አንተነህ ቸሬ
ለጋዜጠኝነት የነበራቸው ፍላጎትና ፍቅር እንግሊዝ ድረስ ሄደው እንዲማሩ የተወሰነላቸውን የትምህርት መስክ እንዲተውት አስገድዷቸዋል፡፡ ልዩ የማንበብና የመጻፍ ፍቅር አላቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን በውጭ ቋንቋዎች ላቅ ያለ ችሎታ ማሳየት እንደሚችሉ ያስመሰከሩ አንጋፋ ባለሙያ ናቸው፡፡ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛን አቀላጥፈው ይናገራሉ፤ በጣሊያንኛም አይታሙም፡፡ በ1935 ዓ.ም የተቋቋመው የአንጋፋው የ‹‹ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ (The Ethiopian Herald)›› ጋዜጣ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዋና አዘጋጅ ናቸው … ያዕቆብ ወልደማርያም!
ያዕቆብ የተወለደው በ1921 ዓ.ም ነቀምቴ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ከሕፃንቱ ጀምሮ ነገሮችን የማወቅ ጉጉት የነበረው ያዕቆብ፤ በወቅቱ በከተማው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ በአባቱ አማካኝነት ፊደል ቆጠረ፡፡ አማርኛ ማንበብና መጻፍም ቻለ። አባቱ አቶ ወልደማርያም ሹባ ይህንን እውቀት ያገኙት ከነቀምቴ ወደ ደብረ ሊባኖስ እና ዝቋላ ገዳማት ለ11 ቀናት ያህል በእግራቸው እየተጓዙ ነበር፡፡ ሕፃኑ ያዕቆብም በትጋትና በጽናት ከተገኘው የአባቱ እውቀት ተቋዳሽ መሆን ቻለ፡፡
ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስትወር ያዕቆብ የሰባት ዓመት ታዳጊ ነበር፡፡ ለትምህርት በነበረው ፍቅር የተነሳ ያለቤተሰቦቹ እውቅናና ፈቃድ የጣሊያንኛ ትምህርት ቤት ገብቶ ለሦስት ዓመታት ተማረ። ጣሊያኖች ሲወጡ ደግሞ ከውጭ የገቡት የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮች ትምህርት ቤቱን ተረክበውት ስለነበር በመደበኛ ትምህርት እንግሊዝኛን መማር ጀመረ።
ቀጥሎም ተፈሪ መኮንን አንደኛ ደረጃ የመንግሥት ትምህርት ቤት ስለተቋቋመ እዚያ ገብቶ መማር ቀጠለ፡፡ ይህን ቆይታውን እንዳጠናቀቀ በአዲስ አበባ፣ ኮተቤ፣ የመጀመሪያው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከፍቶ ስለነበር ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቱ እንዲገቡ ሲደረግ ያዕቆብ ፈተናውን በጥሩ ውጤት አልፎ ስለነበር ኮተቤ ትምህርት ቤት ገባ፡፡ በዚያም ከ8ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ለአምስት ዓመታት ያህል ተምሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቁ ሌላ የትምህርት እድል አገኘ፡፡ ላስመዘገበው ከፍተኛ ውጤት ከቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ እጅ ሽልማት ተቀብሎ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ለንደን ተላከ፡፡
