ረፋድ ላይ በቅዱስ ጳውሎስ ቲቢ ስፔሻሌይዝድ ሆስፒታል ለሥራ ተገኝቼ ነበር። የሄድኩበት ጉዳይ እስከሚጀምር ድረስ በግቢው ውስጥ መዘዋወር ጀመርኩ። መቼም በሆስፒታልና እስር ቤት ተገኝቶ መንፈስን የሚያስደስት ነገር ለማየት አይታሰብም። ምክንያቱም ማንም ቢሆን ጤነኛ ሆኖ አልያም ጤነኛ ለማየት ወደ ሆስፒታል አይሄድምና። የሆስፒታሉን ግቢ ከዓመታት በፊት ስለማውቀው ከወትሮው የተለየ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ለማየት ችያለሁ። ገና ስገባ በስተግራዬ ያለውና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝው ሕንፃ ቀልቤን ስቦት ነበር።
እናም ባለችኝ ጊዜ ውስጡን ብጎበኝ ሌላ የተሻለ ነገር አያለሁ ብዬ ወደ ውስጥ ዘለቅኩ። አዲስ ሕንፃ፣ አዲስ ወንበር፣ አዲስ ቁሳቁስ…ለግቢው ውበት ሆኖታል። በየእርምጃዬ መካከል ሕንፃውን ብቻ ሳይሆን በውሰጡ የሚንቀሳቀሱትንም ሰዎች እየቃኘሁ ነበር። አብዛኛው ሰው በጥድፊያ ይንቀሳቀሳል። የተቀመጡትም ወረፋ በመጠባበቅ ቆዝመዋል። ወደ ማዋለጃው ክፍሉ ስደረስ የሚጨባበጡና የሚሳሳሙን አናቶች አስተዋልኩ።
«እልልልልል…» የሚል አንድ ሁለት ድምፅም ሰምቻለሁ። እነርሱም ቢሆኑ እየተጣደፉ ነው። በተለይ ነጫጭ ጋውን የለበሱት የሆስፒታሉ ሠራተኞች ወረቀትና አንዳንድ ቁሳቁስ በእጃቸው ይዘው ሲሮጡ መንገድ ለማስለቀቅ ሰዉን ይገፋሉ። ቦታው ሆስፔታል እንደመሆኑ የምጠብቀው ስለነበር አልገረመኝም።
የውስጥ ጉብኝቴን ጨርሼ ከሕንፃው ስወጣ ለዛሬ ጽሑፌ ብእሬን እንዳሾል ያደረገኝ ገጠመኝ ተፈጠረ። የሆስፒታሉ በረንዳ ላይ የታጠቡ ጥቁርና ቢጫ በግምት አንድ ሜትር ርዝማኔ ያላቸው የቆሻሻ ማስቀመጫዎች ተደርድረዋል። ጥቋቁር ጓንት ያደረጉና መጥረጊያና መወልወያ የያዙ የፅዳት ሠራተኞች በእነዚሁ ትንንሽ የፕላስቲክ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳዎች ዙሪያ ደፋ ቀና ይላሉ። ግማሾቹ በቆሻሻ የተሞሉ ተመሳሳይ ገንዳዎችን በጎማቸው እየገፉ ከሕንፃው ያወጣሉ። ቆይቼ እንዳስተዋልኩት በእያንዳንዱ ገንዳ ላይ የተለያዩ ጽሑፎች ሰፍረዋል ። «ደረቅ ቆሻሻ»፣ «የተበከሉ ዕቃዎች» የሚሉ።
ከእነዚህ ድርድሮች በአንዱ ጫፍ እኔንና ሌላውን ተገልጋይ የሚስብ ጭቅጭቅ በመስማታችን ትኩረታችንን ወደዛው አደረግን። አንዲት እናት በግምት ከሦስት እስከ አራት ዓመት የሚሆናትን ልጅ ይዛ በወዲያኛው ጥግ ለቆመ ወጣት ዘለፋና ስድብ ትወረውራለች። በየቃላቷ መካከል ደግሞ «ሲጀመር አንተ ምን አገባህ!» የሚለውን ኃይለ ቃል ትደጋግማለች። በሃሳቤ «በቃ ዘንድሮ ትዳርና የቻይና ዕቃ አልበረክት አለ» እያልኩ ወደ እነርሱ አመራሁ። እንግዲህ በእኔ እይታ ሴትየዋና ወጣቱ ባልና ሚስት አድርጊያቸው ነበር። ከዚያ ቢያልፍ እንኳ ወድምና እህት አልያም ዘመድ ቢሆኑ ነው። እቦታው ስደርስ ያሰበኩትና እውነታው ፍፅም የተለያየ ነበር።
