ውብሸት ሰንደቁ
ፕሮፌሰር ሁንዱማ ዲንቃ ይባላሉ:: ምዕራብ ኦሮሚያ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ሀባቦ ጉድሩ ወረዳ ተወልደው ነው ያደጉት:: የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት በዚያው በተወለዱበት ሥፍራ ነው:: ከዚያም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ህክምና ዲግሪያቸውን ሠርተዋል:: በገጠር ሕይወታቸው በከብት ማገድና ከእንስሳት ጋር በነበራቸው ጥብቅ ቁርኝት የእንስሳት እንክብካቤ ማነስና አያያዝ ያስቆጫቸው ነበርና ነው ወደዚህ ዘርፍ አዘንብለው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ሊሠሩ የቻሉት:: በእንስሳት ዙሪያ ብዙ አሳዛኝ ነገሮች አሉ፤ ብዙ አሳዛኝ ክስተቶችም ያጋጥሙናል ይላሉ ፕሮፌሰር ሁንዱማ:: ሀገሪቱ በርካታ የቀንድ ከብት እንዳላት ከታች ክፍል ጀምሮ ሲማሩ እንደነበርም ያስታውሳሉ:: በአካባቢያቸው ለእንስሳት የሚሰጠው ትኩረት በጣም አናሳ ስለሆነ ከዚህ ጋር በተያያዘ የእንስሳት ሕክምናን ለመማር በውስጣቸው ፍላጎት አድሮ ይኸው ይህንኑ ዘርፍ ዛሬም በቴክኖሎጂ ለማስታጠቅ እየተጉ ይገኛሉ::
‹‹ከተማርኩበት ጊዜ ጀምሮ በተለይ በእንስሳት ጤና ላይ የተለያዩ ምርምሮችን ሳደርግ ቆይቻለሁ›› የሚሉት ፕሮፌሰሩ በተጨማሪም ተማሪዎችን በተለያዩ ቦታዎች እንዳሠለጠኑ ይናገራሉ:: ሀገሪቱ ከእንስሳት ተዋፅዖ ማግኘት የነበረባትን ጥቅም ማግኘት እንዳትችል ያደረጋት አንዱ ምክንያት የእንስሳት ጤና ስለሆነ በእንስሳት ጤና ላይ ለምን ቴክኖሎጂን ተጠቅመን የእንስሳት ጤና ችግርን አንፈታም የሚለው ውስጣቸው ስላደረም ባዮ ቴክኖሎጂን በዶክትሬት ዲግሪ ተምረዋል::
ባዮ ቴክኖሎጂ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ላይ ሁሉ ተግባራዊ ማድረግ የሚቻል የቴክኖሎጂ ዘርፍ ነው:: ባዮ ቴክኖሎጂ ሲባል በእንስሳትና በዕፅዋት እንዲሁም ሰዎችን የሚመለከት የቴክኖሎጂ ዘርፍ ነው:: ከ65 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት የሰው ልጅ የጤና እክሎች መነሻቸው ከእንስሳት ነው:: በመሆኑም እንስሳት ጤና ላይ በመሥራት የሰውን ችግር መፍታት ይቻላል ይላሉ ፕሮፌሰር ሁንዱማ:: በቅርቡ የተከሰተው ወረርሽኝ ኮቪድ 19ን ወስደን ብናይ እንኳን መነሻው ከእንስሳት ነው:: ይህ ለመቅረፍ ይቻል ዘንድም የሰውንም ይሁን የእንስሳትን በሽታ አስቀድሞ መጠቃቱን መርምሮ ማወቅ በሚያስችል ቴክኖሎጂ ላይ እንደሠሩም ይናገራሉ::
በኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ይሄ ነው የሚባል ደረጃ ላይ አይደለም:: ገና በጅምር ላይ ያለ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ነው:: በባዮ ቴክኖሎጂ ያለው የሠለጠነ የሰው ኃይል በጣም አናሳ ነው:: ለአብነት ያህልም በሀገር ደረጃ በዘርፉ በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቀ ሰው የለም:: ገና በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመስጠት ላይ ናቸው:: ስለዚህ እንኳን ሕዝቡ የተማረው ማህበረሰብም ስለዘርፉ ምንነት ያን ያህል ግንዛቤ አለው የሚባል አይደለም:: ሆኖም ዘመኑ የቴክኖሎጂ በመሆኑ ከውጭ የሚመጣውን ቴክኖሎጂ እንኳን መጠቀም የሚቻለው በሥርዓቱ ዘርፉ ላይ የተማረና የሠለጠነ የሰው ኃይል እና ለማህበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር የሚችል የተማረ ዜጋ ሲኖር ነው:: ለዚህ ሲባልም ዘርፉ ላይ በሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ደረጃ ተማሪዎች እየሠለጠኑ ነው:: ፕሮፌሰር ሁንዱማም በዚህ ሂደት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ሠልጣኞች ላይ የራሳቸውን አስተዋፅዖ እያበረከቱ ይገኛሉ::
በሀገራችን በእንስሳት ልማቱ ላይ ከሚታዩ እክሎች በማዳቀል ላይ የሚታየው ችግር አንዱ እንደሆነ ይታወቃል:: ማዳቀል ለእንስሳት ተዋፅዖ ምርት ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ሀገሪቱ ከእንስሳት ሀብት ልማት ተገቢውን ጥቅም እንዳታገኝ እያሰናከሏት ነው:: ይህንን አስመልክተው ፕሮፌሰሩ እንዲህ ይላሉ:: በባዮ ቴክኖሎጂ ውስጥ የማዳቀል ቴክኖሎጂ አንድ ውስን ዘርፍ ነው:: ይህ በሴቷ እንቁላል እና በወንዱ ፍሬ የሚካሄድ ማዳቀል ብዙ ዓይነት ጠቀሜታዎች አሉት:: ለምሣሌ ወተት ልማት ላይ የተሠማራ ሰው የሚፈልገው ብዙ ላሞች እንዲኖሩት ነው:: ባዮ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጊደሮች ብቻ እንዲወለዱ ማድረግ ይቻላል፤ በተመሳሳይ ሥጋ ምርት ላይ የተሠማራ ሰው ደግሞ ለሥጋ የሚሆኑ ኮርማዎችን ብቻ ማስወለድና ማደለብ እንዲችል ይደረጋል:: ነገር ግን ይህ ቴክኖሎጂ ሲተገበር የተለያዩ ህፀፆች ስለሚፈጠሩ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ ይህ ዓይነቱ ቴክኖሎጂ ብዙም ተቀባይነት ሳይኖረው ቆይቷል:: ሆኖም ቴክኖሎጂው ላይ ምንም ዓይነት መጥፎ ነገሮች አይታዩም:: ማዳቀል የተለያዩ ሂደቶችን አልፎ ነው ለፍሬ የሚበቃው:: በላቦራቶሪ ውስጥ የወንዱን ፍሬ ለማቆየት ለየት ያለ ሁኔታን ይፈልጋል:: ፈሳሽ ናይትሮጅን የወንዱን ፍሬ ለማቆየት የሚረዳ ሲሆን ይህን ሳያገኝ የቆየ የዘር ፍሬ ይቃጠላል::
የሚያዳቅለው ቴክኒሽያን ስለዚህ ነገር ግንዛቤ ከሌለው የሞተውን የዘር ፍሬ ነው ወስዶ ለማራባት የሚሞክረው:: በዚህ ምክንያት ለሚፈጠሩ እንከኖች አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂው ውጤታማ ስለማይመስለው ላይቀበለው ይችላል:: ሌሎችም እንዲህ ዓይነት ተግዳሮቶችም በተመሳሳይ ሊፈጠሩ ይችላሉ:: ሆኖም እነዚህ ዓይነት ነገሮች እንዳይፈጠሩ በአግባቡ የሠለጠነ የሰው ኃይል ቦታው ላይ ካሰማራን ቴክኖሎጂውን ከመቀበል የሚያመነታ የለም:: በሌሎች ሀገራትም ይህ የማዳቀል ቴክኖሎጂ ውጤታማ ሆኖ አገልግሏል:: በማዳቀል ቴክኖሎጂ የሚያዳቅለው ቴክኒሽያን ግንዛቤ ከጎደለው ለማዳቀል ትክክለኛ ሰዓቱ፤ በማዳቀል ጊዜ የወንዱ የዘር ፍሬ መቀመጥ የሚገባው ቦታ እና በላሟ ማህፀን እንዴትና የት መቀመጥ እንደሚገባው ግንዛቤ ከሌለው ችግር ስለሚፈጠር ይህን ችግር ለመፍታት በዘርፉ በርካታ ባለሙያዎችን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር አሠልጥነናል::