ያዕቆብ ወደ ለንደን ሲሄድ የሚያጠናው የትምህርት ዓይነት ተወስኖለት ነበር፡፡ በጊዜው የኢትዮጵያ መብራት ኃይል እና የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት መስሪያ ቤቶች መሐንዲሶችን በብዛት ይፈልጉ ነበር። የኢትዮጵያ መብራት ኃይል በሳይንስና በሒሳብ ትምህርቶች የጨረሱትን ስፖንሰር በማድረግ እንዲማሩ ያደርግ ስለነበር ያዕቆብና አንድ ሌላ ተማሪም የኤሌክትሪካል ምህንድስና እንዲማሩ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ወደ ለንደን ተሸኙ።
እዚያም ደርሶ በ‹‹ኢምፔሪያል የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ሕክምና ኮሌጅ (Imperial College of Science, Technology and Medicine) ውስጥ ትምህርቱን መከታል ጀመረ፡፡ ያዕቆብ በኮሌጁ ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ ቀጥሎ የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን ትምህርቱን የመቀጠል ፍላጎቱ እየተቀዛቀዘ መጣ። እናም ከዚሁ እየጠላው ከመጣው ትምህርት ጎን ለጎን በግሉ የተለያዩ የፍልስፍና መጻሕፍትን ማንበቡን ተያያዘው። በብዙ የዓለም ቋንቋዎች የተጻፉና የተተረጎሙ የበርካታ አገራት ድርሰቶችንም ማንበብ ቻለ፡፡
ቀስ በቀስም እንዲማር የተላከበትን የኤሌክትሪካል ምህንድስና ትምህርቱን እየተወው መጣ፡፡ ስለጋዜጠኝነት የሚገልፁና የሚያወሱ ሙያዊና ታሪካዊ መጽሐፍትንም በጥልቀት ማንበብ ቀጠለ፡፡ ‹‹The Observer››፣ ‹‹The Daily Telegraph››፣ ‹‹The Guardian››ን ጨምሮ ሌሎች ጋዜጦችንና መጽሔቶችንም ያነብ ነበር፡፡ በዚያው መጠን የጋዜጠኝነት ሙያን እየወደደው መጣ። በአፃፃፍ ቴክኒኮች እየተደነቀ «እኔ ብሆን» የሚል መንፈሳዊ ቅናትም ያድርበት ጀመር፡፡ በዚህ ወቅት በኮሌጁ ይማሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ያቋቋሙት መጽሔት ነበርና የያኔው ወጣት ያዕቆብም የተለያዩ መጣጥፎችን በማዘጋጀት በዚች መጽሔት ብዕሩን አሟሸ። የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (YMCA) አባል ስለነበረም በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በንቃት ይሳተፍ ነበር፡፡
ቀጠለናም በተለያዩ የእንግሊዝ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ሃሳቡን የማስፈር ጥረት አደረገ። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ወዳጅና የስመ ጥሩ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እናት የነበሩት ወይዘሮ ሲልቪያ ፓንክረስት ያሳትሙት በነበረው ‹‹New Times and Ethiopia News›› ጋዜጣ ላይም ይጽፍ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለ የራስ ሕመም ስለነበረበት እረፍት እንደሚያስፈልገው ተነግሮት ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ:: የተላከበትን ትምህርቱን ማቋረጡና ወደ ኢትዮጵያ መመለሱ በወቅቱ ሹማምንት ዘንድ አልተወደደለትም፡፡
