በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ300 ቀናት ቆይታን አስመልክተው ንግግር አድርገዋል። በወቅቱ ከወጣት ሥራ አጥነት ጋር ተያይዞ ከምክር ቤቱ ለተነሳላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ «የመዋቅር ችግር አለ፤ ከዓመታት በፊት መንግሥት ለተዘዋዋሪ ፈንድ አስር ቢሊየን ብር መድቦ ነበር። ከዚህ ውስጥ ዘጠኝ ነጥብ ሁለት ቢሊዮኑ ለክልሎች የተለቀቀ ቢሆንም እስከአሁን የተመለሰው ግን አንድ በመቶ ብቻ ነው። በመሆኑም ይሄ ሳይመለስ ተጨማሪ መስጠት ያስቸግራል። ተዘዋዋሪ ፈንድ ሽልማት አይደለም። አበድሮ መልሶ መሰብሰብ፤ ሰብስቦም ለሌላ ማበደር ይጠበቃል። ሥራ አጥነት ለሁሉም ሀገር ፈተና ቢሆንም ለኢትዮጵያ ግን ቀጣይነት ያለው ፈተና ነው።
«በ1986 የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት 53 ሚሊየን ነበር አሁን በእጥፍ እድጓል። ከሠላሳ ዓመት በኋላ ደግሞ በእጥፍ ያድግና በ2050 የሀገሪቱ ህዝብ ብዛት ሁለት መቶ ሚሊየን ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን ሥራ ፈላጊ ይፈጠራል። የሥራ ዕድል እየተፈጠረ ያለው ግን አንድ ሚሊዮን ለሚሆነው ብቻ ነው።
«በግብርናው መስክ ብቻ ያለው ሲታይ የአርሶአደር ልጆች ሆነው በቤተሰብ ላይ ተዳብለው የሚኖሩት 41 በመቶ ደርሰዋል። ይህም ወጣቶቹ በየቤታቸው በአንድ ሰው ይሠራ የነበረውን ሥራ እየተሻሙ እየሠሩ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ይሄ ካልተስተከከለ የህዝብ ብዛት በጨመረ ቁጥር ችግሩም እየጨመረ የሚቀጥል ይሆናል። በመሆኑም በህዝብ ቁጥር ልክ ዕድገቱም መጨመር አለበት። በሌላ በኩል እንደ ጥጥ ለቀማና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ባሉት የሥራ መስኮች ሥራ ኖሮም ሠራተኛ የማይገኘበት ሁኔታም አለ። በመሆኑም እንደ ግለሰብ ሥራ ያለበት ሄዶ የመሥራት መልመድ መዳበር አለበት። እንደ መንግሥት ደግሞ ሥራ የሚጀምሩትን በተለይ ለሴቶች ድጋፍ ማድረግ፣ ኢንቨስተሮችን መሳብና እንዲሁም በመላው የሀገሪቱ ክፍል ምቹና ሰላማዊ የሥራ ሁኔታ እንዲፈጠር መሥራት ይጠበቃል» በማለት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት መንግሥት ለዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠር ግዴታና የዜጎች በነፃነት ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብት በህግም የተደነገ ነው። የኢፌዴሪን ህገ መንግሥት ስንመለከት ስለ ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሚደነግግበት ክፍል ሁለት የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና የባህል መብቶችን በተመለከተ በአንቀጽ 31 ቁጥር ሁለት ላይ «ሁሉም ኢትዮጵያዊ መተዳደሪያውን፣ ሥራውንና ሙያውን የመምረጥ መብት አለው» ይልና በቁጥር ስድስት ደግሞ «መንግሥት ለሥራ አጦችና ለችግረኞች ሥራ ለመፍጠር የሚያስችል ፖሊሲ ይከተላል፤ እንዲሁም በሚያካሂደው የሥራ ዘርፍ ውስጥ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሥራ ፕሮግራሞችን ያወጣል፤ ፕሮጀክቶችን ያካሂዳል» ይላል። በቁጥር ሰባት ደግሞ «መንግሥት ዜጎችን ጠቃሚ ሥራ የማግኘት ዕድላቸው እየሰፋ እንዲሄድ ለማድረግ አስፈላጊ ዕርምጃዎችን ይወስዳል» ይላል። እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት የህገ መንግሥት አንቀጾች በሙሉ መንግሥት አቅሙ በፈቀደ መጠን ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንዳለበት የሚያመላክቱ ናቸው።
