በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ሦስት ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚመለከቱ አዋጆች የነበሩ ሲሆን፤ እነርሱም የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532/1999፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ስነምግባር ለመደንገግ የወጣ አዋጅ ቁጥር 662/2002 ናቸው። ከእነዚህ ሕጎች ውስጥ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጠንካራ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ የሆነ የምርጫ አስፈፃሚ ተቋም ሆኖ እንዲደራጅ ለማድረግ በተቋቋመው ሥራ ከአዋጅ ቁጥር 532/1999 ውስጥ የቦርዱን መቋቋም፣ ሥልጣንና ተግባሩን፣ የአባላቱን አሰያየምና አነሳስ እንዲሁም የቦርዱን አሠራር የሚመለከቱትን አንቀጾች በማሻሻል የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠውን የምርጫ ሕጎችን መሠረት በማድረግ በአዋጅ የተቋቋመ ተቋም ሲሆን፤ ማቋቋሚያ ሕጉም “የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011” ተብሎ ይጠራል። አዋጁ የተሻሻለው የኢትዮጵያ ምርጫ አዋጅ ቁጥር 532/1999 ላይ የነበሩ የምርጫ አስፈፃሚ ተቋሙን አመሰራረትና ኃላፊነቶች ድንጋጌዎችን በመሻር መጋቢት 23 ቀን 2011 ዓ.ም ፀድቆ ሥራ ላይ ውሏል፡፡
ቀን 2011 ዓ.ም ፀድቆ ሥራ ላይ ውሏል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ የተሻሻለበት ዋና ዓላማ የዜጎችን እራስን በራስ የማስተዳደር መብት ከማንኛውም አካል ነፃ በሆነ የምርጫ አስፈፃሚ ተቋም እንዲመራ፤ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላትን አመላመልና አሿሿም ግልጽ ለማድረግ እና በተወዳዳሪ ድርጅቶች እና በመራጮች ዘንድ ያለውን ተአማኒነት እና የማስፈፀም አቅም ለማሳደግ እንዲረዳ ነው። የማቋቋሚያ አዋጁ ስለቦርዱ ሥልጣንና ተግባር፣ ስለቦርድ አባላት አሰያየም እና ሥነ ምግባር የሚደነግጉ ዝርዝር ክፍሎችን የያዘ ሲሆን፤ አዲስ በተሻሻለው ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት የቦርዱ ሥልጣንና ተግባር ምን እንደሚመስል እንደሚከተለው ይዘንላችሁ ቀርበናል።
የቦርዱ ሥልጣንና ተግባር
ቦርዱ በሕገ መንግሥቱ እና በምርጫ ሕግ መሰረት የሚካሄድ ማንኛውንም ምርጫ እና ህዝበ ውሳኔ በገለልተኝነት ማስፈፀም፣ የመራጮችና የስነዜጋ ትምህርት መስጠትና ተመሳሳይ ትምህርት ለሚሰጡ አካላት ፈቃድ መስጠት፣ መከታተልና መቆጣጠር፣ የፖለቲካ ድርጅቶችን መመዝገብ፣ በሕጉ መሰረት መከታተልና መቆጣጠር፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግበትን መስፈርት ማውጣትና በመስፈርቱ መሰረት ድጎማውን ማከፋፈል፣ በምርጫ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎችን መገናኛ ብዙሃንን አጠቃቀም መወሰን፣ የምርጫ ክልሎችን አከላለል በተመለከተ ጥናት አድርጎ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ ማቅረብ የምርጫ ቦርዱ ሥልጣን ነው፡፡
እንዲሁም ለምርጫ ታዛቢዎች ፈቃድ መስጠት፣ የመከታተልና መቆጣጠር፣ የቦርዱን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በሁሉም ክልሎችና ከዚያ በታች ባሉ የአስተዳደር እርከኖች ማደራጀት፣ ምርጫን ለማስፈፀም የሚያስፈልጉ የምርጫ ጣቢያዎችን ቁጥር መወሰን፣ ምርጫን ለማስፈፀም የሚያስፈልጉ የምርጫ ክልልና የምርጫ ጣቢያዎችን በመላ አገሪቱ ማደራጀት፣ ገለልተኛ፣ ብቃትና የህዝብ አማኔታ ያላቸው የምርጫ አስፈፃሚዎች መመልመልና ማሰልጠን፣ ከምርጫና ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ማሰባሰብ፣ ማጠናቀር፣ የምርጫ ሕጎችንና አፈፃፀምን በመገምገም ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች ለይቶ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ መድረክን ማስተባበር፣ የምርጫው ውጤቶችን ማረጋገጥና ይፋ ማድረግ፣ በምርጫ ሂደት ለሚቀርቡ ቅሬታዎች አስተዳደራዊ መፍትሄ መስጠት፣ በምርጫ ሂደት የምርጫ ውጤትን የሚያዛንፍ የሕግ ጥሰት ተከስቷል ብሎ ሲያምን ውጤቱን መሰረዝና ድጋሚ ምርጫ ማካሄድ ከተግባሮቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ።
