ነስር ወይም የአፍንጫ መድማት ብዙዎች ላይ የሚከሰት ችግር ነው። በጊዜው ሲፈጠር ቢያስደነግጥም፣ በአብዛኛው ከባድ ወይም አስከፊ የሚባል ሁኔታን አያመለክትም። ውስጠኛው የአፍንጫችን ክፍል (ከፊት ወይም ከኋላ) ብዙ የደም ስሮች አሉት፤ በጣም ስስ ስለሆኑ በቀላሉ ሊደሙ ይችላሉ። ነስር አዋቂዎች ላይ እና ከ3-10 ዓመት የሆኑ ሕፃናት ላይ የበለጠ ይታያል። ነስርን በሚደሙት የደም ስር ዓይነቶች የፊተኛው ነስር እና የኋለኛው ነስር በማለት ለሁለት እንከፍለዋለን።
የፊተኛው የአፍንጫ መድማት በውስጠኛው የአፍንጫ ክፍላችን ከፊት የሚገኙ ደም ስሮች ተበጥሰው ሲደሙ የሚከሰት ሲሆን የኋለኛው የአፍንጫ መድማት ደግሞ በውስጠኛው የአፍንጫ ክፍላችን ከኋላ ወይም ከስር የሚገኙት ስሮች ሲደሙ ነው። በዚህ ጊዜ ደም ወደ ጎሮሮአችን ሊሄድ ስለሚችል የኋለኛው የአፍንጫ መድማት አስከፊ ሊሆን ይችላል።
ነስር በምን ምክንያት ሊመጣ ይችላል?
የአፍንጫ መድማት ወይም ነስር ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላል። ድንገት የሚመጣ ወይም ብዙ ጊዜ የማይደጋገም ከሆነ ብዙውን ጊዜ አሳሳቢ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን ድግግሞሹ ከጨመረ አስቸኳይ የጤና እርዳታ ሊያስፈልግ ይችላል። ደረቃማ አየር የነስር ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል።
ነፋሻማ እና ደረቃማ የአየር ንብረት ላይ የሚኖሩ ሰዎች ለዚሁ የቤት ማሞቂያ የሚጠቀሙ ሰዎች የአፍንጫቸው የውስጠኛው ክፍል በጣም ይደርቃል። ይህ ድርቀት ቀስ በቀስ ሲቀረፍ ወይም አካባቢው ሲቆጣ እና ድንገት ከነካነው ይደማል። የአለርጂ መድሐኒቶች የሚወስዱ ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ የውስጠኛው የአፍንጫ ክፍል ስለሚደርቅ እንዲሁ ሊደማ ይችላል። በተደጋጋሚ አፍንጫ ላይ የሚደርስ ምት ወይም አደጋ እንዲሁ የአፍንጫ መድማትን ሊያመጣ ይችላል።
የተለመዱ መንስኤዎች
– አፍንጫ ውስጥ ባእድ ነገር ካለ
– ኬሚካሎች
– አለርጂ
– አፍንጫ ላይ ጉዳት ከደረሰ
– በተደጋጋሚ ማስነጠስ
– አፍንጫን የመጎርጎር ልማድ
– ቀዝቃዛ አየር
– ጉንፋን
– ከፍተኛ የአስፕሪን መጠን መውሰድ
ብዙ ያልተለመዱ የነስር መንስኤዎች
– ከፍተኛ የደም ግፊት
– የመድማት ችግር
– የደም መርጋት
– ካንሰር
ሃኪሞት ጋር መቼ መሄድ አለብዎት?