በዚህ ሥራም 2004 ዓ.ም አካባቢ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የዋንጫ ሽልማትና ዕውቅና አግኝተናል:: አዳቃዮችን አሰልጥነን እንዲሠሩ ከማድረግ በተጨማሪ አርሶ አደሮች ሥልጠናውን እንዲያገኙ አድርገናል:: ሂደቱ ለተካሄደው ጥናት አንዱ የምርምር ውጤት ሲሆን በማዳቀል ዙሪያ የቱ ጋር ነው ችግር ያለው የሚለውን ከለየን በኋላ ሥልጠናው የመፍትሄው አንድ አካል በመሆኑ ይህን ልናደርግ ችለናል::
ምርታማ ዝርያዎችን ከማዳቀል ባሻገር በእንስሳት ላይ የሚታዩ የተለያዩ በሽታዎችም በሀገሪቱ እንስሳት ተዋፅዖ የውጭ ሽያጭ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ:: ይህንም ፕሮፌሰሩ እንዲህ ያብራሩታል:: በኢትዮጵያ ውስጥ አስጊ የሚባሉ የእንስሳት በሽታዎች አሉ:: በተለይም የፍየሎችና የበጎች በሽታዎች ትኩረት ሊሰጣቸውና ሊሠራባቸው ይገባል:: ፒ.ፒ.አር በመባል የሚታወቀው በቫይረስ የሚመጣ የፍየሎችና የበጎች በሽታ በዓለም አቀፍ ደረጃም ለማጥፋት ዘመቻ የተከፈተበት ነው:: ኢትዮጵያም ይህን ዘመቻ ተቀላቅላ በሽታውን ለማጥፋት እየሠራች ትገኛለች:: ይህ በሽታ አንዴ ከያዘ ብዙዎቹን ስለሚያጠፋ እንደ ሀገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ነው:: በተጨማሪም ፍየሎች፣ በጎችንና ሌሎች የቤት እንስሳትን የሚያጠቃ አፍ ተግር የሚባል በሽታ አለ:: ይህ በሽታ የእንስሳትን አፍና እግር የሚያቆስል ነው:: በዚህ ምክንያት የቤት እንስሳት የሚፈለገውን ውጤት አይሰጡም:: ለምሳሌ በዚህ የተያዘ በሬ እግሩ ስለሚታመም የእርሻ አገልግሎት መስጠት አይችልም:: ወተት የምትሰጠዋ ላምም መመገብ ስለማትችል አስፈላጊው የወተት ምርት መገኘት አይችልም:: የእንስሳት የሳንባ ነቀርሳም በኢትዮጵያ እንስሳት ላይ የተጋረጠ ሌላ ችግር ነው:: ይህ በሽታ ደግሞ እንስሳትን ይዞ የሚያቆም ዓይነት አይደለም:: ከእንስሳት ወደ ሰው የመተላለፍ ዕድሉ ሰፊ ነው:: እንዲህ ዓይነት በሽታዎችን ለመከላከል ነው ወተት ፓስቸራላይዝ መሆን አለበት የሚባለው::
በሀገሪቱ ውስጥ ጥሩ የእንስሳት ሀብት ያለ ቢሆንም ወደ ውጪ ገበያ ተልኮ ተገቢው ጥቅም እንዳይገኝ የሚያደርጉ ምክንያች ዋነኛው የእንስሳት በሽታ ነው:: የተለያዩ ሀገራት የራሳቸው የሆነ ፖሊሲ አላቸው:: በሽታው ወደ ሀገራቸው እንዳይገባ ይፈልጋሉ:: ሰዎች የነዚህን ተዋፅዖ በመመገባቸው በሽታ እንዳይተላለፍባቸውና በሀገራቸው የሚገኙ እንስሳትም በዚህ በሽታ እንዳይጠቁ ለማድረግ ከውጭ የሚገቡ የእንስሳት ተዋፅዖ ምርቶች ላይ ቁጥጥር ያካሂዳሉ:: ኢትዮጵያ ሥጋ ኤክስፖርት የምታደርግ አገር በመሆኗ በዚህ ሥጋ ምክንያት የተለያዩ በሽታዎች ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ ስለሚፈሩ አንድ የበሽታ ዓይነት በዚህ ሀገር አካባቢ አለ ከተባለ ምርት መቀበል ያቆማሉ:: ኢትዮጵያ የእንስሳት ተዋፅዖዎችን ወደ ውጪ እንዳትልክ የሚያደርጋት ከላይ የተጠቀሱት የእንስሳት በሽታዎች ናቸው:: የእንስሳት ሳንባ ነቀርሳና አፍ ተግር የመሳሰሉት እንዳሉ ያረጋገጡ ሀገራት ወዲያውኑ ምርቱን መቀበላቸውን ያቆማሉ:: ይህ ነገር የውጭ ምንዛሬ ግኝትንም አደጋ ውስጥ ይከታል::
