ታምራት ተስፋዬ
ከጥቂት ወራት ወዲህ የሚታየው የሸቀጦችና የተለያዩ ምርቶች ዋጋ ጭማሪ፣ አገሪቱ በታሪኳ ዓይታው የማታውቀው ነው ለማለት ያስደፍራል። ህዝቡ አብዝቶ የሚጠቀምባቸው የዕለት ተዕለት የምግብ ሸቀጦች ዋጋ በሚያስደነግጥ መልኩ ወደ ላይ ንሯል። እንደ ልብ ማግኘትም አዳጋች ሆኗል።
በዓል በተቃረበ ቁጥርም በተለያዩ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረቶችን ማስተዋል ብርቅ አይሆናም። በተለይ በፆም ወቅቶች ምእመናኑ ከእንስሳት ውጤቶች ነፃ የሆኑ ምግቦችን ምርጫቸው ስለሚያደርጉ የአትክልትና ፍራፍሬ ተጠቃሚዎች ቁጥር ይጨምራል፡፡
በፆም ወቅቶችም አብዛኞቹ የአትክልትና ፍራፍሬ መሸጫ ሱቆች በሸማቾች እና ተቀምጠው በሚጠቀሙ ደበኞች ይጨናነቃሉ። የፆሙን እግር ተከትሎም አንዳንድ ነጋዴዎች ወቅቱን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ በምርቶቹ ላይ ጭማሪ ያደርጋሉ። በተለይ በሽንኩርት (ቀይና ነጭ)፣ ቲማቲም፣ ቃሪያ፣ ድንች፣ የጎመን ዓይነቶች፣ ሰላጣ፣ ቆስጣ እንዲሁም ፍራፍሬ አናናስ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ሙዝና ብርቱካን፣ አቮካዶ ጨምሮ ሌሎች ፍራፍሬ ምርቶች ዋጋ ከወትሮው ይጨምራል፡፡
ከቀናት በፊት በተጀመረው አብይ ፆም ያስተዋልነውም ይህው ነው። ሰሞኑን በተለያዩ ገበያዎች ተዘዋውረን ለመጠየቅ እንደሞከርነው፤ በተለይ በአዲስ አበባ የአትክልት እና ፍራፍሬ ዋጋ ጭማሪን አሳይቷል። ያነጋገርናቸው ሸማቾችም በዋጋ ጭማሪው መማረራቸውን ገልፀውልናል፡፡
በሾላ ገበያ ግብይት የሚፈፅሙት ወይዘሮ ትንሳኤ ገመቹ፣ ‹‹ ከጊዜ ወደ ጊዜ የዋጋ ጭማሪ ይታያል። ምርቶቹ በተለያዩ ቀናት የተለያየ ተመን የሚጠየቅባቸው በመሆኑ ከቤት ይዤ ከምወጣው ገንዘብ ጋር የማይመጣጠን ሆኖብኛል፣ የሚጠይቁት ዋጋም ከማስገረም አልፎ አስደንጋጭ ሆኗል›› ይላሉ፡፡
ቀይ ሽንኩርት በኪሎ 16 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት 100፣ ካሮት 45፣ ድንች 18፣ ፎሶሊያ 45፣ ቃሪያ 70፣ ሎሚ 60 በተለይ ቲማቲም እስከ አምስት ብር ጭማሪ ማሳየቱን 19 ብር መግባቱን ይናገራሉ። በተለይ ካሮት ከሳምንት በፊት ከ 25 ብር እስከ 30 ብር ይሸጥ እንደነበር የሚያስታውሱት ወይዘሮ ትንሳኤ፣ አሁን ላይ በኪሎ አርባ አምስት ብር መግባቱን ይጠቁማሉ። ‹‹ሰላጣም በኪሎ ከአስር ብር በላይ ጭማሪ በማሳየት 60 ብር ገብቷል›› ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መዝናኛ ክበብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳኛቸው አንሳ፣ ከፆም በፊት እና በኋላ አትክልት እና ፍርፍሬ ምርቶች ዋጋ ከፍተኛ ጭማሬ እንዳሳየ ይገልፃሉ። ኪሎ ግራምን የመለኪያ መስፈርት በማድረግ የምርቶቹ ዋጋ ልዩነት ሲገልፁም፣ ጥቅል ጎመን ከ 9 ወደ 16፣ ዓሣ ከ 70 ወደ 120፣ ሱፍ ከ42 ወደ 65፣ ቲማቲም ከ 8 ወደ 16፣ ቃሪያ 45 ወደ 80፤ ሽንኩርት ከ10 ወደ 16፣ ካሮት ከ15 ወደ 45፣ ቀይስር ከ12 ወደ 18፣ ድንች ከ 12 ወደ 17፣ ፎሶሊያ ከ 20 ወደ 40፣ የፉል ባቄላ ከ40 ብር ወደ 60 ብር፣ ምስር ከ60 ወደ 85፣ ድፍን ምስር ከ40 ወደ 60፣ ሽሮ ከ80 ወደ 110፣ ፣ በርበሬ ከ110 ወደ 170 ብር ጭማሪ አሳይቷል በማለት ዘርዝረው ይናገራሉ፡፡
