የዓለም ኃያላንንና ጠቢባንን እየፈተነ ከክትባት የዘለለ መፍትሄ ያልተገኘለት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፤ በኢትዮጵያም በሞት ዜና ታጅቦ ትናንት የአንድ ዓመት ሻማውን ለኩሷል።ኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ተገኘ ከተባለበት ከመጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ከትናንስ በስቲያ መጋቢት 3 ቀን 2013 ዓ.ም እስከወጣው መረጃ ድረስ ለሁለት ሚሊዮን 214 ሺህ 180 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 172 ሺህ 571 ደርሷል፡፡
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምንም እንኳን መነሻው ቻይና ናት ይባል እንጂ፤ በአውሮፓ እና አሜሪካ እንዲሁም እንደ ብራዚል ባሉ የላቲን አሜሪካ አገራት የብዙ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ119 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በቫይረሱ ሲያዝ፤ ከሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።በኢትዮጵያም ቢሆን በመቶ ሺህ የሚቆጠር ዜጋ በቫይረሱ ሲያዝ፤ ሺዎች የሚቆጠሩ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
መጋቢት 3 ቀን 2013 ዓ.ም ጤና ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ፤ በ24 ሰዓታት ውስጥ ለስድስት ሺህ 985 ሰዎች በተደረገ የላቦራቶሪ ናሙና ምርመራ አንድ ሺህ 361 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።በዕለቱ 355 ከበሽታው ማገገም የቻሉ ቢሆንም፤ 454ቱ በጽኑ ታምመዋል።እንዲሁም በ24 ሰዓቱ ውስጥ 27 ሰዎች ሞተዋል።ይህ መረጃ የሚያሳየው ደግሞ ቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱና አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው፡፡
እንደ አጠቃላይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተረጋገጠ በኋላ ባሉት 365 ቀናት ውስጥ ለሁለት ሚሊዮን 214 ሺህ 180 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተደርጎ 172 ሺህ 571 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፤ 141 ሺህ 195 ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ ማገገም ችለዋል።ይሁን እንጂ ሁለት ሺህ 510 ዜጎች በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ይህ ማለት ግን በቫይረሱ የተያዙትም ሆነ የሞቱ ወገኖች ቁጥር ይሄ ብቻ ነው ማለት አለመሆኑን ልብ ማለት ይገባል።ምክንያቱም የተያዙትንም ሆነ የሞቱትን መግለጽ የተቻለው መመርመር በተቻለው ልክ ሲሆን፤ ከዚህ በላይ መመርመር ቢቻል ከዚህ የላቀ ቁጥር ሊገኝ እንደሚችል ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት፡፡
ከዚህ ሁሉ በኋላ በቅርቡ ክትባቱ የተገኘ ቢሆንም፤ የበለጸጉ አገራት ሽሚያ ላይ በመግባታቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ እና ድሃ አገራት ደግሞ በእርዳታ ከሚደርሳቸው ጥቂት ምጽዋት ያለፈ ገዝተው እንኳን ለዜጎቻቸው ሊያደርሱ የሚችሉበት እድል እንደሌላቸው በግልጽ እየታየ ነው፡፡
ምክንያቱም እነ አሜሪካ ዜጎቻቸውን በሙሉ የመከተብ አቅጣጫ አስቀምጠው ሲሰሩ እና ዜጎቻቸውን ካዳረሱ በኋላ ለሌላው እድል እንደሚሰጡ በግልጽ ሲናገሩ፤ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ያላቸው ታዳጊ አገራት ደግሞ ከሰሞኑ ካገኘችው ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የኮሮና ቫይረስ ክትባት መድሃኒት ያለፈ እዚህ ግባ የሚባል ነገር እንዳልያዘች መመልከት ተችሏል፡፡
በኢትዮጵያ እየታየ ያለው መዘናጋት እና ቸልተኝነት ደግሞ ለቫይረሱ መስፋፋት ምቹ ሁኔታን ፈጥሮለታል፡ ምክንያቱም አሁን ላይ በተለያዩ ሃይማኖታዊ፣ ማህበራዊ እና ሌሎችም የገበያና መሰል ስፍራዎች ህብረተሰቡ ያለምንም ስጋትና ጥንቃቄ ሲንቀሳቀስ ይታያል።አፍ አውጥተውም የቫይረሱን መኖር በመጠራጠር ሲናገሩም ይደመጣል።አንዳንዱም ክትባቱን ተስፋ ሲያደርግ ይታያል፤ ሌላው ደግሞ የቅርብ ቤተሰብና የስራ ባልደረቦችን በቫይረሱ መሞታቸውን ሲያውቅ መደናገጥ ውስጥ ሲገባ ይስተዋላል፡፡
ይህ ደግሞ ሰዎች በራሳቸው ካልደረሰ በስተቀር በተለያየ መልኩ የሚሰጠውን የግንዛቤ ትምህርት እየተቀበሉ አለመሆኑን የሚያስረዳ ሲሆን፤ ይሄን መሰል መዘናጋት ደግሞ የበለጠ ዋጋ የሚያስከፍል ነው።ምክንያቱም ዛሬ ላይ የኮሮና ቫይረስ ማገገሚያ ተቋማት ጉዳዩ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑን እየተናገሩ፤ የሞት ምጣኔውም እያደገ መሆኑን እያስረዱ ይገኛል።የጥቂቶች ጥንቃቄ ችግሩን ሊያቃልል እንደማይችል እና ህብረተሰቡ ስለ ችግሩ ስፋት ተገንዝቦ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሱን፣ ቤተሰቡን፣ ወዳጅ ዘመዶቹን፣ ጓደኞቹን በጥቅሉ ህዝቡን ሊታደግ የሚችል ስራ እንዲያከናውንም ምክራቸውን ይለግሳሉ፡፡
ቫይረሱ ደግሞ ቀድሞ እድሜያቸው ከገፉ ሰዎች እና የጎንዮሽ ህመም ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ያጠቃል የሚል ግንዛቤ ነበር፤ አሁን ደግሞ ህጻናትና ወጣቶችን ሳይቀር ለሞት እያዳረገ እንደመሆኑ፤ ትልቅ ትኩረት እና ጥንቃቄ የሚፈልግ መሆኑን እሙን ነው።እና ችግሩ የባሰ ስር ከመስደዱ እና የሞት ጽዋው በየጎጇችን ከመግባቱ በፊት፤ በባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን በመተግበር ራሳችንንም ሌላውንም ልንታደግ ይገባል፡፡
በመንግስት በኩልም የአንድ ዓመት ጉዞውን በመፈተሽ በችግሩ ስፋትና አስከፊነት ልክ ተገቢው እርምትና ማስተካከያ በማድረግ ዜጎችን የመታደግ ኃላፊነትን መወጣት የግድ ይላል።እናም በአንድ ዓመት ሺዎችን የነጠቀን የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ሌላ አንድ ዓመት አብሮን እንዳይዘልቅ እና ሺዎችን ዳግም እንዳያሳጣን፤ እንደ መጀመሪያው ጊዜ ሁሉ ከግለሰብ ጀምሮ ባለሀብቶች፣ ተቋማት፣ መንግስትና ሌሎችም ባለድርሻዎች በጋር በመስራት ለወገን አሳቢነታችንን ልናሳይ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2013 ዓ.ም