ከመፍትሄዎች እየራቁ ግጭቶችን ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ማንንም አያተርፍም !

የአማራ እና የትግራይ ሕዝቦች ለዘመናት በጉርብትና የኖሩ፤ ተመሳሳይ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እና ማህበረሰባዊ እሴቶችን የሚጋሩ ናቸው። በኢትዮጵያም የሀገረ መንግስት ግንባታ ታሪክ ውስጥ ሰፊ ስፍራ ያላቸው፤ ሀገርን አጽንቶ በማስጠበቅ ያላቸውም አበርክቶ ከፍያለ ነው። ጉርብትና በፈጠረው ወንድማማችነትም ዘመናትን በሰላም አብረው መኖር የቻሉ ሕዝቦች ናቸው።

እነዚህ ሕዝቦች በዘመናት ታሪካቸው ከሚጋሯቸው መንፈሳዊ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ እሴቶች የተነሳ፤ ቋንቋ ከሚፈጥረው መለያየት ባለፈ፣ በብዙ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብሮቻቸው ተመሳሳይነት የሚንጸባረቅባቸው ሕዝቦች ናቸው። ይህም በመካከላቸው የነበረውን ጉርብትና ወደ ላቀ ወንድማማችነት እንዲለወጥ አቅም የሚፈጥር ነው፤ ፈጥሯልም።

አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር በነበራቸው ሰፊ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ለዘመናት ክፉ እና ደግ ቀናትን አብረው አሳልፈዋል። ተጋብተው እና ተዋልደው ማህበረሰባዊ መስተጋብሩን ወደ ቤተሰባዊነት በመለወጥ ረጅሙን የግንኙነት የታሪ ክ ምእራፋቸውን ስኬታማ አድርገው መጥተዋል።

ከአስተዳደር መስመር እና ከቋንቋ ልዩነት በላይ የሆነው የሁለቱ ሕዝቦች ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት፤ በተለያዩ ወቅቶች የሕዝቦቹን የጋራ ፍላጎት መሠረት ባላደረጉ ፈተናዎች ውስጥ ለማለፍ የተገደደባቸው ሁኔታዎችም ተከስተውበታል። ሆኖም ፈተናዎቹን በዘመናት ውስጥ በተፈጠረ ጉርብትና፤ እና ጉርብትናው በፈጠረው ወንድማማችነት መሻገር ችለዋል።

ከዚህ የተነሳው የሕዝቦቹ የአብሮነት ትርክት፤ ከፍ ባለ ጉርብትና ላይ የተመሠረተ ወንድማማችነትን የሚያዜም እና የሚያጸና ነው። በተመሳሳይ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶች የተገመደ፤ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን፤ ከጥርጣሬ ይልቅ መተማመንን ማስረጽ የሚያስችል ነው።

ይህም ሆኖ ግን ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት እንደ ሀገር ከመጣንበት የተጎረባበጠ የፖለቲከ መንገድ የተነሳ፤ የእነዚህን ሕዝቦች የቀደመ አብሮነት እና ወንድማማችነት የሚፈታተኑ ክስተቶች ተፈጥረዋል። ባልተገባ ትርክት፤ አክሳሪ የፖለቲካ እሳቤ እና ሴራ ሕዝቦቹን እንደ ሕዝብ ወደ ግጭት ለመውሰድ ሰፊ ጥረቶች ተደርገዋል።

አንዳንድ ሃይሎች ቋንቋን መሠረት ባደረገ የአስተዳደር ወሰን መስመር ሕዝቦቹን ከፍለው ”አንተ ከእዚህ ነህ፤ አንተ ደግሞ ከእዚያ ነህ” በሚል ለዘመናት የቆየውን አብሮነታቸውን በማደብዘዝ፤ በመካከላቸው አለመተማመን እና ጠላትነትን ለመፍጠር፤ ይህንንም የፖለቲካ መቆመሪያ ካርድ አድርጎ ለመጠቀም ረጅም ርቀት ሄደዋል።

በተለይም አዲሱን ትውልድ በተዛባ የታሪክ ትርክት እና የሕዝቦችን የጋራ ማንነት በሚያደበዝዝ የሴራ ፖለቲካ ጠልፎ ለመጣል በስፋት ተንቀሳቅሰዋል። ባለፉት ሰባት አስርት ዓመታት የተፈጠሩ የሁለቱ ሕዝቦችን የለውጥ ፍላጎት ባልተገባ መንገድ በመግራትም፤ ለዚህ እኩይ ፍላጎት ማስፈጸሚያ ለማድረግ ሞክረዋል።

በዚህም ምክንያት የአስተዳደር ወሰኖችን የተመለከቱ አለመግባባቶች እንዲፈጠሩ ተደርጓል። አለመግባባቶችን የፖለቲካ መቆመሪያ ካርድ አድርጎ ለመጠቀም በተደረጉ ያልተገቡ ሙከራዎች በዋነኛነት ሁለቱ ሕዝቦች ተጎጂ ሆነዋል። ለግጭት እና በግጭት ለሚፈጠር መፈናቀል ተዳርገው፣ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ ሆነዋል።

እነዚህ በሕዝቡ የሚቆምሩ ሃይሎች ከትናንት ስህተታቸው መማር፤ ከጥፋት መንገዳቸው መመለስ ባለመቻላቸው ዛሬም በሕዝቦቹ መካከል አለመተማመንን እና ጠላትንትን ለመፍጠር እና ለማስቀጠል እየተጉ ነው። የሕዝቦቹ የዘመናት አብሮነት እና ከእዚህ የሚመነጨውን ወንድማማችነት በአስተዳደር ወሰን መስመር አግተው ወደ አልተገባ ግጭት ለመውሰድ እና ክእዚህም አትራፊ ለመሆን እየሠሩ ነው።

የሁለቱ ሕዝቦች የዘመናት የአብሮነት ታሪክ፤ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት እና በድርድር መፍታት የሚያስችል ነው። የሕዝቦቹ ዘመን አሻጋሪ ገዥ መንፈሳዊ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ እሴቶችም ቢሆኑ፤ በመካከላቸው ሊፈጠሩ የሚችሉ እና የተፈጠሩ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የገዘፈ አቅም እንዳላቸውም ይታመናል።

ችግሮችን አግባብ ባለው መንገድ ዘመኑን በሚዋጅ ሕገመንግስታዊ ስርዓት፤ በሰላማዊ መንገድ መፍታትም ሌላ ተጨማሪ አማራጭ ነው። ከዚህ ውጪ ለፖለቲካ ትርፍ ችግሮችን ፈጥሮ፤ ከመፍትሄዎቻቸው እየራቁ ግጭቶችን ለመፍጠር የሚደረግ የትኛውም አይነት ጥረት ሁለቱን ሕዝቦች፤ ከዛም አልፎ ሀገር እና ሕዝብን ላልተገባ ጥፋት ከመዳረግ ባለፈ ማንንም አያተርፍም። ዘላቂ መፍትሄ ሆኖ ሊቀጥልም አይችልም።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You