(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
ሥጋትና ተስፋ
በድንጋጤና በእንባ ዓለማችንን ከአጥናፍ አጥናፍ ካነጋገሩ የዘመናችን ክስተቶች መካከል የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ያህል በተጋጋለ ዜናና መርዶ አየሩ ተሞልቶ እንደማያውቅ ብዙዎች ይስማማሉ:: ኮቪድ ጓዳ ጎድጓዳችንን የዳበሰ ክፉ ወረርሽኝ ብቻም ሳይሆን ዓለማችንን በእንቆቅልሽ የረታና በውስብስብ ምሥጢራት የተተበተበ መሆኑ ጭምር መከራው እንዲከብድ ምክንያት ሆኗል::
ወረርሽኙ ከምንንና እንዴት ሊከሰት ቻለ? እንደምንስ በብርሃን ፍጥነት ምድራችንን አዳርሶ ለድንጋጤና ለእልቂት ሊዳርግ በቃ? ሕይወታቸው ለተቀጠፈው በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የሰው ዘሮች፣ ደዌው አማቆ ላጎሳቆላቸውና እስትንፋሳቸው ከሞት አፋፍ ተነጥቆ ለተመለሰው ገመምተኞች፣ ድቅቅና እምሽክ ላለው የምድራችን ኤኮኖሚ የጥፋቱ ምክንያት “እከሌ” ተብሎ ጣት የሚጠቆምበት ተጠያቂ ማነው? እኒህና በርካታ መሰል ጥያቄዎች “ይመስለናል” እየተባለ ካልሆነ በስተቀር እስከዚህ ዕለት ድረስ ተብራርተው በቂ ምላሽ ሊያገኙ አልቻሉም::
የዓለማችንን ውሎ አዳር የሚመዘግቡ በርካታ ጠበብት እንደሚገልጹት ከሆነ ምድራችን እስከዛሬ ያስተናገደቻቸው “ሉላዊ ጦርነቶች”፣ መሰል ወረርሽኞችና መከራዎች ሁሉ ቢደመሩ የኮቪድ 19 ያህልን ጥፋትና ድንጋጤ እንዳላስከተሉ ይታመናል:: የሰው ዘር እርስ በእርሱ ተፈራርቶ የተራራቀበት፣ አገራት ድንበራቸውን ጠርቅመው አትድረሱብን ያሉበት፣ በሣር ቅጠሉ ላይ የኮቪድ ቫይረሱ ስላለ ተጠንቀቁ እየተባለ የታወጀበት፣ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ አየርን እንኳን በነፃነት እንዳይምግ በጭምብል የታጀለበት፣ ወረርሽኙ የዳበሰውም በሩን ጠርቅሞ የተገለለበት፣ ኃላያላን የተንበረከኩበት፣ ሀብታሞች የተከዙበት፣ “ዝግ ነው!” የሚሉ የተዘወተሩ ዜናዎች የናኙበት ወዘተ. ስንቱ የመከራ ዓይነት ተዘርዝሮ ይቻላል? ኮቪድ ያላዘነበብን ምድራዊ አሣር ምን ቀረ ያሰኛል::
ዛሬም “ጋላቢው ሞት” ስላልተገታ፣ ዛሬም የተናጋው የምድራችን ኢኮኖሚና ማሕበራዊ ቀውስ ገና ተረጋግቶ “መከራው ስላላባራ” ድምር ውጤቱ ይህንን ይመስላል ብሎ ከድምዳሜ ላይ መድረስ አልተቻለም:: በዚህም ምክንያት ዓለማችን የተጎናጸፈችውን የሐዘን ከል ለውጣ “ከመከራ ፍራሽ” ላይ ገና አልተነሳችም:: ሥጋቷና እምባዋም ገና አልታበሰም:: የክትባት ፈጣሪ ጠቢባን ልጆቿም ቀን ከሌት ለፍተው ያሳዩን የተስፋ ውጋገንም በምልዓት ፈክቶ “ሃሌሉያ” አሰኝቶ ሊያዘምረን ገና አልቻለም::
ስለዚህም ኮቪድ በወራሪነቱ እንደበረታ፣ በቀባሪነቱም እንደ ጀገነ ዛሬም “ገዳይ ደሞ!” እያለ በማንጎራጎር ላይ ነው:: የሀገራችን ሁኔታም ከዕለት ዕለት እየተባባሰበት መሆኑ መርዶው እየደረሰን ነው:: ወገኔ ሆይ እባካችሁ ጥቂቷን የጤና ባለሙያዎች ምክር በመቀበል ይህንን ክፉ ወራሪ “ጦርና ጋሻውን፣ ሰይፍና ጎመዱን፣ ጠብመንጃና ዝናሩን” ለማስጣል ሁላችንም ሠለስቱ ትዕዛዛትን በመተግበር እንዝመትበት:: ትዕዛዛቱ እጅግም አይከብዱም፤ ማሕበራዊ ርቀታችንን እንጠብቅ፣ የአፍና የአፍንጫ ጭንብላችንን በአግባቡ እንጠቀም፣ እጆቻችንን አዘውትረን በንጽህና እንጠብቅ፤ ከሣሙናና ከሣኒታይዘር ጋርም የጠበቀ ወዳጅነት እንመስርት:: እነዚሁ ናቸው::
ሢሶው ለማን? ሢሶው ወዴት?
