የእረሱነኝ ወገኔ
ጎበዝ ናፈቀኝ:: አይገርምም! ዛሬ ላይ ሆኖ ወደ ኋላ ተመልሶ የማያውቁትን ፣ነበር ያሉትን ሰመናፈቅ:: ሰው እንዴት የቆመበትን፣ ዘመኑን ነቅፎ የሌሉትን ያለፉበትን ዘመናት ይናፍቃል? ጉድ ነው:: እናም ወደ ኋላ ተመልሼ የድሮ ዘመንን ማሰብ ያልነበርኩበትን እንዲህ ነበር የተባለውን ሰምቼ መናፈቅ ጀምሬያለሁ:: ግን ቆይ ጎበዝ የናፈቅኩትን ማመኔ አያስገርምም? ድሮ ነበር የተባለውን ሁሉ አምኜ መቀበሌ በራሱ እጅግ ያስገርማል::
ዛሬ ላይ ተቆሞ ድሮ እንዲህ ነበር ተብሎ በሰፊው ይነገራል:: አቤት የድሮ ሰው ታማኝነቱ፣ የገባውን ቃል መጠበቁ፤ ለእምነት እና አቋሙ ሟችነቱ ይጠቀሳል:: የዱሮ ሰው በግ በአንድ ብር ገዝቶ፣ ቆዳውን በ3 ብር ይሸጥ ነበር፣ አንድ ጣሳ ጋብዥው ነው ወዳጄ ይሄንን አንድ ሺ ካሬ የሰጠኝ፣ ወንድ አያትህ ለሴት አያትህ ለወር አስቤዛ አንድ ብር ነበር የሚሰጠው፤ እሷም የምትፈልገውን ገዛዝታ የተወሰኑ ሳንቲሞችን ለችግር ጊዜ ብላ ታስቀምጥ ነበር እየተባለ ይነገራል:: ይሄ ታዲያ አይናፍቅም?
ድሮን ባልኖርበትም ሲሉ የሰማሁትን ዘመን በኖርኩበት ምን ነበር አልኩ:: ድሮ ነበር የሚባለውን ሁሉ ዛሬ ማግኘት ቢቻል ብሎ ማሰብ በራሱ ደስ ይላል:: እውነትና እምነት በርክቶ ይገኝ የነበረበት፣ ሰው ለቃሉ ታምኖ ለእምነቱ አድሮ በሰፊው ይታይ የነበረበት ዘመን ለምን አይናፍቅ፤ ያን ዘመን በመናፈቄ አልተሳሳትኩም::
ዛሬ ላይ ቆመን ትናንትን እንድንናፍቅ የሚያደርገው ዋናው ምክንያት ደግሞ በዚህ ዘመን ውሸት እየጎለበተ መምጣቱ ነው:: በዚህ ዘመን ውሸት የተጠባቸው ጥቂት አይደሉም:: ወዳጆቼ ውሸት ከመበርከቱ የተነሳ ማደሪያችን የሆነ እየመሰለኝ መጥቷል:: እውነተኛ እያለ ውሸታም ሲሸለም እውነትን ቢጠራጠሩ ምን ችግር አለው? የቀደመውን ዘመን እውነት ቢናፍቁስ ምን ችግር አለው?
ከሰዎች ጋር ለመግባባት ሁሉም ውሸታም ሆኖ መገኘት አለበት፤ ለእዚህም ውሸት ላይ ያለንን እምነት ከፍ ማድረግ ግድ ይለናል:: ዛሬ ለእውነት እቆማለሁ፣ እውነትን እንጂ በፍጹም ውሸት አልናገርም ካሉ ሰሚና አማኙ ትንሽ ነው:: እውነት እንዲድበሰበስ ውሸት ጎላ ብሎ እንዲታይ እየተደረገ ነው:: ለምን ?
ትንሽ ትልቁ ከውሸት እያተረፈ ነው፤ በውሸት ሀብታም እየተሆነ ነው፤ በአይናችን በብረቱ ያየነውን በውሸት ሳቢያ እንድንጠራጠር ለማድረግ እየተሞከረ ነው:: በሀሰት መረጃ እውነታን ሸፍኖ የጥፋት አላማን ለማሳካት መሞከር ሩጫው በዛ:: በውሸት ሀገር ተዘረፈ፤ እየተዘረፈ ነው፤ በውሸት ተመልሶ ስልጣን ለመቆናጠጥ ብዙ ድንጋይ ተፈነቀለ::
ለፅሁፌ መነሻ የሆነውን ገጠመኜን ላካፍላችሁ:: ክልል የሚኖር አንድ ወዳጅ አለኝ:: የት ክልል እንዳትሉኝ፤ ሆሆ … እሱን ነግሬ ደግሞ ያወራሁትን ሁሉ ውሸት ነው አንቀበልህም ልትሉኝ ነው:: ብቻ ዝም ብላችሁ በእምነት የምለውን ሁሉ ከተቀበላችሁኝ ከሆነ አገር የተደወለ ስልክ ነው ብላችሁ ውሰዱት::
ወዳጄ ከደወለልኝ ረጅም ጊዜ ሆኖ ነበርና እየተገረምኩ በምን አስቦኝ ይሆን ብዬ ስልኩን አነሳሁት:: ከስልኩ ወዲያኛው ጫፍ ወደኔ የመጣው የመጀመሪያ ድምፅ “ሀሎ ተረፍክ፤ ደህና ነህ፤ ወዳጄ እዚያ ችግር አለ ሲሉ በጣም አሰብኩህ” አለኝ::
ተናግሮ እስከሚጨርስ ስንቱን አሰብኩ መላችሁ:: እሱ የደወለበት ምክንያት ግን ፍሬ ከርስኪ የሚሉት አይነት ነው:: ጉዳዩ ሰሞኑን እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ በአንድ ወጣት ላይ የተፈጸመ ግድያን የተመለከተ ነው:: የወጣቱ አሳዛኝ ህልፈት ወደ ክልል ሲደርስ ሌላ መልክ ተሰጥቶት ኖሯል:: “አዲስ አበባ ላይ አንድ ወጣት ተገሎ ረብሻ ተነስቷል መባሉን ሰምቼ ነው የምደውልልህ:: አልተጎዳህም፤ ምንም አልሆንክም” ሲለኝ ግራ ተጋባሁ:: የምን ረብሻ፣ ኧረ ወዳጄ በፍፁም እንዲህ አይነት ነገር እዚህ የለም፤ ወሬው የተሳሳተና ውሸት ነው:: ብዬ ላስረዳው ሞከርኩ:: ቅር እያለው ተቀበለኝ::
