(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
መራር ወግ – ሣግና ሣቅ
“ትግላችን ከድህነታችን ጋር ነው!” ይሉት ዓይነት አደንቋሪ መፈክር የዕለት ቋንቋችንና የሠርክ ማስተዛዘኛችን ከሆነ ሰነባብቷል። “እጅግ የከፋው ድህነታችን…” የሚለው ገለጻማ ጭራሽ ሀገራዊ ስሜትን ያጠለሻል። ድህነትም ወግ ደርሶት እንደ በኸር ልጅ በአንደበታችን አንቀልባ ላይ ታዝሎ እሹሩሩ እየተባለ በየቀኑ ሲንቆለጳጰስ መኖሩ አሌ አይባልም። በተለይም ቀደም ባሉት ዓመታት ያለዚህ መፈክር ንግግር አይደምቅ ይመስል ከቀበሌ እስከ ቤተ መንግሥት፣ ከዲፕሎማሲ አደባባይ እስከ መንግሥታት ጆሮ ስናንቆረቁረው የኖርነው የድህነታችንን የግዝፈት ሥዕል በማጉላት ነበር። ያውም እኮ ስሙን የምንጠራው ድህነት እያልን ሳይሆን “ድህነታችን” እያልን በማሽሞንሞን ጭምር ነው።
“በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” (ማቴዎስ 5፡3) የሚለውን የቅዱስ መጽሐፍ ጥቅስ “አሜን!” በማለት ከተቀበሉት የዓለም አማኒያን መካከል እንደ እኛ ጠበቅ አድርጎ የያዘ ሕዝብ ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን ያስቸግራል። ድህነትን እንደ ብፅዕና፣ “የሌማታችንን ባዶነት” እንደ ጽድቅ እያወጅን የኖርነው “እኛ” እና “እኛ” ብቻ ሳንሆን እንደማንቀርም መጠርጠሩ አይከፋም። ድህነትም ቢሆን ለእርሱ ያለንን ፍቅር በሚገባ ተረድቶት እንደሆን እንጃ በአናታችን ላይ ወጥቶ ፊጥ ካለ እነሆ በርካታ ሥርዓቶች ጠብተው መሽቶባቸዋል።
ለመሆኑ የድህነት መገለጫው ምንድን ነው? አንዳንድ “የድህነት አጥኚና መረጃ ሰብሳቢ ልሂቃን” በሞራል ልዕልናና ብቃት ደፍረው “በምርምር ውጤታቸው ውስጥ” የማይጠቅሱትን የእኛን የድሆች የዕለት ሕይወት አስመልከተን ጥያቄ እንጠይቅ። “ጥያቄ አቅርቤያለሁ መልስ ብትሰጡኝ” ያለው ድምጸ መረዋ ከያኒ ማን ነበር? ዘነጋሁት መሰለኝ። እርሱ ጠይቆ መልስ ያላገኘበትን ጉዳይ መልሼ መጠየቁ “የጅል በትር” እንዳያስመስልብኝ የራሴን ስሜት ለአንባቢያን ብገልጥ ይሻላል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ መቶ አሥራ አምስት ሚሊዮን መድረሱን የሀገሪቱ የእስታስቲክስ ጽ/ቤት ሳይሆን የሕዝብ ዕድገቱን አካሄድ እንገምታለን ባዮች ምሁራን የሚነግሩንን ቁጥር ዋቢ በማድረግ ክርክራችንን እንጀምር። ለምሳሌ፤ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ድሃ ነው” እያሉ እኛን ዜጎችን በሽንገላ፣ እርዳታ ለጋሾቻችንን ደግሞ በማማለል ልብ ከሚሰርቁት የድህነታችን ጠበቆች መካከል “ሀ” ብለን ከአንደኛው እንጀምር።