በተጨማሪ በምርጫ ሂደት የተፈፀመ የሕግ መጣስ፣ ማጭበርበር ወይም የሰላምና ፀጥታ ማደፍረስ ድርጊት የፈፀሙ ግለሰቦችን በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ፣ በጀት አዘጋጅቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረብ፣ ማፀደቅና በሥራ ላይ ማዋል፣ በየደረጃው የሚካሄዱ ምርጫዎችን መርሃግብር ሰሌዳ እንዲዘጋጅ ማድረግ ማጽደቅ እንደአስፈላጊነቱ ማሻሻልና መፈፀሙን መከታተል፣ ለሕዘብ ተወካዮች ምክርቤት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ማቅረብ፣ በዚህ ሕግና በሌሎች ሕጎች የተሰጡትን ሃላፊነቶች ለመወጣት አስፈላጊ የሆኑ ማንኛውንም ተግባራትን ማከናወንም እንዲሁ የቦርዱ ስልጣኖች ናቸው።
የሥራ አመራር ቦርድ ሥልጣንና ተግባር
የሥራ አመራር ቦርድ በአዋጅ ቁጥር 1133/2011 አንቀጽ 7 ለቦርዱ በአጠቃላይ ከተሰጠው ሥልጣንና ተግባራት በተጨማሪ የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል። ደንቦችንና መመሪያዎችን ያወጣል፣ ለቦርዱ የተሰጡ ዝርዝር ሥልጣኖችን የሚመለከቱ የፖሊሲ አቅጣጫዎን ያስቀምጣል፤ ተግባራዊነታቸውንም ይከታተላል፤ የቦርዱ የመጨረሻው ቅሬታ ሰሚ አካል ሆኖ ያገለግላል፤ የምርጫ ውጤቶችን ይፋ ከመደረጋቸው በፊት ያፀድቃል፤ የምርጫ ውጤትን የሚያዛንፍ የሕግ ጥሰት በተከሰተ ጊዜ የምርጫ ወጤቶችን ይሰርዛል። እንዲሁም ድጋሚ ምርጫ ያካሂዳል፤ የሥራ አመራር ቦርዱ፣ የቦርዱ ጽህፈት ቤት፣ የቦርዱ ሠራተኞች የሥራ ሂደት እንዲሁም ቦርዱ ከሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጋር የሚያደርጋቸው ግንኙነቶች የሚመሩበትን ፖሊሲ ያዘጋጃል፤ በሥራ ላይ ያውላል፤ የቦርዱን ጽህፈት ቤት ሃላፊና ምክትል ሃላፊ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ይሾማል፤ የሥራ አመራር ቦርዱ አባላት የሚመሩበትን የሥነ ምግባር መመሪያ ያወጣል፤ ተግባራዊነቱን ይከታተላል፡፡
የቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ተግባርና ሃላፊነት
እያንዳንዱ የቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በሥራ አመራር ቦርዱ እና በሥራ አመራር ቦርዱ ሰብሳቢ እንዲሁም እንደ አግባብነቱ በቦርዱ ጽህፈት ቤት ሃላፊ በሚሰጠው አጠቃላይ መመሪያና አቅጣጫ መሰረት የሚከተሉት ተግባርና ኃላፊነት ይኖረዋል። በክልል ደረጃ የሚካሄደውን ምርጫ ይመራል፤ ያስተባብራል፤ ይቆጣጠራል፤ በሥሩ የሚቋቋሙት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶች ስለሚደራጁበት ሁኔታ ለቦርዱ ጽህፈት ቤት ሀሳብ ያቀርባል፤ ለምርጫ የሚያስፈልጉ ሰነዶችና ቁሳቁሶች ለሚመለከታቸው ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶችና የምርጫ ክልልና ጣቢያዎች በወቅቱ መድረሳቸውን ይከታተላል፣ ያረጋግጣል፤ ከቦርዱና የሥራ ሂደቱ ሃላፊነት ያለው የሥራ አመራር ቦርድ አባል በሚሰጠው መመሪያ መሰረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የስነዜጋና የመራጮች ትምህርት ይሰጣል፤ ያስተባብራል፤ የመራጮች አመዘጋገብ፣ የእጩዎች አቀራረብና የድምጽ አሰጣጥ ሥርዓት ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት እየተካሄደ መሆኑን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፤
በዚህ አዋጅ አንቀጽ 24 ንዑስ አንቀጽ 5 በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ የሚነሱትን ቅሬታዎችና ተቃውሞዎች በክልል ደረጃ እየመረመረ ቦርዱ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት ይወስናል፤ የክልሉን የምርጫ ሂደትና ውጤት በሚመለከት ለቦርዱ ጽህፈት ቤት ሪፖርት ያቀርባል፤ ለምርጫ አፈፃፀም በሚያመች መልኩ አግባብነት ያላቸውን መረጃዎች እየሰበሰበና እያጠና በየጊዜው ለቦርዱ ጽህፈት ቤት ሪፖርት ያቀርባል፤ ስለሥራ እንቅስቃሴው በየወቅቱ ለቦርዱ ጽህፈት ቤት ሪፖርት ከማድረግ በተጨማሪ፤ የሥራ አመራር ቦርዱ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት በክልል እና በምርጫ ጣቢያ ደረጃ የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ መድረክ እንዲዋቀር ያደርጋል። በክልል የሚቋቋሙ የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ መድረክ ያስተባብራል፤ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ ቦርዱ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ያቋቁማል፤ የሥራ አመራር ቦርዱ ሰብሳቢና የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት ያከናውናል፡፡
ምንጭ:- የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 የተወሰደ
አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2013