“ጠንካራ የፈተና ዝግጅት ሥራ በመሠራቱ ፈተናው በውጤታማነት ይጠናቀቃል” እሸቱ ከበደ (ዶ/ር)

እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር

በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያየ መንገድ ፈተናዎች ይሰጣሉ። እነዚህ ፈተናዎች ደግሞ የቀጣይ እድልን በመወሰን በኩል ፋይዳቸው አይተኬ ነው። በቀጥታ በሥራ ለመሰማራት ያስችላል:: በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችም ገብተው ክህሎታቸውን እንዲያበለጽጉ ያግዛል። ፈተና እንደ መንጃ ፈቃድ ያሉ ሥልጠናወችን ለመውሰድም ሁነኛ መሸጋገሪያ ነው:: ለ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ደግሞ ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲመደቡና የከፍተኛ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚያደርጋቸው የቀጣይ እጣ ፋንታቸው መወሰኛ ነው። ከዚህ አንጻርም ከፈተናው ዝግጅት ጀምሮ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት እንደሚገባ እሙን ነው።

የእኛ ትኩረት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሲሆን ምን ምን አይነት ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሆኑ ከትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ጋር ቆይታን አድርገናል። እርሳቸው እንዳሉት፤ ፈተናው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው። የብዙ ዜጎችን የቀጣይ ሕይወት ይወስናል:: በዚህም እንደ ሀገር በርካታ ሥራዎች በትኩረት ተከናውነውበታል። ባለፉት ዓመታት በተደረጉ የፈተና ሥርዓት ውስጥ ሕዝብን የሚስቡ ሀሳቦች ተፈጥረዋል። ትኩረት የሚስቡ በርካታ ሁኔታዎችም ታይተዋል።

በፈተና ሂደቱ ውስጥም የተለያዩ ተግዳሮቶች ማጋጠማቸው አይረሳም። ሲፈትኑን የቆዩ ሁኔታዎች ነበሩ:: ለአብነት የፈተና ስርቆት እና የፈተና ኩረጃ በዋናነት ይጠቀሳሉ::ስለዚህም አገልግሎቱ እነዚህ ተግዳሮቶች የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተጽዕኖ በመለየት እንደ ሀገር ሶስት መሰረታዊ የሚላቸውን ተግባራት በትኩረት እንዳከናወነ ያነሳሉ::

አንዱ ረጅም ጊዜ ወስዶ እና ብዙ ገንዘብ ፈሶበት የተዘጋጀን ፈተና የመሰረዝ እርምጃ ነው። ይሄ ሀገርን እና ኢኮኖሚውን በብርቱ የጎዳ እና ለክስረት የዳረገ አሳዛኝ ክስተት ነበር:: ፈተናውን በሚወስዱና ብዙ ዝግጅት ባደረጉ ተማሪዎች ዘንድም የፈጠረው ጫና በቃላት ሊገለጽ የሚችል አይደለም። ብዙዎቹ ላይ ሥነ ልቦናዊ እና አእምሯዊ ጫና እንዳሳደረባቸው ይገልፃሉ:: በወላጆችና በማኅበረሰቡ ላይም ተመሳሳይ ጫና ስለማስከተሉም ያወሳሉ:: የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ ዘርፉም ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል እንዳልነበረ ያስረዳሉ::

ጥራት እርካታን ብቻ ሳይሆን ስኬትን የሚያጎናጽፍ በሁሉም ዘርፍ ውስጥ ሊኖር የሚገባው ቢሆንም ለሁሉም ሙያ ዘርፎች መሰረት የሆነው ፈተና ነው። ስለዚህም በመሰረታዊነት በልዩ ትኩረት ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ያነሳሉ::

