በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር በሚሊየን እንደሚቆጠር መረጃዎች ያሳያሉ:: ይህ የህብረተሰብ ክፍል የተሻለ ኑሮ ፍለጋ፤በፖለቲካ ተጽእኖ፤ ለትምህርት ወዘተ ሀገሩን ለቆ የወጣና ኑሮውንም በአውሮፓና አሜሪካ ሌሎች አገራትም የመሰረተ ነው::
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ እስካሁን በነበረው ሁኔታ በሀገር ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና ልማት እንዲረጋገጥ ድምጹን ሲያሰማ ቆይቷል:: በተለይም ቀደም ሲል የነበረው መንግሥት የሚፈጽማቸውን የመብት ጥሰቶችንና አፈናዎችን በመቃወም በህዝብ አመጽ እንዲገረሰስ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል::
በዶክተር አብይ የሚመራው የለውጥ መንግሥት ስልጣኑን ከያዘ በኋላ የዲያስፖራው ተሳትፎ ከመቃወም ወጥቶ በተለያዩ ልማቶች ላይ አሻራውን ወደ ማሳረፍ ተሸጋግሯል::ለህዳሴ ግድብ፤ለገበታ ለሀገር፤ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍና በየጊዜው ለሚደርሱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ያለውን ገንዘብ በማዋጣትና በሀሳብና በዕውቀት በመደገፍ ሀገራዊ ግዴታውን በመወጣት ላይ ይገኛል::
በተለይም በቅርቡ በትግራይ ክልል የተካሄደውን ህግ የማስከበር ዘመቻ በመደገፍ ያሳየው ሀገራዊ ተቆርቋሪነትና አለሁ ባይነት በእጅጉ የሚያስመሰግነው ነው:: የህወሓት ቡድን ራሱ ቆስቁሶ በጋየበት የሕግ የበላይነትና የህልውና ዘመቻ ህዳር 19 ቀን 2013 ዓም በአንጸባራቂ ድል ቢጠናቀቅም በውጭ ሀገራት የሚገኙ የቡድኑ ርዝራዦች የከፈቱት ሀሰተኛ የሚዲያና የኮሚኒኬሽን ዘመቻ ግን መጠነ ሰፊ ነው:: በዚህ የሀሰት ፕሮፖጋንዳም ኢትዮጵያ በውጭው ዓለም ዘንድ ስሟ እንዲጎድፍና ኢትዮጵያም አንገታቸውን እንዲደፉ እስከዛሬም ያላበራ ውርጅብኝ እየደረሰባቸው ይገኛል:: ከዛም አልፎ ኢትዮጵያ ያልተረጋጋችና ለመፍረስ የቀረበች ሀገር እንደሆነች አድርጎ በመሳል የውጭ ኃይል እንዲወራትም ግፊትም በማድረግ ላይ ይገኛሉ::
የጁንታው ርዝራዦች የሚያደርጉት ሀገር የማጠልሸትና ሉዓላዊነትን ለባዕዳን ኃይሎች አሳልፎ የመስጠት ክህደት ያሳመማቸው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቀፎው እንደተነካበት ንብ ከዳርእስከዳር መንቀሳቀስ ጀምረዋል:: በዋሽንግተን፤ በጣሊያን፤ በካናዳ ኦታዋ፣ ሞንትሪያል፣ በቶሮንቶ፣ በክችነር፣ በሎንዶን ኦንታሪዮ፣ በኤድመንተን፣ በሊትብሪጅ እና በካልጋሪ ከተሞች ሰፊ ጸረ ጁንታና ሉዓላዊነታችንን አትጋፉ ሰልፎችን በማድረግ ለሀገራችን ያላቸውን ቀናኢነት አሳይተዋል::በተለይም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግሥት የወሰደውን የህግ ማስከበር እርምጃ የሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑ እየታወቀ የጁንታው ቡድን ባናፈሰው ፕሮፓጋንዳ አንዳንድ ዓለምአቀፍ ተቋማት እና መንግሥታት እውነታውን ባለገናዘበ መልኩ እየወሰዱት ያለውን ጣልቃ ገብነት እንደሚቃወሙ ባካሄዱት ሰልፍ ገልጸዋል::
ተጎጂውን በዳይ አድርጎ የሚፈርጅ አቋም በመያዝ በሃገር ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ለማሳረፍ የከፈቱትን ያልተገባና ከእውነት ያፈነገጠ ጫና እንደሚቃወሙም ሰልፈኞች የገለጹ ሲሆን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ የሚገቡ ተቋማትና አገራት ድርጊታቸውን እንደሚቃወሙና የጁንታው ቡድን በንጹሃን ላይ ያደረሰው ጭፍጨፋ እንደሚያወግዙም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስረድተዋል:: በሂደቱም የኢትዮጵያ መንግሥት ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ለወሰደው እርምጃ ያላቸውን ድጋፍም ገልፀዋል::
ሰልፈኞች በወቅቱም የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት በተለይም የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አባላት የሆኑት የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ መንግሥታት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባትና የማይገባ ጫና ከመፍጠር እንዲቆጠቡ የኢትዮጵያን ህዝብ እንዲደግፉ የሚያሳስብ ደብዳቤም አቅርበዋል:: ለቻይና፣ ሩስያና ህንድ ኤምባሲዎች ደግሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ ላሳዩት ታማኝነትና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት ላደረጉት ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል::
በአጠቃላይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ከሀሰተኛ ፐሮፖጋንዳ ለመታደግ እያደረጉት ያለው ጥረት የሚበረታታና በሰው ሀገር ከኑሮ ጋር ግብግብ እየገጠሙም ቢሆን ለሀገራቸው ቅድሚያ እንደሚሰጡ ያሳየ አኩሪ ገድል ነው:: ያለምንም የብሄርና የኃይማኖት ልዩነትም በተለያዩ የዓለም ሀገራት ያደረጉት ሉዓላዊነት የመታደግ ተግባርም በታሪክ የሚመዘገብ አኩሪ ተግባር ነው::
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውስጥና ከውጭ ኃይላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ ያሉትን የህወሓት ቡድን ርዝራዦችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድና የተረጋጋች፤ የበለጸገችና የታፈረች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ በዲያስፖራ አባላት የተጀመረው ሀገርን የመታደግ ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት!
አዲስ ዘመን መጋቢት 3 ቀን 2013 ዓ.ም