መርድ ክፍሉ
የሰው ልጅ አንዱ በሌላው ላይ ጥገኛ ነው። እንደ ሰው ልጅ በዓለማችን አንዱ ከሌላው ፈላጊ የሆነ ፍጡር አይገኝም። አንድሰው በጫካ አለያም በዋሻ ተገልሎና ፍራፍሬ እየተመገበ ከዱሩ ሳይወጣ የሚኖር ካልሆነ በስተቀር በከተማ ወይም በመንደር ኑሮ መስርቶ ያለ ሌሎች እገዛ ፈፅሞ መኖር አይችልም። ማኅበራዊ ሕይወት ከውልደት እስከ ሞት የሚኖር እና ቀጣይነት ያለው ሂደት ሲሆን በትምህርት እና ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት የሚዳብር ነው። የሰው ልጅ ስለራሱ እና ስለሚኖርበት ማኅበረሰብ የሚኖረውን ዕውቀት በተለያየ መልኩ ማለትም የመግባቢያ ቋንቋ በመማር፤ አካባቢያዊ ሁኔታውን በመመልከት እንዲሁም ማኅበራዊ ክህሎቶችን በመማር እያሳደገ ይሄዳል። ይህ የማኅበራዊ ሕይወት ክህሎት በአግባቡ መዳበር ለተሟላ ስብዕና እና ዕድገት ወሳኝነት አለው፡፡
አገር መውደድ ማለት ጥልቅ ትርጉም አለው። አገር ማለት ሕዝብ፤ ሕዝብም ማለት አገር ነው። አገርና ሕዝብ የማይነጣጠሉ አንዱ ከአንዱ ትርጉም የማይኖረው እጅግ የተቆራኙ ነገሮች ናቸው። አገር መውደድ ማለት ሕዝብን መውደድ፣ ሕዝብን ማገልገል፣ ለሕዝብ መሞት፣ ለሕዝብ መጎዳት ማለት ነው። አዎ አገር ወዳድ ዜጋ ማለት ራሱን ለብዙኃኑ ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ፣ ብዙኃኑም ስለአንዱ የሚገዳቸው ማለት ነው። ይህ ነው የአገር ፍቅር፤ ይህ ነው የሕዝብ ፍቅር ማለት።
በብዛት ወጣት ከሚገኝባቸው አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት። በኢትዮጵያ ታዲያ ወጣቱ ክፍል ከመስራትና አገርን ከማሳደግ ይልቅ ባልባሌ ትርክቶች ተጠምዶ እርስበእርስ ሲጋጭ ማስተዋል ከተጀመረ ዋል አደር ብሏል። በአገሪቱ የሚሰራ ሥራ ጠፍቶ ሳይሆን አለመስማማቶች በመበራከታቸው የሚሰሩ እጆች ለጥፋት እየዋሉ ይገኛሉ። በመንግሥትም ደረጃ ጠንከር ያሉ ሥራዎች ባለመከናወናቸው ዝርፍያና ቅሚያ በከተሞች አካባቢ እየተስፋፋ ይገኛል፡፡
ይህን ጉዳይ ያለ ምክንያት አይደለም ያነሳሁት። ለጥፋት የሚውሉ እጆች እንዳሉ ሁሉ ለበጎ ተግባራት የሚሰነዘሩ እንዳሉ ለማሳየት ፈልጌ ነው። የተቸገሩ አረጋውያንንና የጎዳና ተዳዳሪዎችን የሚደግፉና አለንላችሁ የሚሉ በርካታ በወጣቶች የተመሰረቱ ማህበራት እንዳሉ በዚሁ አምዳችን አስቃኝተናችሁ ነበር። አብዛኛዎቹ ማህበራት እውቅናና ፈቃድ አግኝተው እርዳታ በማሰባሰብ ድጋፍ የሚያደርጉ ናቸው።
በቅርቡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ለከፍተኛ የኑሮ ጫና መዳረጋቸው ይታወሳል። ይህንን ክፉ ጊዜ ለማለፍ ደግሞ የደጋግና ቅን ልቦች መኖር ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን ስንመለከት የመረዳዳት ባህላችን ዛሬም ጠንካራ መሆኑን እንገነዘባለን። ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ በወጣቶች ስለተቋቋመው እንደራሴ ምግባረ ሰናይ ማህበር እንቃኛለን። የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ወጣት ዳግማዊ ቀማው ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ማህበሩን መስርቷል። ከወጣት ዳግማዊ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተው አቅርበነዋል፡፡