ሌላው በዚሁ በፈተና ጉዳይ ላይ ተወስዶ ነበር ያሉት እርምጃ ድጋሚ ፈተናውን እንዲወስዱ የተደረገበትን አማራጭን ነው። ይህም እንደ መጀመሪያው ከባድ የሚባሉ ችግሮችን በሁሉም ላይ ፈጥሮ ያለፈ ነው። ለአብነት አገልግሎቱ ድጋሚ ጥያቄ ከማዘጋጀት ጀምሮ ያለው ውጣ ውረድ ዘርፉን ለተመሳሳይ ጫና ከከተቱት መካከል ስለመሆኑ ይናገራሉ::ተማሪውና የተማሪ ወላጆችም እንዲሁ በብዙ የተጨነቁበት እንደነበረ አልሸሸጉም።

ሦስተኛው የመፈተኛ ቦታዎች መቀየር ርምጃ ሲሆን፤ ሁሉም በየደረጃው ተፈትኖበት ያለፈ እንደነበር ጠቅሰው፤ አሁን እነዚህ ችግሮች ዳግም እንዳይፈጠሩ ለማድረግ አገልግሎቱ በትኩረት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ያስረዳሉ። ከዝግጅቶቹ መካከልም የመፈተኛ ቦታ መረጣ አንዱ ሲሆን ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች፤መምህራን ማሰልጠኛዎች፤ አዳሪ ትምህርት ቤቶች፤ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች፤ የግል ትምህርት ቤቶች ለመፈተኛነት ከተመረጡ ሥፍራዎች ውስጥ እንደተካተቱ ይጠቅሳሉ::

ፈተናው በበይነ መረብ የሚሰጥ በመሆኑም ተማሪዎች በበኩላቸው መፈተኛ ኮምፒውተሮች እና መሰረተ ልማቶቹ ባሉበት ቦታዎች እንደሚፈተኑ ለማድረግ እየተሠራ ስለመሆኑም ያመላከታሉ። ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲን ኮምፒውተርን ተጠቅመው ያለምንም ችግር ፈተናቸውን እንዲወስዱ ለማድረግም አገልግሎቱ በተለይ ከተማ ላይ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ዝግጁ እንዲሆኑ የማድረጉን ሥራ አጠናቋልም ይላሉ:: ተማሪዎቹ ከዚህ ቀደም ትምህርት ሲማሩ በነበረበት ቦታ ላይም እየተመላለሱ ፈተናውን እንዲወስዱ ምቹ ሁኔታ ስለመፈጠሩም ይናገራሉ::

እንደ እሸቱ (ዶ/ር) ማብራሪያ፤ አሁኑ ላይ አገልግሎቱ ለዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተና የመፈተኛ ቦታ ቀይሮ የመፈተን እና ፈታኞችን እና ሌሎችን ፈተና የሚያስተዳድሩትን ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል አዛውሮ ለመሥራት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ተማሪዎች ባሉበት ሆነው የፈተናውን ስርቆትና ኩረጃ በሚቀንስ መልኩ በበይነ መረብ ፈተናውን እንዲወስዱ ማድረግ ዘለቄታዊነት ያለው መፍትሄ በመሆኑ አሁናዊ ከሆነው የፈተና ዝግጅት ሥራ ባሻገር በዚያ ጉዳይ ላይም በትኩረት እየሠራ ነው::

የ12ኛ ክፍል ፈተና የበይነ -መረብ አሰጣጥ እርምጃ ሥርዓት ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በወረቀት ከሚሰጠው ፈተና ጎን ለጎን መተግበር መጀመሩን የጠቀሱት ዋና ዳሬክተሩ፤ በፈተና አሰጣጥ ዙሪያ የሚገጥሙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ያስቻለ እንደሆነም ያነሳሉ:: የመሰረተ ልማት ሥራን እና የኮምፒውተሮች አቅርቦትን አጠናክሮ በመቀጠል በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችል መሰረት ውስጥ ለመግባትም መደላድል ሆኖ እያገለገለ ስለመሆኑም ያወሳሉ::

ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ ዘመኑ ዓለም በፈጣን የቴክኖሎጂ እድገት ውስጥ የገባችበት ነው:: የዓለም ሕዝቦች ከዚሁ ቴክኖሎጂ ፍጥነት ጋር በጋራ እየተራመዱ ናቸው። እኛም በዚያ ልክ እንድንጓዝ ብርቱ ሥራን ይጠይቀናል:: በተለይም ተማሪዎችን ተወዳዳሪ ለማድረግና ዘመኑን የዋጁ ለማድረግ ግድ የትምህርቱ ዘርፍ ቴክኖሎጂውን መረዳትና ከእርሱ ጋር አብሮ መጓዝ ይኖርበታል። የትምህርት ፍትሃዊነትን እና ተደራሽነትን ለማረጋገጥም ከዚህ ውጪ አይቻልም።

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እንቅፋት ከሆኑ ተግዳሮቶች ደግሞ የፈተና ኩረጃ እና የፈተና ስርቆት ዋንኞቹ ናቸው:: እነዚህን ጉዳዮች የማያዳግም ታሪክ አድርጎ የሚያስቀር ዘላቂ የፈተና አሰጣጥ ሥርዓት ደግሞ በበይነ-መረብ የሚሰጥ ፈተና ነውና እርሱን በተጠናከረ መልኩ ማስኬድ ላይ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ ዋና ዳይሬክተሩ እሸቱ (ዶ/ር) ያስረዳሉ ::

የበይነ- መረብ ፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱ ዘንድሮም ይቀጥላል:: ጎን ለጎንም በወረቀት ፈተናው እንዲሰጥ ይደረጋል:: በወረቀት የሚሰጠው ፈተና ቁጥሩ እየቀነሰ በበይነ መረብ የሚሰጠው ፈተና ደግሞ ቁጥሩ እየጨመረ እንዲሄድም ይተጋልም ብለዋል:: ከዚህ አንጻርም ዘንድሮ በበይነ- መረብ ፈተናውን የሚወስዱት ተማሪዎች ቁጥር ከ304 ሺህ 50 በላይ (ወይም ከአጠቃላይ ተፈታኞቹ ከግማሽ የበለጠ) መሆኑ አመላክተዋል።

አሁን ላይ ይሄንን መሰረት በማድረግ እንደ አገልግሎቱ ከ608 ሺህ 100 ተማሪዎች በላይ ምዝገባ አካሂዶ የፈተና ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ለመሥራት ተችሏል:: ፈተናውን በበይነ – መረብ እና በወረቀት ለመውሰድ ከተመዘገቡት ከ608 ሺህ 100 ተማሪዎች መካከል ከሌሎች ዓመታት በተለየ መልኩ የተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ተፈታኞች በቁጥር በልጠው እንደሚገኙ አብራርተዋልም::

በዘንድሮ የፈተና ዘመን በወረቀት ፈተናውን የሚፈተኑት ተማሪዎች መሰረተ ልማት ያልተሟላባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሲሆኑ፤ ኮምፒውተር እና ኢንተርኔት ኮኔክሽን በበቂ ያላገኙም እንዲሁ ፈተናውን በወረቀት እንዲወስዱ እንደሚደረጉም ያነሳሉ:: ለዚህም በየክልሉ ያሉ ጉድኝት ኃላፊዎች፤የፈተናውን ሥራ የሚሠሩ ሱፐርቫይዘሮች፤ ፈታኞች፤ ጣቢያ ኃላፊዎች እንዲሁም ማእከል ኃላፊዎች ምልመላ ተጠናቋል፤ ምደባም እየተከናወነ ይገኛል ሲሉም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል::

እንደሳቸው ከሆነ፤ አማራ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በወቅቱ ትምህርት ያልተማሩ ተማሪዎች ፈተናውን እንደማያይወስዱ ታውቋል:: ክልሉ እያደረገላቸው ባለው ልዩ ድጋፍ ተምረው የጨረሱት አሁን ከሚፈተኑት ጋር ፈተናውን እንዲወስዱ በማድረጉ ረገድም አገልግሎቱ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ እና ከትምህርት ሚኒስቴር አመራሮች ጋር በጋራ እየሠራን ይገኛል:: ትምህርት የጀመሩና ለፈተናው ያልደረሱትን ጉዳይ አስመልክቶም ቢሆን አገልግሎቱ ዝም አላለም፤እንዲሁ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር እየተመካከረ የሚገኝበት ሁኔታ አለ።

ፈተናው ከሰኔ 23/2017 ጀምሮ የሚሰጥ ሲሆን፤ ሰኔ 23/2017 የሚጀምረው የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ይሆናል። በቀጣይነት የሚሰጠው ደግሞ የማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት መስክ ፈተና ነው::ፈተናው ሐምሌ 8/2017 ቀን ይጠናቀቃልም ሲሉ ነው የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ::

ከፈተናው ይዘት ጋር አያይዘው እንዳነሱትም ፈተናው ተማሪዎቹ የተማሩበትን ፤እጃቸው ላይ ያለውን መጽሐፍ መሰረት ያደረገ በመሆኑ ተፈታኞቹ ካላስፈላጊ ጭንቀትና ፍርሃት መቆጠብ እንዳለባቸው አሳስበው፤ ማጣቀሻ መጽሐፍትን ታሳቢ ማድረጉን መዘንጋት እንደሌለባቸው አስረድተዋል። በተጨማሪም ውድድሩ እንደቀድሞው የሚማሩበት ትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን ሀገር አቀፍ ካለው ተማሪ ጋር በመሆኑ ከፍርሃት ወጥተው በጥበብ ለመሥራት መትጋት ይኖርባቸዋል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::

የተፈታኞች የበይነ- መረብ አጠቃቀም፤ የመብራት መቋረጥ፤ የኢንተርኔት መቆራረጥ ክፍተት ሊሆን የመቻሉን ጉዳይ አስመልክተውም አገልግሎቱ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አንስተዋል:: አክለውም የበይነ መረብ-አጠቃቀምን ችግር ለመፍታት ከማእከል እስከ ክልል ዞን እና ወረዳ እንዲሁም ታች ትምህርት ቤት ድረስ ችግሩን የሚፈታ የአሰልጣኞች ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰዋል:: ተፈታኞቹ አሁን ላይ ይሄን ችግራቸውን የሚፈታ ልምምድ እያደረጉ ስለመሆኑም አብራርተዋል::

ሁሉም የበይነ -መረብ መፈተኛ ጣቢያዎች ጀነሬተር እና ችግሩን መፍታት የሚያስችል ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው የኮምፒውተር አቅርቦቶች ተዘጋጅተዋል:: የትኞቹም ችግሮች ቢፈጠሩ ከሁለት እስከ ሦስት ሰዓት የዘለቀውን የተማሪ ሰዓት አይነኩምም ብለዋል::

ፈተናውን ለመኮረጅም ፤ ለመስረቅም ሆነ ለማሰረቅ በተለያየ አጋጣሚ የፈተናውን ደህንነት ጉዳት ላይ ለመጣል፤ ኢ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ቀድሞ መረጃ ለማግኘት ያልተገባ የፈተና ውጤት ለማስመዝገብ በተጨማሪም ሌላኛው እንዳያገኝ፤ አጠቃላይ ሥርዓቱን ለመረበሽ የሚደረጉ ተግባራት ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጸው፤ ይህ እንዳይሆን በአገልግሎቱ በኩል ጠንካራ ሥራ እየተሠራ በመሆኑ እንደ አገልግሎት ፈተናው በውጤታማነት ይጠናቀቃል ብለው እንደሚያምኑና ማንኛውም ሰው ስጋት እንዳይገባው ሲሉም አብራርተዋል። መልካም የፈተና ዝግጅት ጊዜ!

በሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You