ጽጌሬዳ ጫንያለው
ልጆች እንዴት ናችሁ፤ ትምህርት እንዴት ይዟችኋል? መቼም ከኮሮና ራሳችሁን እየጠበቃችሁ በሚገባ ትምህርታችሁን እየተከታተላችሁ እንደሆነ እገምታለሁ። ኮሮና በጣም እየከፋ እንደሆነ ታውቃላችሁ አይደል ? ስለዚህም በጣም ጥንቁቅ መሆን አለባችሁ። እጃችሁን ሳትታጠቡ ምግብ መብላትም ሆነ ፊታችሁን መነካካት አይገባም። አፋችሁንም ቢሆን በአፍ መሸፈኛ ጭንብል /ማስክ/ መሸፈን እንዳትረሱ። ከዚያ በተጓዳኝ ደግሞ ትምህርታችሁን በደንብ ማጥናት አለባችሁ። ዛሬ በጅማ ዞን ዲዴ ወረዳ ኢላላ ቀበሌ ያገኘኋቸውን ተማሪዎችና ምን ምን እንደሚያደርጉ እነግራችኋለሁ።
ልጆቹ ቤተሰቦቻቸውንም ሆነ መምህሮቻቸውን በጣም ያከብራሉ። ትምህርት ቤታቸውንም በማጽዳትና ግቢያቸው ውስጥ አትክልቶችን በመንከባከብ ይታወቃሉ። እኔ ያገኘኋቸው ደግሞ አርብ ቀን ሲሆን፤ ትምህርት ቤታቸውን ከቤታቸው ውሃ በጀሪካን ወስደው አጽድተው ሲመለሱ ነው። በግቢያቸው ውስጥ ውሃ የሚባል ነገር የለም። ነገር ግን እነርሱ ጎበዞች ስለሆኑ ውሃ ካለበት ቦታ ድረስ ሄደው በማምጣት አትክልቶቻቸውን ያጠጣሉ። ክፍላቸውንም በሚገባ ያጥባሉ። ለመሆኑ በየጊዜው ምን ምን ትሰራላችሁ ብዬ ጠይቄያቸው ነበርና ያሉኝን ልንገራችሁ
መጀመሪያ ምን ምን እንደምትሰራ የነገረችኝ ሱመያ ኮዲ የምትባለው አላላ ትምህርት ቤት ተማሪ ነች። እርሷ በጠዋት ተነስታ ፊቷን ታጥባና ቁርሷን በልታ ትምህርት ቤታቸው ራቅ ስለሚል በፍጥነት ነው ከቤቷ የምትወጣው። ትምህርት ቤት ከደረሰች በኋላ ደግሞ መምህሮቿ የሚያዟትን ሁሉ ታደርጋለች። በተለይም በጋራ መስራት ላይ በጣም ጎበዝ ነች። የቤት ስራም ሳትሰራ ክፍል ውስጥ ገብታ አታውቅም። በዚህም ከክፍሉ ሰቃይ ተማሪ ነች። ሁሉም ልጅ ደግሞ ይወዳታል። ስለዚህ ልጆች በሁሉም እንዲወደዱ ከፈለጉ የተባሉትን ማድረግና ጎበዝ ተማሪ መሆን አለባቸው ትላለች።
ሌላዋ ተማሪ አስናቲ ነጅብ የምትባል ስትሆን፤ እንደ ሱመያ ጎበዝ ተማሪ ነች። እርሷም ቤተሰቧ የሚላትንና መምህሮቿ የሚያዟትን ትሰማለች። ብቻዋን ማንበብ ትወዳለች። ሆኖም አግዥኝ ያላትን እንቢ አትልም። ትምህርት ቤት ላይ በሚደረገው ሥራ ቀርታ አታውቅም። ለብቻዋ ተከልሎ የተሰጣት ችግኝ ስላለ ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት ውሃ ይዛ በመሄድ ታጠጣለች። አርብ ሲደርስም ተራዋ ከሆነ ክፍሏን ታጸዳለች። የእርሷ መልዕክት ደግሞ ልጆች የተሰጣቸውን ሀላፊነት መወጣት አለባቸው የሚል ነው። ይህንን ካደረጉ ሁሉም ሰው ይወዳቸዋል ብላለች።
በመጨረሻ ያነጋገርኩት ልጅ ካሊድ አወል ይባላል። የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ነው። እንደእነ ሱመያ ሁሉ ጎበዝ ነው። ከዚያ በተጨማሪ በእግር ኳስም ሀይለኛ ነው። እርሱም እንደ እነ አስናቲ የተባለውን የሚያደርግ ነው። ስለዚህም ልጆች ቢያደርጉት የሚለው ተሰጥዋቸውን ለይተው ማደግ ቢችሉ ነው። ደስ ይላሉ አይደል? ጎበዞች የመከሯችሁን እንዳትረሱ። በሌላ ጊዜ ሌላ ጉዳይ እስክናቀርብላችሁ መልካም ሰንበት ይሁንላችሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2013 ዓ.ም