(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
የተውሶ ሐሳብ መዘከሪያ፤
ድህረ ፋሽስት ዓመታት (ከ1933 ዓ.ም በኋላ) ከተጻፉት ድንቅ የሀገራችን መጻሕፍት መካከል አንዱ የራስ ቢተወደድ መኮንን እንዳልካቸው “አርሙኝ” በቀዳሚነት ይጠቀሣል። መጽሐፉ የተለያዩ የቴያትርና የአጫጭር ልቦለድ ታሪኮች የተሠባሰቡበት ሲሆን፤ ታሪኮቹ በአብዛኛው የፋሽስቶችን አስከፊ ወረራና የተፈፀሙ ግፎችን በሥዕላዊ አቀራረብ የሚተርኩ ናቸው።
በተለይም ለዚህ ጽሑፍ ርዕስ ስመርጥ ትዝ ያለኝ ተቀራራቢ ሐሳብ “አልሞትኹም ብዬ አልዋሽም” የሚለው የመጽሐፉ አንድ ታሪክ ነው። ታሪኩ የወራሪዎቹን ግፍና የአንድን የጦር ሜዳ ጀግና እና የቤተሠቡን አሣዛኝ ፍጻሜ በሥዕላዊ ድርሠት ቁልጭ አድርጎ የሚያሣይ ስለሆነ የ”አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቤተኞች” መጽሐፉን ፈልገው እንዲያነቡ እየጋበዝኩ ለጽሑፌ ርዕስ መነሻ ስለሆነኝም ምሥጋዬን ለደራሲው በማስቀደም ወደዛሬው ጉዳዬ አቀናለሁ።
አስገባሪው ዘመነ ኢንፎርሜሽን፤
“የኢንፎርሜሽን ወጀብ” የዘመናችን ጠቅላይ ገዢ ከሆነ ሠነባብቷል። ይህ ዘመነ ቴክኖሎጂ በሁለት ወገን እንደተሣለ ሠይፍ አቅሙ የበረታና ተጽዕኖ ፈጣሪነቱም የጀገነ ስለመሆኑ እጅግም መሥካሪ አያስፈልገውም። “ድንበርና ወታደራዊ ኃይል ሣይገድበው” ዓለማችንን ከአጥናፍ አጥናፍ ተቆጣጥሮ “ዘመናይ ነኝ ባይ ትውልዳችንን” እያስገበረ ምርኮኛ በማድረግ ወደ ግዳይ ቀጣናው በፍጥነት እየገሠገሠ ሠፊዋን ዓለማችንን አጥብቦ መዳፋችን ውስጥ አስገብቶልናል።
ምን ማለት ነው?
ከጥቂት ዓመታት በፊት “ዓለም እንደ መንደር ጠባለች” እየተባለ የሚደሰኮረው እውነት ዛሬ…ዛሬ መልዕክቱ ጠውልጎ ጊዜው በፈጠራቸው እጅግ ውስብስብ ሚጢጢ ኮምፒውተሮች አማካኝነት “ዓለማችን እንደ መንደር መጥበብ ሣይሆን በሁለት ጣቶቻችን ውስጥ ገብታለች” ወደ ማለቱ ተሸጋግረናል። አባባሉ ጥቅም ላይ የዋለው እያንዳንዱ ሰው በየዕለቱ የእጅ ስልኩን ለመረጃ ልውውጥ በጣቶቹ ሣይጠነቋቁል እንደማይውል ለማሣየት ነው።
እንደ ቀደምት ዘመናት የመረጃ ዋና ምንጭ ተደርገው ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የየዕለቱን ጋዜጦች ለመግዛት ከማተሚያ ቤት ደጃፎች ላይ መሠለፉ ከቴክኖሎጂው ፍጥነት አንፃር ሲታይ ተረት ሆኖ ሊወራ ዳር ዳርታው የፈጠነበት ጊዜ ይመሥላል። በ1970ዎቹ እና በ1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ግድም ይህንን የአዲስ ዘመን ጋዜጣና በግፈኞች ግድያ የተሠዋችውን ታናሽ እህቱን “የዛሬይቱ ኢትዮጵያን” ገዝቶ ለማንበብ የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት ደጃፍ እንዴት በሠልፍ ይጥለቀለቅ እንደነበር ሣስብ የዘመኑ የሩጫ ፍጥነት በእጅጉ ይደንቀኛል።
