ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ሀገር.. የአበው የሊቃውንት መፍለቂያ፣ የጥበበኞች እልፍኝ መንደር ናት። የራሷ የሆነ የዘመን አቆጣጠር ያላት፣ የራሷ የሆነ ፊደል የራሷ የሆነ አኩሪ ባህል ያላት፣ ከሰማኒያ በላይ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ተፈቃቅረውና ተቻችለው የሚኖሩባት የገነት ህዝቦች መኖሪያም ናት። እኛ ለዓለም ጥበብን ያሳየን፣ የእውቀት የስልጣኔ ፈር ቀዳጆች፣ በዚህኛውና በዚያኛው ዓለም የነበርን በኩረ ዘፍጥረት ቀዳማውያን ነን።
ኢትዮጵያዊነት ሲነሳ አብሮ የሚነሳ በርካታ ታሪክና ትውፊት አለን። ከሀበሻዊነት ጋር የተቆራኙ ዘመን ተሻጋሪ ገድሎች ወግ፣ ባህል፣ ልማድ፣ ስርዓት፣ ታሪክ፣ ቅርስ፣ አለባበስ፣ የሰርግና የለቅሶ ሥነሥርዓቶች እኚህ ሁሉ የእኛ መገለጫዎች ናቸው። በየትኛውም ዓለም የሌሉ የእኛ ብቻ የሆኑ ሀበሻዊ ጥበብ፤ ሀበሻዊ ሥርዓት ኢትዮጵያዊ ቀለም አለን። ይሄን ታላቅነታችንን ተመልክተው ጥንታዊ የግሪክ ጸሀፍቶች ስለ ኢትዮጵያና ስለህዝቦቿ ብዙ ብለዋል። እንዳውም በግሪክ የሥነ ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ እንደ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ የተወሳ፣ የተደነቀና የተሞገሰ ሀገርና ህዝብ የለም። ከግሪክ አማልዕክቶች አንዷ አትዮጵያዊቷ ንግስት ካሲዮጳ እንደሆነች ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ? አምነን መቀበል አልቻልንም እንጂ ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ጥበበኞች መፍለቂያ ሀገር ናት። እውቀትን ለተለያዩ ዓለም ሀገራት ያስተማሩ ጥንታዊ አባቶች ነበሩን። ስልጣኔን፣ ዘመናዊነትን ለዛሬዎቹ ልዕለ ሃያላን የሰጠን እኛ ነበርን። የዛሬዋ ዓለም የኢትዮጵያ አባቶች የተጽዕኖ ውጤት ናት ብል አጋነንክ እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ። እኛ አምነን አልተቀበልንም እንጂ ዓለም ታላቅነታችንን የዘከረችበት ብዙ አጋጣሚዎች ነበሩ። እኛ አምነን አልተቀበልንም እንጂ ብዙ የዓለም ሀገራት ኩሩና ቀደምት ስልጡን ህዝቦች ሲሉ እውቅና ሰጥተውናል።
በቀላሉ እንኳ በጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ የሰላም ኖቤል ሽልማት ፕሮግራም ላይ የዓለም የኖቤል ኮሚቴ ሊቀ መንበር ቤሪት ሬይስ አንደርሰን የተናገሩትን ማስታወስ በቂ ነው…. ‹ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ናት። ስለዚህም ሁላችንም የዓለም ህዝቦች ኢትዮጵያዊ ነን› ነበር ያሉት። ከዚህ በላይ ክብር፣ ከዚህ በላይ ምን ልዕልና አለ? እኛ አምነን መቀበል አልቻልንም እንጂ ዓለም በአንድነት ያጨበጨበልን ስልጡንና ገናና ህዝቦች ነበርን። ሌላው ለሁላችንም ትምህርት የሚሆንን
አንድ ነጭ ስለ ኢትዮጵያ የተናገረውን ልንገራችሁ። ፈረንጁ ከፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማ ጋር ወዳጅ ነው፤ በጨዋታቸው መሃል እንዲህ አለ ‹ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ሳስብ በጣም የሚገርመኝ አንድ ነገር አለ፣ እኛ ምንም የሌለን ነጮች በኢትዮጵያ ተፈጥሮ ቀንተን እናተን ለመሆን በምንጥርበት በዚህ ጊዜ እናንተ ምንም የሌለንን እኛን ለመሆን የምታደርጉት ጥረት ሁሌ ይገርመኛል ነበር ያለው። ወደ ራሳችን እንመለስ፣ ወደታላቅነታችን እናማትር። ምን እንደነበርን እናስታውስ። ሁሉን አጥተን ባክነን የምንኖረው ማን እንደሆንን ስላላወቅን ነው። በድህነት በኋላ ቀርነት ስማችን የሚነሳው እንደ ቀደሙ አባቶቻችን ህብረት ስለሌለን ነው።
ማሰብ ብንችል ኖሮ ከላይ የተገለጹት አባባሎች እኛን ለማስተማር በቂዎች ነበሩ። የእኛን ያክል በተፈጥሮ ሀብት ያልታደሉ በርካታ ሀገራት አሉ። የእኛን ያክል ወጣት የሌላቸው ፤ የእኛን ያክል የህዝብ ቁጥር የሌላቸው ብዙ ሀገራት ሞልተዋል። ግን ከእኛ በተሻለ እየኖሩ ነው። በፖለቲካ በኢኮኖሚ በስነ ልቦና በልጠውን ከፊታችን ናቸው። እኛ አንድነት አጥተን ስንባላ፣ ፍቅር አጥተን ስንናቆር እነሱ በስራ ላይ ነበሩ። እኛ የተሰራ ስናፈርስ እነሱ ግንባታ ላይ ነበሩ። እኛ እዚም እዛም ሰው ስናፈናቅል፣ ወንድም እህቶቻችንን ስንጎዳ እነሱ በሚያስገርም አንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘው ተአምር እየሰሩ ነበር። ወደ አባቶቻችን እንመለስ ወደ ቀደመ ፍቅራችን፣ ወደሚደነቀው አንድነታችን እናማትር። በአባቶቻችን ጎዳና ላይ እንራመድ። ዳናቸውን እንከተል። ኢትዮጵያ የአራዳዎች መፍለቂያ ሀገር ናት፣ ይሄን ደግሞ ብዙዎች መስክረዋል። ከጥንት እስከዛሬ በጀግንነታቸው በሀገር ወዳድነታቸው በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ የሚታወሱ ሀገር ወዳድ አራዳዎች አሉን። እኔና እናተ የአራዳነት ትርጉም ጠፍቶን እርስ በርስ እንባላለን። እርስ በርስ እንጋፋለን። አራዳነት መልካምነት ነው። አራዳነት በደልን መርሳት ነው። አራዳነት ለህዝብና ሀገር ዘብ መቆም ነው። የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጸሀፍቶች አራዳነትን ከመልካም ስብዕና ጋር ያዛምዱታል። አራዳነት በጎ ተግባር እንደሆነ የሚናገሩም ብዙዎች ናቸው። ለሀገር መሞት፣ ሀገርን በእውነተኛ ስሜት ማገልገል አራዳነት ነው። ብዙ አራዳዎችን ያፈራች ሀገር ዛሬ ላይ አራዳ ነን በሚሉ ፋራዎች ስትታመስ ማየት የእውነት ያማል። ብዙ ነገር እያለን ምንም እንደሌለው ሀገርና ህዝብ በድህነት መኖራችን እንደ ዜጋ ያስቆጨኛል።