ምክንያቱስ? ቢባል ድህነት የሚለው ቃል እየተንጎማለለ ሲዘባነን የሚውለው እነርሱ ዘንድ ስለሆነ ቀዳሚውን ምንጭ መጠቆሙ ይበልጥ ተዓማኒነት ይኖረዋል። “ድህነታችን” እያሉ የርሃባችንን ለቅሶ የሚያለቅሱልን ባለ አምስትና አሥር ቪላና ፎቅ ባለቤቶች፣ ባለ 35 ታርጋ የእርዳታ መኪኖችን እየቀያየሩ የሚዘባኑትና መብነሽነሻቸውን እንጂ የወር ደሞዛቸው ስንት እንደሆነ የማያውቁት ሁሉ ተደምረው በድህነታችን ቁጥር ውስጥ ይካተቱ ይሆን? ከሆነ ፍትሐዊ አይደለም።
እነርሱም እንደ እኛ እንደ ተራ ዜጎች “የርሃብን ጉንፋን” ስለማይስሉ ከሚሊዮኖቹ ጋር አብረው መጨፍለቃቸው ደግ አይደለም። ግን አይመስለኝም። ቢያንስ ቢያንስ ግን በምድር ተሞላቀው ኖረው በሰማዩ ዘላለማዊ ቤታችንም የነፍስያችንን ማረፊያ እየተሻሙ እንዳያጣብቡን ከወዲሁ ከዝርዝራችን ውስጥ ብንሰርዛቸው ይሻል ይመስለኛል። ስለ ሰማዩ ጉዳያቸው ከሆነ ፈጣሪ እንደ ፍጥርጥራቸው ያድርጋቸው። “ድህነታችን” የሚለው መዝሙር ከተስማማቸውና መዘመር አናቆምም ካሉ ግን እኛን ግፉዓንን ለቀቅ አድርገው በፈለጉት የእስታስቲክስ ቀመር እየተጠቀሙ በስማችን ሳይሆን በስማቸው ልመናቸውን ሊያጧጡፉ ይችላሉ። (ደጋጎቹንና ቅኖቹን ይህ ብያኔ አይመለከትም።)
ማስረጃችንን ለማወፈር እንዲመቸን የዋናይቱን መዲናችንን ክብርት ከንቲባ ሪፖርት ለማሳያነት በመጥቀስ ሌላ ምሳሌ እናመላክት። በገንዘብ ሲተመን ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት 1,333 ሄክታር (13,389,955 ካሬ ሜትር) በወረራ የተቀራመቱ ባለጊዜዎችም “ከድህነታችን” ጎራ ውስጥ ተዳብለው ለዓለም በሚበተነው የድህነታችን ሪፖርት ውስጥ የማይካተቱ ከሆነ የእነርሱም ብዛት ተሰልቶ “ከድህነት ፋይል” ውስጥ እንዲቀነስልን ግድ ይላል። እስከ አሁን የሰረዝናቸውን ብንደምር ጥቂትም ቢሆን ከመቶ ሚሊዮን ወረድ ያልን ይመስለናል።
ወደፊት እንቀጥል። የመንግሥት ኃላፊነታቸውን ደጀንነት ተማምነው ሥልጣናቸውን መከታ በማድረግ የሕዝብ ገንዘብ የሚዘርፉትን፣ በዘረፉት ገንዘብም ልጆቻቸውን አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ እየላኩ “በልጆቻችን የድህነት ቁስል ላይ እንጨት የሚሰዱትም” ቁጥራቸው ታስቦ ሊቀነሱ ይገባል። ያለበለዚያ የውሸት እስታስቲክስ ማቅረብ “በምድርም ሆነ በሰማይ ስለሚያስጠይቅ” የእነርሱም ብዛት ተሰልቶ ፖለቲካው እንኳን አቅፎ ቢይዛቸው “ከድህነታችን” ዶሴ ውስጥ መሰረዛቸው ግን የግድ ነው። ቀድሞውንስ ድህነትን መች አውቀውት? የድህነትን ሸማ አውልቀው የጣሉት እኮ የተሾሙ ዕለት ነው።
የዕለት ጉሮሯችንን እንዳናሸንፍ ከስግብግብ ነጋዴዎች ጋር እየተሞዳሞዱ በኑሯችን ህመም ላይ ጥዝጣዜ የሚጨምሩትና እነርሱ ከኋላ ሆነው ወደፊት “ግፋ በለው” እያሉ ለዘረፋ የሚያንደረድሩ የመንግስት ሹመኞችም ሊቀነሱ ይገባል። ሃያና ሠላሳ ኮንዶሚኒዬም በስማቸው፣ በትዳር አጋራቸው፣ በልጆቻቸውና በልጅ ልጆቻቸው ስም እየተቀራመቱ፣ አየር በአየር ንግድ ውስጥ ተንሰራፍተው ስለ “ድህነታችን” የሚያወሩትና የሚያሰወሩትም ተሰልተው ከሚሊዮኑ ቁጥር ላይ መቀነስ እንዳለባቸው አቤቱታ ማቅረብ ግድ ይሆንብናል።
