ዓለም እንደምን ሠለጠነች?

ዓለም የሚለው ቃል በሰባቱም አህጉራት ያሉትን ሀገራት ያካተተ፣ በአጠቃላይ በምድር ላይ ያሉ ነገሮች በሙሉ ማለት ነው። ዓለም አቀፍ ሲባል በምድር ላይ ያሉ ነገሮችን ሁሉ ያቀፈ ማለት ነው። ያም ሆኖ ግን ዓለም አቀፍ የሚለውን ቃል የምንጠቀመው ለዓለም ሀገራት ግንኙነት ነው። በሁሉም ሀገራት የሚዳረስ ነገር ማለት ነው።

አገላለጹ በእንግሊዘኛ ሲሆን፤ አማራጮች አሉት። ‹‹Global›› እና ‹‹International›› በሚል ይገልጹታል። በአማርኛ ሁለቱንም ዓለም አቀፍ ብለን ነው የምንገልጸው። የእንግሊዝኛው ግን ልዩነት አለው። የመጀመሪያው(Global) ሲሆን፤ ሁሉንም በዓለም ላይ ያሉ ነገሮች የሚገልጽ ነው። ለምሳሌ፤ የሙቀት መጠን መጨመር በሁሉም የዓለም ክፍል እያሰጋ ስለሆነ ‹‹Global Warming›› ተብሎ ይገለጻል። በአማርኛ ሲሆን “የዓለም የሙቀት መጠን መጨመር” እንለዋለን።

ሁለተኛው(International) ሲሆን ግን በምድር ላይ ያሉ ነገሮችን ሁሉ ሳይሆን በሀገራት መካከል የሚደረግ ግንኙነት ይሆናል። የግንኙነቱ ሀገራት ብዙም፣ ትንሽም ሊሆኑ ይችላሉ።

በብዙ አጋጣሚዎች “ዓለም አቀፍ” የሚለውን ቃል እንጠቀማለን። ዓለምን ሁሉ ያቀፈ ማለት ነው፤ ያም ሆኖ ግን የምንጠቀመው የአንድ ወይም የሁለት ሀገራትን ጉዳይ ብቻ ሊሆን ይችላል።

ለመንደርደሪያ ያህል እግረ መንገድ እነዚህን ነገሮች አነሳሁ እንጂ የትዝብቴ ርዕሰ ጉዳይ የሠለጠኑት ሀገራት “እንዴት ሠለጠኑ?” የሚለውን መቃኘት ነው። ዓለም ሲባል ቀድሞ ትዝ የሚሉን የሠለጠኑት ሀገራት መሆናቸው አልቀረም። ብዙ ነገሮች ዓለም አቀፍ የሚባሉት ወይም “የዓለም” እየተባሉ የሚጠሩት የአውሮፓና አሜሪካ ሀገራት ሲያደርጓቸው ነው። ለምሳሌ፡- አንደኛውም ሆነ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት “የዓለም” እየተባሉ የሚጠሩት በመላው ዓለም ተደርገው ሳይሆን በአውሮፓውያኑ ኃያላን ሀገራት መካከል የተደረጉ ስለነበሩ ነው። የእስያ ሀገራት ቢኖሩበትም መነሻው ከአውሮፓውያኑ ነው። ያም ሆኖ ግን የጦርነቱ ጦስ ለዓለም ይተርፋል። በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት መካከል ጦርነት ቢደረግ ግን “የአፍሪካ” እንጂ “የዓለም ጦርነት” ብለው የሚገልጹት አይመስለኝም። ምክንያቱም ዓለም ማለት አውሮፓና አሜሪካ ብቻ መስሏል።