የየዕለቱን ዜና በራዲዮና በቴሌቪዥን ለማድመጥም ምሽት ሁለት ሰዓት ቀጠሮ መያዙ አርጅቶ ካፈጀ ብዙ ሐሙሶች አልፈዋል። ምናልባትም የቴሌቪዥን መስኮታችንን የምንከፍተው ከዜና ጥማት ይልቅ የመዝናኛው ጉዳይ ግድ ብሎን ሊሆን እንደሚችል ይታመናል። የእነዚህ መደበኛ ሚዲያዎች (Mainstream Media) አገልግሎት እየፈዘዘ ያለው ለከተሜው ቤተኛ ብቻም ሣይሆን “ገጠሬው ባለሀገር” ደጃፍም አንቴናው፣ ዲሹና ዋይፋዬው እየተቃረበለት ስለሆነ የሥልጣኔው ልዩነት እዚያና እዚህ መባሉ ቀርቶ በፈጣን ርምጃ እየጠበበ በመሄድ ላይ መሆኑን በዓይነ ሥጋችን እያስተዋልን ነው።
በእጃችን መዳፍ ውስጥ የምናሽሞነሙነው የእጅ ስልካችን የዜና፣ የመዝናኛ፣ የትምህርት ምንጭ ብቻ ሣይሆን የሐሰትና የበሬ ወለደ መረጃዎችንም ከመቅጽበት ስለሚያደርስልን መደበኛ ሚዲያዎችን ከመፈለግ እንድንቆጠብ እያስገደደን ነው። መረጃዎቹ “የቅድስና” መሣለሚያዎች ብቻም ሣይሆኑ “የእርኩሰት” መናኸሪያም መሆናቸው በእጅጉ እያሣሰበ ስለመሆኑም አሌ አይባም። ለጠቃሚ ኢንፎርሜሽንና ትምህርት ሐሰሣ ፍላጎት ብቻም ሣይሆን “የጎንዮሽ ውጋት የሆኑ ኢሥነ ምግባራዊ ትዕይንቶችን የማነፍነፍ ፍላጎትም” ሕዝበ አዳምን የሱስ ያህል ስለተጠናወተው ሚሊዮኖችን አስገብሮ አሜን አሠኝቷል። “ለልጄ የእጅ ስልክ ገዝቼ የሰጠሁት ከሣጥናኤል ጋር አብሬ ነው” ያሉ የአንድ አባት ንግግር እውነታ ሁሌም እንዳስደነቀኝ አለ።
በዚህም ምክንያት እንደ አውሎ ነፋሥ ወጀብ ከግራ ከቀኝ የሚያላጋንን የኢንፎርሜሽን “ሱናሚ” ለመቋቋም ትንፋሽ አጥሮን “ስንንቦጫረቅ የምንውለው” ወደን ሣይሆን “ሱሱ” እያስገደደን ይሆን? ብሎ መጠየቁ ክፋት የለውም። ከአዛውንት እስከ ጨቅላ ሕጻናት፣ ከሹም እስከ ሠርቶ አደር፣ ከፖለቲከኛ እስከ ሃይማኖተኛ፣ ከተማሪ እስከ መምህር፣ ከነጋዴ እስከ አርሶ አደር ስንቱ ተዘርዝሮ ይዘለቃል? የእጅ ሥልኩን በጣቶቹ ሣይጠነቋቁል የሚውል የዓለም ዜጋ ማግኘት በእጅጉ ብርቅ የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
እንዲያው ለነገሩ ሞባይል ይሉት የእጅ ስልክ ሀገራችን ባልገባበት ዘመን እንደምን እንኖር እንደነበርና በምን ዘዴ ተቀጣጥረን እንደምንገናኝ ወይንም ሥራችንን እንደምንከውን ዞር ብሎ ማሰቡ በራሱ ጉዳዩን ይበልጥ ያጠራልናል። ጨከን እንበል ካልንም “የሞባይል ስልክ” ጨርሶ ከዓለም ላይ እንዲጠፋ “በተዓምራዊ ኃይል ቢወሰን” የምርኮኛው ሕዝበ አዳም ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል? ብሎ ማሰቡ ብዙ ያወያያል! ያስደምማል! ያስጨንቃል! ያሣስባል!