ከሥራቸው ተቀምጣ ነገሩን በጥሞና ስትከታተል ከነበረች ወጣት እንደተነገረኝና እኔም በኋላ እንደተረዳሁት ከሆነ ሰዎቹ አይተዋወቁም። እዚያች ቦታ ላይም የተገኙት ለየራሳቸው ጉዳይ ነው። እነርሱን ለጭቅጭቅና እላፊ ለመነጋገር ያበቃቸው ነገር የተጀመረው እንዲህ ነበር።
ሴትየዋ ልጇን ለቃት አጠገቧ ካሉ ሰዎች ጋር ታወጋለች። ልጅቱ ደግሞ ኮሪደሩን ተከትላ እየተጫወተች ትሄድና ከቆሻሻ ማጠራቀሚያዎቹ አንዱን መነካካት ትጀምራለች። የልጅቷን እንቅሳቃሴ ቆሞ ሲከታተል የነበረው ወጣት ልጅቷን እንድታርፍ ሲናገራት እየሳቀች በእጇ መነካካቱን ትቀጥላለች። ይሄን ጊዜ ወጣቱ ልጅቷን አምርሮ ይቆጣትና ያስፈራራታል። ልጅቷም ተንስታ ወደ እናቷ ትመለሳለች። ስትመለስ ግን እንዳመጣጧ አንገቷን ደፍታ እየተጫወተች ሳይሆን እንባዋን እያዘራች በለቅሶ ነበር። በዚህ መካከል እናት «ልጄን ለምን ትናገራለህ?» የሚል ጥያቄ ለወጣቱ ትሰነዝራለች። ወጣቱም «እዚያ ቁጭብለሽ ወሬ ከምታወሪ ልጅቷ ቆሻሻ እንዳትነካ አትጠብቂም ነበር? ነገ አንድ ነገር ብትሆን…» ነበር ያላት።
እናትም «ምን አገባህ ምንስ ብትሆን?» ብላ ምላሽ ትሰጣለች። በአካባቢው ያለውም ሰው የተወሰነው እናትን ከፊሉ ደግሞ ወጣቱን «ለምን በስርዓት አይናገርም» እያለ እርስ በእርሱ ይነታረካል። እንግዲህ በዚህ መሀል ነበር አንዲት እናት «ምን ሆናችኋል? ደግሞ ልጅ ለመገሰጽ የማን ልጅ ናት ይባላል እንዴ? ቢቆጣትስ ለሷ ብሎ ነው፤ አትሟሟ፤ የምን ነገር ማክረር ነው?» ሲሉ ሁሉንም ይቆጣሉ። በገላጋይ ቁጣ ነገሩ ይቀዘቅዝና እኔም ወደ ጉዳዬ ተመለስኩ።
«ግን ልጆች የማን ናቸው?» ስል አራሴን ጠየኩ። «ብቻውን ያለማንም ዕርዳታ ልጆቹን ሊያሳድግ የሚችል እናትና አባትስ ይኖር ይሆን?» እንደ እኔ እይታ አንድ ልጅ ምናልባትም ሁለት ዓመት እስኪሞላው ድረስ ከቤተሰቦቹ ጋር በቅርበት ሊቆይ ይችላል። ሦስት ዓመትና ከዚያ በላይ ሲሆነው ግን ወደ ጎረቤትም፤ ወደ ሰፈር ልጆችም ለጨዋታ ጎራ ማለቱ አይቀረም። የቅድመ መደበኛውን ትምህርት ባናነሳው እንኳ አምስትና ስድስት ዓመት ከሞላው በኋላ ከቀኑ አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፈው በትምህርት ቤት ይሆናል። ትምህርት ቤት ደግሞ ከተለያዩ አስተሳሰብ፣ አመለካከትና ባህል ካላቸው የዕድሜ እኩዮቹ ጋር መገናኘቱ የግድ ነው።
እዚያም ቢሆን ለእውቀቱም ሆነ ለስነ ምግባሩ አደራ ተብለው የሚሰጡት ቤተሰቦች አልያም ዘመዶች ሳይሆኑ በቦታው ያሉ መምህራን ብቻ ናቸው። ልጆች ዕድሜያቸው እየጨመረ በመጣ ቁጥር ደግሞ እነርሱም በትምህርት፣ በጥናትና ሌሎች ጉዳዮች ቤተሰብም በሥራና በማህበራዊ ጉዳዮች እየተጠመደ የሚገናኙበት ሰዓት እየቀነሰ ይመጣል።
