ኢያሱ መሰለ
መስሪያቤቴ ባዘጋጀው የጉብኝት መርሐ ግብር መሰረት በእንጦጦ ፓርክ ተገኝቻለሁ። በስተሰሜን በኩል ባለው መግቢያ አድርጌ ግራና ቀኝ እያማተርኩ ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቼ ጋር በመሆን ቁልቁል መንደርደር ጀመርኩ። በዛፍ የተሸፈነው ተራራማ ቦታ በነፋሻማ አየር ታጅቦ ነፍስን በሀሴት ያስፈነድቃል። እራቅ እራቅ እያሉ የተገነቡ ማረፊያና መዝናኛ ቤቶች ዓይንን ይማርካሉ። እልፍ ሲሉ ፈረስ መጋለቢያ፤ እልፍ ሲሉ ብስክሌት መጋለቢያ፣ እልፍ ሲሉ ከዛፍ ወደ ዛፍ መረማመጃ፣ እልፍ ሲሉ የገመድ መንሸራተቻ ብቻ እልፍ ባሉ ቁጥር አዳዲስ መዝናኛዎች ይታያሉ።
አብረውኝ የመጡ የመስሪያ ቤቴ ባልደረቦች ከተወሰነ ጉብኝት በኋላ የተሰጠው ሰዓት ሲያልቅ በመጡበት አቅጣጫ ወደ ኋላቸው መመለስ ጀመሩ። እኔ ግን የምመለከታቸው አዳዲስ ነገሮች ስሜቴን ቆንጥጠው ስለያዙት ወደ ኋላ መመለስ አልፈለግኩም። እንደእኔው በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ መስህቡ ከተመሰጠው አንድ የሥራ ባልደረባዬ ጋር አልፎ አልፎ ፎቶ እየተነሳሁ ወደ ፊት ቀጠልኩ። ዓይኔ አዳዲስ ነገሮችን ማየቱን አላቆመም፤ እየተደመምኩና እየተደሰትኩ ቁልቁለቱን ወርጄ የመጨረሻ መዳረሻው ላይ ደረስኩ።
ትልቁ መዝናኛ ቦታ ይመስላል። በርካታ አስተናጋጆች ወዲያ ወዲህ ይላሉ። ማረፊያ ቦታው ገላጣማ በሆነ ስፍራ ላይ ያረፈ በመሆኑ ቁልቁል ሲመለከቱ የአዲስ አበባ ከተማን ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ማራኪው ቦታ ላይ ትንሽ አረፍ ካልኩ በኋላ በስተደቡብ በሚያስወጣው በር አመራሁ። ልቤ ከፓርኩ ግቢ ውስጥ እንደቀረ በመውጫው አስፋልት ላይ እየተምነሸነሽኩ ቁስቋም ማርያም ቤተክርሲቲያን አካባቢ ደረስኩ። የሥራ ባልደረቦቼ እዚያው መግቢው አካባቢ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ በመጡበት መኪና በዚያው ሄደዋል።
እኔም ወደ አራት ኪሎ ለመሄድ አስፋልት ዳር ቆሜ ታክሲ በመጠባበቅ ላይ ሳለሁ በጀርባዋ እንጨት የተሸከመች እናት አስፋልቱን ይዛ ቁልቁል ስትወርድ ተመለከትኳት። እኔ እንጦጦ ፓርክ ተዝናንቼ እንዲህ የደከመኝ እርሷ እንጨት ለመልቀም ዳገት ቁልቁለቱን ስትወጣና ስትወርድ ውላ አንዴት ሊደክማት እንደሚችል አሰብኩ። በዚህም ላይ በጀርባዋ የተሸከመችው እንጨት ብዛቱ ያስፈራል። ጠጋ ብዬ ላናግራት አሰብኩ፤ ፊቷ ላይ ላብ ይታያል፤ ከንፈሯ ደርቋል። ከእሾህና ከእንቅፋት የማያድን አሮጌ የፕላስቲካ ጫማ ተጫምታለች፤ ወገቧን በሰፊ መቀነት ታጥቃ ቁና ቁና እየተፈሰች አጠገቤ ደረሰች። ሰላምታ አቀረብኩላት፤ አጸፋዋን ሰጠችኝ።
