረታዊ ጥያቄ ነው ያነሳሽው፤ ብዙ እርቆችም ሲካሄዱ አይተናል:: ብዙ ኮንፈረንሶችም ተካሂደዋል:: ነገር ግን የተካሄዱት ኮንፈረንሶችና እርቆች እንዳልሽው በፖለቲከኞች መካከል ነው :: የሚጣሉም ሆነ የሚታረቁት እነሱ ናቸው :: በመሰረቱ እኔ ሕዝብ ለሕዝብ ተኳርፏል፤ ተጣልቷል ብዬ አላምንም:: የችግሩ ሰለባ ግን ሕዝቡ ነው የሆነው:: ፖለቲከኞቹ አቅማቸውን ማጎልበት የሚችሉት ሕዝብና ሕዝብን በማጣላት ነው :: በእኔ እምነት የቋንቋ ወይም የብሄር ፖለቲካን የሚያራምዱ ሰዎች ሃሳባቸውን ለህብረተሰብ ሽጠው በየትኛውም መንገድ የፖለቲካ መዋቅር መዘርጋት የማይችሉ፤ የሃሳብ ድክመት ያለባቸው ሰዎች ናቸው :: የብሔር ፖለቲካን ስታመጪ ቁስል ነው የምታኪው :: ዛሬ ላይ ሆነሽ የትላንትን ቁስል ነው የምታኪው:: ያውም የዛሬን እኮ አይደለም! የትናንትን ቁስል ነው የምታኪው :: አሁን ላይ ያሉት ፖለቲከኞች አማራጭ ከማቅረብ ይልቅ የህብረተሰቡ ያለፈ ቁስል ማከክና ሕዝብና ሕዝብን ማባላት ነው ምርጫቸው ያደረጉት:: በነገራችን ላይ በህብረተሰቡ መካከል ጥል ስለሌለ ነው እንጂ ችግሩ ከዚህም የከፋ ሊሆን ይችል ነበር:: ህብረተሰቡ መካከል ጥል ቢኖር እኔና አንቺ አብረን ልንቀመጥ አንችልም ነበር :: እርስበርስ እንጋደል ነበር::
አሁንም ቢሆን ህብረተሰቡ አጠቃላይ ኑሮው አንድ ላይ ነው የሚከውነው፤ በጋራ የመኖር እሴቱም አብሮት አለ:: ወደ ፖለቲካው ማህበረሰብ ስትገቢ የተለየ ነገር ነው የምታይው:: ፖለቲከኞቹ የእነሱን ልዩነት የሚያወርዱት ማህበረሰብ ላይ ነው:: ለእኔ እነሱ እውነተኛ እርቅ ቢያደርጉ በህብረተሰቡ መካከል ጥል ስለሌለ ችግሩ ይፈታል የሚል እምነት አለኝ :: ነገር ግን ፖለቲከኞቻችን በመካከላቸው ያለውን ችግር ቢፈቱም ለህብረተሰቡ የሚያቀርቡለት አጀንዳ ስሌላቸው ሰላሙን አይፈልጉትም :: ምክንያቱም ልዩነት ካልፈጠሩ አጀንዳ አይኖራቸውም :: አጀንዳቸው ምንጊዜም በልዩነት ላይ የተመሰረተ ነው:: ስለዚህ ፈጣሪ ልቦና ሰጥቷቸው ወደ እርቅና ወደ ሰለጠነ ፖለቲካ ቢመጡ በማህበረሰቡ መካከል ያለው መቆራቆዝ ይቆማል ባይ ነኝ :: በመሰረቱ ፖለቲከኞች አንድ ነገር ካላሉ በስተቀር ህብረተሰቡ አይጋደልም :: ለምሳሌ ባለፈው ዓመት እንደምታስታውሽው አንዱ ፖለቲከኛ ተከበብኩኝ ስላለ ሲቀሰቀስ በነበረው ወጣት አማካኝነት ምንም የማያውቅ ማህበረሰብ እንዲሞት ተደረገ :: ቀጠለናም አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ማን እንደገደለው በማይታወቅ ሁኔታ ‹‹ተገደለልህ›› ተብሎ ወጣቱ እንዲነሳ በሚዲያ ሳይቀር ቅስቀሳ በመደረጉ ምንም የማያውቅ ምስኪን ሕዝብ አለቀ:: በእኔ እምነት አንዱም ችግር ፈጣሪ ሚዲያው ነው:: ያለን ሚዲያ የዘር ሚዲያ ነው:: የአማራ፣ የኦሮሞ፤ ትግራይ እየተባለ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራው ስለዚያ ብሔረሰብ ብቻ ነው:: አንዳንዱም የሌላኛውን መጥፎ ነገር ወይም ውድቀቱን ብቻ ነው የሚሰራው:: ብንሰለጥን ኖሮ ስለአማራ መልካም የሚያነሳው ስለኦሮሞም ቢያነሳ ኖሮ ይሄ ችግር አይፈጠርም ነበር::