እንደራሴ ምግባረ ሰናይ ማህበር ታኅሣሥ 29 ቀን 2011 ዓ.ም ለበጎ ተግባር በተነሳሱ 15 ወጣቶች የተመሰረተ ነው። ይህም የሆነው በአካባቢው በፕላስቲክ ቤት ተጠልሎ የነበረን ወጣት በመርዳት ነው። በወቅቱ ከወጣቱ ጋር በዓልን ለማክበር በተኬደበት ወቅት ማህበር ለመመስረት ሀሳብ መጣ። አስራ አምስት ወጣቶች በመሆን በጎ ሥራ ለማከናወን ህብረት ተፈጠረ።
ማህበሩ ያከናወናቸው ተግባራት
ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ የተለያዩ ሥራዎችን አከናውኗል። የገቢው ምንጭ ከማህበሩ አባላት የሚሰበሰበው ወርሃዊ መዋጮ ሲሆን አቅም ያላቸው ሃያ ብር ሲያዋጡ አቅም የሌላቸው ደግሞ አስር ብር እንዲያዋጡ ይደረጋል። በሚሰበሰበውም ገንዘብ በአካባቢው የሚገኙ አቅመ ደካማ እናቶችን ቤት ማደስ፣ በአካባቢው የምትገኝ የኩላሊት ህመምተኛ የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራ ማከናወንና የእምነት በዓላት በሚሆኑበት ወቅት የገቢ ማሰባሰቢያ የማድረግ ሥራ ተከናውኗል። ሌላው በተያዘው ዓመት መስከረም ወር እቅድ ተይዞ ሲሰራ የነበረው ለሦስት እናቶች ቋሚ የቀለብ አቅርቦት እየተከናወነ ነው። ሦስቱ እናቶች የተመረጡት ምንም ዓይነት ደጋፊና የገቢ ምንጭ የሌላቸው መሆናቸው ተረጋግጦ ነው፡፡
በቋሚነት ድጋፍ ከሚደረግላቸው ውስጥ አንድ አካል ጉዳተኛ አሉ። ሌሎቹ ደግሞ ከሦስት እስከ አምስት ቤተሰብ ያላቸው ናቸው። ለነዚህ ሦስት ቤተሰቦች ዱቄት፣ ሩዝ፣ ማካሮኒ፣ በርበሬ፣ ዘይትና ሳሙና በየወሩ እንዲሰጣቸው ይደረጋል። በተጨማሪም የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላት ሴት ያለች ሲሆን የቤት ኪራይዋን እንድትሸፍን በየወሩ ማህበሩ አንድ ሺህ ብር ይሰጣል። ሥራዎች የሚሰሩት ከአባላት በሚገኝ መዋጮ ነው።
ሌላው ‹‹ምሳን ከወገን ጋር መጋራት›› በሚል በየሦስት ወሩ የሚዘጋጅ መርሃ ግብር አለ። እስካሁን መርሃ ግብሩ ሦስት ጊዜ ተከናውኗል። በዚህ መርሃ ግብር አልባሳትን ከየሰዉ በመሰብሰብና የምግብ መዓድ በማዘጋጀት ድጋፍ ለሚሹ ሰዎች አልባሳቱ ይሰጣሉ። በተጨማሪ አልባሳቶቹ በጎዳና ላይ ለሚገኙ አረጋውያን፣ ሕፃናት እንዲሁም ለወጣቶች እንዲሰጥ ይደረጋል። መዓድ ማጋራቱ ሲጀመር መቶ ሰዎችን በመመገብ ነበር በአሁኑ ወቅት ግን ከሁለት መቶ በላይ ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎችን የመመገብ ሥራ ተከናውኗል፡፡
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት በየአካባቢው ጀሪካኖችን በማስቀመጥ የእጅ ማስታጠብ ሥራ ተከናውኗል። ነገር ግን አንዳንድ ቦታዎች ጀሪካኖች የማንሳት ሁኔታዎች ነበሩ። በወቅቱ ሳሙናና ሳኒታይዘር በማዘጋጀት ኅብረተሰቡ እንዲጠቀምበት ተደርጓል። በታክሲ ተራ ቦታዎች ላይ ርቀት መጠበቂያ መስመሮችን የመስራት ሥራም ተከናውኗል። በተጨማሪም አቅም ለሌላቸው የፊት ጭንብልና ሳኒታይዘር ቤት ለቤት እንዲሰጥ ተደርጓል።