በድካም ላይ ያለችን ጎስቋላ እናት አስቁሞ ማናገሩ ቢከብደኝም ትንሽ ሰዓት ሰጥታኝ እንዳናግራት ጠየቅኳት፤ የተሸከመችውን እንጨት ቀጨኔ መድሃኒዓለም ወስዳ ከሸጠች በኋላ ተመልሳ እንጦጦ ማርያም እንደምትገባና ሰዓት እንደማይበቃት ነገረችኝ። ላግባባት ሞከርኩኝ፤ አሁን ደግሞ ሌላ ምክንያት ነገረችኝ። እንጨቱን ተሸክማ ማውራት እንደሚከብዳት፤ ካወረደችው በኋላም የሚያሸክማት እንደማይኖር ነግራኝ ጉዞዋን ጀመረች። የተናገረችው ሁሉ እውነትነት ያለው ነው። ግን ሃሳቧን ማግኘት ስለፈለግኩኝ ድርቅ አልኩባት። እኔና ጓደኛዬ ልናሸክማት እንደምንችል ነገሬያት ካሳመንኳት በኋላ ሸክሟን አውርዳ ወደ ወጋችን ገባን።
ጎስቋላዋ የልጆች እናት ለሃያ ዓመታት እንጨት እየለቀመች በመሸጥ ኑሮዋን ለማሸነፍ ታግላለች። ከልጅነቷ ጀምሮ የጉልበት ሥራ እየሠራች እራሷን ለማኖር ጥራለች። ከማግባቷ በፊት የተለያዩ የቀን ሥራዎችን ሠርታለች፤ ጉልበት በነበራት የወጣትነት ዘመኗ ግንባታዎች በሚከናወኑባቸው ቦታዎች ባሬላ እየተሸከመች እራሷን ረድታለች፤ የተለያዩ የቀን ሥራዎችን በመሥራት ኑሮዋን ለማሸንፍ ታትራለች። ዛሬም ባለትዳር እና የአራት ልጆች እናት ሆና እንጨት እየለቀመች በመሸጥ ቤተሰቧን ታስተዳድራለች። ጠዋት አንድ ሰዓት ወደ ጫካ ተሰማርታ ማታ አስራ ሁለት ሰዓት ሽጣ ወደ ቤቷ ትገባለች። እንጨት ለቅሞ ገበያ እስከማቅረብ ባለው ሂደት ቀን በቀን ከሃያ እስከ ሠላሳ ኪሎ ሜትር በእግሯ ትጓዛለች፤ በዚህም ላይ በጀርባዋ ተሸክማ።
ከዚህ ሁሉ ስቃይ በኋላ የምታገኘው ገንዘብ ከሃምሳ እስከ ስድሳ ብር አይበልጥም። ይህንንም ለቤተሰቦቿ ዳቦ፣ ድንች እና ጥራጥሬ ገዝታ ትገባለች። የቤት ኪራይ፣ የልጆች ልብስ፣ የህክምና ወዘተ ወጪዎች ይጠብቋታል። ምስኪኗ እናት ቀደም ሲል ተከራይታ የምትኖርበት ሽሮሜዳ አካባቢ የቤት ኪራይ ሲጨምርባት እርሱን ለቅቃ እንጦጦ ማርያም አካባቢ ለመግባት መገደዷን ትናገራለች። ያም ሆኖ አሁንም ከኑሮ ጋር በብርቱ ትግል ውስጥ ነች። ይቺ ምስኪን እናት ለችግር እጇን ላለመስጠት የምታደርገው ጥረት ለሌሎች አቅም ሊፈጥር ስለሚችል ለዚህ አምድ አንግዳ በማድረግ ከአንደበቷ የሰማነውን እንዲህ አቅርበነዋል።
ፀሐይነሽ ጎልጃ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው በደቡብ ክልል ነው። ሠርታ ለመለወጥ፣ ህይወቷን ለመለወጥ በማሰብ አዲስ አበባ ከተማ ከመጣች ከሃያ አምስት ዓመት በላይ ሆኗታል። ፀሐይነሽ አዲስ አበባ መጥታ ጥቂት ከሠራች በኋላ ኑሮን ተደጋግፎ ለማሸነፍ በማሰብ በሥራ አጋጣሚ ከተዋወቀችው ሰው ጋር ትዳር መስርታ መኖር ትጀምራለች። ወዲያውም ልጅ ትወልዳለች። በዚህን ወቅት ከነፍሰ ጡር እስከ እመጫትነት ጊዜዋ ድረስ የቀን ሥራ መሥራት ስለማትችል እቤት ተቀምጣ የባለቤቷን እጅ እየጠበቀች ለመኖር ትገደዳለች። በባለቤቷ ገቢ ብቻ ወራትን መግፋት ያልቻለችው ፀሐይነሽ የእመጫትነት ጊዜዋን ሳትጨርስ ወደ ሥራ ትገባለች። ልጅ አዝላ እንደበፊቱ የጉልበት ሥራ ለመሥራት ስለማያመቻት ከምትኖርበት ሽሮ ሜዳ አካባቢ ልጇን አዝላ ወደ እንጦጦ ጫካ ወጣ እያለች እንጨት እየለቀመች መሸጥን ትለማመዳለች። ፀሐይነሽ ከጀርባዋ እንጨት ከፊቷ ሕፃን ልጅ እያዘለች መጠነኛ ገንዘብ በማግኘት ኑሮዋን ለማሸነፍ መጣሯን ታስታውሳለች። ግን በየጊዜው እየተባባሰ ከሚሄደው የኑሮ ውድነት አንጻር ጠብ ያለላት ነገር እንደሌለ በምሬት ትናገራለች።