በአብዛኛውም ለመግብና ለእንዳንድ ጉዳዮች ካልሆነ በቀር ከልጆች ጋር የሚገናኘው ለጥቂት ደቂቃዎች ሊሆን ይችላል። የሳምንቱ ማጠናቀቂያ ቅዳሜና ዕሁድም ቢሆን ለአብዛኛው ሰው ከሃይማኖታዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ጊዜውን ከልጆቹ ጋር የሚያሳልፍ አይደለም። ስለዚህ ፈቅደንም ሆነ ሳንፈቅድ ልጆቻችንን ማህበረሰቡ እንዲያስተምርልን፣ እንዲጠብቅልን አሳልፈን መስጠታችን የማይቀር ነው። ማህበረሱቡም በአጋጣሚም ሆነ ሆነ ብሎ ለልጆች እድገት የሚያደርገው አስተዋፅኦ ይኖራል ማለት ነው።
ሁለተኛው ሃሳቤ ደግሞ «አንድ ልጅ እንዴት የወላጆቹ ብቻ ሆኖ ሊቀር ይችላል? » የሚለው ነበር። በአንድ ቤተሰበብ ያለ ልጅ ተምሮ ጥሩ ውጤት አምጥቶ አልያም ጠንካራ ሠራተኛ ሆኖ የተሻለ ህይወት መምራት ከቻለ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ህብረተሰቡን ማገልገሉ አይቀርም። በተቃራኒው ደግሞ በብልሹ ስነምግባር ተጠልፎ፤ በአልባሌ ሱሶች ተጠምዶ፤ ተገቢ ያልሆኑ ተግባራትን የሚከውንም ከሆነ ከጎረቤት እስከ ሰፈር ቤተሰብን ተከትሎ የአካባቢው ማህበረሰብ የችግሩ ተካፋይ መሆኑ አይቀርም። ስለዚህ የእገሌ ልጅ የእገሌ ብቻ ሆኖ አይቀርም ለማለት ነው።
ሌላው ህብረተሰብ በልጆች ስነምግባርና ማንነት ላይ አሻራ እንዳላቸው የሚያሰየን አንድ እውነታ አለ። አዲስ አበባን እንደ ምሳሌ ብንወስድ የእንትን ሰፈር ልጆች ተደባዳቢ፤ የዚህ ሰፈር ልጆች ቀማኛ… ወዘተ ሲባል በተግባርም ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ልጆች ለሰፈሩ መጠሪያነት በተሰጠው ተግባር ተሰልፈው እናገኛቸዋለን።
እንግዲህ የዚያ አካባቢ ነዋሪ አልያም እነዚያ ልጆች የተማሩበት ትምህርት ቤት ለዛሬ የልጆቹ ማንነት የራሱን አሻራ ማስቀመጡ የሚያጠራጥር አይመስለኝም። አዲስ አበባ ውስጥ ሆነው ትምህርት ማቋረጥ፣ መታሰርና ከጋብቻ በፊት አባቱ ያልታወቀ ልጅ መውለድ ብርቅ የማይሆንባቸው ሰፈሮች ጥቂት አይደሉም። በአንጻሩ የእስር ቤትና የፍርድ ቤት ጣጣን የማያውቁ፤ በሰኔና በሀምሌ በምረቃት፤ በጥርና በሚያዝያ በሠርግ ድንኳኖች የሚደምቁ ሰፈሮችም እንዳሉ እናውቃለን። እነዚህ ሁሉ በማህበረሰቡ ዘንድ በስፋት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በአሸናፊነት ለመወጣት በግለሰብ ደረጃ የሚደረግ ትንቅንቅ መኖሩን ያመላክተናል። ለምሳሌ የጎረቤቱ ልጅ ስትመረቅ የተጠራ አባት ለልጆቹ ምን ሊያወራና ወዴት ሊመራቸው እንደሚችል መገመት የሚያዳግት አይመስለኝም። ሳይሳካ ቢቀር እንኳ እንዳታዋርጅኝ የሚሉት ተግሳጾች በልጆቹ ላይ አንዳች አደራን የሚያሰንቁና የሚያስጠነቅቁ ናቸው።
