በየዕለቱ እየጨመረ የመጣው የዋጋ ግሽበት በሁሉም የፍጆታ ዕቃዎች ላይ እየተስተዋለ ይገኛል። በተለይም በዋና ዋና የሀገሪቱ ከተሞች የኑሮ ውድነቱ እየዬ ያሰኛል። ያም ቢሆን ግን ዜጎች ለመኖር መብላት ግዳቸው ነውና የቻሉትን ያህል ሸምተው ይመገባሉ። በአሁኑ ወቅት በተለየ ሁኔታ የእህል ዋጋ እንደ ሰማይ እየራቀ መምጣቱ ግን ዜጎችን ይበልጥ እያስጨነቀ ነው ።
በአዳማ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ኩሪ በዳዳም የእህል ዋጋን ጨምሮ አጠቃላይ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ መናር ከሚያስጨንቃቸው ዜጎች መካከል አንዷ ሲሆኑ፤ የእህል ዋጋ አዳማ ከተማ ላይ የጨመረው ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነም ያስታውሳሉ። ምንድነው ሲባል በልግ ዝናብ በመጥፋቱ በበልግ መሸፈን የሚገባው ማሳ ባለመሸፈኑ የሚል ምላሽ ይሰጣል። ዓምና በ2012 ዓ.ም ምክንያቱ በማይታወቅ ሁኔታ የእህል ንረቱ ቀጥሎ ደረጃ በደረጃ እያደገ ዛሬ ላይ ተደረሰ። ዘንድሮ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተደረገው ጭማሪ ታሳቢ ተደርጎ አንድ ኪሎ ማኛ ጤፍ 47 ብር ኩንታሉ ደግሞ አራት ሺ 700 ብር እየተሸጠ ይገኛል። ይህ ዋጋ ማስፈጫውንና የጉልበት ዋጋን ሳይጨምር ማለት ነው።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሻፊ ኪቤ እንደሰጡን አስተያየት አንድ ኪሎ አጃ በ100 ብር እየተሸጠ ነው። አጃውን አብስሎ ለመብላት የሚያስችለው ዘይቱ፣ ማገዶውና ማጣፈጫው ሲታሰብ የወጪው ብዛት እቤት ውስጥ አብስሎ ለመመገብ እጅግ አዳጋች መሆኑን ይናገራሉ ። በአሁኑ ወቅት በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሕብረተሰብ በልቶ ለማደር እየተሳነው ነው። በአብዛኛው ሕብረተሰብ ዘንድ ለምግብነት ሲፈለግ የማይታየውና ከዚህ አኳያ ዋጋው እርካሽ የነበረው በቆሎ እንኳን ዋጋው የጨመረበት ዘመን ላይ ነን ያለነው። በቆሎ አምና ኪሎው 15 ብር ኩንታሉ ደግሞ አንድ ሺ 500 ብር ነበር። ዘንድሮ ደግሞ አንድ ኪሎው 20 ብር ኩንታሉ ሁለት ሺ ብር ገብቷል።
በቆሎ በዚህ ደረጃ ዋጋው ከናረ አንድ ዳቦ ከሦስት እስከ አምስት ብር ከተሸጠ ታች ያለውና ምንም ገቢ የሌለው የህብረተሰብ ክፍል ምን በልቶ ሊውልና ሊያድር እንደሚችል ሲያስቡት ያስጨንቃቸዋል። ብዙ ልጅና ቤተሰብ ያለው ሰው ጉዳይም እንዲሁ ያሳስባቸዋል። አሁን ላይ በአዳማ ከተማ ስንዴ በየደረጃው፣ ቦሎቄ ፣ የባቄላና የአተር ሽሮ እንዲሁም የጥራጥሬ ዋጋ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል። የሀገር ውስጥና የውጪ ሩዝ በፊት ከነበረበት ዋጋ ከእጥፍ በላይ የጨመረበት ወቅት ነው። በፍፁም መኖር የሚያስችል አይመስልም። መኮሮኒ በኪሎ ከጤፍ ዋጋ በተቀራረበ በአርባ ብር እየተሸጠ ነው። እንዲህ ሆኖም ሁሉም ዜጋ በልቶ ማደሩ ያስገርማቸዋል። ‹‹እየኖርን ያለነው በእግዚአብሄር ኃይል ነው›› ሲሉም አቶ ሻፊ አስተያየታቸውን ይቋጫሉ።
በአዳማ ከተማ ከሚገኙ ወፍጮ ቤቶች የአንዱ ባለቤት የሆኑት አቶ ነገው ዋቅጅራ እንደሚሉት ኩንታል ጤፍ አራት ሺ 600 መቶ ብር ነው እየሸጡ የሚገኙት። ቁጭ ከማለት ብለው እንጂ የሚያስገቡት የእህል ዋጋ ከሚሸጡበት ዋጋ ምንም ያህል ያልተናነሰ ነው። በኪሎ የሚያገኙት ትርፍ ከአንድና ከሁለት ቢበዛ ለጫኝና አውራጅ እንዲሁም ለትራንስፖርት የሚያወጡትን ጨምሮ ከአምስት ብር አይበልጥም። በቆሎ፣ ስንዴ፣ ማሽላና ዘንጋዳ ጨምረዋል። ሆኖም ግን በላተኛው የተመጣጠነ ምግብ ለማግኘት ሲል እየደበላለቀ በማስፈጨት ይጠቀማል።
ከግብርና ሚኒስቴር ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት እንዳገኘነው መረጃ ዘንድሮ በልግ አብቃይ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሙሉ ያሉ ማሳያዎችን በተለያዩ የሰብል ምርቶች ለመሸፈን የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተከናውኗል። ማሳዎች ታርሰው ለዘር የተዘጋጁበት ሁኔታ አለ። ለሀገሪቱ በቀዳሚነት ከፍተኛ ምርት በሚያቀርበው በኦሮሚያ ክልል የክልሉ ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ እንደገለፁልን በዘንድሮ ዓመት 965 ሺ ሄክታር ማሣ የበልግ ምርት ለማልማት ታቅዷል። 500 ሺህ ሄክታር መሬትም ታርሶ ለዘር ተዘጋጅቷል።
እንዲሁም በቀዳሚነት ለሀገሪቱ ከፍተኛ የምርት አቅራቢ በሆነው የአማራ ክልል በዚሁ በዘንድሮ በልግ ምርት ዘመን ወቅት 325 ሺህ ሄክታር ማሳ ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ አለባቸው አሊጋዝ ገልፀውልናል። እንዲሁም የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው እንደገለፁልን በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ለማልማት ከታቀደው አንድ ሚሊዮን 18 ሺ ሄክታር ውስጥ 500 ሺ ሄክታር ማሣ ታርሶ ለበልግ ምርት ዘመን ተዘጋጅቷል። 70 ሺ ሄክታሩም በዘር ተሸፍኗል። ኃላፊዎቹ እንዳስረዱት ይህ በተለይም የ2012/13 የምርት ዘመን ተሰብስቦ የገባው እህል የምግብ እጥረትን ይቀርፋል የናረውን የእህል ዋጋም የሚያረጋጋ ይሆናል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2013