ያዕቆብ ወደ ስራ ዓለም ተቀላቀለ፡፡ በአዲስ አበባ፣ የአምሃ ደስታ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት 300 ብር ወርሃዊ ደመወዝ እየተከፈለው የሒሳብና የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር መሆን የመጀመሪያ ሥራው ሆነ። ውስጡ በነበረው የጋዜጠኝነት ስሜት በመነሳሳትም ከማስተማሩ ጎን ለጎን የተማሪዎች ጋዜጣ እንዲቋቋም አደረገ። ከሁለት ዓመታት በኋላ ወደ ትውልድ ስፍራው ነቀምቴ ተዛውሮ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ማስተማር ጀመረ። በዚያም በተማሪዎች የሚዘጋጅ ተወዳጅ ጋዜጣ በማቋቋም ይበልጥ ወደ ሙያው ተሳበ። በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚዘጋጀው በዚህ ጋዜጣ የያዕቆብ ሚና የእንግሊዝኛውን ክፍል ማረም እና ርዕሰ አንቀፅ ማዘጋጀት ነበር። በወቅቱ ተማሪዎች የሚመኟቸውን ሃሳቦች ጽፈው ጋዜጣው ላይ ሲታተሙ መንግሥትን አያስደስቱም ተብለው በሹማምንት ዘንድ ያልተወደዱ ጽሑፎች ቁጣንና ተግሳፅን ያስከትሉ ነበር።
የትምህርት ቤት ጋዜጣ ሲያሳትም የተመለከታቸው እውነታዎችና ያጋጠሙት በጎና አስቸጋሪ ገጠመኞች የጋዜጠኝነት ሙያ (በተለይ የአርታዒነት ስራ) ምን ያህል ኃላፊነት እና ጥንቃቄ የሚያሻው መሆኑን አስገነዘቡት፡፡ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር ሆኖ ለሁለት ዓመታት ያህል ካገለገለ በኋላ ከአስተማሪነቱ የሚለቅበት አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ደረጀ ትዕዛዙ ‹‹ጉምቱ ጋዜጠኛ – ያዕቆብ ወልደማርያም›› በሚለው ጽሑፉ አቶ ያዕቆብ ይህን አጋጣሚ እንዲህ ሲሉ እንደሚያስታውሱት ጽፏል፡፡
« … ያኔ የልዑል መኮንን መታሰቢያ ሆስፒታል በነቀምቴ ይሰራ ነበር፡፡ አቶ ኤፍሬም የተባሉ የወቅቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ማዘጋጃ ቤት ሰብስበውን ለሆስፒታሉ ገንዘብ እንድናዋጣ ጠየቁ። እኔ ጥያቄው አልተመቸኝም ነበር፡፡ ‹ከደመወዜ አሥር ብር አሰጣለሁ› አልኩ። የሚፈለገው የአንድ ወር ደመወዝ ነበር። በዚህ ጊዜ ተቃውሞ ገጠመኝ። ‹አድማ መምራት ነው› ተባልኩኝ። በዚሁ ምክንያት ሥራዬን ትቼ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ። በአንድ ጓደኛዬ ጥቆማ አማካኝነት መብራት ኃይል ባለሥልጣን በ360 ብር ደመወዝ በመስመር ዝርጋታና ቴክኒክ ክፍል ተቀጠርኩ። ሥራው ግን አልተመቸኝም …
… ይህን የተረዳው ኃይለልዑል ጠብቄ የተባለ እንግሊዝ አገር አብረን የተማርን ጓደኛዬ ‹ለምን ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ አትገባም? ዋና አዘጋጁ ዶክተር ዴቪድ ኤ ታልቦት ጋዜጠኛ ይፈልጋል፤ ሂድና ተፈትነህ ግባ› አለኝ። ይህን ሊለኝ የቻለው እንግሊዝ አገር እያለን በተለያዩ ጋዜጦች ላይ በምጽፋቸው ጽሑፎች ፍላጎቴንና አቅሜን ስለተረዳ ነው። እንደነገረኝ ሄድኩና ስጠይቅ ‹ሂድና ቤትህ ጽፈህ ና› ብሎ ፈተናውን ሰጠኝ። ‹የለም! እዚሁ እፅፋለሁ› አልኩት። ‹በእንግሊዝኛ አርቲክል ጻፍ› አለኝ፡፡ እኔም ጻፍኩ። ከፈረንሳይኛ ወደ እንግሊዝኛ የሚተረጎም ጽሑፍ ሰጠኝ፤ በጥሩ ሁኔታ ተረጎምኩ። በጣም ተገረመ። ደስ እያለው ‹እንፈልግሃለን› አለ፡፡ ገባሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ ጋዜጠኛ ሆንኩ፡፡»