በነገራችን ላይ አሁን እየተረሳ ቢሆንም፤ የአንደኛው ዓለም፣ የሁለተኛው ዓለም እና ሦስተኛው ዓለም ትውልድ የሚባል አገላለጽ ነበር። የአንደኛው ዓለም የሚባለው የሠለጠኑት ሀገራት(አውሮፓና አሜሪካ) መሆኑ ነው። ሁለተኛው ዓለም ደግሞ መካከለኛ ሥልጣኔ ላይ ያሉ(እስያ) ሀገራት መሆናቸው ነው። የሦስተኛው ዓለም ትውልድ የሚባለው ግን የአፍሪካ ሀገራትን ነው። ሰውነት ደረጃ ወጣለት ማለት ነው። ለእዚህ ያበቃን ደግሞ የምርም ብዙ ኋላቀር ድርጊቶች ስላሉብን ነው። ብዙ የእስያ ሀገራት ፈጣን ርምጃ በመውሰድ እነ ጃፓን እና ቻይና ዓለምን የሚገዳደሩ፣ እነ አሜሪካን ያስናቁ የሥልጣኔ ባለቤቶች ሆነዋል። አሁን ላይ አንደኛ ዓለም፣ ሁለተኛ ዓለም የሚባል ቢኖር ኖሮ አንደኛ የሚሆኑት ምናልባትም እነ ቻይና ሊሆኑ ይችሉ ነበር። አፍሪካውያን ግን ዛሬም የእርስ በርስ ጣጣ ላይ ነን።

ሰሞኑን በአውሮፓዊቷ ሀገር ፈረንሳይ ለ19 ዓመታት ያህል የቆየ አንድ ኢትዮጵያዊ ሰው አግኝቼ ነበር። በሠለጠኑት ሀገራት ለረጅም ጊዜ ቆይቶ የመጣ ሰው ሳገኝ የምጠይቀው ጥያቄ፤ የዴሞክራሲ ሥርዓታቸውን ወይም የመሠረተ ልማት ደረጃቸውን አይደለም። እኔ የምጠይቀው የማህበረሰቡን ባሕል እና ሥነ ልቦና ነው። አንድ የነገረኝ ነገር ገርሞኝ አላበቃም፤ የገረመኝ ከእኛ ከኢትዮጵያውያን ሥነ ልቦና አንፃር ስላየሁት ነው።

ስግብግብነት የሚባል ነገር የለባቸውም። አውሮፓ ውስጥ ያለ አንድ ነጋዴ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ አንድ ነጋዴ አነፃፀረልኝ። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ አንድ ነጋዴ ጠቅላላ ገቢው አውሮፓ ውስጥ ካለ አንድ ነጋዴ የሚበልጥ ይሆናል እንበል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የተሻለ ገቢ ያለው ነጋዴ አውሮፓ ውስጥ ካለው አነስተኛ ገቢ ከሚያገኝ ነጋዴ የበለጠ ስግብግብ እና አጭበርባሪ ነው። ስለዚህ ችግራችን የገንዘብ ብቻ ሳይሆን የአዕምሮ ድህነት ነው ማለት ነው።

በዓይኑ ያየውን፣ ለብዙ ዓመት የቆየበትን አንድ ባሕል ነገረኝ። ለአንድ ኢትዮጵያዊ ሐበሻ ወይም ሌላ አፍሪካዊ ጥቁር በረንዳ ወይም ሌላ ቦታ ለሥራ ብለው ይሰጡታል። ያ ጥቁር በገቢ ነጮችን ሊበልጣቸው ሁሉ ይችላል። እነርሱ ቦታ ሰጥተውት በገቢ ሲበልጣቸው፤ እንኳን ሊናደዱ ይቅርና የአድናቆት መአት ያወርዱለታል። ከእነርሱ በላይ ገቢ ማግኘቱ ምንም አይመስላቸውም፤ ሀብታም የሆነው መንፈሳቸው ነው። ሐበሻ ወይም ሌላው ጥቁር ግን በስደት ሕይወት ውስጥ እየኖረ እዚያው አውሮፓ ውስጥ እርስ በርሱ ይመቀኛኛል። “ሐበሻ ምቀኛ ነው” የሚባለው ተለምዷዊ አነጋገር ዝም ብሎ የመጣ አይመስልም።

ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሆን ብላችሁ አስቡት። በአግባቡ አገልግሎት የሚሰጥ መጸዳጃ ቤት የሌለው የባርና ሬስቶራንት ባለቤት ምግብና መጠጥ በተጋነነ ዋጋ እየሸጠ፣ ለአንዲት ምስኪን የጀበና ቡና ሻጭ ግን በረንዳውን በውድ ዋጋ ያከራያል። ይቺ ልጅ የአንድ ወር የበረንዳ ኪራይ አልሞላላት ቢል ያስነሳታል። በገንዘብ ሀብታም ቢሆንም ሕሊናው ግን ድሃ ነው። እርግጥ ነው በረንዳው የራሱ ነው፤ ለአንዲት ምስኪን ድሃ በነፃ የመስጠት የሕግ ግዴታ የለበትም። ሕሊና ቢኖር ግን ለእዚያች ልጅ በነፃ ቢሰጣት ብዙ ትጠቀማለች። ለአንዲት ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ውለታ ውሏል። ምክንያቱም ያቺ ልጅ የበረንዳ ኪራይ መክፈል ቢቸግራት ጎዳና ልትወጣ ትችላለች። በእዚህ ልክ መተሳሰብ ቢኖር ለሀገራችን ውለታ እንውላለን ማለት ነው።

የሠለጠኑ የሚባሉ ሀገራትን የሠለጠኑ ያደረጋቸው የገንዘብ አቅም ብቻ አይደለም። የመንፈስ ሀብታምነት ነው። አውሮፓ ውስጥ የሚኖር ሁሉ ብዙ የቀን ገቢ ያለው ሀብታም ነው ማለት አይደለም። ዳሩ ግን አዕምሮው ሀብታም ነው፤ ሊያጭበረብርና ምቀኛ ሊሆን አይችልም። ሐበሻ ግን ጥሩ የቀን ገቢ እያለው ሁሉ ሊያጭበረብር ይችላል። ከራሱ ገቢ ይልቅ የጓደኛው ገቢ መብለጥ ያሳስበዋል። እኩል አብሮ ድሃ ቢሆን ይሻለዋል።

በምግብ ውስጥ ባዕድ ነገር የሚቀላቅሉ፣ ሀሰተኛ (ፌክ) ዕቃ የሚሸጡ … የሚበሉት የቸገራቸውና ያጡ የነጡ ድሃዎች ሳይሆኑ የተሻለ ገቢ ያላቸው ናቸው። የሠራተኛ ደመወዝ የሚከለክሉት ሌላ ተጨማሪ ንግድ ቤት ለመክፈት ነው። ሰካራም በሰበረው ብርጭቆ ከምስኪን ድሃ አስተናጋጅ ላይ ደመወዝ የሚቆርጡት የቤት ኪራይ ቸግሯቸው ሳይሆን ለተጨማሪ ዕድገት ነው። ዕድገት አይከለከልም፤ እንዲያውም የጎበዝ እና የታታሪ ነጋዴ መገለጫ ነው። ዳሩ ግን ሕሊና የሚባል ነገር መኖር አለበት።

ይሄ ማለት ግን ሁሉም ናቸው ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ ዳሩ ግን አብዛኛው ደግሞ ስግብግብ ነው። በአንድ አጋጣሚ ሲወድምበት ግን “ወይኔ ዕድሌ!” እያለ ፈጣሪውን ወይም መንግሥትን ያማርራል። መንፈሳችን ሀብታም ሲሆን ግን ነገሮችን በሁኔታቸው ልክ ለመቀበል ያስችላል።

የሠለጠኑ ሀገራት የሠለጠኑት ከገንዘብ በፊት በአዕምሮ ነውና የአዕምሮ ሥልጣኔ እና መተሳሰብ ይኑረን!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You