ትንፋሽ ያጠረው የሀገራችን ሚዲያ፤
የጭፍን ፍረጃ ሆኖ አይቆጠር እንጂ በርካታ የሀገራችን የኅትመትም ሆኑ የኤሌክትሮኒክስ መሪ ሚዲያዎች (Mainstream Media) ተሥፈንጣሪውን የቴክኖሎጂ ሩጫ ለመመከት ትንፋሻቸው የተመጣጠነ አይመሥልም። “ከጤፍ አቅም ጉርሶ” (ጤፍ እንኳንም ሥትፈጭ ሽርክት ሆና ቀርቶ በአፈጣጠሯም ጥንቱኑ ደቃቅ መሆኗን ለመግለጽ ነው) እንዲሉ በርካታ የሀገራችን ሚዲያ ዱሮውንም አልሆነላቸው ዘንድሮም የተዋጣላቸው አይመሥልም።
የኢትዮጵያ የሚዲያ ተቋማት ነፃ እንደሆኑ የሚሠብኩት ፖለቲከኞች እንጂ ጓዳ ጎድጓዳቸው የተተበተበው በአፈጀ የቢሮክራሲ አሠራር እንደሆነ የሚገለፀው በቤተኞች የሹክሽክታ ሐሜት ብቻም ሣይሆን በሩቅ ውጨኞችም ጭምር ነው። በብዙዎቹ የሚዲያ ተቋማት ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችና አመራሮችም “በቂ የትምህርት ዝግጅት እንጂ ቆራጥና የሕዝብ ወገነተኛነት ወኔ” እንዳልተላበሱ የሚታሙት በየአደባባዩ ነው።
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ለኢትዮጵያ የሚዲያ ተቋማት እጅግም ባዕድ አይደለም። ቢያንስ ከልጅነት እስከ እውቀት የሀገሩን የሚዲያ ጠረን በገለልተኛነት ቀረብ ብሎ በሚገባ ለማሽተት ዕድል ነበረው። በዚሁ የረዥም ዓመታት ተሣትፎውም ብዙ ታዝቧል፤ ትዝብቱንም በብዕሩና በድምጹ ሲያስተጋባ ኖሯል።
ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ የኢትዮጵያ የሚዲያ ባለሙያዎችና ሹማምንት የሚተማመኑት በአቋማቸውና በብዕራቸው ብርታት (Mighty Pen) ሣይሆን በፖለቲከኞች አለንላችሁ ባይነትና በመንግሥት የሥሜት ሙቀትና ቅዝቃዜ “ቴርሞ ሜትር” መለኪያነት ይመሥላል። እውነት ሥትሰቀል እያዩ “ይበላት!” የሚሉ ድንጋይ አቀባዮች ባሉበት ሀገር “ሚዲያ ነፃ ወጥቷል” ብሎ መናገር ድፍረትም እፍረትም ይሆናል።
“እንደ ንጉሡ ያጎንብሱ!” የሚል እሴት ያላቸው ሚዲያዎች የመብዛታቸውን ያህል በአንጻሩም “በቀስታቸው ጫፍ ላይ መርዝ ለቅልቀው የሚያስወነጭፉና በሬ እናዋልዳለን” ባዮችም ቁጥራቸው የት የሌለ ስለመሆኑ እንኳን እኛን መሠል የንባብና የዓይን ምሥክሮች ቀርቶ መንገደኛና አልፎ ሂያጅ ምንግዴዎችም ቢሆኑ በማተባቸውና በእምነታቸው እየማሉ እውነቱን መመሥከራቸው አይቀርም።
የሀገሬ ሚዲያዎች መቼ ተፈውሠው እንደሚፈውሱን ለመተንበይ ያሥቸግራል። ብዕራቸውን ከእምነታቸው ጋር አጋብተውና እውነትን አስቀድመው የሀገርና የሕዝብ ድምጽ ለምን መሆን እንዳልቻሉ ማሠቡም በራሱ አቅል ያሥታል። አረም የበዛበትን የማሕበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ተቋቁሞና ነጥብ አሥጥሎ በአሸናፊነት ከመውጣት ይልቅ ራሣቸው በአረሙ ተተብተበውና ተልኮስኩሰው ማየት እንደምን አያሣዝንም።
ክርስቶስ በምድር ይመላለስ በነበረበት አንድ ወቅት ርቦት ወደ አንዲት የበለስ ዛፍ ፍሬ ፍለጋ ጠጋ ብሎ ቢመለከት ቅጠል ብቻ መሆኗን ተመልክቶ እንደረገማት ሁሉ የእኛ ሚዲያዎችም “ፍሬያቸው በፍርሃት ዋግ እንዲመታ” ማን ረግሟቸው ለድርቀትና ለፍሬ አልባነት እንደተጋለጡ መመርመሩ አይከፋም።
እውነትን ተናግሮ ከመሸበት ከማደር ይልቅ “የመንግሥትንና የዙፋን ጠባቂውን ፓርቲ የዓይን ውሃ እየተመለከቱ” መኖር ምን ርካታ እንደሚሰጣቸው እየኖሩበት ያሉት ምንዳቤዎች (ችግርተኞች) በአደባባይ ቢናዘዙ የፈውሣቸው የመጀመሪያ ርምጃ ሊሆን በቻለ ነበር። “ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ” እንዳለችው የተረት እናት በርካቶቹ የሀገራችን ሚዲያዎች “አራተኛ መንግሥት” የመባሉ ለበጣ እንኳን ቀርቶባቸው የሚዲያን ትክክለኛ ባህርይ በወጉ ቢላበሱ ባልከፋ ነበር።
እንዲህ ጫን ብለን በድፍረትና በአደባባይ የምንገስጻቸው ወደን ሣይሆን “የሕዝብ ልሣን” የመሆናቸው ሥልጣን በአደባባይ ሲነጠቅ እያስተዋልን ነው። “የሞታቸውን አሟሟት” በግላጭ እየተመለከትን ማላቀሱ ፍሬቢስ መሆኑን ስለምንረዳም “ትንፋሽ አጥሯቸው” ባይዝለፈለፉብን እንመርጣለን። በተለይ…በተለይ ግን “የመንግሥታችን የማደጎ ጨቅላ ሕጻናት የሆኑ” አንዳንድ ሚዲያዎች “በጥበብ፣ በቁመት፣ በሞገስ” በሕሊናቸውና በሕዝብ ልብ ውስጥ አድገው የምናይበት ቀን አብዝቶ ያጓጓናል።
የሦስት አሠርቱ ሙት ዓመት በሚዘከርለት ዘመነ ደርግ የተፈፀመ አንድ ታሪክ ትዝ ይለኛል። “ሠርቶ አደር” በሚል ሥያሜ ይታወቅ የነበረው የሥርዓቱ ጋዜጣ የመጀመሪያ ዕትም ይፋ ሆኖ እንደ ምረቃና መተዋወቂያ በቃጣው አንድ መርሃ ግብር ላይ ከታደሙት እንግዶች መካከል ነፍሰ ሄር ጸሐፌ ተውኔት መንግሥቱ ለማ አንዱ ነበሩ። በዚህ ፕሮግራም ላይ በክብር እንግድነትና በአስተዋዋቂነት መድረኩን የተቆጣጠሩት የሀገሪቱ ሁለተኛ ሰውና ጎምቱ ሹም ነበሩ። እኒህ “ለምድርና ለሠማይ የከበዱ ደርገኛ ባለሥልጣን” ስለ ጋዜጣው ጅማሮና አስፈላጊነት ብዙ ሐተታ ከሰጡ በኋላ በዚያ ጉባዔ ውስጥ የተገኙት እንግዶች በሙሉ “የጋዜጣው ዓምደኛ መሆን እንደሚገባቸው” ትዕዛዝ አከል ሐሳብ በመሠንዘር “መድረኩን ለውይይት ክፍት” አደረጉ።
በዚህ አጋጣሚ ነበር “ተረበኛው” አብዬ መንግሥቱ ለማ እጃቸውን ከፍ አድርገው በማውጣት የንግግር ፈቃድ ሲሰጣቸው ሐሳባቸውን እንዲህ በማለት የገለጡት። “ምን ችግር አለ! ዕድሜ ለፀሐዩ መንግሥታችን ይሁንና” (ይህ አገላለጽ የእኔ የጸሐፊው የብዕር እልፊት መሆኑ ይታወቀልኝ) አረንጓዴ ጽሑፍ ጻፉ ባላችሁን ጊዜ ጽፈናል፣ ቀይ ጽሑፍም ጻፉ ብትሉን አይገደንም! አሣምረን እንጽፋለን!” (ቀለማቱን የመረጡት ሆን ብለው ነበር። በወቅቱ አረንጓዴ ዘመቻ በመባል የሚታወቀውን ንቅናቄና የሠርቶ አደር ጋዜጣና የኮሚኒስቶቹ ቀለም ቀይ መሆኑን በምፀት ለመሸንቆጥ አስበው መሆኑን ልብ ይሏል።) አብዛኞቹ የዛሬዎቹ ሚዲያዎቻችንም ከዚህ ተረብ ነጻ የወጡ ስላልሆኑ ደርግን አስፈቅደን በዘመነ ብልጽግና አባባሉን እንዳለ ብንዋስ ቀጭም ሆነ ተቆጭ ይሠለጥንብናል ብለን አንፈራም፤ አናፍርምም።