ያዕቆብ በ1951 ዓ.ም በ400 ብር ደመወዝ የጋዜጠኝነት ሙያን ተቀላቀለ፡፡ ወዲያውም ታላላቅ ጉዳዮችን እያነሳ ዜናዎችንና መጣጥፎችን ባማረ እንግሊዝኛ ማቅረብ ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ የመብራት ኃይል ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰይፉ ማህተመሥላሴ በያዕቆብ ጽሑፎች እጅግ ተገረሙ፤ ችሎታ ያለው ሰው እንዳጡም ቁጭት ተሰማቸው። ሥራ አስኪያጁም ያዕቆብን አግባብተው እንደገና ቢመልሷቸውም ወዲያውኑ የወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት ‹‹ንጉሡ ዘንድ ሄጄ እከሳለሁ›› በማለት ከፍተኛ ቁጣ ስላስነሱ ያዕቆብ እንደገና ወደ ‹‹ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ›› ጋዜጣ ተመለሰ፡፡
በወቅቱ ከጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ዶክተር ዴቪድ ታልቦት ቀጥሎ ሁለተኛ ሰው ያዕቆብ ነበር፡፡ አዘጋጅ ሆኖ ጽሑፍ ያርማል፤ ሌሎች ጋዜጠኞችን ለሥራ ያሰማራል፤ በፈረንሳይኛ እና በጣሊያንኛ ከውጭ የሚላኩ ዜናዎችንና ሌሎች ጽሑፎችን ይተረጉማል፡፡ ሥራው ፋታ የማይሰጥ ቢሆንም የሚወደውና የሚመኘው ሙያ ነበርና በትጋት ቀጠለበት፡፡
በሂደትም ይከፈለው በነበረው ደመወዝ ላይ 100 ብር ተጨምሮለት ወደ ምሽት አርታኢነት (Night Editor) ተዛወረ፡፡ አራት ገጽ ያለው ጋዜጣ ለማዘጋጀት እስከ ንጋት 11 ሰዓት ድረስ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ውስጥ እየቆየ ጽሑፎችን የማረምና ለህትመት የማመቻቸት ሥራ ይሰራል። ምሽት ላይ የሚመጡ መግለጫዎችን በተለይም ከማስታወቂያ ሚኒስትሩ በቃል እየተቀበለ በመስራት በማግስቱ እንዲወጣ ያደርጋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ለስድስት ወራት ያህል ሰራ፡፡
የጋናው መሪ ክዋሜ ንክሩማህ ዶክተር ታልቦትን ለጉብኝት ጋብዘዋቸው ለሦስት ወራት ወደ ጋና በሄዱበት ወቅት ግን ሌላ ነገር ተፈጠረ፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትሩ አቶ አምደሚካኤል ደሳለኝ ጋዜጣውን በቅርብ ኃላፊነት ይከታተሉት ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው ለምን የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ አይሆንም የሚል ቁጭት ስላደረባቸው በዚህ አጋጣሚ ጥሩ ለሚሰራ ሰው ሹመት መስጠት ፈለጉ፡፡ እናም ለቦታው ይመጥናሉ ብለው ያሰቧቸውን አቶ ያዕቆብ ወልደማርያምን፣ አቶ ነጋሽ ገብረማርያምን እና አቶ አያሌው ወልደ ጊዮርጊስን ወደ ቢሯቸው አስጠርተው «በሉ ከሦስታችሁ አንዳችሁ ዋና አዘጋጅ ትሆናላችሁ፤ ፈተና ልስጥ ወይንስ እናንተ ከመሀላችሁ ትመርጣላችሁ?» ብለው ጠየቁ፡፡ ሁለቱም አቶ ያዕቆብ እንዲሆኑ ተስማሙ፡፡ ምርጫው ፀደቀ፡፡ አቶ ያዕቆብ ወልደማርያም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የ«ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ» ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኑ:: የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ የነበሩት ዴቪድ ታልቦት ቤተ መንግሥቱ ድረስ የዘለቀ ታዋቂነትና ተቀባይነት ስለነበራቸው የእርሳቸው ከዋና አዘጋጅነት መነሳት አንዳንድ ሹማምንትን አስቆጥቶ ነበር፡፡
ያዕቆብ የዋና አዘጋጅነቱን ቦታ እንደያዙ በጋዜጣው ቅርጽና ይዘት ላይ ለውጥ አደረጉ፡፡ ለወትሮው የውጭውን ዓለም ታሪክና ዜና ከማቅረብና የንጉሡ እንዲሁም የሹማምንቱን አንዳንድ ክዋኔዎች በዜናነት ከማውጣት በዘለለ ሌሎች የማህበረሰቡን ክንዋኔዎች ዳስሶ የማያውቀው ‹‹ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ›› ጋዜጣ አሁን የተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ሌሎች ሁነቶችን በስፋትና በጥልቀት መዘገብና ማስተናገድ ጀመረ፡፡ ጋዜጣው አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮሩ አቶ ያዕቆብን አስመሰገናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያንም አቅም እንዳላቸው አስመሰከሩ፡፡
አቶ ያዕቆብ የሌሎች አገራት መልካም ተሞክሮዎችን እያመሳከሩ ለኢትዮጵያ የሚበጁ ሃሳቦችን በርዕሰ አንቀጽ እና በሌሎች ገጾች ላይ ይጽፉና እንዲስተናገዱ ያደርጉ ነበር፡፡ በተለይ ስለ መሬት ከበርቴው፣ ስለ ሲቪል ሰርቪስ መቋቋም፣ ስለ ጡረታ ሕግ አወጣጥ፣ ስለ ቤት ኪራይ እና ስለ ሹም ሽረት ሥርዓት ጉዳዮች ብዙ ጽፈዋል።
ያዕቆብ ዋና አዘጋጅ ሆነው ለሁለት ዓመታት ከሰሩ በኋላ ከጋዜጣው ለቀቁ፡፡ ለዚህ ምክንያት የሆናቸውን አጋጣሚ እንዲህ ይገልፁታል።
« … በዚሁ ኩዴታ (1953 ዓ.ም) ወቅት ሕዝቡ ‹እነ ጀኔራል ጃገማ ኬሎ መንግሥት ሊገለብጡ ነው› እያለ በመራበሽ ልጆቹን ከትምህርት ቤት ማውጣት ጀመረ፤ ታዲያ እኔ ‹ዜና በትክክል ቢሰጥ ኖሮ ይህ ሁሉ ውዥንብር አይፈጠርም ነበር› ስል በርዕሰ አንቀፅ ጻፍኩኝ፡፡ በዚህ ጊዜ በ‹መነን› መጽሔት እንግሊዝኛው ውስጥ የሚጽፍ ስሚዝ የተባለ አፍሮ-አሜሪካዊ ሃሳቤን ይዞ ለውጭ አገር ሚዲያዎች አስተጋባ። ይህ ሲሆን የውጭ ጋዜጦች በአገራችን የጋዜጠኝነት ነፃነት የሌለ መሆኑን በመግለጽ ማስታወቂያ ሚኒስቴርን በመተቸት ወሬውን ተቀባበሉት፡፡ በዚህ ጊዜ በመንግሥት ጥርስ ተነከሰብኝ:: ወዲያውም ደጃዝማች ግርማቸው ወልደሐዋርያት እኔ ከጋዜጣው ሥራ እንድነሳ አደረጉ … »
ከዚያም በወቅቱ «አዣንስ» ተብሎ ወደሚታወቀውና በአሁኑ አጠራሩ «የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ» ወደሚባለው መስሪያ ቤት የእንግሊዝኛው ክፍል ተዛወሩ፡፡ እዚያም ለጥቂት ጊዜያት ያህል እንደሰሩ ወደ ‹‹መነን›› መጽሔት የእንግሊዝኛው ክፍል ተዛውረው መስራት ጀመሩ፡፡ ዋና አዘጋጅም ሆኑ፡፡
‹‹መነን›› መጽሔት በሐገር ፍቅር ማኅበር ስር ትተዳደር ነበር፡፡ አቶ ያዕቆብ የመጽሔቷ ዋና አዘጋጅ እንደሆኑ የወሰዱት የመጀመሪያ እርምጃ ከአማርኛው ጋር ተዳብላ የነበረችውን መጽሔት ራሷን ችላ እንድትወጣ ማድረግ ነበር፡፡ መጽሔቷ በቅርፅና ይዘት ደረጃ ከሌሎች የውጭ አገር መጽሔቶች ባልተናነሰ ሁኔታ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ዘመናዊነትን ተከትላ መዘጋጀቷ ብላታ ግርማቸውንም ሆነ ሌሎች ሹማምንትን አስደሰተ፡፡አቶ ያዕቆብ መጽሔቷን ወደ ተሻለ ብቃት ያሳደጓት የውጭ መጽሔቶችን አርአያነት እየተከተሉ ነበር፡፡ ብዙ ማንበባቸውና ሙያውን ማፍቀራቸው ሁልጊዜም የተሻለ ሥራ እንዲሰሩ ብርታት እየሆናቸው ቀጠሉ፡፡
በዚች መጽሔት ላይ ለተወሰኑ ዓመታት እንደሰሩ የእንግሊዝኛዋን «ቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ/Voice of Ethiopia» ጋዜጣንም ደርበው እንዲያዘጋጁ ኃላፊነት ተሰጣቸው፡፡ በኋላም ከ‹‹መነን›› መጽሔት በቋሚነት ወደ ‹‹ቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ›› ጋዜጣ ተዛውረው ለሰባት ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡
የእንግሊዝኛው ‹‹ቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ›› ጋዜጣ ሕትመት ሲቋረጥም በዚያ ይከፈላቸው በነበረው ደመወዝ ወደ ‹‹ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ›› ጋዜጣ ተመልሰው በአማካሪነት ተመደቡ። ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ስልጣን እስከያዘበት ጊዜ ድረስ ከማማከሩ ጎን ለጎን በፍላጎታቸው ርዕሰ አንቀጽና መጣጥፎችን ያዘጋጁ ነበር፡፡ ደርግ ሥልጣን ሲይዝ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የእንግሊዝኛው ‹‹የካቲት›› መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆነው አገልግሎታቸውን ቀጠሉ:: በዚሁ ኃላፊነታቸው ላይ ሆነው ሳለ ጡረታ ሊወጡ ስድስት ወራት ያህል ሲቀራቸው በ1980ዎቹ አጋማሽ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዛውረው ለጥቂት ጊዜያት ያህል አገልግለዋል፡፡ ጡረታ ከወጡ በኋላም በእንግሊዝኛው የሪፖርተር ጋዜጣ (The Reporter) ላይ አርታኢ በመሆን አገልግለዋል፡፡
በተለይ በዛሬዎቹ ጋዜጠኞች ዘንድ ስላለው ክፍተት ሲናገሩ ‹‹ … የቀደሙት ጋዜጠኞች አንባቢዎች ነበሩ:: የዛሬዎቹ በንባብ ራስን በእውቀት የማበልፀግ ትጋት ላይ ክፍተት ይታይባቸዋል፡፡ የማያነብ ጋዜጠኛ እንዴት ሊጽፍ ይችላል? አንድ ጋዜጠኛ የራሱን አቅም የሚለካው ሌሎች የደረሱበትን ሲያውቅ ነው፡፡ የሀገር ውስጥን ብቻ ሳይሆን የሌሎች አገሮች ጋዜጠኞች እንዴት እንደሚጽፉ መረዳት አለበት፡፡ ዓለም አቀፋዊ እውቀት ሲኖር ነው ብስለት ያለው ሥራ መስራት የሚቻለው» ይላሉ:: ያም ሆኖ ተስፋ የሚጣልባቸው ጎበዝ ጋዜጠኞች መኖራቸውና ሙያው በዘመናዊ ትምህርት እየተደገፈ መምጣቱ የዘርፉን እድገት እንደሚያመለክት ይናገራሉ፡፡
በማስታወቂያ ሚኒስቴር በጋዜጠኝነት ሥራ ብቻ ከ34 ዓመታት በላይ የሰሩት አቶ ያዕቆብ፤ የጋዜጠኝነት ሙያን በቀጥታ ከትምህርት ተቋም ባይማሩትም ወደ ተለያዩ አገሮች ሄደው በሥልጠናና በጉብኝት ያገኙት እውቀት ቀላል አይደለም፡፡ አቶ ያዕቆብ ለስራዎቻቸው ልዩ ልዩ ሽልማቶችንና እውቅናዎችን አግኝተዋል፡፡ ለአብነት ያህል ከቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የተቀበሉት የፈረሰኛ ኮኮብ ኒሻን እና በ2007 ዓ.ም ያገኙት ‹‹የበጎ ሰው›› ሽልማቶች ይጠቀሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ እንዲሻሻል ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱትና በቤተሰባዊ ሕይወታቸው እንደሚደሰቱ የሚናገሩት አቶ ያዕቆብ ወልደማርያም፤ የ10 ልጆች አባት ሲሆኑ በርካታ የልጅ ልጆችንም አይተዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 08/2013