ብዙዎቹ የነስር መንስኤዎች ህክምና አይፈልጉም፤ ነገር ግን የአፍንጫ መድማቱ ከ20 ደቂቃ በላይ ከቆየ እንዲሁም በአደጋ ወይም በጉዳት ምክንያት (ለምሳሌ – መውደቅ፣ የመኪና አደጋ፣ በቡጢ መመታት) ከመጣ የኋላ የአፍንጫ ነስር ሊሆን ስለሚችል ሀኪም ዘንድ መሄዱ ይመከራል።
በተጨማሪም የሚከተሉት ምልክቶች ካሉ በአስቸኳይ ወደ ህክምና መሄድ ይገባል።
– በአጭር ጊዜ ልዩነት በተደጋጋሚ የሚነስርዎ ከሆነ
– ራስ ማዞር ወይንም ራስዎን የሚስቱ ከመሰለዎት
– የልብ ምትዎ የሚጨምር ከሆነ እና ለመተንፈስ ከተቸገሩ
– ደም የሚያስመልስዎ ከሆነ
– በሰውነትዎ ላይ ሽፍታ ከኖረ
– ትኩሳት ካለዎት
– ከነስር ሌላ ከሌሎች የሰውነት ክፍሎች መድማት የሚኖር ከሆነ
– በቀላሉ የመበለዝ ምልክቶች በሰውነትዎ ላይ ከተገኙ
– ደምን ለማቅጠን የሚጠቅሙ መድኃኒቶችን የሚወሰዱ ከሆነ
– የደም መርጋትን የሚያስተጓጉሉ ማንኛውንም ዓይንት ሕመም ካለዎት
– የኬሞቴራፒ ሕክምና በቅርቡ ወስደው ከነበረ
ምርመራ
ሃኪሞ የአፍንጫዎን ውስጠኛ ክፍል በመሳሪያ በማየት ባእድ ነገር መኖር አለመኖሩን ያረጋግጣል። የተለያዩ ጥያቄዎችን ይጠይቅዎታል። እንዲሁም ብዙ የደም ምርመራዎችን በማዘዝ ምክንያቱን ለመለየት ይሞክራል።
ህክምና
የአፍንጫ መድማት ህክምናው በዓይነቱ ይለያያል። ይህ ማለት በውስጠኛው የአፍንጫ ክፍል ከፊት በኩል ያሉት የደም ስሮች በተለያየ ምክንያት ሲደሙ ነው። ይህ ዓይነት ነስር በቤት ውስጥ መታከም ይችላል።
ቁጭ በማለት ስሱን የአፍንጫ ክፍል ጠበቅ አድርጎ መያዝ ይመከራል። የአፍንጫዎ ቀዳዳዎች ሙሉ ለሙሉ መዘጋጀታቸውን ያረጋግጡ፤ ይህንን ቢያንስ ለ10 ደቂቃ ይቀጥሉ። ከዚያ በኋላ ትንሽ ወደፊት በማጋደል በአፍዎ ለመተንፈስ ይሞክሩ።
ነስርን ለማቆም በጭራሽ በጀርባዎ እንዳይተኙ። በጀርባ መተኛት ወደ ጉሮሮ እንዲሄድ በማድረግ ጨጓራ እንዲቆጣ ሊያደርግ ይችላል። ከ10 ደቂቃ በኋላ አፍንጫዎን በመልቀቅ መድማት ማቆሙን ያረጋግጡ፤ ካላቆመ ይህንኑ በቅደም ተከተል ይድገሙ።
በተጨማሪም ሰርንዎ ላይ በረዶ መያዝም ይረዳል። እነዚህን አድርገው ለውጥ ካልመጣ ግን ወድያው ሀኪሞ ጋር መሄድ ይኖርብዎታል።
ነስርን እንዴት መከላከል እንችላለን?
– በደረቅ እና ነፋሻማ አካባቢ ለሚኖሩ የአየሩን እርጥበት የሚያስተካክል (Humidifier) መጠቀም
– አፍንጫ መጎርጎር ልማድን ማስወገድ
– አስፕሪን በሀኪም ትዕዛዝ መሰረት ብቻ መጠቀም
– የአለርጂ መድሐኒት ለረጅም ጊዜ አለመጠቀም
– የአፍንጫ የውስጠኛው ክፍል እንዳይደርቅ የሚረጭ ወይም የሚቀባ ማለስለሻ (Petroleum jelly) መጠቀም
– ሲጋራ ማጨስ አፍንጫን በማድረቅ ለነስር ስለሚዳርግ ማስወገድ
ምንጭ፦ ከዶክተር ጤና ፌስቡክ ገፅ
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2014