
ዜጎች በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ተንቀሳቅሰው የመኖር ሀብት የማፍራት… ወዘተ ሕገ መንግሥታዊ መብት አላቸው። ይህንን መብታቸውን የሚገዳደር ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያው ምክንያት የሕዝቦችን አብሮ የመኖር ዘመናት የተሻገረ ሀገራዊ እሴት ከመሸርሸር እና አካባቢያዊ አለመረጋጋት ከመፍጠር ባለፈ ተቀባይነት አይኖረውም።
እኛ ኢትዮጵያውያን እንደሀገር ጸንተን በዘለቅንባቸው ረጅም ዘመናት፤ በሀገሪቱ ያሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ሕዝቦች በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ከአንድ የሀገሪቱ ጥግ ወደ ሌላ የሀገሪቱ ጥግ፣ ከአንድ የሀገሪቱ ክፍል ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በመንቀሳቀስ ተስማምቶና ተፋቅሮ የመኖር ከፍ ያሉ ማህበረሰባዊ እሴቶች እና ትርክቶች ባለቤት ነን።
ዘመናት ባስቆጠረው የሀገረ መንግሥት ታሪካችን ውስጥ በሀገሪቱ ያሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ተከባብሮ እና ተቻችሎ በሰላም አብሮ ከመኖር ባሻግር፤ አንዱ ከአንዱ ጋር በወዳጅነት እና በጉርብትና ከእዛም አልፎ በጋብቻ ተሳስሮ ዘመናትን አስቆጥሯል። ይህም የሕዝባችንን አንድነት ያጠናከረ፣ እንደ ሀገር ያጋጠሙንን ፈተናዎች በጋራ ተሻግረን ዛሬ ላይ እንድንደርስ አድርጎናል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሕዝባችን እንደ አንድ ትልቅ ባለብዙ ታሪክ የጥንታዊ ሀገር ሕዝብ፣ መንደር እና መንደርተኝነት፣ ዘር እና ዘረኝነት በሚፈጥረው የተዛባ እሳቤ፣ “ማነህ? ከየት ነህ?” በሚል አጠቃላይ ማህበረሰባዊ ማንነታችንን በሚገዳደር የተዛነፈ የፖለቲካ ትርክት እና ትርክቱ በሚፈጥረው ጥፋት ተፈትኖ አያውቅም።
የቀደሙት ዘመናት ዜጎች ስለ ሕገመንግሥታዊ መብት የዳበረ መረዳት ሳይኖራቸው፣ ሕገ መንግሥት የሚባል ነገር ባልነበረበት ዘመንም፤ ሰብአዊ በሆኑ ማህበረሰባዊ እሴቶችን ታምነው፤ በልባቸው የተሳለውን እና የጸናውን ትልቁን ሀገራዊ ምስል ይዘው በፈለጉበት የሀገሪቱ ክፍል በእንኳን ደህና መጣችሁ ወንድማዊ አቀባበል፤ የራሳቸውን ኑሮ መስርተው አግብተው እና ወልደው ለሕይወት ስኬት በቅተዋል።
የአሁኗ ኢትዮጵያ መልክም በእዚህ መንገድ የተፈጠረ የማህበረሰብ አዎንታዊ መስተጋብር ውጤት ነው። እውነታው በየዘመኑ እንደ ሀገር ከተፈጠሩ አስተዳደራዊ መስመሮች ልኬት በላይ የገዘፈና መስመሮቹን ተሻግሮ የሄደ ነው። “ማነህ? ከየት ነህ?” ከሚል የተዛነፈ እሳቤ የመነጨ ሳይሆን ከወንድማማችነት ሰብአዊ እሳቤ የተቀዳ ነው።
ለእዚህ ደግሞ እንደ ሕዝብ በዘመናት ውስጥ ያካበትናቸው መንፈሳዊ፣ ማህበረሰባዊ እና ባሕላዊ እሴቶቻችን ዋነኛ አቅሞቻችን ነበሩ። ወንድማማችነት እና አብሮነትን፣ ጉርብትና እና ከጉርብትና የሚመነጭ ፍቅር እና መከባበርን አጽንተው የሚሰብኩት፤ እንደ ሕዝብ ትናንት ላይ ላሳለፍናቸው መልካም ቀናቶች ተጠቃሽ ናቸው።
ብዙዎቻችን ዛሬ ላይ የምንናፍቃቸውን እነዚህን ቀናቶች ለመመለስ፣ ከእዛም አልፈን እንደ ሕዝብ የተሻሉ ነገዎችን በጋራ ለመፍጠር እነዚህን ዘመናትን ያሻገሩንን ወርቃማ እሴቶቻችንን ዓይናችንን ከፍተን ልንመለከታቸው፣ የተዛነፈ ትርክቶች በላያቸው ላይ የፈጠሩትን አዋራ አራግፈን ዳግም ልናጸናቸው፣ የማህበረሰባዊ መስተጋብሮቻችን መሠረት ልናደርጋቸው ይገባል።
በተለይ አሁን ላይ እንደ ሀገር እየፈተነን፣ ከፈተናም ባለፈ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ያለውን የከፋ ራስ ወዳድነት፣ አግላይነት፣ ዘረኝነት፣ መንደርተኝነት፣ ከእዚህ የሚመነጭ ጽንፈኝነት፣ ዳተኝነት እና ባንዳነት ለዘለቄታ ለመሻገር እና በብዙ ትውልዶች ዋጋ የተከፈለበትን ሀገራዊ ሰላም እና ልማት ለዘለቄታው እውን ለማድረግ፣ ለእነዚህ ወርቃማ ማህበረሰባዊ እሴቶች ልባችንን መክፈት ይጠበቅብናል።
በተለይም አሁን ላይ ያለው ትውልድ እንደ አንድ ለለውጥ የተነቃቃ ትውልድ፣ ለራሱ እና ለመጪ ትውልዶች የተሻለች ሀገር ለመፍጠር የጀመረው መነሳሳት ተጨባጭ ፍሬ አፍርቶ በታሪክ ውስጥ የደመቀ ምዕራፍ እንዲኖረው ከሁሉም በላይ ለእነዚህ ወርቃማ ማህበረሰባዊ እሴቶቻችን ሁለንተናውን መስጠት፣ ለእዚህ የሚሆን ዝግጅነት መፍጠር ይጠበቅበታል። ይህንን በማድረግ፤ ትናንቱን አወቆ፣ ዛሬን አርሞ፣ ነገን የተስፋው መዳረሻ የማድረግ ትውልዳዊ መሻቱ አልፋ እና ኦሜጋ ነው!
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም