ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የሶስት ወራት እድሜ ብቻ ይቀራል፡፡ በእስከ አሁኑ የምርጫው ዝግጅት በተለይ በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል በርካታ ተግባሮች ተከናውነዋል፡፡ ባለፈው ዓመት መካሄድ የነበረበት ይህ ብሄራዊ ምርጫ በኮቪድ 19 የተነሳ ወደእዚህ ዓመት እንዲዛወር ከመደረጉ በስተቀር ሁሉም የምርጫ ሂደት በታሰበው መልኩ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎች ተለይተዋል፤ ምልክቶቻቸውም ታውቀዋል፤ የእጩዎች ምዝገባ ተጠናቅቋል፤ የምርጫ ቅስቀሳዎችም ተጀማምረዋል፡፡ በምርጫው ለመሳተፍም 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ 8ሺ209 እጩዎችን ማስመዝገባቸውን ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ ከእጩዎቹ መካከልም 125ቱ በግል ለመወዳደር የቀረቡ ናቸው፡፡
እነዚህ ከምርጫው ሂደቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የመራጮች ምዝገባና የተፎካካሪ ፓርቲዎችና የግል ተወዳዳሪዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ እና የመድረክ ላይ ክርክሮ ች በጉጉት እየተጠበቁ ናቸው፡፡
መንግስት ምርጫው ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲፈልጉት የኖሩት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚጀመርበት እንዲሆን ከለውጡ ማግስት አንስቶ በትኩረት ሰርቷል፡፡ የለውጡ አመራር ለፖለቲካ ሃይሎች ሁሉ ያደረገውን ጥሪ ተከትሎም በሀገራችን ተንሰራፍቶ የቆየውን አፋኝ አገዛዝ ሸሽተው በውጭ ሀገር ይኖሩ የነበሩ፣ መሳሪያ አንስተው ጫካ ወይም በረሃ የገቡ ፖለቲከኞች ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡ በእስር ላይ የነበሩትም ተለቀዋል፡፡ ሁሉም ለውጡ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የፖለቲካ አመለካከታቸውን ሲያራምዱ ቆይተዋል፡፡
ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዳይኖር እንቅፋት ሆኖ የቆየውን የቀድሞውን የምርጫ ህግ በማሻሻል የተጀመረው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የመገንባቱ ስራ በሀገሪቱ የምርጫ ታሪክ ገለልተኛ ያልነበረው ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በቦርዱና በተሻሻለው የምርጫ ህግ መሰረት የምርጫው ሂደት እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ፓርቲዎች በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር ሁሉም ፓርቲዎች በምርጫው ለመሳተፍ ቦርዱ እና የምርጫ ህጉ የሚጠይቁትን ሁሉ አሟልተው በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ማከናወን ያለባቸውን አከናውነዋል፤ እያከናወኑም ናቸው፡፡
ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነት የሚበጀውም ይሄው ነው ፡፡ በምርጫ ለመወዳደር ዝግጁ እንደሆነ ፓርቲ በቦርዱ
የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መጓዝ ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነት ዝግጁ ሆኖ የመገኘት መገለጫ ተደርጎም ሊወሰድ ይገባዋል፡፡ ዝግጁነቱ በዚሁ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
ለምርጫው ዝግጁ ሳይሆኑ የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ እያሉ ከዚህ ታላቅ የምርጫ ማእድ የወጡ እንዳንድ ፓርቲዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ሊያጋጥሙ በሚችሉ ተግዳሮቶች መሸነፍም አይገባም፡፡ ይህን ሁሉ አልፋችሁ በምርጫው ለመሳተፍ የተመዘገባችሁ ፓርቲዎች እንደ እስከ አሁኑ ሁሉ በምርጫ ቦርድና በራሳችሁ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ዝግጅታችሁን አጠናክሩ፡፡
አገር እመራለሁ ብሎ የተነሳ ፓርቲ በፓርቲ የውስጥ እና አንዳንድ ውጫዊ ችግሮች መፈታት የለበትም፡፡ ችግሮችን በራሳችሁ ለመፍታት ከመሞከር በተጨማሪ መንግስትን ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ከሌሎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት እውን መሆን ከሚሰሩ ተቋማት ጋር ስሩ፡፡
ፓርቲዎችም ሆናችሁ የግል ተወዳዳሪዎች የህዝብ ወኪሎች ናችሁ፡፡ ህዝቡ ሀገሪቱ ለዘመናት ስትፈልገው የኖረችው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን ይፈልጋል፤ የሀገሪቱና የመንግስትም ፍላጎት ይሄው ነው፡፡ ይህን ተረድቶ መስራት ከፓርቲዎች ይጠበቃል፡፡ ይህ ደግሞ ለችግሮች በቀላሉ አለመበገርን ይጠይቃል፡፡
በዚህ ምርጫ የውስጥ ችግሮቻቸውን በወቅቱ ፈተትው በምርጫው መሳተፍ የነበረባቸው አንዳንድ ፓርቲዎች ይህን ባለማድረጋቸው ከምርጫው ውጪ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ መንግስት ይህን ያን ካላደረገ በምርጫው አንሳትፍም ብለው ራሳቸውን ከምርጫው አግልለዋል፡፡ ይህ የህዝብን አደራ እንደ መብላት ይቆጠራል፡፡ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን ብለው ለዘመናት የከፈሉትን መስዋእትነት ዋጋ ማሳጣትም ይሆናል፡፡
አሁን በምርጫው ለመሳተፍ ተመዝግባችሁና እጩዎቻችሁን ያዘጋጃችሁ ፓርቲዎች በቀጣይም ፈተናዎች ሊገጥሟቸው እንደሚችሉ አምናችሁ ፈተናዎችን ለመፍታት ከወዲሁ መዘጋጀት ይኖርባችኋል፡፡
በቀጣይ የምርጫ ቅስቀሳ ስራዎችና የመድረክ ላይ ክርክሮች በስፋት እንደሚካሄዱ ይጠበቃል፡፡ እነዚህ ደግሞ በህዝብ ውስጥ የሚከናወኑ ተግባሮች ናቸው፡፡ በዚህ ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችን በጥበብ ማለፍ ያስፈልጋል፡፡
መንግስት በለውጡ ወቅት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት በገባው ቃል መሰረት እየሰራ ስለመሆኑ የእስከ አሁኑ የምርጫ ሂደት ያመለክታል፡፡ ምርጫው ዴሞከራሲያዊ ፣ፍትሃዊ፣ ተአማኒና ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ለማድረግ መስራቱን አሁንም አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በቀጣይም ምርጫውን ሊያጠይም የሚችል ምንም አይነት ደንቃራ ሲያጋጥም ፈጥኖ ለማስወገድ በመስራት ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ማረጋገጡን ማጠናከር ይኖርበታል፡፡
ምርጫው በጊዜ ሰሌዳው መሰረት እየተፈጸመ ነው፡፡ ቀሪው ጊዜ ውስን ነው፡፡ ይህን ጊዜ በአግባቡ በመጠቀም ፕሮግራምን ማስተዋወቅና ህዝቡ ያስተዳድረኛል የሚለውን እጩ በመረጃ ላይ ተመስርቶ እንዲመርጥ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ፓርቲዎች መጪውን ጊዜም በአግባቡ ተጠቀሙበት!
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2013 ዓ.ም