የልጆቿ ቁጥር እየበዛ ሲሄድ የፀሐይነሽ የኑሮ ትግልም እየበረታ መጣ። ፀሐይነሽ ዛሬ የአራት ልጆች እናት ሆናለች። ሁለቱ ለትምህርት የደረሱ፤ ሁለቱ ለትምህርት ያልደረሱ ናቸው። የማስተማር አቅም ስለሌላት አንዷን ልጇን ወላጆቿ እንዲስተምሩላት በማሰብ ክፍለ ሀገር ልካታለች። ሦስት ልጆቿን ለማሳደግ እላይ ታች ትላለች። ባለቤቷ አንድ ወጥ የሆነ ሥራ እንደሌለው የምትናገረው ፀሐይነሽ አብዛኛውን ጊዜ የሰዎችን ሸማ በመሸጥ እንደሚያሳልፍ ትናገራለች። አንዳንዴ አርሷ የምታገኘውን የቀን ገቢ የሚያህል እንኳ ሳያገኝ እንደሚውል ትገልጻለች።
ፀሐይነሽ ቀደም ሲል እንጨት እየለቀመች በመሸጥ ቤተሰቧን ቀጥ አድርጋ እንደያዘች ትናገራለች። አሁን አሁን ግን እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ተከትሎ ወጪው ከእርሷና ከባለቤቷ ገቢ በላይ ስለሆነ ኑሮን ማሸነፍ እያቃታት መሆኑን ትገልጻለች። ፀሐይነሽ ላቧን አንጠፍጥፋ የምታገኘውን አብዛኛውን ገንዘብ የምታውለው ለቤት ኪራይ እንደሆነ ትናገራለች። ሠርታ ለቤት ኪራይ ብቻ የሚከፈል ቢሆንባትም እጅ ላለመስጠት ስትል ግን ደፋ ቀና ማለቷን አልተወችም።
በአዲስ አበባ ከተማ የቤት ኪራይ የተንገፈገፈችው ፀሐይነሽ በአንድ በኩል የቤት ኪራይ ክፍያ ለመቀነስ፣ በሌላ በኩል እንጨት እየለቀሙ ለመሸጥ እንዲያመቻት በማሰብ ከምትኖርበትን ሽሮ ሜዳ ለቅቃ እንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ አንድ ክፍል ቤት በሰባት መቶ ብር ተከራይታ መኖር ትጀምራለች። ያም ሆኖ ለትምህርት የደረሰውንና አጠገቧ ያለውን ልጇን ማስተማር ፈተና ይሆንባታል። ቦታው ለእርሷ ሥራ አመቺ ቢሆንም የሰው ልብስ እየሸጠ መጠነኛ እገዛ ለሚያደርግላት ባለቤቷ ደግሞ ሌላ ፈተና ይሆንበታል። ቀን በቀን ከእንጦጦ ማርያም ሽሮሜዳና መርካቶ እየተመላለሰ ለመሥራት ይገደዳል። የሚያገኛት ገንዘብ ተመልሳ በትራንስፖርት እያለቀች ስታስቸግረው አንዳንዴ እቤት መዋልን ይመርጣል።
ፀሐይነሽ በየቀኑ ጠዋት ጠዋት ልክ እንደ እርሷ ካሉ የመንደሯ ነዋሪዎች ጋር እንጨት ለቀማ ትሰማራለች። ምንም እንኳን በእርሷ ላይ የደረሰባት ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለ ብትጠቅስም እንጨት መልቀም የተለያ አደጋዎች እንዳሉት ትናገራለች። በዚህ ሁሉ ስጋት ውስጥ ሆና የሰበሰበችውን ጭራሮ ሽጣ ባገኘቻት ገንዘብ ዳቦ፣ ድንች ፣ ስኳር ፣ ጥራጥሬና ቡና እየገዛች ማታ ወደ ቤቷ ትገባለች።
የእንጦጦ ፓርክ እንደእርሷው እንጨት ሲለቅሙ ለነበሩ በርካታ እናቶች የሥራ እድል ቢፈጥርም እርሷ ዘግይታ በመመዝገቧ ምክንያት የእድሉ ተጠቃሚ ሳትሆን ቀርታለች። ይህን እድል አለማግኘቷም ያስቆጫታል። እንደውም ሥራ እቀይርበታለሁ ብላ ተስፋ ያደረገችበት ፓርክ በመከለሉ ምክንያት እንደድሮው ከጫካው የምታገኘውን ጥቅም አሳጥቷት እርቃ ለመሄድ መገደዷን ትገልጻለች። ፀሐይነሽ ቀን በቀን ከሃያ እስከ ሠላሳ ኪሎሜትር እየተጓዘች ኑሮዋን ለማሸነፍ ትጥራለች። ከቀን ወደ ቀን ኖሮዋን ለመለወጥ አስባ ብትታትርም ጭራሽ የእለት ጎሮሮን ለመሸፈን እያቃታት መምጣቷን ትገልጻለች።
ከሰሞኑ የምግብ ሸቀጦች መጨመራቸውን ተከትሎ በእያንዳንዱ እቃ የዋጋ ግሽበት እንደታየበትና የኑሮ ውድነቱ እየተባባሰ መምጣቱን የተናገረችው ፀሐይነሽ ጭማሪው እርሷ በቀን ከምታገኘው ገቢ ጋር እንደማይጣጣም ትጠቅሳለች። በተለይም የዳቦ መጠን መቀነስና የዋጋው መጨመር ኑሮዋን እንዳመሰቃቀለባት ትናገራለች። ከአምስት ዓመት በፊት አንድ መቶ ግራም ዳቦ አንድ ብር ከሠላሳ ሳንቲም ትገዛ እንደነበር የምታስታውሰው ፀሐይነሽ አሁን ዋጋው ከእጥፍ በላይ እንደጨመረ፤ የዳቦው መጠንም እንደቀነሰና እርሱም ቢሆን በሚፈለግ ጊዜ እንደማይገኝ ትጠቅሳለች። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እምብዛም እንጨት አይጠቀሙም የምትለው ፀሐይነሽ ወትሮም ቢሆን እንጨት የሚገዟት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ያሉ ሰዎች በመሆናቸው ዋጋውን ጨምሮ በመሸጥ እየተባባሰ ከሚሄደው የዋጋ ግሽበት ጋር አብሮ ለመጓዝ እንደማያስችል ትናገራለች።
የአዲስ አበባ መስተዳድር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተስብ ክፍሎችን ለመደጎም ሸገር ዳቦን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማዳረስ አስቦ መሥራቱ ጥሩ ድጋፍ ነው ትላለች። ነገር ግን የሚከፋፈለው ዳቦ ውስን በመሆኑ ወዲያውኑ አልቋል እንደሚባልና በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ባለመሆኑ እንደ እርሷ ዓይነት የህብረተሰብ ክፍሎችን እምብዛም እየጠቀማቸው አለመሆኑን ትናገራለች። አንዳንድ ነጋዴች ዳቦውን እየገዙ አትርፈው ይሸጣሉ ያለችው ፀሐይነሽ የሚመከታቸው ባለድርሻ አካላት ለተገቢው ሰው እንዲደርስ ማድረግ ይጠበቅባቸዋልም ትላለች። የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በኑሮ ውድነት እየማቀቁ ላሉ እንደ እርሷ ዓይነት አቅመ ደካሞች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ፀሐይነሽ ትማጸናለች።
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2013