ቀደምቱና ሀገራዊው የዘመነ ፊውዳል የዘውድ ሥልጣን ክፍፍል ለይስሙላም ቢሆን አዘውትሮ ሲገለጽ የኖረው፤ “ሢሶው ለነጋሽ፣ ሢሶው ለአንጋሽ፣ ሢሶው ለቀዳሽ” እየተባለ ነበር:: የመንግሥት ሥልጣኑ የሢሶ መብት “ሞዓ አንበሳ ዘእም ነገደ ይሁዳ” ለተባሉት የነገሥታት ዘሮች በቋሚነት መመደቡን፣ ሢሶ ለአንጋሽ መባሉም “ተራው ሕዝብ” የአንድ ሦስተኛ ሥልጣን ተጋሪ መሆኑን፣ “ሢሶ ለቀዳሽ” መሰኘቱም “የቤተ ክህነቱን” የመንበረ ሥልጣን ተጋሪነት ለማመልከት ነበር::
ይህንን ታሪካዊ የሥልጣን ሽንሻኖ “ይባል ነበር” ትርክት ለማስታወስ የተገደድኩት የዘውዳዊ አገዛዙን የአርባ ዓመት የሙት ዝክሩን ለማስታወስ በመፈለግ ሳይሆን ብሂሉ ርዕሰ ጉዳዬን የሚያብራራልኝ ስለመሰለኝ ነው::
ምሥጋና ለመንግሥታችንና ለሀገራችን የጤናው ክፍል መሪዎች ይሁንና በመላው ዓለምና በሀገራችን እንደ “በላ” የወረደብንን ይህንን የኮቪድ ወረርሽኝ መመከቻ የሚሆን 2.2 ሚሊዮን ያህል የክትባት መድኃኒት የተሸከሙ ብልቃጦች በርዳታ ይሁን በግዢ መረጃው ባልተሰጠን ዘዴ ሀገራችን መግባታቸው ተረጋግጦ ወደ እድለኞቹ ዜጎቻችን የደም ሥር ውስጥ መላክ ተጀምሯል:: በሥነ ጽሑፉ መራቀቁ ለጊዜው ይቆይና ክትባቱ ተጀምሯል ማለቱ ብቻ ይበቃል:: ወደፊትም ጥረቱ ተጠናክሮ በመቀጠል እስከ ታኅሣሥ ወር ድረስ 20 ከመቶ ዜጎቻችን ዘንድ ተስፋው እንደሚቃረብ እየተገለፀልን ነው:: አበጃችሁ!