በአጠቃላይ ግን እርቅ የሚደረገው በህብረተሰቡ መካከል አይደለም :: ያኔ በሩዋንዳ ወይም ደቡብ አፍሪካ በህብረተሰቡ መካከል የሚደረገው እርቅ በህብረተሰብና በህብረተሰብ መካከል ወይም በነጭና በጥቁር መካከል እንዲሁም በሁቱና በቱትሲ መካከል ችግር ስለነበረ ነው:: መገዳደል ስለነበረ ነው :: አሁን እኛ አገር ያለው ሁኔታ ከዚያ ይለያል:: በአማራና በኦሮሞ ሕዝብ መካከል ችግር የለም:: በርካታ የአማራ ሕዝብ ኦሮሞ ውስጥ ይኖራል:: ቁጥሩ ወደ 400 ሺ የሚሆን ኦሮሞ ወሎ ውስጥ ይኖራል:: የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት ቢሆን ኖሮ እስካሁን አብሮ መኖር ባልቻለ ነበር :: እስካሁን በህብረተሰቡ መካከል ጥል አልተፈጠረም፤ አይፈጠረም ማለት ግን አይደለም::
አዲስ ዘመን፡– በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ከፖለቲካው ተገለው የነበሩ ፖለቲከኞች ከለውጡ በኋላ የተሰጣቸውን መልካም እድል ተጠቅመውበታል ተብሎ ይታመናል?
ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ፡- ለውጡ ካመጣው ጥሩና መጥፎ ነገር አንዱ ውጭ የነበሩ ፖለቲከኞቻችን ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉ ነው :: መልካም አጋጣሚው ይሄ ነው :: በውጭ አገር ሆነው መልካም አመለካከት አለን፣ ብንመረጥ የእኛ ፖለቲካ ይህችን አገር ወደ በጎ ያሻግራል ብለው የሚያስቡ ሰዎች መምጣታቸው መልካም ነው:: በሌላ መንገድ ደግሞ ምንም ይሁን ምን የፖለቲካ መስመራቸው አገር ለማተራመስ ብቻ የተፈጠሩ ፖለቲከኞች መግባታቸው የፈጠረው ችግር አለ :: በመሰረቱም እነዚህን ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች የፈጠሯቸው አገር ለማተራመስ ዓላማ ያላቸው ኃይሎች አሉ :: እነ ግብፅ እኛን ለማተራመስ ተኝተውልን አያውቁም :: ምክንያቱም ግብፆች የአባይን ውሃ እንደልብ መጠቀም የሚችሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ትርምስ ሲኖር ነው::
ኢትዮጵያ ውስጥ ትርምስ እንዲኖር ደግሞ የሚፈጥሯቸው የፖለቲካ ድርጅቶች አሉ :: ምንም አይነት የፖለቲካ ዓላማም ሆነ ግብ የሌላቸው፤ ነገር ግን አገር ሲያተራምሱ የነበሩ ፖለቲከኞች አሉ:: እነዚህ ፖለቲከኞች ሁሉም ነገር ተመቻችቶላቸው ከመጡ በኋላ የተሰሩበት ስሪት መሰረታቸው ሌላ ስለነበር ሁሉም ከተመቻቸ በኋላ በዚያ በተመቻቸው መንገድ መሄድ አልፈለጉም:: ምክንያቱም በእነሱ ዓላማ ስላልተቋቋሙ ነው ::
ፈጣሪዎቻቸውም ስለማይፈቅዱላቸውም ነው አገሪቱን ከፍተኛ የሆነ ችግር ውስጥ ሲገቡ የሚስተዋሉት :: እንደ አጠቃላይ እድሉን የተጠቀሙበት መኖራቸው መልካም ቢሆንም እድሉን አገር ለማተራመስ እየተጠቀሙበት ያሉ መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም :: ግን ደግሞ በትክክለኛ ምርጫ ሥልጣኔን አሳልፌ ለመስጠት ፍቃደኛ ነኝ የሚል ጠቅላይ ሚኒስትር ነው ያለው :: በእርግጥ ያስረክቡ፤ አያስረክቡ ሌላ ነገር ነው፤ ቢያንስ ግን ይህን የሚል አመራር መኖሩ በራሱ እንደመልካም አጋጣሚ መጠቀም ነው የሚገባው ባይ ነኝ ::
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለው ሁኔታ ፓርቲዎች ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጁ ናቸው ብለው ያምናሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፤ በመጀመሪያ በምርጫው ላይ ያለኝን አመለካከት ልንገርሽ:: ለእኔ አሁን ባንበት ሁኔታ አገራችን ምርጫ ለማካሄድ የምትችልበት ደረጃ ላይ አይደለችም :: ሕዝብ እየተፈናቀለ ነው፣ አገሪቱ በውስጥም በውጭም ይፋ ባልሆነ ጦርነት ላይ ነች :: በሱዳን እስከ 40 ኪሎ ሜትር ድረስ ወረራ ተደርጎብናል :: በዚህም ከፍተኛ የሆነ ሕዝብ ተፈናቅሏል፤ አርሶአደሩ አንድ አመት የለፋበት ንብረት ተዘርፏል:: ከአባይ ጋር በተያያዘ ግብፅና ሱዳን ተቀናጅተው በሃገራችን ላይ ችግር ለመፍጠር ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ያሉበት ሁኔታ ላይ ነው ያለው :: በመተከል ከግብፅ ጋር በተያያዘ እና የትህነግ ቡድን እየፈፀመ ያለው ሴራ እንደተጠበቀ ሆኖ አገር ለማተራመስ ከፍተኛ የሆነ ችግር ያለበት ወቅት ላይ ነው ያለነው :: በወለጋና ጉጂ አካባቢ ኦነግ ሸኔ የሚባል ኃይል ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ባለበት ሁኔታ እንዲሁም በገዢው መደቡ ውስጥ ያሉ ፖለቲከኞች አንድ ባልሆኑበት ሁኔታ ምርጫውን ማካሄድ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም :: ከዚህም ባሻገር የከተማዋም ሆነ የገጠሩ ሕዝብ የኑሮ ሁኔታው ውድነቱ ጣሪያ በነካበት ሁኔታ ፣ አንበጣና የኮቪድ ችግር ገና ባልተቀረፈበት ሁኔታ አንድና ሁለት አመት ምርጫ ማራዘም ለእኔ ያን ያህል ችግር የሚፈጥር ነው ብዬ ስለማላምን ምርጫ መደረግ የለበትም የሚል እምነት ነው ያለኝ ::
አዲስ ዘመን፡– ምርጫው አለመካሄዱ በራሱ የሚያመጣው ጣጣ አይኖርም? ደግሞም እንደ ህወሓት ያሉ ቡድኖች በምርጫ ሰበብ የፈጠሩትን አይነት ችግር ላለመፈጠሩ ምን ዋስትና ይኖረናል?
ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ፡– ትክክል ነሽ፤ በነገራችን ላይ ህወሓት ምርጫው ስለተራዘመ ነው ችግር የተፈጠረው በሚባለው ነገር ላይ አልስማማም :: ሰበብ ነው :: ምርጫው ህወሓት ባለው ጊዜ ቢካሄድም ይሄ ችግር መፈጠሩ አይቀርም ነበር :: ነገር ግን አሁን እኮ እኛ ሆነን ነው እንጂ የሰለጠኑት አገራት ቢሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ ውስጥ መግባት የነበረብን አገር ናት ያለችን:: ሕዝብ እያለቀ ነው:: በረሃብም፤ በጦርነትም:: ይሄ በሆነበት ሁኔታ በአስቸኳይ ጊዜ ውስጥ ሆና አገሪቱ ይህንን ሁኔታ ማለፍ ይገባት ነበር ባይ ነኝ:: ምርጫው ቢራዘም ችግር እንፈጥራለን ይሉ የነበሩ
ፖለቲከኞች አሁን ምርጫውን በራሳቸው መንገድ ትተውታል:: ምክንያቱም ሲጀመርም ምርጫውን እነሱ አይፈልጉትም:: ምርጫው ከዚህ በላይ ቢራዘምም እንዴትም ብለው ብዙ ችግር መፍጠራቸው አይቀርም:: ምርጫው ሊካሄድ ነው ሲባል ደግሞ አሁን መደረግ የለበትም የሚሉት እነሱ ራሳቸው ናቸው ::
ከዚህ አንፃር ምንም ይሁን ምን መንግሥት ወስኖ ምርጫው ይካሄዳል ከተባለ እኔ ካልተመቸኝ በሚቀጥለው እሳተፋለሁ ብዬ ከመንግሥት ጎን ሆኜ በጎ አስተዋፅኦ አደርጋለሁ ማለት ሌላ ነገር ነው:: ሰበብ ፈጥረሽ ግን ከፖለቲካ መንገድ መራቅ ደግሞ ፈፅሞ አሳማኝ አይደለም:: ያውም ደግሞ 40 እና 50 ዓመት እድሉ ስላልተፈጠረልኝ እንጂ ለሕዝቤ የሚያሻገር ፖለቲካ አለኝ ሲል የኖረ ፓርቲ ሁሉም ነገር ሲመቻችለት ከምርጫ አይሸሽም ነበር :: ግን እንዳልኩሽ ከመጀመሪያው ትክክለኛ ዓላማ ስላልነበረው ነው ወደኋላ እያፈገፈገ ያለው :: ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ምርጫም ቢደረግ መተዋቸው አይቀርም :: ቢደረግም ‹‹ለምን ይሆናል?›› ማለታቸው አይቀርም::
እንደእኔ እምነት እንዳውም አብዛኛው የፖለቲካ ድርጅት ዘንድሮ ምርጫ እንዲካሄድ የሚፈልግ አይመስለኝም :: ምክንያቱም መንግሥት ያለውን የአገሪቱን ችግር አጉልቶ ማሳየት ይጠበቅበታል ብዬ ነው የማምነው:: ትግራይ ውስጥ ያለው ችግር እኮ አሁንም አበቃለት የምንለው አይነት አይደለም:: የአገሪቱን ኢኮኖሚ ነው እየበላ ያለው :: ሱዳን የፈፀመችው ወረራም ቀላል አይደለም :: መተከልና ጉጂ ላይ ያለው ችግርም በቀላሉ የሚታይ አይደለም :: አገሪቱ ውስጥ ያለው የኑሮ ውድነት ቀላል አይደለም :: ከዚህም ባሻገር የፖለቲከኞች እርስበርስ አለመስማማት ሌላው ችግር ነው ::
ይህ በሆነበት ሁኔታ ላይ ምርጫውን በማራዘም ከሚመጣው ችግር ይልቅ ከምርጫው በኋላ የምርጫው ውጤት የሚያመጣው ችግር የበለጠ ያሳስበኛል :: ለዚህ ነው ዘንድሮ ቢያልፍና በርካታ ችግሮችን ፈተን፣ ወደ ሰላምና ወደ እርቅ አምጥተን ምርጫው ቢደረግ የተሻለ ነው የምለው:: ለመሆኑ በሥነልቦና የተጎዳ በርካታ ማህበረሰብ ባለበት እንዴት ነው ምርጫ ልናካሂድ የምንችለው? እንዴት ነው ወልቃይት አካባቢ የምርጫ ቅስቀሳ ልታካሂጂ የምትችይው? መተከል ላይ ያ ሁሉ ሕዝብ በተፈናቀለበት እና እናቶችና ህጻናት የሚበሉት ባጡበት ሁኔታ ላይ እንዴት ነው ምርጫ የሚከናወነው?:: በነገራችን ላይ በእኛ አገር ፖለቲከኛ የሚኮነው አገርን አሻግራለሁ ተብሎ ሳይሆን እንዴት ራሴን እጠቅማለሁ ተብሎ ነው :: ለሕዝቡ ለመሞት ተዘጋጅቶ የሚገባ የፖለቲካ ፓርቲ አባል የለም::