ምን ቀረን? ገና ምን ተነካና! ግማሽ አዲስ አበባንና አብዛኞቹን የክልል ከተሞች ሰፋፊ መሬቶች እንደ ገና ዳቦ ገምድለው በመውሰድ እኛ ድሆች “ከኪራይ ተራ ወጥተን” ጎዳና ላይ እንድንወድቅ “በሪል ስቴት ስም” ሚሊዮኖች ብር እየመደቡ በአየር ላይ ብሎኬት እየደረደሩ፣ በእጅ አዙር ስልት ለፍጥረት ሁሉ እኩል የተቸረችውን ምድር እየተቀራመቱና እያቀራመቱ በጭካኔና በግፍ ተፈናቅለን እንድንንከራተት የፈረዱብንም ከዚሁ “የድህነት” ሰልፍ ውስጥ ተቀላቅለው ከሆነ እነርሱም “ስማቸው በጥቁር ቀለም ተሰርዞ እንዲወገዱ” ማድረጉ አግባብ ነው። እኛም በተጋነነ ቁጥር “ድሆች እየተባለን የልመና ሀብት መለመኛ አቁማዳ” ሆነን ዕድሜያችንን እንዳንፈጅ በእኛም ውሳኔ ሆነ በፈጣሪ ፍርድ ፈጥነው ቢቀነሱልን መከራችን ትንሽም ቢሆን የሚቀል ይመስለናል። “ለቃላቸው የሚተጉ፤ በተግባራቸው የተፈተኑ ስመ መልካም የሪል ስቴት አልሚዎችን ይህ ፍረጃ አይመለከታቸውም።)
ዘርፎ የከበረው፣ አዘርፎ የናጠጠው፣ “በፖለቲካ አለሁ ባይነት መንኩሶ” ሀብት በእጅ በእግር የገባለት፣ ፈጣሪ የሰጠንን የተፈጥሮ ሀብት በአልጠግብ ባይነት ሰብስቦ “መሬት የጠበበው” ሁሉ እየተመነጠረ ከሕዝባችን ቁጥር ውስጥ እስካልተነቀሰ ድረስ እንዲሁ የዝማሬው ቅላጼ አማረልን ብለን “ትግላችን ከድህነት ጋር ነው፤ ህዝባችንም የድሃ ድሃ ነው” እያልን በረጂዎቻችን ሥር ብንርመጠመጥና በለጋሽ ሀገራት ፊት ብንቁለጨለጭ የምናተርፈው ትዝብት እንጂ ጥሪት አይሆንም።
የቀናነስነውን ቀናንሰን “እኛ ኦርጂናሌ የሀገሪቱ ድሆች” ምናልባትም ቁጥራችን በግማሽ ዝቅ እንዲል ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም “ከሰድቦ ለሰዳቢ” ልንታደግ ስለምንችል በቁጥር ቅነሳ ዘመቻው ላይ ብንበረታ አይከፋም። ይህንኑ ምክረ ሃሳብ የሕዝብና የቤት ቆጠራ እንዲያካሂድ “በትረ ሥልጣን” ለተሰጠው ተቋም ቀድመን ምክረ ሃሳቡን ብንጠቁመው ሊጠቀምበት ይችል ይሆናል።
ድሃ ማነው? ድህነትስ?
ወጉ አይቅር ለማለት ጠየቅን እንጂ መልሱ እጅግ ሲበዛ ቀላል ነው። “ድሃ” ማለት “ስም ይወጣል ከቤት፤ ይከተላል ከጎረቤት” የሚለውን ብሂል እንድንሸከም የተፈረደብን እኛው የሀገሪቱ ዜጎች ነን። “የድህነት” ብያኔም ቢሆን የሚጀምረው ከአእምሮና ከአስተሳሰብ ስለሆነ የማቴሪያል እጦት ብቻውን “ምስኪን” አሰኝቶ አያስፈረጅም። ስለዚህም የህሊና ነፍሱ የተራቆተ፣ ስግብግብ ማንነት ምርኮኛ አድርጎ ያስገበረው፣ እምነቱና ጸሎቱ “እኛ” ሳይሆን “እኔ” ብቻ ሆኖ የራሱን ጣዖት አቁሞ ለራሱ የሚሰግድ ሁሉ “ድሃ” ያውም የሞራል እርቃኑ የተጋለጠ የድሃ ድሃ ብቻ ሳይሆን፤ የድህነት መገለጫ ጭምር ነው።
እንደ ሕዝብ “ድሆች ነን” እያልን ስንናገር እንኳንስ እርጥባን የሚለግሱን ቀርቶ ተፈጥሮ ራሷ ታዝባ የምትንቀን ይመስለናል። ቀላል መሟገቻ እንምዘዝ። ተፈጥሮ ያጎደለችብን ምን አለ? የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሃ? ለም አፈርና ልምላሜ? ምቹ የአየር ንብረት? የከበሩ ማዕድናትና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች? ወይስ ምን? “እናት ተፈጥሮ” ምን አሳጥታናለች? ምንስ ነፍጋናለች? – መልሱ ምንም የሚል ነው።