የተለያዩ በዓላትን ምክንያት በማድረግ አቅመ ደካማ ለሆኑ ግለሰቦች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል። ማህበሩ በሚገኝበት አካባቢ ለሚገኙ ሁለት አቅመ ደካማ እናቶች የቤት እድሳት የተደረገ ሲሆን በተለያዩ ቦታዎች በርካታ ችግኞችን እንዲተክሉ ተደርጓል። በመቀጠል ማህበሩ በተሻለ መልኩ ለመንቀሳቀስ፣ ለመስራት እና የኢኮኖሚ አቅምን ለማሳደግ ማድረግ በሚገቡ ተግባር ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን በሀገር በቀል የሲቪል ማህበርነት ለመመዝገብ በጠቅላላ ጉባኤ በወሰነው መሠረት ለሲቪል ማህበራት ማደራጃ ኤጀንሲ በማመልከት ኤጀንሲውም ማህበሩ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች ከገመገመ በኋላ ጥቅምት 20 ቀን 2012 ዓ.ም ማህበሩ ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ማህበር በማለት የሕጋዊነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬቴ ተሰጥቶናል።
በኩላሊት ህመም ምክንያት ህክምና ላይ ለሚገኝ ወጣት የገቢ ማሰባሰቢያ በማዘጋጀት ከዝግጅቱ የተገኘውን ገንዘብ ለግለሰቡ ህክምና እንዲውል ተደርጓል። ሁለት ሕፃናትን ለብቻዋ የምታሳድግ እና የኢኮኖሚ ችግር ያለባትን አንድ እናት በማህበሩ ስር በመያዝ እስከ ዓመቱ መጨረሻ በየወሩ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል። ዓለም አቀፍ በሆነ መልኩ የተከሰተውን ኮሮና ቫይረስ ለመከላከል 40 ለሚሆኑ ግለሰቦች የአልኮል እና የማስክ ድጋፍ ሲደረግ በተጨማሪም በተለያዩ ቦታዎች የእጅ መታጠቢያ በርሜሎችን የማስቀመጥ እና በትራንስፖርት ቦታዎች ላይ የርቀት መጠበቂያ መስመሮችን መስራት ተችሏል።
ማህበራችን በሚገኝበት አካባቢ የሚገኙ አቅመ ደካማ የሆኑ እና አነስተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸውን አራት ግለሰቦችን በመለየት የቀለብ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል። በአነስተኛ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ቤተሰብ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሕፃን በተሻለ የትምህርት ተቋም እየተማረ ነው። በጎዳና ለሚኖሩ ወገኖቻችን በያዝነው ዓመት ውስጥ በሦስት ዙር አልባሳት የማልበስ እና ምግብ የመመገብ ሥራን ያከናወንን ሲሆን በዚህ ሥራ 500 የሚሆኑ ግለሰቦች ተጠቃሚ ሆነዋል። ማህበሩ በሚገኝበት አካባቢ የሚገኙ በሱስ የተጠቁ ሥራ አጥ ወጣቶችን በማወያየት ከሱስ የሚላቀቁበትን እና ሥራ የሚያገኙበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ ነው። የአዕምሮ ችግር ያለበትን ወይም ያለባትን ግለሰብ በጉዳዩ ላይ ከሚሰሩ ባለሙያዎች ጋር በማገናኘት ጤናቸው የሚስተካከልበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ ነው።
