በአሁኑ ወቅት በኮሮና ምክንያት ለሞት ከሚዳርጉ ተጓዳኝ ከሚባሉ የጤና ችግሮች መካከል የኩላሊት ህመም አንዱ ነው።ስለሆነም ለኩላሊት ህመም ከምንወስዳቸው መድሃኒቶች ጎን ለጎን አመጋገባችን ወሳኝነት አለው።ከኩላሊት ህመም ጋር ተያይዞ መመገብ ያለብን ገደብ እንደየህመሙ ደረጃ ይወሰናል። ቢሆንም የራሱ አስተዋጽኦ አለው። የኩላሊት ህመምተኞች በአመጋገብ ወቅት መገንዘብ ካለባቸው ነጥቦች መካከል የሚከተሉትን ንጥረ ነገሮች መጠን ወይም ገደብ ማወቅ ነው፡-
- ሶዲዬም፡- ሶዲየም (ጨው) ያላቸው ምግቦችን መገደብ ይመረጣል፤ ምክንያቱም በአግባቡ ሳይጣሩ ሲቀር የኩላሊትን ሥራ ጫና ላይ ከመክተት ባለፈ የደም ግፊት እንዲጨምር ያደርጋል። ሰለሆነም በቀን 2000 ሚ.ግ በታች ነው መጠቀም የሚኖርብን።
- ፖታሲየም፡- ይህም ተያይዞ የሚመጣውን የግፊት መጨመር ለመቆጣጠር እንድንችል መገደብ ይኖርብናል፤ በቀን 2000 ሚ.ግ በታች መጠቀም ይመከራል።
- ፎስፈረስ፡- በተጎዳ ኩላሊት ለመጣራት ባለመቻሉ የኩላሊትን ሥራ ጫና ላይ ይከታል ለዚህም በቀን ከ800-1000 ሚ.ግ በቂ ይሆናል።
- ፕሮቲን፡- ይህም ሌላኛው መገደብ ያለበት ሲሆን፤ ኩላሊታችን በአግባቡ ስለማያጣራው መጠኑን ማስተካከል ተመራጭ ይሆናል፤ ነገር ግን የመጨረሻ ደረጃ ላሉ (ዳያሊስስ) ለሚያደርጉ ያስፈልጋል።
ለኩላሊት ህመምተኞች ተመራጮች የሆኑ ምግቦች
1. የአበባ ጎመን፡- ይህ በንጥረ ነገር የበለጸገ ሲሆን፤ እንደ ቫይታሚን ሲ፣ ኬ እና ቢ (ፎሌት) የያዘ ነው። ብግነትን ያበርዳል (anti-inflammatory)፤ የፋይበር ምንጭ ነው፤ አንድ ስኒ የበሰለ አበባ ጎመን በውስጡ፡- ሶዲየም (19ሚ.ግ)፣ ፖታሲየም (176ሚ.ግ) እና ፎስፈረስ (40ሚ.ግ) ይይዛል።
2. ዓሣ (የ Sea bass ዝርያ)፡- ፕሮቲን እንዲሁም ኦሜጋ 3 ይይዛል። የበሰለ 85 ግራም ዓሣ በውስጡ፡- ሶዲየም (74ሚ.ግ)፣ ፖታሲየም (279ሚ.ግ) እና ፎስፈረስ( 211ሚ.) ይይዛል።
3. ቀይ ወይን፡- ከጣፋጭነቱ ባለፈ ቫይታሚን ሲ እንዲሁም አንቲ ኦክሲደንት ይይዛል። ይህ ደግሞ በሰውነት የሚከሰቱ መቆጣቶችን ያክማል። ግማሽ ስኒ (75ግራም) ውስጥ፡- ሶዲየም (1.5 ሚ.ግ)፣ ፖታሲየም (144ሚ.ግ) እና ፎስፈረስ (15ሚ.ግ) ይይዛል።
4. ነጭ ሽንኩርት፡- ብዙ ጊዜ የኩላሊት ህመምተኛ ጨው እንዲቀንስ ይመከራል፤ የዚህን መተኪያ ጣእምን ለመተካት ታዲያ ምርጫችን ማድረግ ይመከራል። ከዚህ ባለፈ ግን የበዙ ንጥረ ነገሮች ምንጭም ጭምር መሆኑ የበለጠ ጥቅሙን ያጎላዋል። ሦስት ፍሬ ነጭ ሽንኩርት በውስጡ፡- ሶዲየም (1.5ሚ.ግ)፣ ፖታሲየም (36ሚ.ግ) እና ፎስፈረስ (14ሚ.ግ )ይይዛል።
5. የወይራ ዘይት፡- ከፎስፈረስ ነፃ መሆኑ ለብዙ የኩላሊት ህመምተኞች ተመራጭ ያደርገዋል። በውስጡ ጠቃሚ የሚባለውን ቅባትም ይይዛል። አንድ የሾርባ ማንኪያ የወይራ ዘይት በውስጡ፡- 0.3ሚ.ግ ሶዲየም፣ 0.1ሚ.ግ ፖታሲየም እና 0ሚ.ግ ፎስፈረስ ይይዛል።
6. የዶሮ ሥጋ፡- ጠቃሚና ተመጣጣኝ ፕሮቲን በውስጡ ይይዛል። 85 ግራም የዶሮ ሥጋ ውስጥ 63 ሚ.ግ ሶዲየም፣ 216 ሚ.ግ እና 192 ሚ.ግ ፎስፈረስ ይይዛል።
7. ቀይ ሽንኩርት፡- የምግብ ልመት የተስተካከለ እንዲሆን ያግዛል። አንድ መካከለኛ ቀይ ሽንኩርት፡- 3ሚ.ግ ሶዲየም፣ 102 ሚ.ግ ፖታሲየም እና 20 ሚ.ግ ፎስፈረስ ይይዛል።
8. አናናስ፡- አነስተኛ ፖታሲየም ከሚይዙ ከሌሎቹ ፍራፍሬዎች ለየት ያደርገዋል። 165 ግራም አናናስ በውስጡ፡- ሶዲየም (2ሚ.ግ)፣ ፖታሲየም (180ሚ.ግ) እና ፎስፈረስ (13ሚ.ግ) ይይዛል።
ምንጭ ፦ከዶክተር አለ
አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2013