የአትክልት ዋጋ ከወትሮው ለምን እንደናረ የጠየካቸው አቶ ሀብታሙ ከፍያለው የተባሉ ነጋዴ በአንፃሩ ጭማሪው የምርት እጥረት በመኖሩና የፆም ወቅት በመግባቱ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ከመናገር ውጭ ትክክለኛ ምክንያቱን እነሱም እንደማያውቁት ገልፀው፣ ዋጋውም ሸማቹን ብቻ ሳይሆን ነጋዴውንም የሚያሳቅቅ እንደሆነ ነው የሚገልፁት፡፡
ሌላኛዋ ነጋዴ ወይዘሮ ትብለፅ ሃጎስ ደግሞ አትክልትና ፍራፍሬ በፆም ወቅት ፈላጊው ብዙ ነው። በመሆኑም ከቦታ ቦታ የጥራትና የዋጋ ተመኑ ተመሳሳይ እንዳልሆነ ትገልፃለች። ‹‹ገበሬው በስፋት ሲያመርት የዋጋ ቅናሽ ይኖራል፣ የምርት እጥረት ሲያጋጥም ደግሞ ይወደዳል›› የምትለው ወይዘሮ ትብለፅ፣ ከምርት እጥረት ጋር ተያይዞ ነጋዴው ከገበሬው በውድ ዋጋ ስለሚገዛ እና ሌሎች ወጪዎቹንም ደምሮ ለሸማቹ ስለሚያቀርብ የመሸጫ ዋጋው ከፍ እንደሚል ታስረዳለች፡፡
ወይዘሮዋ ትንሳኤ በሌላ በኩል የዋጋው ጭማሪ ‹‹እጥረት ተፈጥሮ ነው›› እንደማያስብል ይገልፃሉ። ከአዲስ አበባ በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ክልል ውስጥ የተመረቱ ምርቶች፣ አዲስ አበባ ሲገቡ ሁለት እና ሦስት እጥፍ መጨመራቸው፣ የምርት አቅርቦት ሳይሆን ያለአግባብ የመክበር መሻት ውጤት እና የግብይት ሥርዓቱ ቅጥ አንባሩ መጥፋት ስለመሆኑም ይናገራሉ፡፡
አቶ ዳኛቸው አንሳ የወይዘሮ ትንሳኤን ሃስብ ይጋሩታል። ከሁሉ በላይ መንግሥት ነፃ ገበያ የሚለውን አባባል በመተው፣ ገበያውን ለማረጋጋት ጣልቃ ገብቶ የዋጋ ተመን ከማውጣት ጀምሮ ነጋዴውን መቆጣጠር እንዳለበት ነው አጽዕኖት የሰጡት። የችግሩ ዋነኛ ገፋች ቀማሽ የሆነው ህዝብም ገበያውን ለማረጋጋት ህገወጦችን ከማጋለጥ እና በተለያዩ ድጋፎች ከመንግሥት ጎን መቆም እንዳለበት ሳይጠቁሙ አላለፉም።
በኢትፍሩት ሲገበያዩ ያገኘናቸው ሸማቾች፣ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡላቸው መሆናቸውን ገልፀው ሆኖም ግን ሁሉም አትክልቶች በየጊዜው ስለማይቀርብ አስቦ ወደ ገበያው ቦታ የሚሄድ እንደሌለ ይገልፃሉ። አጋጣሚ እግር የጣለው ሰው ያገኘውን ገዝቶ እንደሚሄድ ነው የተናገሩት።
በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ እና ንግድ ሚንስቴር ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉት አካላትን ለማነጋገር ብንሞክርም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ማካተት አልቻልንም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2013