የሆነው ሆኖ ግን ተስፋችን የተንጠለጠለው ከውጭ በሚገቡ “ፈረንጅ ሠራሽ” ክትባቶች ላይ እንጂ የባህል መድኃኒቶቻችንን በተመለከተ እስከ ዛሬ ከጉርምርምታ ውጭ በይፋ ምንም ያለመባሉ እኛን ተራ ዜጎችንም ሆነ ሀገራዊ የባህል መድኃኒት ጠቢባኑን ማጠያየቁ አልቀረም:: ደፈር ብለን እንጫን ካልንም መረር ያለ ቅይማት ማስከተሉንም እያደመጥን ነው::
በዚህ ጸሐፊ እምነት “ግዛዋ ሳለ ከደጅሽ ለምን ሞተ ልጅሽ” በሚል ድንቅ ብሂል ዜጎቿን ስታጽናናና ስታክም የኖረች ሀገር ለራስ በቀል እውቀቶቿ ለምን ባዕድ እንደምትሆንና ጠቢባን ልጆቿንም ለምን ፊት እንደምትነሳቸው በእውነቱ ሊገባን አልቻለም:: የገባቸው ካሉም ብዥታችንን ቢያጠሩልን አይከፋም:: “በእጅ ያለ ወርቋ መደብ የሆነባት ሀገር” ከሀገሬ ውጭ ሌሎችም ካሉ ቢገለጽልን ተጽናንተን “በሆድ ይፍጀው” ትዕግሥት ማለፍ እንችላለን::
ሀገር በቀል ጠቢባኖቻችን “መፍትሔ በእጃችን አለ እባካችሁ ስሙንና እድል ስጡን!?” እያሉ ቢወተውቱም ከነአካቴው ጆሮ የሰጣቸው ያለ እስከማይመስል ድረስ ጩኸታቸው በዝምታና በቸልተኝነት እየታለፈ ነው:: የሚመለከታቸው የጤና ተቋማት ኃላፊዎችም በሳይንሳዊ ትንታኔና መላምት ልንረዳው የማንችለውን ምክንያት እየደረደሩልን ጉዳዩን ሲያድበሰብሱ እያስተዋልን መታዘባችን አልቀረም:: ከመሞት የሚያሰነብት “ሀገር በቀል መፍትሔ” አለን የሚሉት ቢደመጡና ቢደገፉ ምን ክፋት አለው? ደፋር መልስ ሰጭ ባይኖርም ደግመን ደጋግመን እንጠይቃለን:: አልሰማ ካሉም ታሪክን ምስክር አቁመን “ተው ስማኝ ሀገሬ” እያልን እናንጎራጉራለን::
የፈረንጁን የክትባት ምጽዋት የሚመፀውቱን አገራት በሳይንስ ተራቀናል፣ በምርምር ረቅቀናል ብለው ሳይኮፈሱ በአብዛኛው ትኩረት የሚሰጡት ለባህል ጥበባቸውና ጠቢባኖቻቸው ነው:: በቀዳሚነት ቻይናን ጠቅሰን በርካታ የአፍሪካ አገራትን ብናስከትል ለምሳሌነት ይበቁናል:: “እኛ በድህነታችን የምንሞላቀቀው ግራ ገብ ኩሮዎች” ደግሞ ሀገር በቀል እውቀትንና አዋቂዎችን እየገፈታተርን የመፍትሔ ድምፃቸውም ሆነ የምርምር ውጤታቸው እንዳይገለጥ በምክንያት አልባ ሰበብ እንጋርዳቸዋለን፤ እናጥላላቸዋለን:: ተቃርኖ ይሏል እንዲህ ነው::
የሆነው ሆኖ ከሕዝባችን ቁጥር ጋር ሲነፃፀር ሁለት ከመቶ የሚገመት የክትባት “ዶስ” ደጃፋችን ደርሶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ጥቂት ቀናት ተቆጥረዋል:: የጤና ባለሙያዎቹ እንደሚገልጹልን ከሆነ አንድ ሰው ክትባቱን መውሰድ ያለበት ለሁለት ተከታታይ ጊዜያት ስለሆነ የተገኘው የክትባት “ዶስ” ሊሸፍን የሚችለው ከሕዝባችን ቁጥር አንድ ከመቶውን ብቻ ይሆናል ማለት ነው:: የጨዋ ስሌታችን ጎልድፎ ከሆነ ባለሙያዎቹ ቢያርሙንና ትክክለኛውን መረጃ ቢሰጡን አይከፋም:: እንዲህም ቢሆን እንኳን መች ከፋን! በጅማሮው ሃሌታ ያላመሰገነ በፍፃሜው ስኬት “ሃሌሉያ” ብሎ ሊዘምር ስለማይችል ጥረት አድርገው ይህቺኑ ያህል ተስፋ “ላቃመሱን” መንግሥታችን፣ ለጤና ሚኒስትራችን፣ ለተባባሪ አገራትና ተቋማት ምሥጋናችንና አድናቆታችንን ባንገልጽ ኅሊናችን ይገስፀናል::