ነገር ግን በህገ መንግሥቱ የተቀመጠውም ሆነ በመንግሥት የተሠሩት ሥራዎች እንዳሉ ሆነው በፌዴራልም ሆነ በክልል እየተፈጠረ ያለው የሥራ ዕድል በቂ አለመሆኑ ግልጽ ነው። ይሄ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳስቀመጡት ከክልል ከተሞች ወጣ ሲልና ወደ ገጠሩ ሲገባ ችግሩ ይበለጥ እየሰፋ ይመጣል። በሀገሪቱ የገጠር አካባቢዎች የሥራ ዕደል እየተፈጠረ ያለው በአብዛኛው ከመሬት ጋር በተያያዘ በግብርና ሥራ ነው። የሀገሪቱ መሬት ደግሞ ውስን በመሆኑ የፈጠራ ሥራ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂና ምርታማነትን የሚጨምሩ ግብአቶች ካልታከሉበት ውጤቱ አመርቂ አይሆንም። በመሆኑም መሽቶ በነጋ ቁጥር ምርትና ምርታማነትን እየጨመሩ መሄድ ካልተቻለ ያለችውን መሬት እየተቀራመቱ መሄዱ የሚያዋጣ አይሆንም። ዛሬም በዓመት ሁለት ወቅት የሰማይ ዝናብ ጠብቆ የሚያመርት አርሶአደር መሬቱን በየወቅቱ ለልጆቹ ሸንሽኖ እየሰጠ የትም መድረስ አይቻልም።
የተሻለ ሥራ ለማግኘት በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የሚሰደዱት ወጣቶች ቁጥር በየዕለቱ እየጨመረ ይገኛል። የአረቡ ዓለም ባይሆንም በሀገር ውስጥ የሚደረገውም የሥራ ፍለጋ እንቅስቃሴ እንዲህ ቀላልና አልጋ በአልጋ የሚባል አይደለም። ከአንዱ ክልል ወደ አንዱ የሚጓዙት በሺዎች የሚቆጠሩ ሥራ ፈላጊዎች እንዳሉ ሆነው፤ አብዛኞቹ መዳረሻውን የሚያደርጉት ግን አዲስ አበባ ነው።
ይህ አካሄድም ቢሆን በአንድ ወገኑ ሲታይ ህጋዊ መሰረት ያለው ነው። በህገ መንግሥቱ ከላይ በተጠቀሰው ክፍልና አንቀጽ ቁጥር አንድ «ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት አለው» ይላል። በመሆኑም ከየትኛውም ክልል ወደ ሸገርም ሆነ ሌሎት ክልሎች የሚደረገው የሥራ ፍለጋ ጉዞ በህግ አግባብ የተፈቀደነው ማለት ይቻላል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የዛሬዋ አዲስ አበባ ከልመና እስከ ዝሙት አዳሪነት፤ ከቀን ሥራ እስከ ቢሮ ሠራተኝነት፤ ለሁሉም ቀዳሚ ተመራጭ ከተማ እየሆነች መጥታለች። ለዚህም ከተማዋ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ቋት መሆኗ አንዱ ምክንያት ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ከየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በተሻለ ሰላሟ የተረጋጠባት መሆኗ ነው። ይህም እስከአሁን የመጡትንና እየመጡ ያሉትን የሥራ ፈላጊዎች ብቻ ሳይሆን ነገን ተስፋ አድረገው የሚመጡትም ቁጥራቸው ቀላል እንደማይሆን አመላካች ነው።
ከዓመታት በፊት በአዲስ አበባ የሚታወቁት የሥራ መስኮች ለወንዶች የቀን ሠራተኝነት፤ ለሴቶች ደግሞ በቤት ሠራተኝነት መቀጠር ነበር። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኮንስትራክሽኑን ዘርፍ ተመራጭ ሆኖ ቆይቷል። አሁን ደግሞ የጎዳና ላይ ንግድ ለብዙ ወጣቶች መተዳደሪያ እየሆነ መጥቷል። በዚህም የሥራ መስክ እንደ ቀን ሥራውና የቤት ሠራተኝነቱ ሁሉ አብዛኞዎቹ ሠራተኞች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ወጣቶች ናቸው።
እነዚህ ወጣቶች ህጋዊ ባልሆነ መንገድ በኮንትሮባንድ የሚገቡ ዕቃዎችን የሚነግዱት ከፖሊስና ደንብ አስከባሪ ጋር አባሮሽ እየተጫወቱ ለኪሳራና ለአደጋ እየተጋለጡ ነው። ሥራው በጊዜያዊነትም ቢሆን ወጣቶቹን ተጠቃሚ ስለሚያደርጋቸው በርካቶች በየቀኑ የትምህርት ገበታቸውን እየተው እየተቀላቀሉት ይገኛሉ።
መንግሥት የወጣቶችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲማሩና እውቀታቸውን እንዲያሻሻሉ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ይሰማኛል። በመሆኑም በየትኛውም አካባቢ ቢሆን የሚፈጠረው የሥራ ዕድል ዘላቂ እንኳ ባይሆን ወጣቶቹን ደህንነታቸውን፣ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋጥና ማህበራዊ ዋስትና የሚያገኙበትና ህጋዊ መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ። የጎዳና ላይ ንግድ ከከተማዋ ነዋሪዎች ሰላም አንፃርም መታወቂያ የሌላቸውና መታወቂያ ለማውጣት ዕድሚያቸው ያልደረሱ ወጣቶች መብዛት ለሀገሪቱ ለሰላምና ደህንነት ስጋት መሆኑ አይቀርም።
በአጠቃለይ እስከአሁን የሥራ ዕድል በመክፈት ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግ የተሄደበት ጉዞም እንደ ሀገር መፈተሽ አለበት። ከአስር ዓመት በፊት ዶክተር አርከበ እቁባይ የከተማዋ ከንቲባ በነበሩበት ጊዜ የተጀመሩት እንቅስቃሴዎች ተጠቃሚ ያደረጉት የህብረተሰብ ክፍል ያለ ቢሆንም በታሰበላቸው ልክ ግን ውጤታማ አልነበሩም። አንደኛ በአምስት ዓመት ውስጥ የተሰጧቸውን ሱቆችና መነሻ ጥሪት በመጠቀም ራሳቸውን አብቀተው ለሌሎች ቦታ እንዲለቁ ታስቦ የተጀመረ ነበር። ይሁን አንጅ አሁንም ድረስ በዚው ሥራ ውስጥ የሚገኙት በርካቶች ናቸው። ይሄ ሲሆን እንግዲህ በየቀኑ ዕድሜያቸው ለአቅመ ሥራ እየደረሰ በየመንገዱ ዳር የሚቀመጡትን ወጣቶች መንግሥት መላ እንዳይላቸው በር እየተዘጋባቸው እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል።
በተመሳሳይ ዛሬም ከዓመታት በኋላ በጥቂት ወጣቶች የተጀመረው ህገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድ በሺዎች የሚቆጠሩትን እያስተናገደና ለብዙዎችም በህገወጥ መስመር ተስፋን እያሰነቀ ይገኛል። ዛሬ ዕለት ከዕለት እየጨመረ የመጣው የጎዳና ላይ ንግድ መንግሥትን ወደማይቆጣጠረው አቅጣጫ ይመራዋል የሚልም ስጋት አለኝ።
ትናንት ከየቤታቸው የወጡት ወጣቶች ታናናሽ እህትና ወንድሞች ደግሞ ነገ ወደ ሸገር በማቅናት የህይወታቸውን መስመር አቅጣጫ ለማስያዝ ማሰባቸውና መንቀሳቀሳቸው የማይቀር ነው። በመሆኑም ዛሬ ያሉትን ወጣቶች በቀን በቀን እየተቀበሉ ማስተናገድ ለነገዎቹ በር መክፈት በመሆኑ መንግሥት ለምን? መቼ? እና የት? የሥራ ዕድል መክፈት እንዳለበት በጥንቃቄ መፈተሽ ይኖርበታል።
በቅርቡ መንግሥት ወጣቶችን ለማባበል በሚመስል መልኩ በየክፍለ ከተማውና በየወረዳው እየሰበሰበ ተስፋ ሰጥቷቸዋል። ይህን ተከትሎ በየጥጋጥጉ የህዝብን ሰላማዊ እንቅስቃሴ በሚገዳደር፣ የከተማዋን ውበት በሚያጠፋና የእግረኛ መንገዶችን በመዝጋት በእንጨት፣ በላስቲክ እንዲሁም በቆርቆሮ አነስተኛ ሱቆችን እየተሠሩ ነው። የከተማ አስተዳድሩ ይሄ ሥራ ተገቢ አለመሆኑን በማመን ጉዳዩ መቆም እንዳለበትና ዕርምጃ እንደሚወስድም ቃል ገብቷል። ሥራው ግን እንዲህ በቀላሉ በደንብ ማስከበርና በፖሊስ ግፊት ይፈታል ብሎ መጠበቁም አስቸጋሪ እንደሚሆን ግልጽ ነው። ምክንያቱም እነዚህ የሸገርን ኑሮ የመረጡ ወጣቶች ነገ ወደ መጣችሁበት ተመለሱ ቢባል በቀላሉ የሚቀበሉ አይመስሉም። ወደ ህጋዊ መስመርም ለማስገባት ቢታሰብም ከፍተኛ ገንዘብና ሰፊ ቦታ ይጠይቃል።
