
ከቦታ ቦታ፣ ከዓውድም ዓውድ የተለያየ ቢሆንም፤ በዘመናት ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችን መነሻ በማድረግ የሚነሱ አመጾች ተፈጥረዋል፤ እንደየሚዛናቸውም ለውጤት ሲበቁ ታይተዋል። በሀገራችንም መሰል ሕዝባዊ አመፆች በተለያዩ ጊዜያት ተነስተው ፍሬ አፍርተዋል። አንዳንዶቹም ከመሐል፣ አንዳንዶቹም ከጅምሩ ተቀጭተዋል።
እነዚህ አመጾችና እንቢተኝነቶች ታዲያ፤ አንድም ሕዝባዊ ባሕሪን ተላብሰው ይከሰታሉ። አንድም ቡድናዊ ውክልናን ደርበው ይገለጣሉ። ይሄ የፖለቲካ ተፈጥሯዊ ዑደት ነው። ዋናው ጉዳይ ግን፤ ይሄን መሰል ሕዝባዊ ጥያቄን ይዘው የሚነሱ ቡድኖች አንዳንዴም ግለሰብ ተኮር ስብስቦች፣ በእርግጥ ይዘው የተነሱት ዓላማ የሕዝብ ጥያቄው እንዲመለስ የሚሄዱበት መንገድስ ሕዝቡ የሚደግፈውና የሚሳተፍበት ነውን? የሚለው ነው።
በእዚህ ረገድ የሕዝብ ጥያቄን ተገን አድርገውና በራሳቸው መልክ አሳድገው የሚቀርቡ ራሳቸውን የሕዝብ እንደራሴና ጠበቃ የሚያደርጉ ስብስቦች ነበሩ፤ አሁንም አሉ። ከእዚህ አለፍ ብለውም የሕዝብን ጥያቄ ቀምተው የራሳቸው በማድረግ ራሳቸውን ሕዝብ በማድረግ የሚከሰቱ ቡድኖችም ነበሩ፤ አሁንም አሉ። እነዚህ ስብስቦች የሕዝብ አጀንዳን በራሳቸው መልክ መሥራታቸው ብቻ ሳይሆን፤ አጀንዳውንም፣ ጥያቄውንም፣ የጥያቄውን ማቅረቢያና መፍትሔ ማፈላለጊያ መንገድንም በራሳቸው ፍላጎት የሚመሩ ናቸው።
ለምሳሌ፣ ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከሃሳብ ይልቅ የጠብመንጃ አፈሙዝን የመፍትሔ መንገድ አድርገው የሚጓዙ አንጃዎች በየአካባቢው ይታያሉ። በኦሮሚያ፣ በአመራ እና በሌሎችም ቦታዎች አንዴ ነጻ አውጪዎች፤ ሌላ ጊዜ የሕዝብ ጠበቃዎች፤ … በመሳሰለው መልክ ራሳቸውን ሰይመው ለሕዝብ እንታገላለን የሚሉ ጽንፈኛ ታጣቂ ኃይሎች ተበራክተዋል።
እነዚህ ኃይሎች ሕዝብ በሰላማዊ መልኩ ጠይቆ እንዲመለሱለት የሚገባውን ጥያቄ ነጥቀው የራሳቸው የፖለቲካ ፍላጎት ማሳኪያ፤ የሥልጣን ጥማት ማስታገሻ ለማድረግ ጠብመንጃን አንግተው ሁከት በመፍጠር እና ሕዝቡን ሰላም በመንሳት በየጫካውም፣ በየከተማው ጥጋጥግም የሚተራመሱ ናቸው። ሕዝብ ሰላም ሲል፤ እነርሱ ጦርነት ይቀሰቅሳሉ። ሕዝቡ ልማት ሲል፤ እነሱ መሠረተ ልማት ያወድማሉ። ሕዝቡ እውቀት ሲል፤ እነርሱ ትምህርት ቤቶችን ያፈርሳሉ፤ መምህራንን ይገድላሉ።
እነዚህ ስብስቦች በሁሉም አካባቢ ቢሆን በእዚህ መልኩ የሕዝብ አጀንዳን ቀምተው በሕዝብ ስም ራሳቸውን እየሰየሙ፤ ነገር ግን ከሕዝብ ጥያቄ የወጡ፣ ከሕዝብ ፍላጎትም የተቃረኑ ተግባር ላይ የተሠማሩ ናቸው። በአማራ ክልልም ያለው ይሄው እውነት በመሆኑ፤ የክልሉ ሕዝብ ከሰሞኑ በተለያዩ ቦታዎች ባካሄዳቸው ሰልፎች እነዚህን ጽንፈኛ ኃይሎች ሲያወግዝ፤ ስለ ሰላምና ልማቱ እድል እንዲሰጡት ሲጠይቅና ሲማጸን፤ መንግሥትም ስለሰላምና ልማቱ እንዲሠራለት ሲያሳስብ ተደምጧል።
ይሄ በጥያቄዎችም፣ በማውገዝም የተደገፈው ሕዝባዊ ሰልፎች ታዲያ፤ እነዚህ ኃይሎች ምን ያህል የሕዝቡን መንገድና ፍላጎት ተቃርነው መገኘታቸውን የሚያጋልጡ ናቸው። ሕዝቡ ምን ያክል ከእነዚህ ቡድኖች ጋር ተለያይቶ ያለ መሆኑን የሚናገሩ ናቸው። ሕዝቡ ምን ያህል በእነዚህ ኃይሎች ምክንያት የልማት ችግር ውስጥ፤ የሰላም እጦት ውስጥ እንደገባ ምስክር ሆነው የተገለጡ ናቸው።
የክልሉ ሕዝብ በጽንፈኞች አካሄድና የጸረ ሰላም መንገድ እጅጉን መሰላቸቱንም ፣ መማረሩንም የገለጸበትን መንገድ ሰልፍ አስመልክቶ ይሄንን ሕዝባዊ ሰልፍ አስመልክቶ፤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፣ “የክልላችን ሕዝብ ለሰላም መስፈን ያለውን ጽኑ አቋም በተግባር አረጋግጧል፤ ሕዝባችን በአደባባይ ወጥቶ የዛሬውን እና የወደፊት አንጡራ ፍላጎቱን አንጸባርቋል። የክልላችን ሕዝብ ሰላም መሻቱን እና ልማት መፈለጉን ከፍ ባለ የሞራል ልዕልና ስላሳየን ልባዊ ምሥጋናዬን በራሴና በክልላችን መንግሥት ስም አቀርባለሁ፤” ሲሉ መናገራቸውም ለእዚሁ ነው።
በተመሳሳይ መልኩ፣ የአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ፤ “ሕዝባዊ ሰልፉ ለሕግ የበላይነት መቆምን ያሳየ፣ አፍራሽ አካሄድን በመጸየፍ ለሀገራዊ አንድነት እና ሉዓላዊነት መጽናት ያለውን ጽኑ ፍላጎት እና ቁርጠኛ ትግል ያመላከተ ነው። …መልማት፣ ማደግ፣ መለወጥ፣ መበልጸግ እና ከዓለም ጋር በዕውቀት መወዳደር የክልሉ ሕዝብ ዋነኛ ፍላጎት ነው፤” ሲሉ በጸረ ሰላም ኃይሎች ታፍኖ የቆየው የሕዝብ ፍላጎት በሰልፎቹ ላይ መንጸባረቁን አረጋግጠዋል።
ይሄን ሕዝባዊ ሰልፍ ያስተጋባውን ጥያቄ ተከትሎም፣ በመንግሥት በኩል ለጥያቄው መልስ ለመስጠት አልዘገየም። በተለይም የአማራ ክልል ሕዝብም የግጭት ጠማቂዎቹን እና የተላላኪዎቹን አጀንዳ በሚገባ ተገንዝቦ መንግሥት ሰላም እንዲያሰፍን በተደጋጋሚ ጥያቄዎችን በተለያዩ አግባቦች ሲያቀርብ መቆየቱን በማስታወስ፤ መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ዛሬም እንደ ትናንቱ በትጋት እንደሚሠራ በመንግሥት ኮሙኒኬሽን መሥሪያ ቤቱ በኩል አረጋግጧል።
በአንጻሩ ግን፣ ዛሬም የሕዝብን ጥያቄ ቀምቶ ብቻ ሳይሆን፤ ሕዝብን ከልማቱም ከሰላሙም አናጥቦ እረፍት የሚነሳው ጽንፈኛ ቡድን ከተሳሳተ መንገዱ ለመመለስ የሚያስችል ምንም ፍላጎት አለማሳየቱ በተለያዩ አውዶች እየተደመጠ ነው። በእዚህ ረገድ፣ ከስህተታቸው ተምረው ወደ ሰላማዊ መንገድ የተመለሱና እየተመለሱ ያሉ የጽንፈኛው ቡድን ኃይሎች መኖራቸው እሙን ነው። እነዚህ የሕዝብ ፍላጎት ተገዢ ሆነዋልና ምስጋና ይገባቸዋል።
ይሁን እንጂ፣ ዛሬም በሕዝብ ስም የሚነግዱ፣ ከግጭትና ጦርነት ብቻ ከፍ ያለ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡ የቡድኑ ሰዎች፤ ይሄ ሰላማዊ መንገድ ፈጽሞ አይመቻቸውም፤ የሕዝቡ ተማጽኖና ጥሪም ከጆሯቸው አይደርስም። ይሄ ለምን ሆነ፤ በእርግጥ እንደሚሉት የሚታገሉት ለሕዝብ ከሆነ ለምን የሕዝቡን ጥያቄ ማድመጥና መረዳት ተሳናቸው? ሊመልሱት የሚገባ ጉዳይ ሊሆን ይገባል!
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም