መንግሥት በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዕርምጃ መውሰድ ከጀመረ አንስቶ ጥቂት ሀገሮችና መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ከጁንታው ርዝራዦች በሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎች በመደናገር በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና ለማድረግ ሲሞክሩ በግልፅ ታይቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ እውነትን በመግለጥ ባካሄደው የዲፕሎማሲ ሥራ እውነቱ እየታወቀ በመምጣቱ አላስፈላጊና ተገቢ ያልሆነ ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚደረገው ሙከራ እየረገበና ፈር እየያዘ መጥቷል። ነገር ግን አንዳንድ የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተኑ ኃይሎች የሀገሪቷን ውስጣዊ አንድነት መሸርሸር አልያም በተለያዩ ማዕቀቦች ጫና ለማሳደር ዕለት ተዕለት ሲጥሩ ይታያል።
በትግራይ ክልል ከሚደረገው የሰብአዊ ዕርዳታ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው የሚሸፈነው በኢትዮጵያ መንግሥት ሆኖ እያለ፣ ጁንታው በጣጥሷቸው የሄደውን የኤሌክትሪክ መስመሮች እንደገና ተጠግነው ወደ አገልግሎት እየተመለሱ ሳለ፣ በጁንታው የወደሙ ፋብሪካዎች እና መሠረተ ልማቶች ጥገና ተደርጎላቸው እንደገና ሥራ እየጀመሩ ባለበት ሁኔታ እነዚህ በሉዓላዊት ሀገር ላይ ጣልቃ ለመግባት የሚሞክሩ ሀገራትና አንዳንድ ሚዲያዎች ዘመናዊ የጁንታው ርዝራዦችን በማደራጀት የአገርን ገጽታ ለማበላሸትና አንድነትን ለመሸርሸር ሌት ተቀን በመስራት ላይ ይገኛሉ። ሆኖም የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነቱ የማይደራደር ከመሆኑም ባለፈ ለወገኑ ምን ማድረግ እንዳለበት ጠንቅቆ የሚያውቅ በመሆኑ ከየአቅጣጫው የሚፈጠሩ የሀሰት መረጃዎችን በተረጋጋ ሁኔታ በማጋለጥ የጁንታው ርዝራዦችን የሀሰት ውንጀላ ለዓለም ማህበረሰብ ለማሳወቅ በዓድዋ ድል መንፈስ በመረባረብ ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ክብሯ እንድትመለስ፣ ሕዝቡም በሰላምና በነፃነት የተረጋጋ ሕይወት እንዲመራ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲያራምዱ፣ ዜጎች በሀገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፣ እና ለመጪው ትውልድ ብሩህ ተስፋ እንዲፈነጥቅ መስራት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው። ከዚህ አንጻር ሁሉም በየፊናው ለኢትዮጵያ መፃኢ ተስፋ እውነትን ይዞ በውጭ ሀገራትና በሀገር ውስጥ አደባባይ እየወጣ አጋርነቱን ማሳየቱ ለኢትዮጵያውያን ኅብረት አንዱ ማሳያ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ለሺህ ዓመታት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረች እዚህ የደረሰችው ለውጭ ጠላቶች አልንበረከክም በሚለው አርቆ አሳቢነትና አስተዋይነት መሆኑን ሁሉም ልብ ሊለው ይገባል። ቅድመ አያቶቻችን በዓድዋ ተራራ ከውጭ ወራሪ ኃይል ጋር ፊት ለፊት ገጥመው የኢትዮጵያን ታላቅነት እንዳስመሰከሩ ሁሉ ይህ ትውልድም የውስጥ ችግሮቹን በመተጋገዝና በመረዳዳት መንፈስ በመፍታት አንድነቱን መጠበቅና ማስጠበቅ ይኖርበታል።
ወጣቱ ትውልድ ኢትዮጵያ ለገጠሟት ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች ምላሽ ለመስጠት ከሴረኞቹ በሚደርሱት የሃሰት መረጃዎች ሳይደናገር ለኢትዮጵያ ህልውና ሽንጡን ገትሮ መከራከርና በሀገሩ ጉዳይ ንቁና ብቁ ተዋናይ ሆኖ መገኘት ይጠበቅበታል።
በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ መደፍረስን በመታከክ አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት ጥረት የሚያደርጉትን አካላት ተዉ ማለትም የግድ ነው። አሁን ባለው ሁኔታም የሚስተዋለው የዲያስፖራውም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚኖረው ሕዝብ ለሀገሩ ያለው ንቃተ ህሊናና ድጋፍ ተስፋ የሚጭር ነው ማለት ያስችላል፡፡ በተለይም በዚህ ወቅት በየሀገራቱ የተመደቡ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ውሸትን በማጋለጥና እውነታውን በማስረዳት አገሪቱን መታደግ ቁልፍ ሥራቸው ሊያደርጉት ይገባል። የሀገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም ከማስከበር ባለፈ በኀዘኑም በደስታውም የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህልና ትውፊታችንን ለማጠናከር ዲያያስፖራው ለአገርና ለወገኑ ድጋፍ እንዲያደርግ የተጠናከረ ሥራ ሊሰሩም ይገባል።
በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ሆኖ ሳለ በሁለት መንግሥታት መካከል የሚካሄድ ጦርነት አድርገው ለመሳል የሚሞክሩ የጁንታው ርዝራዦችም ውሸት ዕድሜ እንደሌላት በማወቅና በመገንዘብ ከተያያዙት አፍራሽ ተግባር ሊቆጠቡ ይገባል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የራሷን ችግር ለመፍታት የውጭ ጣልቃገብነትን የማትሻ በመሆኗ መላው ኢትዮጵያዊ በአንዳንድ የውስጥና የውጭ ኃይሎች የተጠነሰሰውን የኢትዮጵያን ሥም የማጠልሸት ሴራን በአንድነት ለማምከን እንዲሁም ይህንን ወቅት ለመሻገር ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ የሚጠበቅበት መሆኑን ሊገነዘበው ይገባል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 7/2013 ዓ.ም