በመሆኑም መንግሥት ሱቅ የገነቡትን ማስነሳት ቢችል እንኳ በጎዳና ላይ የሚያደርጉትን ሩጭ ግን መግታት አይችልም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከቤት ውስጥ መገልገያ እስከ አልባሳትና የምግብ ዕቃዎች በመደብሮች ያሉት ሸቀጦች ሁሉ በጎዳና ላይ እየተሸጡ ይገኛሉ። በመሆኑም ችግሩ ከዚህም ባለፈ በህጋዊ መንገድ ተመዝገበውና ግብር ከፍለው የሚሠሩትንም ነጋዴዎች ተስፋ የሚያስቆርጥ ይሆናል።
ዛሬም ለመንግሥት ጊዜው የረፈደ አይደለም። በአንድ በኩል የፌዴራል መንግሥት አዲስ አበባ ላይ የተከማቸውን የኢኮኖሚ፣ የሰላምና የማህበራዊ ምቹነት በተቻለ መጠን በሌሎቹ የክልል ከተሞች ላይ ማስፋፋት ይጠበቅበታል። በሌላ በኩል ለአርሶአደሩ እየተደረገ ያለውንም ድጋፍ በማጠናከር ዓመት ሙሉ ሊሠራና ሊያመርት የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት። እንደ ጥጥና ሰሊጥ ወቅትን ጠብቀው በሚሠሩ ሥራዎችና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ዜጎች መብታቸው ተክብሮ፤ ሊያገኙ የሚገባቸውን ጥቅም እያገኙ እንዲሠሩ ጥበቃና ከለላ ማድረግም ሌላው የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል።
ወደ አዲስ አበባ ስንመለስ የከተማዋ አስተዳደር ማንኛውም ዜጋ በፈለገበት ቦታ፤ የፈለገውን ሥራ የመሥራት መብት ቢኖረውም በዚህ ሽፋን ህገ ወጥ ሥራዎችን ማበረታታት የለበትም። በዚህ በኩል በጎዳና ላይ ንግድ ከሚሸጡት ሸቀጦች አብዛኛዎቹ በህገወጥ መንገድ ከውጭ የገቡ ሊሆኑ ስለሚችሉ ጥያቄ ያስነሳል። ከዓመት እስከ ዓመት ሳይነጥፍ በጎዳና ላይ የሚሸጥ ምርት እንዴት ሊገባ እንደቻለም ማሰብ ይገባል።
ሸቀጦቹን መንግሥት በኮንትሮባንድ እየያዛቸው ከሆነ ነጋዴዎቹ የኮንትሮባንድ ሥራውን የማያቆሙት ከተያዘው በብዙ እጥፍ የሚበልጥ እያስገቡ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ካልሆነ ከዓመት ዓመት እየተነጠቁ እንዴት በሥራ ውስጥ ሊቆዩ ይችላሉ? ብሎ መጠየቅ ይገባል። የዚህን ያህል ኮንትሮባንድ የሚገባስ ከሆነ የሀገሪቱ ደህንነት ጉዳይ ጥያቄ አያስነሳምን? በህጋዊ መንገድ ያስገቡ ከሆኑ ደግሞ በህጋዊ መንገድ እንዲሸጡ ለምን ቁጥጥር አይደርገም? መንግሥትስ በጨረታ እየሸጠ ከሆነ ፈቃድና መደብር ላላቸው ነጋዴዎች ለምን አይሸጥም? የሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት ይኖርባቸዋል።
ሌላው የሚያስነሳው ጥያቄ አዲስ አበባ ሥራ አለ ብለው የሚመጡ ወጣቶች ያሰቡት ካልሆነ መጨረሻቸው ጎዳና መሆኑ አይቀርም። በቅርቡ የተጀመረው የጎዳና ተዳዳሪዎችን የመለወጥ እንቅስቃሴም ጥያቄ ውስጥ መግባቱ ነው። እነዚህ ወጣቶች ውለው ሲያድሩ የጤና፣ የመኖሪያ ቤትና መሰል አገልግሎት እንደሚያስፈል ጋቸውም መታወቅ አለበት።
የከተማ አስተዳድሩ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ከማበጀት ባሻገር አሁን ያሉትንም ቢሆን ምን ያህል እንደሆኑ፤ በምን የሥራ መስክ እንደተሰማሩ፤ የት ውለው የት እንደሚያድሩ፤ ለንግድ ስርዓቱና ለከተማ ውበት ብቻ ሳይሆን ለሀገርና ለህዝብ ደህንነትም ሲል መመዝገብና ማወቅ ይኖርበታል። በመሆኑም እንደቀልድ የተጀመረው ጉዞ ኋላ ማጣፊያው እንዳያጥር በጊዜ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግና የጀመረውን ህግ የማስከበር ሥራውን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። በተለይም ለህጋዊ የሥራ ፈጠራ ትኩረት መሰጠት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