በልባችን ያመቅነውን ይህን መሠሉን መራር ትዝብት ይዘን ከመሞት እንደ “አርሙኝ” መጽሐፉ ገፀ ባሕርይ እንደ አቶ ተማቹ “አልሞትኹም ብዬ አልዋሽም” ብለው ሚዲያዎቻችን እንዲናዘዙ መጠቆሙ የወዳጅ ምክር እንጂ በጠላትነት አያሥፈርጅም። በውድድር ሜዳው ትንፋሽ አጥሮ ከመሞታቸው አስቀድሞ እያበረታታን ብናጀግናቸውስ ክፋት ይኖረዋል? በግሌ አይመሥለኝም።
ታሪክን የኋሊት፤
“አዲስ ዘመን” ጋዜጣችን የሰማኒያ ዓመት ድፎ ዳቦ የተቆረሠለት በቅርቡ ነው – “አቦይ መልካም ልደት!”። ተወዳጇን የዛሬይቱ ጋዜጣ ኢሕአዴግ ከቀበራትም እንዲሁ ሦስት ዓሠርት ዕድሜ ልትደፍን ነው። ጥንታዊያኑ “ብርሃንና ሠላም እና አዕምሮ” በሚል አርዕስት ይታተሙ የበሩት ጋዜጦችም ታሪካቸው እንጂ መቃብራቸውን ዳዋ ለብሶታል። ከፋሽስት ወረራ በኋላ መተታም የጀመሩትና ለዲፕሎማቲክ ማሕበረሰቡ “የወሬ ምንጭ” ሆነው ያገለግሉ የነበሩት በእንግሊዘኛ፣ በፈረንሣይኛና በኢጣሊያንኛ ይታተሙ የነበሩት በርካታ ዕለታዊ፣ ሣምንታዊና ወርሃዊ ጋዜጦችም ካሸለቡ የአንድ ትውልድ ዕድሜ አልፏቸዋል። የኢትዮጵያ ራዲዮም ለዘጠና ዕድሜ ጥቂት ፈሪ ቀርቶት ምርኩዝ ጨብጦ እያዘገመ እንዳለ እያስተዋልን ነው። በቀደም ዕለት በእርጅናው ከወለደው ከFM 97.1 ልጁ ጋር የረዥም ዘመን ታሪኩን አውግቶንና ምሣ ጋብዞን አስደስቶናል። እግዜር ይስጥልን።
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም የሥልሳ ዓመት ጎልማሣ ለመባል የቀሩት በጣት የሚቆጠሩ ዕድሜዎች ናቸው። የዕድሜውን ያህል ለአንቱታ ስለመብቃትና ያለመብቃቱ እኛና እግዜሩ ጠንቅቀን እናውቀዋለን። ፋናና ዋልታም እንደ እንቦሣ እየቦረቁ በመፈንጠዝ ላይ ስለሆኑ በደስታቸው ላይ ውሃ አንቸልስም። የክልሎቹን፣ የፖለቲከኞቹንና የግሎቹን እያልን በኅትመቱና በኤሌክትሮኒክስ መደባቸው በዘርፍ በዘርፉ እንዳንተነትን “ቀባሪ እንዳናጣ ፈርተን እንጂ” ብዙ ለማለት ሐሳብ አጥሮን አይደለም። ለማንኛውም የሀገሬ ሚዲያዎች ሆይ! “አልሞትኹም ብዬ አልዋሻም” እንዳለው ጀግና ከእንቅልፋችሁና ከሽልብታችሁ እንድትባንኑ በሕዝብ ድምጽ እንቀሠቅሳችኋለን። እረገኝ! እረገኝ! ለካንስ ሥድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ተቃርቧልና? ሠላም ይሁን!
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2013