የክትባቱ ተቀዳሚ ተጠቃሚዎች የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጭ ዜጎች መሆናቸው በእጅጉ ተገቢና ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑንም በአሜንታ እንቀበላለን:: በኮቪድ ወረርሽኙ የፍልሚያ ሜዳ ውስጥ በነፍሳቸው ተወራርደው እያገለገሉን ላሉት የጤና ባለሙያ ጀግኖቻችን እንደ ካሁን ቀደሙ አድናቆታችንና አክብሮታችን ይድረሳቸው:: ከወንበራችን ከፍ ብለንና ኮፍያችንን አውልቀን አድናቆታችንን መግለፃችንም ይገለጽላቸው:: “ጀረ ኬኛ ገለቶማ!::”
በሁለተኛ ደረጃ ይከተባሉ ተብሎ ዕቅድ የተያዘው “ተጋላጭ ለሆኑ የማሕበረሰብ ክፍሎች” ስለመሆኑም ተደጋግሞ ቢገለጽልንም እነዚያ “ተጋላጮች” እነማን እንደሆኑ በይፋ ስላልተነገረን ግርታ እንዳጋጠመን በአደባባይ ባንገልጽ ደግ አይሆንም:: ለመሆኑ እነዚያ ተጋላጭ የሚል “ትንቢት” የተነገረላቸው የማሕበረሰብ ክፍሎች የትኞቹ ናቸው? የዕለት ጉርሷን ለማግኘት እፍኝ ሽንኩርትና ቲማቲም መንገድ ላይ ዘርግታ በአላፊ አግዳሚው ገበያተኛ ትንፋሽ የምትታጠነው ምስኪን እህት? ወይስ ከኮቪድ ፍርሃት ጋር እየታገሉ ልጆቻችንን በእውቀት ለመመገብ ከሺህ ቡቃያዎቻችን ጋር እየተጋፉ የሚውሉ መምህራንና ራሳቸው ተማሪዎች? በክፍለ ጦር፣ በብርጌድና በሻለቃ ተደራጅቶ ነጋ ጠባ በሰልፍ ላይ የወንድም እህቶቹን ጠረን እየተጋራ “የወታድር እናት ታጠቂ በገመድ ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ” እያለ የሚያንጎራጉረው የሠራዊቱ አባል? ለመሆኑ “ተጋላጭ” የሚል መለያ የተለጠፈለት የማሕበረሰባችን አባል የትኛው ነው?
ይህ ብያኔ በሺህ ሜትሮች ሰልፍ በፀሐይ የሚንቃቁትን የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎችንና ተገልጋዮችን ይመለከታል? በኪነ ጥበባት ውጤቶቻቸውና በሰላ ብእራቸው ሕዝባቸውን የሚያገለግሉትን ከያኒያን፣ ደራስያንና ጋዜጠኞችን ያስታውሳል? በሺህ ዶሴዎች ተከበው ከሺህዎች ጋር ለሚውሉት የፍትሕ ሰፈርተኞችስ ደረስኩላችሁ ይላል? ለፀጥታችን ዋስትና ለመስጠት ውሎ አዳራቸውን በሕዝቡ መካከል ላደረጉ የፖለሲና የፀጥታ አባላትስ ቅድሚያ ይሰጣል? በሺህ ጉዳዮች ሺህ ጊዜ እንድንሰለፍ ደስታቸው የሆነውን የሀገራችንን የቢሮክራሲው ክፍል አባላትንስ ይመለከት ይሆን? ወይንስ “ተጋላጮቹ” እነማን ናቸው? ዝርዝሩን ላልዘልቅበት በከንቱ ነካካሁት መሰለኝ?
እርግጥ ነው ለጊዜው የተገኘው የክትባት “ዶስ” መጠን ከሕዝባችን ቁጥር ጋር ሲተያይ “ከጤፍ አቅም ጉርሶ” እንዲሉ እዚህ ግባ እንደማይባል ይገባናል:: ቢሆንም ግን ለተገኘውም ይሁን ወደፊት ይገኛል ተብሎ በተስፋ ለሚጠበቀው የክትባት እድል “የተጋላጮቹ” ዝርዝር በሚገባ ተብራርቶ ቢገለጽልን አይከፋም:: ዜጎች መጠየቅ አስፈፃሚውም መመለስ እንዳለበት ልብ ይሏል:: ሰሚ ከተገኘ!
ጸሐፊው ግራ የተጋባበት ትዝብት፤
የኮቪድ 19 ክትባት መገኘት ብዙ የዓለም ዜጎችንና መንግሥታትን የደስታ ጮቤ ማስረገጡ እንደተጠበቀ ሆኖ አወዛጋቢነቱም የዚያኑ ያህል እያንጫጫ እንዳለ ይታወቃል:: አንዳንዶች ክትባቱን ከመናፍስት ዓለም ጋር ሲያያይዙት ጥቂት የማይባሉትም ከሴራ ሽረባ ጋር አጣምረው ሲቃወሙ እያደመጥን ነው:: ይህንን ውዥንብር ለማለዘብ ይመስላል በምርምር የተገኙት ክትባቶች በሙሉ የተጀመሩት በየአገራቱ መሪዎችና ታላላቅ ሰዎች ክንድ ላይ ነው:: ነገሩ “እኛ ተከትበን ምን ሆንን? ሃሜቱ የጠላት ወሬ ነው” የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ እንደሆነ ይገባናል:: እያደር ግን ይህ ብርዥ ጥርዥ የሚለው የዓለም ዜጎች ሥጋት እየደበዘዘ ሕዝበ አዳም ለመከተብ እየተሸቀዳደመ እንዳለ እያስተዋልን ነው::
ወደ ሀገራችን መለስ ስንልም ክትባቱን “በማስጀመር ሰበብ” የቅድሚያ እድሉን እየወሰዱ ያሉት እነማን እንደሆኑ በትዝብት እየተጠቋቆምን እንዳለን የገባቸው ስላልመሰለን ሹክሹክታችንን በአደባባይ መግለጡ ለንስሐም ይሁን ለትምህርት ያግዝ ይመስለናል:: ሕዝቡ አልከተብም ብሎ አላንገራገረ፤ አልሆነለትም እንጂ እድል ቢገኝ ሁሉም ዜጋ ለመከተብ ዝግጁነቱን አረጋግጧል:: እውነታው ይህ ሆኖ እያለ “የክትባቱን ሢሶ” ከሚኒስቴር እስከ ዞንናና ቀበሌ ድረስ ያሉ ሹመኛ ግለሰቦችና ካድሬዎች ለምን እንደሚሻሙ ሊገባን አልቻለም::
ልብ ብለን አስተውለን ከሆነ በየቦታው “ክትባት ማስጀመር” በሚል ስንኩል ምክንያት የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ካድሬዎች ለሰልፍ ሲሽቀዳደሙ እየተመለከትን ነው:: በማስጀመሩ ሥነ ሥርዓት ላይ የግድ ቅድሚያውን መውሰድ ያለባቸው “እነ እንቶኔ ብቻ” መሆን ይገባቸዋል:: የግድ አስፈላጊ ከሆነ የማስጀመሩ ሥነ ሥርዓት በታላላቅ የሀገር ሽማግሌዎች፣ በታዋቂ ግለሰቦች፣ በደራሲያንና ከያኒያን፣ በመከላከያ ሠራዊት አባላትና በመምህራን ወይንም በነጋዴዎች ቢጀመር አያምርበትም? እንዲህ ቢሆን “ሢሶ ለነጋሽ፣ ሢሶ ለአንጋሽ፣ ሢሶ ለቀዳሽ” ብሂል በእኛ አውድ ትክክለኛ ትርጉሙን ያገኝ ነበር::
የአንድ ከመቶ የክትባት ግኝት ይህንን ያህል ካጨዋወተን ዘንዳ ለወደፊቱ ትምህርት ተወስዶበት ችግሮቹ እንዲታረሙ ቢደረግ መልካም ይሆናል:: ባለ ሁለት ፓስፖርት “የእምዬ ልጆችም” ሰሞኑን “ሁለት ባላ ትከል አንዱ ቢነቀል በአንዱ ተንጠልጠል” በሚል መርህ ቀድመው ወዳዘጋጁት አገራት ክትባት ለመውሰድ መጉረፋቸውን ሹክ ያለን አንድ ውስጥ አዋቂ ወዳጃችን ነው:: ይሁን ደግ! ለእኛም እግዜሩና “መንግሥታችን” አይጨክኑብንም:: ቢጨክኑብንም ይብላኝ ለእነርሱ እንጂ “ርቀታችንን ጠብቀን፣ በጭንብላችን ተጀቡነን፣ እጃችንን በሳሙናና በሳኒታይዘር እያሽሞነሞንን” ይህንን የክፉ ቀን
“ያጣም ያገኝና ያገኘም ያጣና፣
ያስተዛዝበናል ይሄ ቀን ያልፍና”
በሚል እንጉርጉሮ እናልፈዋልን:: ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን መጋቢት 11/2013