እንግዲያውስ ችግሩ ከተፈጥሮ ዘንድ ካልሆነ ምክንያቶቹ እኛው ዜጎች ነን ማለት ነው። ዜጎች ብቻም ሳንሆን የፖለቲካ ሥርዓቱን ሲመሩ የኖሩት የሀገሪቱ መንግሥታትም እኩል ተጠያቂ ሆነው ከህሊና ፍርድ ሸንጎ ፊት ሊገተሩ ግድ ይላል። ለጊዜው የምንኮፈስባቸውንና የምናንቆለጳጵሳቸውን “ባህሎቻችንን” ገሸሽ አድርገን ራሳችንን በግልጽነት እንፈትሽ።
በርግጡ እንደ ማኅበረሰብ ቅንነት መለያችን ነው? ያለንን ቆንጥረን ሳይሆን አካፍለን “ድሆችን” ከድህነት ለመውጣት ነፍሳችን ምን ያህል ርሁሩህ ነች? ለከፍታ የሚንጠራራውን ወገን ቁልቁል እየጎተትን እንዲስተካከለን እንጂ አብረን ተረዳድተን ከስኬት ማማ ላይ ለመድረስ ምን ያህሎቻችን ራሳችንን ለሌላው አሳልፈን እንሰጣለን? ጥቁር ካባ ለብሰን “ምሁር” የመባል ጸጋ የተጎናጸፍን ልሂቃንስ ለሀገርና ለሕዝብ ኖረን ለመሞት ምን ያህል ቁርጠኛ ነበርን/ነን? የፖለቲካ መስፈንጠሪያ ወደ ላይ አጉኖ “ክቡር እና ክብርት” የመባል ጊዜያዊ አክብሮት የተቀዳጁት ሹማምንትስ “ሕዝባችን” እያሉ ለሚሸነግሉት ሕዝብ ምን ያህል የተግባርና የህሊና ታማኞች ናቸው?
የሀገራዊ “ድህነታችን” መንስዔ ንፍገት የፈጠረው አርቴፊሻል እጦት እንጂ የተፈጥሮ እርግማን አይደለም። እስኪ ኪሳችንንና ሀብታችንን እንዳብስ። ለሌላው የሚተርፍ ምንም ትርፍ ጥሪት የለንም? ሥራ ላይ ያልዋለ ሀብትስ በየጓዳችን የለም? እስቲ እውቀታችንን አስተባብረን በአንድነት እንግለጥ፣ እስቲ በተሰየምንበት የኃላፊነት ወንበር በቅንነት አገልግለን እንለፍ፣ ከመተቻቸትና ከመዘነጣጠል ነፃ ወጥተን “አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሺ” የሚለውን ብሂል እያንዳንዳችን ለመተግበር እንሞክር። ከተጣላናት ተፈጥሮ ጋር እርቅ ፈጥረን ምድርን እናልማ፤ ተፈጥሮንም በፍቅር እንንከባከብ።
የፖለቲካ ጦስ ጥንቡሳታችንን ከላያችን ላይ ገፈን ነፃ እንውጣ። የዘረኝነትን ጭንብል ከራሳችን ላይ አውልቀን በመጣል “ሰብዓዊነታችን” ብቻ ግድ ይበለን። ለእኔ ወገን ሳይሆን ለኢትዮጵያ ወገኔ ብለን እንጨክን። በግፍ ፍራሽ ላይ ተጋድመን የክፋት ህልም ማለሙን ትተን እስቲ ሰው ሆነን ሰውን ለመታደግ በብርሃን እንመላለስ። እስቲ የመዘዝነውን “ደም አፍሳሽ” የጥፋት ካራ ወደ ማረሻ ለውጠን ምድርን እናልማበት። ያኔ ድህነት መድረሻና ማረፊያ አጥቶ ሲንከራተትና ሀገር ጥሎ ሲጠፋ እናስተውላለን። የተዘረዘሩትን ሁሉ ተግባራዊ አድርገን ድህነት ካልተረታ ይህ ጸሐፊ ራሱን በራሱ ለሕዝብ ፍርድ አቅርቦ የሚበየንበትን ለመቀበል ጀርባውን ለጅራፍ ያዘጋጃል። ሰላም ይሁን
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2013