ኢትዮጵያ ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሬ የምታገኘው የእንስሳት ተዋፅዖን ወደ ውጭ በመላክ ነው:: የሰውም ይሁን የእንስሳት ጤና ተያያዥ መነሻዎች አሏቸው:: የሰውን ጤና ለማሻሻል የእንስሳትን ጤና መንከባከብ ተገቢ ነው:: ለዚህም በቴክኖሎጂ የታገዘ ምርምር እያደረጉ የመፍትሄ ሃሳቦችን ማፍለቅ ይገባል:: ይህን በቴክኖሎጂ የታገዘ ምርምር ለማካሄድ የተማረ የሰው ኃይል ያስፈልጋል:: ይህን ለማሳካት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ ማሠልጠን የሚያስችል ሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆ ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል:: ፕሮፌሰር ሁንዱማም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከአጠናቀቁ በኋላም የመጀመሪያው ሥራቸው የነበረው ይህን ሥርዓተ ትምህርት ቀርፆ ትምህርት ማስጀመር ነበር:: ይህን ሲያደርጉ ዋናው ዓላማቸውም የተማረ የሰው ኃይል በብዛት ማፍራትና በዘርፉ የሚካሄዱ ምርምሮች እንዲጎለብቱና ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻል ነው:: በዚህ ዘርፍ የሠለጠኑት የመጀመሪያዎቹ ተማሪዎችም በሚቀጥለው ዓመት በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ ይመረቃሉ::
ፕሮፌሰር ሁንዱማ በማጠቃለያቸው በእንስሳት ላይ እየታዩ ያሉ በሽታዎች እና የእንስሳት መኖ መፍትሄ ከተገኘላቸው ኢትዮጵያ በእንስሳት ተዋፅዖ ምርት መላክ በአህጉርም ይሁን በዓለም ደረጃ የሚወዳደራት አይገኝም:: ሀገሪቱ በአግባቡ እየተጠቀመችበት ባይሆንም ተለያይነትና ስብጥር ያለው የእንስሳት ሀብት አለ:: ካሉት የእንስሳት ሀብት ጋር ቴክኖሎጂን መጠቀም ከተቻለ ብዙ ተስፋዎች አሉ:: መንግሥትም ለእንስሳት ሀብት ልማት ልዩ ትኩረት እየሰጠ መምጣቱ በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ሌላው ተስፋ ነው:: ዓለም በሁሉም ዘርፍ በቴክኖሎጂ እየተራመደ ነው:: ኢትዮጵያም ከቴክኖሎጂ ማምለጥ አትችልም:: ስለዚህ ሕዝቡን አስቀድሞ ማንቃትና ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ አበክሮ መሥራት ያሥፈልጋል:: ግንዛቤ ማስጨበጡ እና የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ትኩረት ቢደረግ በዘርፉ ከዓለም ጋር ለመራመድ የሚያስችል ቁመና እንፈጥራለን ብለዋል::
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም