አዲሱ ገረመው
ወደ አሰልጣኝነት ሕይወት ከገባባት ከ1993ዓ.ም ጀምሮ ብዙ ስኬቶችን አጣጥሟል። በእነዚህ አመታትም የፀባይ ዋንጫን ጨምሮ ከ21 በላይ ዋንጫዎችን ለማግኘት በቅቷል፤ 21 ጊዜ ኮኮብ አሰልጣኝ ሆኖ በመመረጥ ሽልማቶች ተበርክተውለታል። በግሉም በእኛ ሀገር ብዙ ያልተለመደውን የህይወት ታሪክ ጽፏል። “ከስደት መልስ እስከ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት” የሚል ግለ ህይወት ላይ ያጠነጠነ መጽሐፍ ነሀሴ 2007 ዓ.ም ለህትመት አብቅቷል። ይህ ሰው ማነው?
አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ይባላል። የሀገራችን የሴቶች የእግር ኳስ ተሳትፎ እንብዛም ባልተስፋፋበት ጊዜ ልቡ ሩቅ በማሰብ የዘርፉን ስፖርት ለማሳደግ ባደረበት ጽኑ ፍላጎት በ1993 ዓ.ም የሴቶች ቡድን ማሰልጠን ጀመረ። ስልጠናውን መስጠት በጀመረበት ወቅት ትልቅ እንቅፋት ሆኖበት የነበረው የኢኮኖሚ ችግር ነው። ይህንንም ለመፍታት ሴቶች ጸጉራቸውን ተቆርጠው የሆያ ሆዬ ጭፈራ እንዲጫወቱ በማድረግ ገንዘብ ሊያገኙ የሚችሉበትን ስትራቴጂ ነደፈ።
ምንም እንኳን አንዳንዶች ድርጊቱን የዘመናዊ ሌብነት መገለጫ ነው በማለት ቢቃወሙትም እርሱ ግን እጁን ሳይሰጥ በአበባ አየሽ ሆይ ጭፈራ እንዲሁም በሌሎች በአላት ወቅት ሎተሪዎችን በማዘጋጀት በሚያገኟት ገቢ ውድድሮችን ማከናወን ጀመረ። በውድድሩ ጊዜም እንዳሰበው ቶሎ ስኬት የማግኘት እድሎ የጠበበ ነበር። የእርሱ ቡድን ተገጣሚዎች ስድስትና ሰባት ግቦችን እያስቆጠሩ ያሸንፏቸው ነበር።ይህም በጊዜው ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንበትም አቅሙን አሟጦ ከስህተቶች በመማር ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻልን በማሳየት ወደ ትልቁ ምዕራፍ መሸጋገር ችሏል።
የልጅነትና የታዳጊነት ህይወቱ በችግር ስንክሳር
ውስጥ ተጠምጥማ የነበረችው ይህ ሰው ሉሲዎችን ለ 12 አመት ማሰልጠን ችሏል። በተሳትፎውም የተለያዩ ጨዋታዎችን በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በማድረግ መልካም የሚባል ውጤትን አስገኝቷል። በወርሀ ሰኔ 2004 ዓ.ም ኢትዮጵያ በሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ከ1994ዓ.ም ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ እንድታልፍ በማድረግ ታሪክ ሰሪ አሰልጣኝ ሆኗል። ሉሲዎቹ የኦሎምፒክ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ጥሩ ፉክክር አድርገዋል፤ ጫፍ ላይ ደርሰው ሳይሳካላቸው ቢቀርም በሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ እንድትጠራ ሆኗል።
አሰልጣኙ ስመ ጥር ከሚባሉ አሰልጣኞች መካከልም ስሙ ሰፍሯል። በአንድ ወቅት በአንድ ወር ውስጥ ብቻ አራት ሽልማቶችን አግኝቷል። ዱዱ ኢንተርቴመንትና የደቡብ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከደቡብ ስፓርት ኮሚሽን በጋራ በመተባበር ባለፉት 22 አመታት ለሴቶች እግር ኳስ ላበረከትከው አስተዋጽኦ ብለው የዋንጫ ሽልማት አበርክተውልታል። ልሣን የሴቶች ስፓርት ኮከብ አሰልጣኝ እውቅና ሰጥቶታል።
ትንግርት የሴቶች ስፖርትና ሶከር ኢትዮጵያም እንዲሁ በየፊናቸው ዝናውን ከፍ ያደረገ የኮኮብ አሰልጣኝነትን እውቀናና ሽልማት ሰጥተውታል።
