አስም የመተንፈሻ አካላችን ባእድ በሆኑ የትንፋሽ አለርጂ ቀስቃሽ ኬሚካሎች ተጽእኖ ከሚገባው በላይ በድንገት ለተወሰነ ጊዜ መጥበብ ነው። ይህ የአየር ቧንቧ ጥበት መድኃኒት ሲወስዱ ወደነበረበት በቀላሉ ሊስተካከል የሚችል ነው። አሁን የምንገኝበት ወቅት ደግሞ ክረምትና ቅዝቃዜ የሚበዛበት በመሆኑ ህፃናት በቅዝቃዜ ምክንያት የሚባባስ የአፍንጫ አለርጂ እና የሳምባ አለርጂ ወይም የአስም በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠቁበት ጊዜ ነው፡፡
የአስም በሽታ ተላላፊ ካልሆኑ የበሽታ ዓይነቶች (major noncommunicable disease) የሚመደብና ሳንባችንን የሚጎዳ የህመም አይነት ነው። በ2019 እ.አ.አ የዓለም ጤና ድርጅት ዘገባ በዓለም ላይ 262 ሚሊዮን ሰዎች የአስም በሽታ ተጠቂዎች ናቸው። 461 ሺህ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው በአስም በሽታ ምክንያት አልፏል፡፡ የአስም በሽታ የሚያጠቃው የሳንባችንን የአየር ቧንቧዎች ሲሆን እነዚህን ቧንቧዎች በማጥበብ እና በቂ አየር ወደ ሳንባችን እንዳይገባና እና እንዳይወጣ በማድረግ እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል፡፡
መነሻ ምክንያቶቹ
ለአስም ዋና ምክንያቱ ተፈጥሯዊ፣ አካባቢያዊ እና ቀስቃሽ በሆኑ ምክንያቶች ይነሳል። የሚፈጠረው መስተጋብር አየር ቧንቧን ለዘላቂ ቁስለት/ብግነት በማጋለጥ አለርጂ ቀስቃሽ በሽታዎች ሲኖሩ የአየር ቧንቧ ከልክ ያለፈ ተለዋጭ ጥበት እና የቆሸሸ አየር ከሳንባ በሚፈለገው ልክ አለመውጣት፣ ሳል እና የመታፈን ምክንያትን ያመጣል። አካባቢያዊ እና ቀስቃሽ ምክንያቶችን መቀነስ ይቻላል።
የአስም አይነቶች
1. በተደጋጋሚ የሚነሳ አስም /recurrent asthma seasonal/፦ ይህ ወቅታዊ ሁኔታዎች የሚያስነሱት አስም ነው። ቀስቃሽ ምክንያቶችን በመቀነስ ድግግሞሹን መቀነስ እና ደረጃውንም መቆጣጠር ይቻላል።
2. ረጅም ጊዜ የቆየ አስም /chronic asthma/
አለርጅ/አስም ቀስቃሾች ምንድን ናቸው?
1. የሲጋራ፣ የከሰል እና የማገዶ ጭስ
2. የአበባ፣ ቆሻሻ፣ የፅዳት መጠበቂያ
/ዴቶል/፣ የሽቶ
እና ላበት ማጥፊያዎች ሽታ
3. ላባ እና ጸጉር ያላቸው የቤት እንስሳት
4. የከብቶች ሽንት እና አዛባ
5. በረሮ የሚረጨው ኬሚካል
6. እርጥበት እና ቅዝቃዜ ያለው ስፍራ
7. የጉንፋን ቫይረስ
8. የኬሚካል ሽታ
9. ጭንቀት እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ
10. ሻጋታ
11. የጨጓራ አሲድ ቅርሻ /Gastro esophageal reflux disease/
12. የአፍንጫ አለርጂ እና ሳይነስ ህመም
ለአስም አጋላጭ ሁኔታዎች
1. የቆዳ አለርጂ/የቆዳ አስም
2. የአፍንጫ እና አይን አለርጂ
3. የምግብ አለርጂ
4. አስም ያለበት የቤተሰብ አባል
5. ከጉንፋን ጋር የሚያያዝ ሳል
የህመም ምልክቶች
1. በቅዝቃዜ ወቅት እና ማታ ማታ የሚባባስ ደረቅ ሳል
2. የደረት መጨነቅ/የመታፈን ስሜት
3. የትንፋሽ መፍጠን
4. የድካም ስሜት
5. የሰውነት መዛል እና ላበት
6. ሙዚቃዊ ትንፋሽ
7. ራስ ምታት፣ የትኩረት መቀነስ፣ እና አቅልን መሳት
አስም አመላካች ነገሮች ምን ምን ናቸው
1. በጥርጣሬ የአስም መድኃኒት ሲሰጥ በቶሎ የሚሻል ከሆነ
2. ወላጅ አስም ወይም አለርጂ ካለበት
3. ነባር የትንፋሽ አለርጂ ካለ
4. ተደጋጋሚ የመተንፈሻ አለርጂ ህጻናት ላይ አስም የምንለው በዓመት ውስጥ ሶስት ጊዜ እና ከዚያ በላይ የሆነ ሀኪም ያረጋገጠው የመተንፈሻ አለርጂ ካለ ነው።
አስምን በምን እናረጋግጣለን
1. የሳንባ ምርመር በጤንነታቸው ወቅት ያላቸው የሳንባ አየር የማስገባት እና የማስወጣት የመጨረሻ አቅም ጋር ሲነጻጸር ምን ያህል በህመሙ ምክንያት ቀነሰ የሚለውን በመለካት።
2. የአየር ቧንቧ ለትንፋሽ ቧንቧ አስፊ ህይወት አድን መድኃኒት ያለውን ፈጣን ምላሽ በማየት።
3.በአለርጂ አምጭ/ቀስቃሽ መድኃኒት አስም የመከሰት እድሉን መሞከር (ይህ ምርመራ ብዙ አይመከርም)
4. በእስፓርታዊ እንቅስቃሴ ያለውን የተቃጠለ አየር የማስወጣት አቅም በመለካት።
የአስም ህክምና
1. የአየር ቧንቧን ጥበት የሚያስተካክሉ መድኃኒቶች
2. የአየር ቧንቧ ቁስለትን/ብግነትን የሚቀንስ መድኃኒት
3. አለርጂን የሚቀንስ መድኃኒት
4. አስም ቀስቃሽ የሆነውን ህመም ማከም
5. ቤትን ከአስም ቀስቃሽ የሆኑ ነገሮች ነጻ
በማድረግ አስም እንዳይነሳ መከላከል
6. በቅዝቃዜ እና ጉንፋን በሚበዛባቸው ወቅቶች የአስም ቅድመ መከላከል መድኃኒት መስጠት
በአጠቃላይ የህጻናት የመተንፍሻ ቱቦ በተፈጥሮ ጠባብ በመሆኑ ምክንያት ከአስም ጋር የሚመሳሰሉ ብዙ ህመሞች አሉ። እድሜያቸው ከ4 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት የሳንባን በአግባቡ መስራት ወይም አለመስራት ለማወቅ ለምርመራ እድሜያቸው ስለማይፈቅድ በብዛት በክትትል ብቻ ነው መለየት የሚቻለው። አካባቢያዊ አስም ቀስቃሽ ሁኔታዎችን በማስተካከል አስምን መከላከል ውጤታማ ነው።
ምንጭ፦ ከዶ/ር ፋሲል መንበረ – የህፃናት ስፔሻሊስት ሀኪም ገጽ
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4/2013