ዛሬ ዛሬ ልንተዋቸው የማይገቡ ነገር ግን ከእጃችን እየወጡ ያሉ በርካት እሴቶች አሉ። ለምሳሌ ልጆችን ተገቢ ባልሆነ ቦታ ስንመለከት የእገሌ ልጅ ነው ሳይባል መቆጣትና መገሰጽ የተለመደ ተግባር ነበር። አሁን ግን በጣም ሕፃናት የሆኑትን ካልሆነ ደፍሮ የሚናገር አይኖርም። ለምሳሌ አንድ የአስራ አራትና አስራ አምስት ዓመት ልጅ ሲጃራ ሲያጨስ፣ ጫት ሲቅም፣ መጠጥ ሲጠጣ ቢታይ ምን ያህሉ ሰው ደፍሮ ሊናገረው ይችላል? ብንል ከጣት ቁጥር የዘለለ የምናገኝ አይመስለኝም።
ዛሬ አስር ዓመት ያልሞላቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች በጣታቸው ሲጋራ ሰክተው፤ በፕላስቲክ ኮዳ ማስቲሽና ቤንዚን እየሰቡ፤ በጉንጫቸው ጫት ይዘው በድፍረት የሚለምኑት ጉድ ብሎ ከማውራት የዘለለ ምንም እንደማናደርግ ስለሚገነዘቡ ይመስለኛል። በየጎዳናው የትምህርት ቤት ዩኒፎርማቸውን ለብሰው ሲንገላወዱ፤ በየጭፈራ ቤቱና ጫት ቤቱ ጎራ ሲሉ የማይሳቀቁትም «የዛሬ ልጆች» ብሎ ከመፈረጅ የዘለለ ምንም እንደማናደርግ ስለሚያስቡ ነው።
ቀደም ባሉት ጊዜያት ውስጣቸው ጥፋት እንደሆነ የሚነገራቸውን ነገር ሲያደርጉ አልያም ጥፋት እንደሆነ እያወቁ አንዳች ስህተት ሲሠሩ አዩኝ አላዩኝ ብለው ነበር። ዛሬ ከማድረጋቸው ለመታየት፣ መጣራቸው ለምን አገባኙ የስህተት መንገድ አንዱ ማሳያ ይመስለኛል። የዚች እናት ቁጣም ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። በመጀመሪያ ወጣቱ ልጅቷን በመቆጣቱ ምንም እንደማያገኝ እርሷና ልጇ ግን ተጠቃሚ እንደሚሆኑ መገንዘብ አልቻለችም። ሁለተኛ ደግሞ ልጇን በጥፋት ሥራ እንድትበረታታ ብቻ ሳይሆን ስለእርሷ ማንም እንደማያገባው እያስተማረች ተግሳጽ እንዳትቀበል እያደረጋቻት መሆኑን አላስተዋለችም።
እናም በዚሁ የስህተት መንገድና ግለኝነት የምንጓዝ ከሆነ፤ ነገ እኛ በየአካባቢያችን በተለያዩ አልባሌ ተግባራት የሚሠሩ ልጆችን ስናይ ጉድ ጉድ ብለን እናልፋለን። በሌላ ቦታ ደግሞ የእኛን ልጆች ሌላው ሰው እያየ «የዛሬ ልጆች የተረገሙ ናቸው» እያለ ያልፋል። በመጨረሻ ሁለታችንም የልጅ ኪሳራ ይገጥመናል። በጋራ ድምር ውጤት ደግሞ እንደ ሀገር የትውልድ ክስረት ውስጥ ለመግባት እንገደዳለን። ቢገባን ጤነኛ፣ የተማረና በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ መኖሩ ጥቅሙ ከቤተሰቦቹ በላይ ለማህበረሰቡ ነው። በመሆኑም በተቻለ አቅም ሁሉም እንደሚያገባንና እንደሚመለከት ልንገነዘብ ይገባናል። የእርሱ ልጅ ጤነኛና ጨዋ መሆን ለእኔ ልጅና ቤተሰብ ደህነነት ዋስትና ነው። የእኔም ልጅ እንደዘያው እንበል። ብለንም ትውልዱን በጋራ እንንከባከብ መልዕክቴ ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