አሠልጣኝ ብርሀኑ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ሥልጠና ያለው፤ በካፍ “ኤ ላይሰንስ ስልጠና የወሰደ፤ በፊፋ የላሊጋ ሜቶዶሎጂ ሥልጠናን ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በአሜሪካ አገር የወሰደና በስኬት ያጠናቀቀ ስለመሆኑ ይናገራል።
ስልጠናዎቹን መሠረት በማድረግና ባካበተው ልምድና ስኬት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሴት እግር ኳስ ቡድንን ከ2004 እስከ 2013 ዓ.ም ከምክትል አሰልጣኝነት እስከ ዋና አሰልጣኝነት በማሠልጠን ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ነው።
የእረፍት ውሎ
ዘወትር ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነሳ ጸሎት እንደሚያደርግ አሠልጣኝ ብርሃኑ ይናገራል። አሠልጣኝ እንደመሆኑ መጠን ራሱን መጠበቅ ስላለበት ስፖርት ይሰራል። የእርሱን እንቅስቃሴ ወደ ልጆቹ በማስተላለፍ ክዋኔውን እንዲተገብሩ ያደርጋል።
አብዛኛውን ጊዜ ከሥራ መልስ ከቤተሰብ ጋር ማሳለፍን እንደሚያዘወትር የሚገልጸው አሠልጣኝ ብርሀኑ፤ ባለው የእረፍት ጊዜም ቤተሰቡን በሥራ እንደሚያግዝ፣ ልጆቹን እንደሚያስጠና ይናገራል። እግር ኳስን በፍቅር ሜዳ ላይ እንደሚያስልፍበት ሁሉ በተመሳሳይ ከቤተሰብ ጋር በፍቅር ማሳልፍን የማይደራደርበት ተግባሩ እንደሆነም ነው የሚገልጸው።
አሰልጣኙ የቀን ውሎው እንዲባክንበት አይፈልግም። ሀይማኖታዊ ክንዋኔዎችን ከማድረግ ጀምሮ ለነፍሱም ለስጋውም የሚበጀውን ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም። እነዚህን በማዘወተሩ አቅሙን በየጊዜው እያሳደገና ለስኬት እንደበቃም ያብራራል።
መጽሐፍትን ማንበብ አሠልጣኙ በእረፍት ጊዜው ከሚያዘወትራቸው ተግባራት መካከል አንዱ ነው። ቴአትርና እግር ኳስን በመመልከት የእረፍት ጊዜውን ያሳልፋል። እንደ እንጦጦ ፓርክ አይነት ያሉና ተፈጥሮአዊ ተውህቦ ያላቸውን ሥፍራዎች መመልከትም እንዲሁ በአሰልጣኙ የእረፍት ውሎ ዝርዝር ውስጥ ይካተታሉ። ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች ድጋፍ ያደርጋል።
መልዕክት
በአሁኑ ወቅት በተለይ ወጣቶች ላይ ብዙ ችግሮች እንዳሉ የሚናገረው አሠልጣን ብርሀኑ፤ ወጣት ችኩል እንደሆነና ሁሉ ነገር ወዲያው እንዲሆንለት ከመፈለጉ አኳያ ለጥፋት ሊዳረግ እንደሚችል ያመላክታል። ይህም በአገር እጣ ፈንታ ላይ መጥፎ አሻራን ሊያሳርፍ እንደሚችል በመግለጽ፤ ለነገሮች ሰከን ማለት እንዳለበትም ይመክራል።
አሠልጣኙ እንደሚለው፤ በስክነት አለማሰብ ኢትዮጵያን ለመከፋፈል ለሚታትሩ ሰዎች በር መክፈት ነው። መንግስት ኢትዮጵያን የበለጸገች ብሎ የሚያሳየን ነገር ቢኖርም፤ አንዳንድ ፖለቲከኞች ደግሞ አገሪቷ ፈጽሞ የደከመችና ልትበታተን እንደደረሰች አድርገው ያሳያሉ፤ ይህም የነገን ተስፋ የሚያጨልም ነው።
“በአይናችን የምናያትን ኢትዮጵያን ሊነጥቁና ለባዕዳን ለመስጠት የሚፈልጉ አካላት እንዳሉ ይታወቃል። ኢትዮጵያን በህመሟ ጊዜ ልንደርስላት የምንችለው እኛው ራሳችን ነን። በተለይም ስፖርት በዓለም ላይ ከፍተኛ ተጸዕኖ ፈጣሪ እንደመሆኑ በዚህ ዘርፍ ያሉና ስመ ጥር ሰዎች የአገር አለኝታ መሆን ይኖርባቸዋል። የአገርን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ለማድረግ እንደታተሩት ሁሉ አገሪቷ ሳትረጋጋ ስትቀር ማስታመም አለባቸው። የማስታረቅ ሥራዎችን በመስራት የኢትዮጵያን ሀያልነት ማስቀጥል ይኖርባቸዋል” ይላል አሰልጣኝ በርሀኑ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2013 ዓ.ም