ቆዩኝማ እኔ አዲስ አበባ ላይ አይደለም እንዴ የምኖረው? እዚህ የሚሆነውና እዚያ የሚነገረው እንዴት ተለያየ፤የሚሆነውና ሆነ የሚባለው ስለምን የዚህን ያህል ይሰፋል::
በአካልም በስልክም ሳንገናኝ ብዙ ጊዜ የሆነን ወዳጄ እንዴት ሸገር ላይ ረብሻ ነበር ተብሎ ተነግሮኝ ነው ብሎ ደወለልኝ? አያችሁ ውሸት ምን ይህል ገኖ እንደሚነገር:: ውሸታሞች ውሸታቸውን ለማስተላለፍ ሰውን ምን ያህል ቧንቧ አርገው እንደሚጠቀሙ ተመልከቱ::
ጎበዝ! ይህ በሰው ልጅ ላይ መጥፎ ስሜት የሚፈጥር፣ በሌለ ነገር ላይ ተመስርቶ ሰው እርምጃ እንዲወስድ የሚያደርግን የሀሰት መረጃ ካልተውነው አደጋ ያስክትላል:: እውነት ከሀሰት በላቀ መልኩ ካልተደመጠ፤ሀያል መሆኑን ማህበረሰባችን ካልተቀበለና ስለእውነት ካልተሰራ መፃኢውን ጊዜ መተንበይ ያዳግታል::ከእውነት የራቀ ልማድ የውሸት ያስኖራልና ሀሰትን የመራቅ ብሎም የማስወገድ ስራ መስራት ይገባል::
ምንም ያህል ጽድት ያለ እውነታ ከእኛ ጋር ቢሆን ሀሰት በበረከተበት ሜዳ ላይ የእኛ እውነት የሚለዝብበት እድሉ ሰፊ ነው:: ወሬ በዝቷል፤ ወሬው ደግሞ ውሸት ነው:: የወሬን አደገኛነት የተገነዘቡት የቀደሙት ሰዎች “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” ብለው ደምድመውታል::
የሀገራችንን የቅርብ ጊዜ እውነታዎች ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይገባል:: ሀገራችን ልጆቿን በየሳምንቱ ሲጨርስባት የነበረውን ጁንታ ለማስወገድ በትግራይ ክልል ለ15 ቀናት ባከናወነችው የህግ ማስከበር ስራ የተጎናጸፈችው ታላቅ ድልና ቀጥሎ ለዜጎች ሊኖረው የሚችለው ቱሩፋት እያለ፣ ጁንታው በማይካድራ በአሰቃቂ ሁኔታ ከአንድ ሺ በላይ ዜጎችን በማንነት ላይ ተመስርቶ የፈጸመው የዘር ማጥፋት ድርጊት እያለ የጁንታው ርዝራዦች የከፈቱት ዘመቻ ይታወሳል::
የጁንታው ርዝራዦች ኢትዮጵያን በሀሰተኛ መረጃ ላይ ተመስርተው ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የከሰሱበት እና ይህ ማህበረሰብም ለእርምጃ አቆብቁቦ የነበረበት ሁኔታ ይታወሳል:: በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ይህን ሀሰተኛ ዘመቻ ለማምከን ባይነሱ ኖሩ ከእውነት ጋር ያለችው ሀገራችንን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በሀሰተኛ መረጃ ምን ያህል ልትጎዳ እንደምትችል መገመት አይከብድም:: ከዚህም ሀሰተኛ መረጃና ሀሰተኞች ምን ያህል ሀገርንና ህዝብን ሊጎዱ እንደሚችሉ መረዳት ይቻላል::
እውነት በሚገባ የሚነገርበት ሀሰት ቀና እንዳይል ተደርጎ የሚንኳሰስብት ዘመን በእርግጥ ይመጣል:: ያኔ የእውነትን ቦታ የያዘ የመሰለው ሀሰት ብን ብሎ ይጠፋል፤ ቆሞ የሚሞግትበት አቅም የለውም:: ይህ ሲሆን ሀሰተኞች ፍጥጥ ብለው ይታያሉ፤ ስራቸውና ኑሯቸው የውሸት መሆኑ ከዳር እስከ ዳር ይረጋገጥና በእውነት ዘመን መኖር ይሳናቸዋል::
እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል እንዲሉ የውሸት እድሜው የጤዛ ያህል ነው፤ ይረግፋል:: እውነት ግን እውነት ነውና እድሜው ረዥም ነው፤ የትም አይሄድም:: እውነት አሸናፊ ነውና በሀሰት ወሬ ሳንሞኝ በእውነት ላይ ጸንተን ስለእውነት እየሰበክን ነጋችንን እናድሰው:: አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን::
አዲስ ዘመን መጋቢት 11/2013