ዓለም ጥልና ክርክርን ንቆ በስልጣኔ ጫፍ በደረሰበት ዘመን እኛ እርስ በርስ መጋፋታችን ያናድደኛል። ተሳስረን ተጋምደን እንዳንለያይ ሆነን ተደባልቀን እንኳን ከሚያዛምዱን ብዙ ነገሮች ይልቅ የሚለዩንን ትንሽ ነገሮች እየፈለግን እንባላለን። የድሮ አባቶቻችን በአንድ ልብ በአንድ ሃሳብ ለአንድ እውነት የቆሙ ነበሩ። ታላቂቷን ሀገር ከፊት አስቀድመው ከኋላ የሚከተሉ በክፉና በደጉ ያልተለያዩ ህዝቦች ነበሩ። በዚህም ዘመናዊ ጦር ታጥቆ የመጣውን ጣሊያንን አሸንፈው በነጻነቷ ከአፍሪካ አልፋ ለመላው ጥቁር ህዝቦች አርአያ የሆነችን አገር ፈጥረውልናል። በኡጋዴን በአንባላጌ በካራማራ ርስታችንን ለጠላት አሳልፈን አንሰጥም ሲሉ ደማቸውን አፍስሰዋል፤ አጥንታቸውን ከስክሰዋል። ባህል ወግ ሥርዓታቸውን ጠብቀው በአብሮነት ኖረው አልፈዋል።
እነሱ አራዳ ካልተባሉ ማን ሊባል ነው? እነሱ ካልተደነቁ ማን ሊደነቅ ነው? አባቶቻችን ድልድዮቻችን ናቸው፣ አባቶቻችን ስልጣኔዎቻችን ናቸው። እነሱ ዛሬን የሰሩልን ዛሬን የፈጠሩልን ህልውናችን ናቸው። እንከታላቸው፣ ነፍሳችንን ከነፍሳቸው እንደባልቅ። እነሱ እኮ ክፉ ሆነው አያውቁም የማረኩትን ጠላት እንኳን በምርኮ ይዘው ከሚበሉት የሚያበሉ፤ ከሚጠጡት የሚያጠጡ፤ አልጋቸውን ትተው መሬት የሚተኙ የመልካምነት ማሳያዎች ነበሩ። አራዳነት እኮ በሀገር ፍቅር መሞት ነው። በአንድነት በፍቅር መቆም ነው። አራዳነት እኮ ሀገር ከምንም በላይ እንደሆነች ማመን ነው። ለሀገርና ህዝብ ሲሉ የራስን ጥቅም አሳልፎ መስጠት ነው።
የአሁኑ ትውልድ ይሄ አልገባውም ለእኛ አራዳነት ጥሩ መልበስ ነው የንግግር ዘይቤን መቀየር ነው። መዋሸት ማታለል፣ ሴቷ ከብዙ ወንዶች ጋር ወንዱ ከብዙ ሴቶች ጋር መታየት ነው። ሱሪን ዝቅ አድርጎ መልበስ ነው፣ ለእኛ አራዳነት መስረቅ መዘሞት ነው። መደነስ ፤መጨፈር፤ መቃም ፤ማጨስ እንዲህ ነው። ጸጉርን ማንጨፍረር ጆሮ ላይ ሎቲ መሰካት እንዲህ ነው። ከሀገር ላይ መስረቅ ህዝብ ማጭበርበር እንዲህም ነው። እንዳባቶቻችን በአንድ ልብ በአንድ ሃሳብ እስካልተጋን ድረስ የምንመኛትን ኢትዮጵያ መፍጠር አይቻለንም። አባቶቹን የሚመስል እንደ አባቶቹ የሚያስብ ሀገርን የጉዳዩ አንደኛ ያደረገ ትውልድ እንዲፈጠር ያስፈልጋል። አሁን እጅግ ስልጡን ዘመን ላይ ነን ለመክሰርም ለመለወጥም ሁሉም ነገር ቅርባችን ነው። ሳይማሩ አራዳ በሆኑ አባቶቻችን የቆመችውን ሀገር በተሻለ ከፍታ ላይ እናያት ዘንድ ከዚህ የተሻለ ምቹ ጊዜ የለንም። ከሁሉም በላይ ግን ኢትዮጵያን እንወቃት፤ክብሯንም የሚመጥን ተግባር እንከውን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2013 ዓ.ም