የኅብረተሰቡ አቀባበል
ኅብረተሰቡ ጥሩ ድጋፍ ለማህበሩ የሚያደርግ ሲሆን በገንዘብ፣ በጉልበትና በሀሳብ አስተዋፅኦ ያደርጋል። ማህበሩ በሚሰራቸው ሥራዎች ኅብረተሰቡ በጣም ደስተኛ ነው። የማዕድ ማጋራት በሚከናወንበት ወቅት በአካባቢው የሚገኙ እናቶች እገዛ ያደርጋሉ። በኮሮና ወረርሽኝ ወቅትም ሲሰሩ በነበሩ ሥራዎችም ኅብረተሰቡ ከፍተኛ እገዛ ሲደርግ ነበር። ሳሙናና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመግዛት ያበረክቱ ነበር። በአሁኑ ወቅት ኅብረተሰቡ ወረርሽኙ ላይ እያሳየ በመጣው ቸልተኝነት የእጅ መታጠቡ ሥራ እየቀነሰ መጥቷል።
ማህበሩን ያጋጠሙ ችግሮች
እነዚህን የበጎ አድራጎት ተግባራት በተሻለ መልኩ ለማከናወን ከገጠሙ አክሎች መካከል ከማህበሩ ድጋፍ የሚፈልጉ እንዲሁም ማህበሩን ለመደገፍ የሚፈልጉ ግለሰቦችን ተቀብሎ ለማነጋገር ቢሮ አለመኖር፣ የገንዘብ እጥረት እና የቁሳቁስ እጥረት በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው። ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ የተለያዩ ችግሮች አጋጥመውት ነበር። የመጀመሪያው ያጋጠመው ችግር የመሰብሰቢያ ቦታ እጥረት ነበር። ማህበሩ በየጊዜው ሲሰበሰብ በየሰው ቤት ውስጥ ነው። የአባላት መዋጮም በሰብሳቢው ቤት በመሄድ የሚከናወን ነው። ማዕድ ማጋራት በሚከናወንበት ወቅት አልባሳት ሲሰበሰብ ማህበሩ እውቅና የለውም በሚል ችግሮች ያጋጥሙ ነበር። ነገር ግን ማህበሩ ፈቃድ ያወጣበትን ወረቀት ይዞ ስለሚንቀሳቀስ ችግሮቹን እዚያው ለመፍታት ይሞከር ነበር፡፡
ደጋፊ የሚፈልጉ ብዙ ተረጂዎች ያሉ ሲሆን ማህበሩ ገና ወደ ሥራ እየገባ የሚገኝ በመሆኑ ለሁሉም መድረስ አልተቻለም። አብዛኛው ሰው በሀሳብና በእውቀት ነው እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው። የማህበሩም የገንዘብ አቅም ዝቅ ያለ ስለሆነ እቅዶችን በደንብ መተግበር አይቻልም። በአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች በደባል ሱሶች የተጠቁ ሲሆን ወጣቱ ከዚህ እንዲወጣ ለማስቻል እንቅስቃሴ አለ። ወጣቱን እራሱን እንዲችል ለማድረግ የገንዘብ እጥረት አለ፡፡
የማህበሩ ቀጣይ እቅድ
ማህበሩ በቀጣይ ያለበትን የቢሮ ችግር ለማቃለል መስራት ይፈልጋል። በቀጣይ በሚደረገው የማዕድ ማጋራት ሥራ ውስጥ አልባሳትን በማሰባሰብ ድጋፍ የማድረግ ሀሳቦች አሉ። የተወሰኑ ወጣቶችን ካሉበት ደባል ሱስ አላቆ ሥራ እንዲያገኙ የማድረግ እቅድ አለ። በትምህርት ዙሪያ ደግሞ በግል ትምህርት ቤቶች በነፃ የሚማሩ ማህበሩ የሚደግፋቸው ልጆች ያሉ ሲሆን ተማሪዎቹ አስፈላጊው ግብዓት እንዲሟላላቸው እየተደረገ ይገኛል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2013