አዲስ ዘመን፡– ይህ እንዳለ ሆኖ በምርጫ ሂደት ውስጥም ሆነ የምርጫ ቅስቀሳው ከጥላቻና ከፀብ የራቀ ለማድረግ ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ፡– እንዳልሽው ምርጫው የግድ መደረጉ ካልቀረ ምርጫ ቢደረግ ደግሞ የምርጫ ቦርድ የሚያወጣው ሕግና ደንብ አለ :: በምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎች ሊከተሉት የሚገባ የሥነ ምግባር ደምብ አለ :: ይህንን የሥነ ምግባር ደምብ ማንኛውም ፓርቲ መተግበር አለብህ ተብሎ ፈርሟል :: መፈረማቸው ብቻ ሳይሆን ሲጀመርም መንግሥትም አገርንና ሕዝብን በሰላም ለመጠበቅ እሰራለሁ ብሎ ቃልኪዳን የገባበት ጉዳይ ነው:: ይሄ የእኔ ክልል በመሆኑ እንዳትመጡ በሚል ችግር እያጋጠመ መሆኑን በተጨባጭ አይተናል:: ይሄ መሆን የለበትም :: በነገራችን ላይ ይህንን ጉዳይ የሚያስፈፅመው የምርጫ ቦርዱ አይደለም :: ይልቁንም መደላደል የሚሆኑ ሕጎችን ነው የሚያዘጋጀው:: ይህንን ሕግ ተግባራዊ የሚያደርገው መንግሥት ነው::
እኛ አገር ችግር የሆነው ገዢ ፓርቲና መንግሥት አንድ መሆናቸው ነው:: መንግስት ይህንን ጉዳይ ማስፈጸም አለበት:: ማንኛውም ክልል ወረዳ፣ ዞን፣ ከተማ አስተዳደር፣ ቀበሌ ‹‹ይሄኛው መጥቶ ቅሰቀሳ ያድርግ ሌላኛው አይችልም›› ብሎ መከልከል አይችልም:: መንግሥት ሕግ፣ ወታደርና ገንዘብ አለው፤ እያንዳንዱ ማህበረሰብ ግብር የሚከፍለውና መንግሥትን ደግሞ በባንክና በታንክ የሚያስታጥቀው ሰላሙን እንዲያስከብርለት ነው:: ማንኛውም ፓርቲ ደግሞ ‹‹ፕሮግራሜ ለህብረተሰቡ ይጠቅማል›› በሚለው መንገድ ሃሳቡን ለሕዝቡ ሲያደርስ መንግስት ጥበቃ ሊያደርግለት ይገባል::
ስለዚህ ይሄ ድክመት የምርጫ ቦርድ ሳይሆን የመንግሥት ነው:: መንግሥት ሕጉን በአግባቡ መተግበር መቻል አለበት :: በሌላ መንገድ ግን የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ፓርቲዎች ማድረግ የሚገባቸው ነገር አለ :: አንደኛ ወጣቱንና ስሜታዊ ሊሆኑ የሚችሉ ዜጎችን ስሜታዊ በማድረግ ጊዜያዊ ትርፍ ሊያስገኝ በሚችል መልኩ ቅስቀሳ ማድረግ ተገቢ አይደለም :: ማንኛውም ፓርቲ ፕሮግራሙንና ምን ለማድረግ እንደፈለገ በዚህች አምስት ዓመት ሥልጣን ውስጥ አገሪቱን ወደየት ማሻገር እንደፈለገና በህብረተሰቡ መካከል ሰላምና ብልፅግናን ለማምጣት እንደፈለገ መቀስቀስ እንጂ የእኔ ፓርቲ ከሌላው የተሻለ ነው ብሎ ሌላውን አባር ብሎ ወጣቱን መቀስቀስ ደካማነት ነው :: በነገራችን ላይ ይህንን የሚያደርጉት በአብዛኛው የብሔር ፖለቲከኞች ናቸው :: የብሔር ፖለቲከኞች ደግሞ ሃሳብ ይጎላቸዋል ::
አስቀድሜ እንዳልኩሽ ሃሳባቸው ቁስል በማከክ ላይ የተመሰረተና ራዕይ የሌለው በመሆኑ ነው ወጣቱን ወደአልሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚከቱት:: በመሆኑም እነዚህ የብሄር ፖለቲከኞች ይህንን አይነት አካሄዳቸውን ቢያስቡበት የተሻለ ነው የሚል እምነት አለኝ:: መንግሥትም ምርጫ ቦርድ ለሚሰጠው ጥቆማና ፓርቲዎቹም በሚያቀርቡት ቅሬታ ላይ ተመሰርቶ መቆጣጠርና ችግር ፈጣሪዎቹን ማስቆም አለበት የሚል እምነት አለኝ :: ከዚህ ባሻገር ግን መንግስት የማይፈፅመው ከሆነ መንግሥትን የመቅጣት መብት ምርጫ ቦርድ ተሰጥቶታል:: ችግር በፈጠሩበት ወረዳ ላይ ያሉትን የመንግሥት አካላት ማገድ ይችላል :: በየአካባቢው ያሉት የመንግሥት አካላት ምንም እንኳን ከፓርቲ የመጡ ቢሆኑም የተቀመጡት መንግሥትን ወክለው ስለሆነ ሁሉንም በእኩል መንገድ ማስተናገድ ይጠበቅባቸዋል :: በትክክለኛና በተፈቀደ ሩጫ ሕግ መሰረት ማስተናገድ ነው ያለባቸው::
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ደጋግመው ያነሱት የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ በምን መልኩ መቋጫ ሊያገኝ ይችላል ተብሎ ይታመናል?
ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ፡- በአጠቃላይ ዝም ብሎ ጦርነት ውስጥ መግባት አያስፈልግም :: ደግሞም ጦርነት አክሳሪ መሆኑን በቅርቡም ትግራይ ውስጥ አይተነዋል:: ባለፉት 27 ዓመታት በትግራይ መሰረተ ልማቶች ተሰርተዋል :: አሁን ላይ ግን በማይሆን መንገድ ነው የጠፉት :: ይሄ የጦርነት አንዱ ገፅታ ነው :: ሱዳን ወረራ አድርጋለች ፣ በቀጥታ በጦርነት መሬታችንን ማስመለስ እንችላለን :: ነገር ግን መንግሥት እየሄደበት ያለው ነገር ጥሩ ነው:: በዲፕሎማሲው ለመጨረስ እያደረገ ያለው ጥረት መልካም ነው :: ትግራይ ውስጥ ጦርነት በሚካሄድበት ጊዜ ሕግ ለማስከበር በርካታ የጦር መሳሪያ ወድሟል፤ ወታደሮቻችንም ሞተዋል፤ ተጎድቷል::
በመሆኑም የጦር መሳሪያ ማዘጋጀት፣ ሎጅስቲኩን ማስተካከል የተበታተነውን ወታደር የሥነልቦናውን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል:: ማሰልጠን ይገባል:: ለዚህ ደግሞ ጊዜና ገንዘብ ያስፈልጋል:: ይህንን ከማድረግ ባሻገር ግን ሱዳን ወረራ ማድረጓን በይፋና በአግባቡ የዓለም ሕዝብ እንዲያውቀው ሲደረግ ግን አይታይም :: እኔ አካባቢውን ካሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የመገናኘት እድሉ ስላለኝ የማውቀው እውነት አለ :: እዛ አካባቢ ያሉ ኢትዮጵያውያን አረብኛ ስለሚሰሙ ሱዳን የምታወጣውን መግለጫ ስታይ ያስደነግጥሻል :: ሱዳን ኢትዮጵያ ወረራ አካሄደችብኝ ነው የምትለው እንጂ እኔ ወርሬያለሁ ብላ አታውቅም:: በየአጀንዳቸው ስለወረራው ነው የሚያወሩት:: በየጋዜጣቸው ይህንን ጉዳይ ነው የሚተነትኑት::
የእኛ መንግስት ግን አገር ተወራ፣ ሰውም ሞቶ ዝምታን ነው የመረጠው :: ምንአልባት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አልፎ አልፎ ከሚሰጠው መግለጫ ባሻገር ጠንካራ እንቅስቃሴ ሲደረግ አይስተዋልም :: ሚዲያውም ሲያስጮኸው አይስተዋልም :: በዚህ መሰረት የአሜሪካ መንግስት የኤርትራ ጦር ይውጣ የሚል መግለጫ ያወጣውን ያህል የአሜሪካን መንግስት ትኩረት እንዲስብ የሚያደርግ ስራ መንግሥታችን ባለመስራቱ ምክንያት የሱዳን መንግስት በወረራ የያዘውን መሬት ለቆ ወደ ድርድር ይግባ የሚል መግለጫ አላወጣም :: የአውሮፓ ህብረትም አላወጣም :: የአፍሪካ ህብረትም እንኳን እዚሀ ተቀምጦ አላወጣም :: ምክንያቱም የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ባለማለቱ ነው:: አንቺ ስታሥጮሂው ነው ጎረቤት የሚደርስልሽ :: ካልሆነ ሊመጣልሽ አይችልም:: ምንአልባት ውስጥ ለውስጥ ሊሰራ የሚችለው ነገር ሊኖር ይችላል:: ነገር ግን የሚወራውንም ነገር እንደ ዜጋ የማወቅ መብት አለኝ:: መንግሥት ዝም በማለቱ ነው አሁን ላይ ከዚህም ከዚያም የተለያየ አይነት ሃሳብ እየመጣ ያለው::
እንደአጠቃላይ መፍትሄው ጦርነት ነው የሚል እምነት የለኝም:: ከጦርነት ባሻገር በድርድር ቢያልቅ ጥሩ ነው የሚል እምነት አለኝ:: ነገር ግን አሁን ሱዳኖች የጦር ካምፕ እየሰሩ ነው፣ ቤቶችና ምሽጎች እየሰሩ ነው:: አሁን ደግሞ ከመጋቢት ግማሽ በኋላ የእርሻ ወቅት ነው፤ እዚያ አካባቢ ያለ ገበሬ ምን እንደሚሆን አላውቅም:: በእርግጥ የእርሻ መሳሪያቸው ተወስዷል፣ ያመረቱት ምርት ተወስዷል:: አሁን ደግሞ በዚያው ድህነት ውስጥ ሊቀጥሉ ነው የሚለው ነገር ያሳስበኛል:: መንግሥት በምን ዓይነት መልኩ እያየው እንደሆነ አላውቅም:: ምንአልባት ከግድቡ ጋር ተያይዞ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እስከሚከናወን ድረስ በዝምታ ማለፉን መርጦ ሊሆን ይችላል:: አሁን የያዘውን ያህል ተጨማሪ ውሃ እንኳን ቢይዝ ውሃው ራሱ ራሱን ይጠብቃል የሚል እምነት አለኝ:: ማንም አይነካውም::
አዲስ ዘመን፡–ይህ የሱዳን ወረራ ከመነሻው የመሬት ጥያቄ ሳይሆን ግድቡን ለማጨናገፍ እንደሆነ ማረጋገጫ አይሆንም?
ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ፡– ሊሆን ይችላል:: ነገር ግን አስቀድሜ እንዳልኩሽ መንግስት ዝም ማለቱ በራሱ ጤናማነት የለውም ባይ ነኝ:: መጨረሻ ላይ እንዳውም የሱዳኑ መሪ የኢትዮጵያ መንግሥት ያዙ ብሎን ነው የያዝነው እስከማለት ደርሷል :: ይህም መንግሥታችንን እንድንጠራጠር ነው ያደረገው :: ከዚያ በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃለአቀባይ ‹‹ወያኔዎች እንዳያመልጡ ጠብቁ እንጂ መሬት ያዙ አላልንም›› የሚል መግለጫ ነው የሰጡት :: እስከእዚያ ድረስ ግን ለእኛ አልተነገረንም ነበር:: እንደዚህ አይነት ነገሮች የመንግሥትን ዋጋ ሊያሳጣን የሚችልና ላልሆነ መረጃ ህብረተሰቡንም ሊያጋልጥ ስለሚችል በየቀኑ ያለበትን ሁኔታ ቢገልፅልን የፓርቲም አጋዥ ነው የሚሆነው :: መንግሥት ዝም ባለ መጠን ግን ጥርጣሬው እየጎለበተ ነው የሚመጣው :: ዓላማው መሬት መያዝ ሳይሆን የግድቡን ግንባታ ማጨናገፍ እንደሆነ ህብረተሰቡም ቢሆን ይረዳል :: መንግሥት ግን ብቻውን አፍኖ ከሚይዘው ቢያወጣውና ብንወያይበት ጥሩ ነው::
አዲስ ዘመን፡– በአሁኑ ወቅት ካለው ችግር አኳያ ትክክለኛውን የአገሪቱን ገፅታ ለዓለም ህብረተሰብ ለማሳየት እየተሰራ ያለውን ስራ እንዴት ይመዝኑታል?
ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ፡– በእኔ እምነት የእኛ ዋነኛ ችግር ሁሉንም ሥራ በጥሩ መልኩ ከሰራን በኋላ በር አናበጅለትም:: ያንን ጦርነት በሙሉ 15 ቀን ጊዜ ውስጥ በጥቂት መስዋዕትነት ከተደመደመ በኋላ ዝም ነው የተባለው:: ያንን ዝምታ ግን የትህነግ ኃይሎችና ፖለቲከኞች እንዲሁም ዲያስፖራዎች ተጠቀሙበት:: በተለይም ማይካድራ ላይ የተደረገውን ጭፍጨፋ በከፍተኛ ደረጃ ዶክመንተሪ እየተሰራ የተደረገውን ሁሉ በዝርዝር ለማሳየት ብንሞክር ኖሮ ይህ ሁሉ ባልሆነ ነበር:: አሁን ላይ ሱዳን የስደተኞች ጣቢያ ላይ ለምን ወጣቶች ብቻ ተቀመጡ? የሚለውን ነገር ከዚህ ወንጀል ሰርተው የተደበቁ ስለመሆናቸው በግልፅ ለዓለምአቀፍ ህብረተሰብ ማስረዳት መቻል ነበረብን:: ዓለምአቀፍ ተቋማት እነዚያን ገዳይ ኃይሎች ለምን አይሰጡንም? ብሎ እስከመጠየቅ መድረስ ነበረበት:: በተከታታይ እውነታውን ለማሳየት ባለመቻላችን ምክንያት ሌሎቹ ወሰዱት:: ‹‹ብጥለው ገለበጠኝ›› የሚባል አባባል አለ:: እነሱ ቀደም ሲል የነበራቸውን የዲፕሎማሲ አቅም፣ የገንዘብ አቅም በመጠቀም ብልጫውን ወሰዱብን :: በዚህ ብቻ አልተወሰኑም :: ጭራሹንም የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ይውጣ በማለት በውስጥ አስተዳደራችን እንዲገቡ አድርገዋል::
በነገራችን ላይ የትህነግ የዲፕሎማሲ ኃይልና በውጭ ያለው የነሱ የፌስቡክ አርበኞች እየተንከባለሉ፣ አለ የሚባለውን መኪናቸውን በማውጣት፣ ህፃናት ልጆቻቸውን ጭምር በማምጣት የትግራይ ሴት ያለአግባብ ስትንገላታ ድራማ በማሳየት የአለምአቀፍ ትኩረት ለመሳብ ችለዋል :: ግን በውሸት ላይ ተመስርተው ነው :: እኛ በእውነት ላይ ተመስርተን ያንን መስራት አልቻልንም :: እውነታውን ያለማሳየት የእኛ ችግር ነው:: ከእነሱ በላይ የሚሆን ዲያስፖራ አሜሪካ ውስጥ አለ :: ምናአልባት እነሱ አንድ አምስተኛ ቢሆኑ ነው :: ያንን የሚያክል ቁጥር ያለው ዲያስፖራ ትህነግ የፈፀመውን ግፍ የዓለም ሕዝብ እንዲያውቀው አላደረገም::
በዚህ ረገድ እንደበለጡን ልንቀበል ይገባል:: ነገር ግን በዚህ መቆም የለብንም:: በዚህ ካልቆምን አሁን እየተደረጉ ያሉ ሰላማዊ ሰልፎች ቢጠናከሩና በተከታታይነት ቢቀጥሉ የዓለም አቀፍ ህብረተሰብ እውነቱን እያወቀ ይሄዳል:: አክሱም ላይ ተጨፍጭፈዋል የተባሉ ሰዎች የናይጄሪያ ዜጎች ናቸው:: ይህንን ነው እንግዲህ አቀነባብረው ያመጡት:: እናም አንዲህ አይነት ነገሮችን ለማጋለጥ እድሉ ነበረን፤ ግን አልተጠቀምንበትም :: ስለዚህ ውጭ ያሉት ዲፕሎማቶቻችን ሥራቸውን በአግባቡ እየሰሩ ነው ለማለት አልችልም :: በውጭ የሚኖሩ ዲያስፖራ እውነታውን ማሳወቅ መቻል አለበት:: የትህነግን ትክክለኛ ገፅታ ለዓለም ህብረተሰብ ባሳወቅን ቁጥር የኢትዮጵያን ሁኔታ በሚዛኑ መታየት ይጀምራል:: የተጀመረው ነገር መቆም የለበትም፤ በመንግስትም ሊደገፍ ይገባል::
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ::
ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ፡- እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ::
አዲስ ዘመን መጋቢት 11/2013